• Dr. Mulugeta Mengist

ጭር ሲል አልወድም!

Updated: Nov 17, 2019

መግቢያ

የአቅም ግንባታ ለረጅም ጊዜ የፓሊሲ ትኩረት አግኝቶ ሲሰራበት የቆየ ጉዳይ ነው። ባንድ ወቅት የአቅም ግንባታ ሚኒስቴር የሚባል ተቋቁሞ ነበር። ከፈረሰም በኋላም ሁሉም የመንግስት ድርጅቶች በአመታዊ አቅዶቻቸው ከሚያካትቷቸው ቋሚ ስራዎች መካከል የአቅም ግንባታ ነው። ለዚህም በየአመቱ ብዙ ገንዘብ ያወጣሉ። የሃገር ውስጥ ገንዘብና በልማት እርዳታ ገንዘብ። በአቅም ግንባታ ስም የምንሰራቸው አብዛኞቹ ስራዎች ተገቢነታቸውና ጥቅማቸው አጠያያቂ ነዉ። ይህን በተከታታይ  ለመዳሰስ እሞክራለሁ። ከዚያ በፊት ግን ለመግቢያነት በጉዳዩ ዙሪያ በቅርብ ጊዜ ከታተመ መጽሃፍ ያገኘሁትን አንድ ጉዳይ ላካፍል።

መጽሃፉ መንግስታት ፍላጎቶቻቸውን ለማሟላት ባላቸው አቅም በደረጃ ያስቀምጣቸዋል። እንደምንገምተዉ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ የሚባሉት ከአርባ በላይ የሆኑ አገራት በአቅም ደረጃቸው የመጨረሻ ናቸው። በእነዚህ አገራት መካከልም እንኳን ደረጃ ማውጣት ይቻላል። አቅምን በምን ያህል ፍጥነት መገንባት ይቻላል የሚለውን ለመመለስ ጸሃፊዎቹ አገራትን አስመልክቶ ያሉ ታሪካዊ የአቅም ዳታዎችን ይጠቀማሉ። መልሱ ተስፋ የሚሰጥ አይደለም። አንድ አገር በደረጃዉ ያለዉን ቦታ በትንሹ ለማሻሻል እንኳን በአማካይ አርባ አመታት ይፈጅበታል። በእርግጥ ይሄ አሁን የበለጸጉ የምንላቸውን አገሮች ተሞክሮ መሰረት በማድረግ ነዉ። ስለዚህ እኛ እንደ እነሱ አርባ አመታት ላይፈጅብን ይችላል። ከኋላ የመጣ ከቀደሙት መማር ስለሚችል ጊዜዉን ያሳጥራል። በዛ ላይ ዘመናዊ ቴኬኖሎጂዎቹ ያግዙናል። እንዲያም ሆኖ ግን ቀላል እንዳልሆነ ግልጽ ነዉ። ያም ሆኖ ግን እነዚህ በልማት ወደ ኋላ የቀሩ አገራት እቅድ ሲያቅድ ለጥጠዉ ነዉ። የሚያስፈልገዉ አቅም እጅግ በፈጣን ሁኔታ ይገነባል በሚል መነሻ እሳቤ። ችግሩ የእቅዱ በሙሉ አለማሳካት ብቻ አይደለም። ጸሃፊዎቹ “ያለጊዜዉ ጭነት” ይሉታል። አቅም ሳይጠነክር ጭነት ማብዛት ይሰብራል። ያላችዉንም ትንሽ አቅም ያሳጣል።

ታዲያ እነዚህ መንግስታት ያለጊዜዉ ጭነት እያበዙ፥ ፍልጎቶቻቸውን እየለጠጡ፥ እና ሳይሳካላቸው እንዴት በስልጣን ሊቀጥሉ ቻሉ? እንዴት ይሄ ጭነት አልሰበራቸውም? ይህንን ለማብራራት ጸሃፊዎቹ የተጠቀሙት ሃሳብ ስላስደነቀኝ እሱን በመጥቀስ ወደ ጉዳየ እገባለሁ። ያልተሰበሩት፥ አሁን እየለጠጡ የሚያቅዱት፥ የማስመሰል ስትራቴጂ ስለሚከተሉ ነዉ ይሉናል። የማስመስል ስትራቴጂ የዱር እንሰሳት ሁሉ የሚጠቀሙበት ነዉ። የአቅመቢስነትን ወይም አቅም ማነስን ለመሸፈን እና ታፍረዉና ተፈርተዉ ለመኖር። አንዳንዱ እባብ ታፍሮና ተፈርቶ የሚኖረው፥ በመርዛማ እባቡ ነዉ። አንዳንዱ ደግሞ መርዘቢስ ነዉ። መርዘቢሱ በመርዝ ተፈጥሮ ብትበድለዉ በሌላ ግን ክሳዋለች፥ በማስመስል። አዎ እንዲህ አይነቶቹ እባቦች በምግባር፥ በፍሬ መርዛማ ባይሆኑም በመልክ ግን መርዛማዎቹን ይመስላሉ። በቅርጽ፥ በቀለም፥ በድምጽና በመሳሰሉት።

መንግስታትም እንዲህ ስለሚያደርጉ ነዉ ይሉናል። ስለሚያስመስሉ። የማስመሰል ስትራቴጂ ግን ሁሌ አይሰራም። በስኬት ለማስመሰል የሚመች ምህዳር ያስፈልጋል። አመቺ የሚባለው ምህዳር ሁለት ዋና መገለጫዎች አሉት። አንደኛ፥ ምህዳሩ ዝግ መሆን አለበት። ማለትም አስመሳዩ በጉዳዩ ላይ ሞኖፓል ሊኖረዉ ይገባል። የስልጣን፥ የመረጃ ሞኖፓል። ተወዳዳሪ ተዋንያን ካሉ፥ በምግባር ወይም በመረጃ ሊያሳጡት ስለሚችሉ። ሁለተኛው፥ በምህዳሩ ዉስጥ አዲስ ሃሳብ የሚገመገምበት/የሚመዘንበት ስልትም የማስመስል ስትራቴጂዉን ስኬት ይወስነዋል። አዲስ ሃሳብን በሁለት ዋና ስልቶች መገምገም ይቻላል። አንደኛው ፍሬ ተኮር ግምገማ ነዉ። ሃሳቡ የሚገመገመዉ በሚያፈራዉ ፍሬ ነዉ። ሁለተኛው የመልክ/የቅርጽ ግምገማ ነዉ። በስርአቱ ዉስጥ አዲስ ሃሳብ የሚገመገመው በመልክ ከሆነ፥ ለአስመሳዮች ይመቻል። ባጭሩ መልእክቱ፥ በተጨባጭ አቅምን ማሻሻል ረጅም ጊዜ የሚወስድ ሆኖ እያለ፥ መንግስታት ፍላጎትን እየለጠጡ እያቀዱ፥ ያሰቡትን ሳያሳኩ ግን ደግሞ አሁንም በተመሳሳይ መልኩ እየለጠጡ እያቀዱ እንዲቀጥሉ ያስቻላቸው በማስመሰል ስልት እንደሆነ ይጠቁማሉ።

መንግስታት ለአቅም ግንባታ የሚያወጡት ወጪ የራሳቸውን እና በእርዳታ የሚያገኙትን ነዉ። እንዴት ነዉ ታዲያ ቢያንስ እርዳታ ሰጪዎች፥ የማስመሰሉ አጋር የሆኑት? ይሄ ከአቅም ግንባታዉ ፓለቲካ ኤኮኖሚ (ተዋንያን፥ የግል እና የጋራ ጥቅሞቻቸው፥ ትጋታቸው፥ እና በመሳሰሉት) የተወሰነ ስለሆነ በሌላ ክፍል እመለስበታለሁ።

የማን አቅም?

በሃገራችን የአቅም ግንባታ ትርክት፥ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ግልጽ የሚሆነው ነገር፥ የአቅም ግንባታዉ የሚመለከተዉ ድርጅታዊ አቅምን ሳይሆን የሰራተኞችና አመራሮች አቅምን ነዉ። የአቅም ግንባታ ስራዎች የሚያተኩሩት የሰራተኞቹን እውቀትና ክህሎት በመጨመር ላይ ነዉ። ስልጠናዎች፥ ወርክሾፓችና ኮንፈረንሶች፥ የዉጭ የቤንችማርኪንግ ጉዞዎች፥ የሃገርና የዉጭ የከፍተኛ ትምህርት እድሎች እና የመሳሰሉት የሚያተኩሩት የሰራተኛውን እና የአመራሩን እውቀትና ክህሎት በመጨመር ላይ ነው።

ይህ በመስረቱ የተሳሳተ ትርክትና እሳቤ ነዉ። አንደኛ ድርጅቱ ማለት ሰራተኞቹ ስላልሆነ። ድርጀቱ እንደ ሰዉ ይከሳል፥ ይከሰሳል። የንብረት መብት ይኖረዋል። ዉል ይዋዋላል። የደርጅቱ ንብረትና ዉል ከሰበሰባቸዉ ሰዎች ንብረትና ዉል ይለያል። ሰዉ ይሞታል። ድርጅትም ሊፈርሰ ይችላል። ነገር ግን ስለ ሰዉ ሞት እርግጠኛ እንደምንሆነዉ፤ ሰለድርጅት መፍረሰ እርግጠኛ መሆን አንችልም። በአለም ረጅም እድሜ ያስቆጠረዉ ድርጅት የትኛዉ እንደሆነ ባላዉቅም፤ ድርጅቶች ረጅም ጊዜ የመቆየት እድል እንዳላቸው ግን እርግጠኛ ነኝ። በሰዎች ሞት ምክንያት የሚመጣን የንብረት መበጣጠስና የኤኮኖሚያዊ፥ ማህበራዊና፥ ፓለቲካዊ እንቅስቃሴዎች መቋረጥን፣ ድርጅታዊ አሰራር ይቀርፈዋል።

ሁለተኛ፥ የሰራተኞቹ አቅም ከድርጅቱ አቅም በሃሳብም በተግባርም የተለየ ስለሆነ ነው። ድርጅት ማለት የሰዎች ስብሰብ ማለት አይደለም። በአግባቡ የተደራጀ ድርጅት፥ ከስራተኞቹ የአቅም ድምር በአይነትም፥ በጥራትም፥ በመጠንም መላቅ አለበት። ያልዚያማ መጀመሪያዉኑ ድርጅት ማቋቋም ስለምን ተፈለገ። ድርጅት ያስፈለገበት ምክንያት የግብይት ወጪን በመቀነስና አቅም አብዢ ስራዎችን በመስራት ዉጤትን ማላቅ ነውና።

የድርጅቱን አቅም ከሰራተኞቹ አቅም በሃሳብም በተግባርም መለየት ካልተቻለ፥ አንደኛ ድርጅት አለ ማለትም ይከብዳል፥ የስዎች ስብስብ እንጂ። ሁለተኛ፥ መንግስት በሰዎች ስብስብ ብቻ የሚጠበቅበትን ሃላፊነት መወጣት አይችልም። ሁሉም የሃገሪቱ ዜጋ የመንግስት ሰራተኛ አይደለም። እጅግ ጥቂቱ ብቻ ነው። ታዲያ ድርጅት ሳይኖር፥ የእነዚህ ጥቂት ሰዎች ስብስብ እንዴት ነዉ አንድ መቶ ሚሊዮን ህዝብ አስተዳድራለሁ የሚለው።  ሶስተኛ በስራተኞቹ ላይ የሚሰራዉ የአቅም ግንባታ ስራዎች በሙሉ ዉጤት የማይኖራቸው ሃብት ማባከኛ ይሆናሉ። የተቀደደ በርሜል በዉሃ የመሙላት ያህል ነዉ። በምንም ያህል ፍጥነት ለመሙላት ብትሞክርና የሞላ ቢመስልህም ዞር ስትል ይፈሳል። በእርግጥ የአቅም ግንባታ ስራ አንዴ ተሰርቶ የሚያልቅ አይደለም። በቋሚነት መሰራት አለበት። ነገር ግን የምንስራዉ አቅምን ለመጨመር (በአይነት በጥራት በመጠን) እንጂ የጎደለን አቅም ለመሙላት መሆን የለበትም። በዚህ አስራር ባለበት ትረግጣለህ እንጂ መሻሻል አይኖርም። አቅም ግንባታ ሲባል ደግሞ መጨመር ማሻሻል እንጂ ጥገና አይደለም።

የድርጅት የእንግሊዘኛው ቃል መሰረቱ ኦርጋኒዝም ነዉ። ኦርጋኒዝሞች በዉስብስብነታቸውና አይነታቸው ይለያያሉ። ሰዉ ራሱ ኦርጋኒዝም ነዉ። እንደ ኦርጋኒዝም የተዋቀርነው በተለያዩ የሰዉነት ክፍሎች፥ ሴሎች፥ ስርአቶች፥ ብልቶች ነዉ። ነገር ግን እኛ የእነዚህ ስብስቦች ብቻ አይደለንም። የእነዚህ ድምር ብቻ አይደለንም። ከዛም በላይ ነን። ከዛም በላይ መሆናችን መገለጫው ህይወት ነዉ። ህይወት ከድምር በላይ ነዉ። እያንዳንዱ ብልት ህይወት የለውም በራሱ። ነገር ግን እንደ ኦርጋኒዝም ሲደራጅ ህይወት ይፈጠራል። በአይነትም፥ በመጠንም፥ በጥራትም የረቀቀ ነገር። ኦርጋናይዜሽን ስንል ይህን የተፈጥሮ ድንቅ የመኮረጅ እሳቤን ያሳያል። ኦርጋናይዜሽን ከሰራተኞቹ፥ ባለቤቶቹ አቅም በላይ ነዉ። በአቅም ብቻም ሳይሆን በማንነትም የተለየ መሆን አለበት። ሰዉ ሰራሽ ስለሆነ ግን፥ ስብስቡ እራሱ ይህን ዉጤት አያመጣም።  መስራት ያለበት ብዙ ስራ አለ።

ከላይ እንደተገለፀው የሰራተኞቹ አቅም እና የድርጅቱ አቅም ይለያያሉ። በአይነት፥ በጥራት፥ በመጠን። መለያየትም አለባቸው። እንዴት ነዉ የሚለያዩት የሚለውን ባጭሩ እንመልከተዉ። አንደኛ፥ ድርጅቱ ስራዎቹን ለመስራት ከሰራተኞቹ በተጨማሪ የሚጠቀማቸው ግብአቶች ወይም የአቅም መሰረቶች አሉ። በተከታታይ ባሉት የጽሁፉ ክፍሎች እነዚህን የአቅም መሰረቶች በሙሉ በደንብ ይብራራሉ። ባጭሩ ግን ድርጅቱ ግቡን ለማሟላት፥ መረጃ፥ ገንዘብ፥ ቴክኖሎጂ፥ ንብረት ይጠቀማል። በተለይ ደግሞ ተቋማት (ማህበራዊ ካፒታል፥ የማስገደድ ህጋዊ ስልጣን)፥ እና የፓለቲካ ካፒታሉ የድርጅቱ የአቅም መሰረቶች ናቸው። እነዚህ መሰረቶች የድርጅቱ አቅም ከሰራተኞች አቅም እንዲለይና እንዲበልጥ የሚያደርጉ ናቸው።

ሁለተኛ፤ የሰዎቹ የተናጥል አቅም እና በድርጅቱ ዉስጥ የሚኖራቸው አቅም ይለያያል። ምክንያቱም ሰዎቹ ያላቸውን አቅም በሙሉ ለድርጅቱ ስራ አይጠቀሙበትም። ለግል ጥቅማቸው ሊያዉሉት ይችላሉ። ሁለተኛ በድርጅቱ ያላቸው ውስን ሚና ነዉ። በመሆኑም ለዚህ ሚና የሚጠቀሙት ያላቸውን አቅም ብቻ ሳይሆን ለሚናቸው የሚገባውን ብቻ ነዉ።

ሶስተኛ፥ ድርጅቱ አቅም አብዢ አሰራሮችን በመከተል፥ የስራተኞችን የተናጥል አቅም በስፔሻላይዜዥሽን እና ግብይት እንዲዳብር ለማድረግ ስለሚችል። ሁሉም ይህን ያደርጋሉ ማለት ሳይሆን፥ የማድረግ እድል ግን አላቸው። ስለዚህ እንዲለያይ የሚያደርገው ሶስተኛ ምክንያት ይሄ ነዉ።

ሰብአዊ አቅም ግንባታ ላይ ማተኮር የሚመጣው፥ የውጤት ማነስ ሁሉ ከእውቀትና ክህሎት ማነስ ነዉ ብሎ ከመነሳት ነዉ። ነገር ግን ሁሉም ውስንነት ከእውቀትና ክህሎት ማነስ አይመጣም። ከግል ጥቅም፥ ከትጋት ጋር የሚያያዙ ውስንነቶች አሉ። እነዚህ ደግሞ በስልጠና ወይም በዉጭ የቤንችማርኪንግ ጉዞ አይገነቡም። ሌላዉ ቢቀር፥ የሰብአዊ አቅም አንድ አካል የሆነው አመለካከት እንኳን በምህዳሩ እና በሌሎች የሚገነባ እንጂ በስልጠና ወይም አደራ አይገነባም። እውቀት ቢሆንም እንኳ ችግሩ፥ የግድ መንግስት ገንቢ መሆን ላይጠበቅበት ይችላል። እነዚህ ነገሮች ሁሉ ወደፊት እንመለስባቸዋለን።

የመረጃ አቅም ግንባታ

ጭር ሲል አልወድም!

የድርጅቶች አቅም ከሰራተኞቻቸው አቅም በአይነት፥ በጥራትና፥ በመጠን እንዲለይ ከሚያደርጉት ነገሮች አንዱ ድርጅቶች ከሰራተኞቻቸው እውቀትና ክህሎት በተጨማሪ የመረጃ አቅም ስለሚኖራቸው ነዉ። መረጃ አቅም ነዉ። የመረጃ አቅም ግንባታን ጉዳይ ለመመርመር በሚከተሉት ወጎች እንጀምር።

የአሜሪካን የወታደር ሃይል የኢራቁን የሳዳም አገዛዝ ከጣለ በኋላ፥ ጊዜያዊ መንግስት አቋቁሞ ሀገሪቱን ያስተዳድር ነበር። በዚህ ዘመን ከተሰሩ ስራዎች መካከል ሳዳም ሁሴን እና ጓዶቹን ለፍርድ ማቅረብ ነዉ። በፍርድ ሂደቱ አያሌ የሰው ምስክሮች መቅረብ ነበረባቸው። ተፈላጊዉን ምስክር በሚፈለግበት ጊዜ በወቅቱ ለፍርድ ቤት ማቅረብና ጥበቃ ለሚያስፈልጋቸው ጥበቃ ማድረግ በራሱ ትልቅ ስራ ነበር። ይህን ስራ እንዲመራ የተቀጠረዉ ደግሞ አንድ የአሜሪካዊ ጠበቃ ነበር።

በምን ሰአት በየትኛው የባግዳድ ጎዳና ምስክሮቹን ወደ ፍርድ ቤት ማጓጓዝ እንዳለበት መወሰን የጠበቃዉ የመጅመሪያዉ እራስ ምታት ነበር። ብዙዎቹ የባግዳድ ከተሞች በትራፊክ የተጨናነቁ ናቸው። እንዲሁም የአሜሪካን መንግስት የሚቃወሙ የተለያዩ ቡድኖች በየመንገዱ የሚጠምዷቸው ፈንጂዎች ቋሚ ስጋት ሆነዋል።

ጠበቃዉ ለዉሳኔዉ የሚያስፈልጉ ሁለት አይነት መረጃዎችን ከሚመለከታቸው ድርጅቶች አሰባሰበ። አንደኛው አይነት መረጃ የባግዳድን የትራፊክ ፍሰት የሚመለከት ነዉ። እያንዳንዱ የባግዳድ ከተማ በባለፊት ጊዜያት የነበራቸውን የትራፊክ ፍሰት ይመለከታል። የከተማዊ ታሪካዊ የትራፊክ ፍሰት መረጃ። የትኛው መንገድ በምን ሰአት በትራፊክ ይጨናነቃል፥ ጭር ይላል የሚለውን ለመለየት ይጠቅመዋል። ሁለተኛው አይነት መረጃ በከተማው የደረሱ የፈንጂ ጥቃቶችን ይመለከታል። ምን አይነት ፈንጂ? በምን ቀን? በምን ሰአት? የደረሰ ጉዳት አይነት? መረጃዉ እነዚህን ይመልሳል። ጠበቃዉ ከዚህ ቀጥሎና ስራዉን ጨርሶ አገሩ ሲመለስ ያደርገዉ ከጠበቃ የሚጠበቅ አልነበረም። ሁለቱን መረጃዎች አገናኛቸው። እራስ ምታቱም ለቀቀው። ሁለቱን መረጃዎች በማገናኘት ምን አገኘ?

የትራፊክ ፍሰቱና የፈንጂ ጥቃቱ ግንኙነት አላቸው። የቦንብ አደጋ የደረሰባቸው ጎዳናዎች ዘወትር በትራፊክ መጨናነቅ የሚታወቁ ናቸው። ነገር ግን የቦንብ አደጋዉ ከመድረሱ ጥቂት ቀናት በፊት ጎዳናዎቹ የነበራቸው የትራፊክ ፍሰት የሚያሳየው፥ እነዚህ ጎዳናዎች ያለወትሯቸው ጭር ማለታቸውን ነዉ። ግን ለምን? የፈንጂ ጥቃት ሰንዛሪዎቹ የአካባቢዉ ሰዎች ናቸው። በመሆኑም የአካባቢዉ ነዋሪዎች ስለታሰበዉ የፈንጂ ቅጣት መረጃ ስለሚደርሳቸው እነዚህ ጎዳናዎች ይርቃሉ። በዚህም ጎዳናዎቹ ጭር ይላሉ። በዚህ ሁኔታ በትራፊክ የተሰላቹና የቸኮሉ የአሜሪካን እንግዳ ወታደሮች፥ ጭር ያለ መንገድ ሲያገኙ ደስታቸው ወሰን የለውም። ያላወቁት ግን ጭር ያለ መንገድ ሁሉ የህይወት መንገድ አለመሆኑን ነዉ።

ጠበቃው መፍትሄዉን አገኘ። በምንም መልኩ ጭር ያለ መንገድን አለመጠቀም። ቢያዘገየዉም ጉዞዉን አሰቀድሞ በመጀመር፥ ምስክሮች በሰአቱና በደህና ፍርድ ቤት ደርሰው እንዲመሰክሩ ማድረግ አስቻለው። የባግዳዱን ስራ ጨርሶ አገሩ ሲመለስ የተመለሰው ወደ ጥብቅናው አልነበረም። በተለያዩ ድርጅቶች የተሰበሰቡ መረጃዎችን በመሰብሰብና በማቀላቀል፥ የሕዝብ አስተዳደር ችግሮችን እና መፍትሄዎችን በመለየት በወቅቱ የኒዉዮርክ ከተማ ከንቲባ ሆነዉ የተመረጡትን ማይክል ብሉምበርግ ማገዝ ነበር። ለምሳሌ፥ የኒዉዮርክ ከተማ እሳት ማጥፋት አገልግሎት የሚሰጠዉ ድርጅት፥ ከማጥፋት በተጨማሪ የእሳት አደጋን የመቀነስ ስራ ይሰራል። ይህን የሚያደርገዉ በከተማዉ ያሉ ህንጻዎችን እና ቤቶችን በኢንስፔክሽን እየገመገመ፥ የጥንቃቄ እርምጃዎች በነዋሪዎቹና ባለቤቶቹ እንዲወሰዱ በማድረግ ነዉ። ለዚህ ኢንስፔክሽን ስራ ያለው የሰዉ ሃይል ውስን ነዉ። ጥያቄዉ ይህን ዉስን የሰዉ ሃይል እንዴት ይደልደል? ሁሉንም ህንጻዎች በአመት እኩል ያህል መጠን ምን ያህል ለአሳት አደጋ እንደተጋለጡ መመርመር ይሻላል? ወይስ በሌላ መልኩ? በምን መልኩ? በወቅቱ የተከተሉት ስልት ብዙ ጥቁሮችና ድሃዎች የሚኖርባቸውን አካባቢዎች የበለጠ ትኩረት መስጠት ነዉ። ግን ትክክል ነዉ? ይህን ለመወሰን መረጃ ያስፈልጋል። ጠበቃዉ በከተማው እስካሁን የደረሱ የእሳት አደጋዎችን አስመልክቶ መረጃዎችን አገኝ። ምን አይነት አደጋ? በምን ምክንያቱ? የጉዳቱ መጠን? እንዲሁም በፍተሻ ስራዎች የተስበሰቡ መረጃዎችን አሰቀረበ። እንዲሁም እያንዳንዱን በከተማዉ ያለ ህንጻና ቤትን አስመልክቶ መረጃ ሰበሰበ። መቼ ተገነባ? ለምን አገልግሎት ይዉላል? ስንት ነዋሪዎች? ተጨማሪ መረጃ ከተባይና የቤት እንሰሳ ተቆጣጣሪ የከተማዉ ድርጅቶች መረጃ አገኘ። ብዙ አይነት ታሪካዊ መረጃዎች ከተለያዩ የከተማዉ መስተዳድር ድርጅቶች ሰበሰበ። ደግነቱ የአሜሪካን ድርጅቶች መረጃ በመሰብሰብ የሚደርስባቸው የለም። ችግሩ በተለያየ ድርጅቶች በአመታት የተሰበሰቡት መረጃዎች መነጣጠል ነበር። እሱ ደግሞ እነዚህን በማገናኘት የከተማዉ መስተዳድር ራስ ምታት የነበሩ ችግሮችን መፍታት ስራዉ አድርጎ ያዘዉ።

14 views
  • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.