• Dr. Mulugeta Mengist

ፍሬው “በልዩ ግንኙነት የተወሰነ” መዋዕለንዋይ

Updated: Nov 17, 2019


መዋእለንዋይ የሚለዉ ቃል በእንግሊዘኛው ኢንቨስትመንት የሚወክለዉን ሃሳብ የሚያስተላልፍ ይመስለኛል። ምንም እንኳን አንዳንዴ ባለሃብት የሚለዉ ቃል ተመሳሳዩን የእንግሊዘኛ ሃሳብ በመወከል ስራ ላይ ቢዉልም። ባለሃብት ለምን ይከበራል፥ ማንኛዉም ሰዉ ከሚከበረው በላይ? ባለሃብት ለምን ማበረታቻ ያስፈልገዋል፥ ማንኛዉንም ሰዉን ከምናበረታታዉ በላይና በተለየ? ወይስ የምናከብረዉና የምናበረታታዉ ሃብቱን ፍሬ በሚያፈሩ ስራዎች ላይ እንዲያውለዉ ነዉ? እንደዛ ከሆነ አስቀድሞ ከማሽቃበጥ፥ ሃብቱን በስራ ላይ ሲያዉለው ማክበሩና ማበረታቱ አይሻልም? አስቀድመዉ ያመሰገኑት ለማማት ይከብዳል ይባላል።

ከዚህ ሁሉ የሚሻለዉ መዋእለንዋይ የሚለዉ ቃል ነዉ። ንዋይን በምርት ስራ ላይ ማዋል። እንዲህ አድራጊዉን ደግሞ ባለሃብት ከምንለዉ “አምራች በንዋዩ” ብንለዉ ይሻላል።

እርግጠኛ ያልሆንኩበት፤ ንዋይ የሚለዉ ቃል ገንዘብን ብቻ ነዉ የሚመለከተዉ ወይስ ጉልበትን፥ ግዜን፥ እና እውቀትን ይጨምራል?

የእንግሊዘኛዉ ቃል ንብረትና ገንዘብን በምርት ስራ ላይ ማዋልን ነዉ የሚመለከተዉ። ነገር ግን ቃሉን በዚህ ጽሁፍ አግባብ የተጠቀምኩበት ጊዜን፥ እና ገንዘብን በስራ ላይ ማፍሰስ ወይም ማዋል በሚል መልኩ ነዉ።

“ፍሬዉ በልዩ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ” ሲባል ለማለት የተፈለገዉ የሚከተለዉን ሃሳብ ነዉ። መዋእለንዋይ ፍሬ ወይም ምርት ያፈራል። ነገር ግን አንዳንድ መዋእለንዋዮች ፍሬ የሚያፈሩት በልዩ ግንኙነቶች ዉስጥ ነዉ። ከግንኙነቶች ዉጭ ፍሬ አያፈሩም። ማለትም ኪሳራ ይሆናሉ። ስለዚህ ግንኙነቱ በተለያየ ምክንያት ከፈረሰ፥ የፈሰሰዉ ንዋይ በርሃ ላይ የፈሰሰ ዉሃ ያህል ነዉ። ነገር ግን ግንኙነቱ ከቀጠለ፥ ንዋዩ ፍሬ ያፈራል።

ለማሳያ ያህል የጫማ ቁጥሩ 66 የሆነን ሰዉ እንዉሰድ። እንዲህ አይነት የጫማ ቁጥር ስለመኖሩም አላውቅም። ግን ምሳሌ ነዉ። ይህ ሰዉ ገበያ ላይ የሚሸጡ ጫማዎች አይሆኑትም። ስለዚህ በትእዛዝና በልኩ ነዉ ማስፋት የሚችለዉ። ጥያቄዉ ምን አይነት ጫማ ሰሪ ነዉ ይህን ጫማ ለመስራት ፈቃደኛ የሚሆነዉ? በምን ያህል ቀብድ? ወይስ ሙሉ ክፍያ አስቀድሞ ተቀብሎ?

ጫማ ሰሪዉ ይህን ጫማ ለመስራት የሚያወጣዉ ጉልበት፥ ጊዜ፥ ቆዳ፥ ክር፥ ማስቲሽ እንደ መዋእለንዋይ ልንወስደዉ እንችላለን። እንዲህ አይነት መዋእለ ንዋይ የሚያፈራዉ ፍሬ በልዩ ግንኙነት ላይ የተመሰረተ ነዉ። ይህ ግንኙነት ከሌለ፥ መዋእለ ንዋዩ በርሃ ላይ የፈሰሰ ዉሃ ያህል ነዉ። ለዛ ነዉ እንዲህ አይነት ጫማዎች ገበያ ላይ የማይገኙትና በልዩ ትእዛዝ የሚሰሩት። ምክንያቱም ንዋይ አፍሳሾቹ ንዋያቸዉን ከማፍሰሳቸዉ በፊት ዋስትና ሰለሚፈልጉ ነዉ።

እንዲህ አይነት ባህሪ ያላቸዉ መዋእለ ንዋዮች የሚከተሉት ዉጤቶች ያመጣሉ

 1. ሰዎች በእንዲህ አይነት ስራ ንዋያቸዉን ለማፍሰስ ይፈራሉ፤ ሌሎች አማራጮች ጭራሽ ከሌሉ በስተቀር

 2. በእንዲህ አይነት ስራ አንዳንድ ሰዎች ንዋያቸዉን ቢያፈሱም፥ የንዋዩ ጥራት ዝቅተኛ ይሆናል።

 3. በተለያየ ምክንያት ንዋያቸዉን ማፍሰስ የጀመሩ ቢኖሩም (ለምሳሌ አማራጭ በማጣት)፤ ንዋያቸዉን በአንዴ አፍስስፈዉ ካልጨረሱ፤ በተለይ ደግሞ የማይመለሱበት ሁኔታ ላይ ካልደረሱና አማራጮች ከተገኙ በፍጥነት ማፍሰሳቸዉን አቁመዉ ከግንኙነቱ ይወጣሉ

 4. ንዋያቸዉን እያፈሰሱ የሚቀጥሉት ወይ ሌላ አማራጭ የሌላቸው ወይም ደግሞ የማይመለሱበት ደረጃ ስለደረሱ ብቻ ነዉ

 5. እነዚህ አይነት ሰዎች አማራጭ ስለሌላቸዉ የመደራደር አቅማቸዉም ዝቅተኛ ነዉ። ስለዚህ በግንኙነቱ የመጨቆን እድላቸዉ ከፍተኛ ነዉ

 6. ግንኙነቱ ድርጅት ከሆነ፥ ድርጅቱ በተለያዩ ጊዜ የሚያገኘው አዲስ ሃሳብና ጉልበት ዝቅተኛ ስለሆነ በጊዜ ሂደት እየበሰበስ ይሄዳል

ለእነዚህ ችግሮች የተለያዩ አይነት መፍትሄዎች ሊተገበሩ ይችላሉ

 1. ንዋያቸዉን ለሚያፈሱ ሰዎች ስለግንኙነቱ ዘላቂነት አስቀድሞ ዋስትና መስጠት፥ ለምሳሌ የስራ ዋስትና።

 2. ከአማራጮች የተሻለ ክፍያ መስጠት

 3. የግንኙነቱን አጣሪነት በተለያየ መልኩ መቀነስ። ለምሳሌ፥ በግንኙነቱ የሚገኙ ልዩ ልምዶችን፥ እውቀቶችን እና ክህሎቶች (በተለይ በሌላ መልኩ የመገኘት እድላቸዉ ዝቅተኛ የሆኑ) እንዲኖሩና እነዚህም ከግንኙነቱ ዉጭ ዋጋ እንዲኖራቸዉ ማድረግ

 4. ለእንዲህ አይነት ልምዶች፥ እዉቀቶችና ክህሎቶች ዋጋ ሊሰጡ የሚችሉ አማራጭ ስራዎች እንዲፈጠሩ ማድረግ

 5. በግንኙነቱ ወቅት የንዋይ አፍሳሹን ጥቅምና ደህንነት መጠበቅ፥ ብዝበዛ እንዳይኖር ማድረግ።

 6. ከገንዘብ ዉጭ ያሉ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞችን ማካተት። ለምሳሌ የማእረግ ጥቅም፥ የሰራተኛዉን ፍላጎት ያገናዘበ የስራ ሁኔታዎች፥ እና ከሌሎች አማራጮች የተሻለ የስራ ጫናና ነጻነት እንዲኖር ማድረግ

 7. ከስራዉ ጸባይና ከድርጅቱ ተልእኮ አንጻር የማይጣጣሙ ባህሪያዎችን አለማበረታት። ሳይቃጠል በቅጠል። ምክንያቱም የሌሎችን ተነሳሽነት ስለሚቀንስ።

ስለጉዳይ ይህን በጠቅላላ ካልን፤ ለማሳያነት ያህል የዩኒቨርስቲ መምህርነትን እና ተመራማሪነትን እንደማሳያነት እንዉሰድ።

የዩኒቨርስቲ ተመራማሪዎችና አስተማሪዎች እጅግ ጠባብ በሆነ የሙያቸዉ ዘርፍ ላይ የምርምር ጊዜያቸዉን ቢያጠፉ በመስኩ በየወቅቱ የሚገኙ አዳዲስ ግኝቶች በፍጥነት ይጨምራሉ። ስፔሻላይዜሽን ምርታማነትን እንደሚጨምር ይታመናል። ነገር ግን የበለጠ ስፔሻላይዝ በማድረግ የሚያጠፉት ጊዜ አዳዲስ እዉቀት ቢያስገኝላቸዉም፥ ይህ እዉቀት ዋጋ የሚኖረዉ በዩኒቨርስቲዎች ብቻ ነዉ። ከዚህ ውጭ ዋጋዉ እጅግ ይቀንሳል። እንደዉም ይህን አዲስ እዉቀት ለማግኘት ብለዉ የሚያጠፉት ጊዜ በሌሎች ቀጣሪዎች ረገድ የመቀጠር እድላቸዉን ይቀንሰዋል። ከእነሱ ይልቅ በጠቅላላ እውቀት ስራ ሲሰራ የቆየ ሰዉ የመቀጠር እድሉ ከፍተኛ ነዉ። ስለዚህ ለቀው መውጣት ይፈራሉ። ቀጣሪዉም ይህን ስለሚያውቅ ፍትሃዊ ባልሆኑ ተግባራት ሊሰማራ ይችላል። ለምሳሌ ብዘበዛ ላይ። ይህ በመሆኑ የተነሳ መጀመሪያዉኑ ሰዎች ጊዜያቸዉን በምርምር ስራ ላይ ለማጥፋት አይፈቅዱም። እንዲሁም በተለያየ ምክንያት ቢፈቅዱም (ለምሳሌ አማራጭ ስለሌለ) ሌሎች አማራጮች እንደተገኙ ጥለዉ ይወጣሉ። በዚህ መልኩ የሚቆዩትት በሌሎች የመቀጠር እድላቸዉ ዝቅተኛ የሆኑት ብቻ ናቸዉ።

ይህን ችግር ለመፍታት የሚተገበሩ መፍትሄዎችን ማየቱ ሃሳቡን የበለጠ ያብራራዋል። አንደኛ፥ የስራ ዋስትና ነዉ። ለምሳሌ በአሜሪካ አንድ የዩኒቨርቲ አስተማሪ ፕሮፌሰርነት ማአርጉን ካገኘ በሗላ በምንም መልኩ ከስራ ሊባረር አይችልም። ከዛ በፊት ግን እጅግ በብዙ ሁኔታዎች ከስራዉ በቀጣሪዉ ሊባረር ይችላል። ሕጉም የሚያደርግለት ጥበቃ አይኖርም። ሌሎች አማራጭ የስራ መስኮችን ስንወስድም ተመሳሳይ ነዉ። ቀጣሪዉ ሰራተኛዉን የማባረር መብቱ ሰፊ ነዉ።

ሁለተኛ የዩኒቨርስቲ መምህርነት እና ተመራማሪነት ከሌሎች አማራጭ የስራ መስኮች ጋር ሲወዳደር ተፈላጊነቱን የሚጨምሩ አስራሮችን ይከተላል። ለምሳሌ የአስተማሪዉና የተመራማሪዉ የስራ ሰዓት እና የስራ ሁኔታ ለሰራተኛዉ ሰፊ ነጻነት የሚሰጥ ነዉ። ከትምህርት ፕሮግራሙ ዉጭ በሆኑ ጊዜያት ደግሞ ነጻነቱ ይጨምራል።

ሶስተኛ ከገንዘብ ዉጭ የሆኑ የተለያዩ ጥቅማጥቅሞች ሰዎችን ለመሳብ ይውላል። ለምሳሌ ምርምርና ህትመት ዝናን ያመጣል። የአካዳሚክ ማእረግ ሌላዉ ጥቅማ ጥቅም ነዉ። እንዲሁም የፈጠራ መብትን ከቀጣሪዉ ጋር የመጋራት አስራር ሌላዉ ጥቅማ ጥቅም ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።

እና ሌሎች ያልጠቀስኳቸዉ አስራሮችና ልማዶች።

እንዲህ አይነት አስራሮች ብቃት ያላቸውን ሰዎች ወደ ስራዉ ለመሳብና ለማቆየት ይረዳሉ። እንዲህና መሰል አሰራሮች ባይኖሩ ኖሮ፥ ወደ ምርምርና ማስተማር የሚገቡት ሰዎች፤ አማራጭ ስራ ማግኘት የማይችሉት ሊሆኑ ይችል ነበር። እንዲሁም የምርምርና ማስተማር ስራ ሰዎች ገብተው ቶሎ የሚወጡበት እንጂ የሚቆዪበት አይሆንም ነበር።

ሃሳቡን ከዚህ በላይ እንዲህ ከገለጽኩት አኳያ፥ ለትንተና እና ግምገማ ሃሳቡ ያለዉን ጥቅም ባጭሩ ልጥቀስና ልጨርስ። ባንድ የስራ መስክ በፈቃዳቸዉ የሚገቡ ሰዎች ቁጥርና አቅም ዝቅተኛ መሆን፥ እንዲሁም ደግሞ አንዴ ከገቡ በሗላ በፍጥነት የመዉጣትና ያለመርጋት ችግር መስተዋል፥ ረጅም ጊዜ ገብተዉ የሚቆይቱም ቢሆን ቢወጡም ሌላ አማራጭ የሌላቸዉ አይነት ሰዎች መሆኑ፥ የስራዉ ባህሪ ከሰራተኛዉ የሚጠይቀዉ መዋእለ ንዋይ ወይም መስዋእት ከፍተኛ ከሆነ፥ ችግሩን የበለጠ ለመረዳትና አግባብነት ያለዉን መፍትሄ ለመፈለግና ለመተግበር በርእሱ የጠቀስኩትና ከላይ ያብራራሁት ሃሳብ ጠቃሚ ነው።

በሃገራችን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በፓሊስነት ከፍተኛ ልምድ ያላቸዉ ሰዎች፥ በግል የደህንነት ኩባንያዎች የመቀጠር እድላቸዉ እየሰፋ መጥቷል። የግል የደህንነት እና የጥበቃ ኩባንያዎች በፊት የተለመዱ አልነበሩም። አሁን እነዚህ መስፋታቸዉን ተከትሎ ለፓሊስ ስራዊት አባላት እድል ፈጥረዋል። እነዚህ ባልነበሩበት ወቅት፥ በፓሊስነት ስራ የተገኘ እውቀትና ልምድ ከፓሊስ ሰራዊቱ ውጭ ሌላ ጥቅም አልነበረዉም ማለት ይቻላል። ስለዚህ እነዚህ አዲስ እድሎች ሰዎች የፓሊስ ሰራዊቱን የመቀላቀል ተነሳሽነታቸዉን ስለሚጨምሩ እንደ ተወዳዳሪ ሳይሆን እንደ አጋዥ መታየት ይኖርባቸዋል።

በሌላዉ አገር የገለሌ መርማሪ ባለሙያዎችና ድርጅቶች አሉ። እነዚህ ባለሙያዎችና ድርጅቶች ብዙ አያሌ ጥቅምች ቢኖራቸዉም ከጉዳዩ ጋር የሚያያዘዉ አንደኛዉ ጥቅም ግን ልክ እንደ ግል የደህንነትና ጥበቃ ድርጅቶች ነዉ። ስለዚህ የገለሌ ምርመራ ጉዳይ ከዚህ ጥቅሙና በዚህ ጽሁፍ ካልጠቀስኳቸዉ ሌሎች ጥቅሞቹ አንጻር በሚገባ ተገምግሞ፥ ስለአስፈላጊነቱ የፓሊሲ ዉሳኔ ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ ነዉ። በእርግጥ እንደ ትምህርትና ምርምር ተቋማት ሁሉ በፓሊስና ዉትድርና ሰራዊት ዉስጥ የተለያዩ ማእረጎች ከገንዘብ ዉጭ ያሉ ጥቅማ ጥቅሞች ተደርገዉ ይወሰዳሉ።

በዚህ ጽሁፍ ያነሳዋቸው ጉዳዮች ለማሳያነት እንጂ ሙሉ ለሙሉ የተነተኑ አይደሉም። ከዚህ በተረፈ አንባቢያን ሃሳቡ የሚኖረዉን ግላዊና የፓሊሲ አንድምታ መርምሩት።

#Ethiopia #Policeservice #relationspecificinvestment #sunkcost

1 view
 • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.