• Dr. Mulugeta Mengist

ዶሮወንዝ የማን ነዉ?

Updated: Nov 17, 2019

ዶሮወንዝ የአንድ ትንሽ ወንዝ ስም ነዉ። ስለዚህ የማን ነዉ? በሕገመንግስቱ መሰረት የኢትዮጲያ ሕዝቦች የጋራ ሃብት ነዉ። ለኢትዮጲያ ሕዝቦች የጋራ ጥቅም በሚያበዛ መልኩ መንግስት ዶሮወንዝን ያስተዳድራል። የትኛዉ መንግስት? የፌዴራሉ መንግስት ምክንያቱም ዶሮወንዝ ፉጣንን፣ ፉጣን ደግሞ በሽሎን፣ በሽሎ ደግሞ አባይን ስለሚቀላቀል።

ዶሮወንዝ ግን ከወንዝ ስምነት አልፎ የመንደር ስም ነዉ። መንደሩ የማን ነዉ? መንደሩ ስንል ጎጆ ቤቱ ከሆነ፣ ዶሮወንዝ የነዋሪዎቹ ነዉ። መንደሩ ስንል መሬቱ ከሆነ፣ ዶሮ ወንዝ የኢትዮጲያ ሕዝቦች የጋራ ሃብት ነዉ።

ዶሮወንዚያን የማን ናቸዉ? የራሳቸዉ። ሰዉ ባለቤት የለዉም። ግን ምንድን ናቸዉ? አማራ? ኦሮሞ? ቅማንት? ጉራጌ? እንዲህ የሚባል ነገር የለም። እያንዳንዱ የዶሮወንዝ ነዋሪ ማንነቱን ይምረጥ። ምርጫ ነዉ። ይሄ በጥናትም ይሁን በድምፅ ብልጫ አይወሰንም።

ዶሮ ወንዝ የትኛዉ ክልል ይካለል? በተለይ በሁለት ክልሎች መሃል ሲሆን። በዚህ ጊዜ በነዋሪዎቹ ፈቃድ ይወሰናል። የክልል ዉሳኔ የባለቤትነት ወይም የማንነት ዉሳኔ አይደለም። እንዲሁም ይህ ዉሳኔ ላንዴና ለመጨረሻ የሚሰጥ አየደለም። በየጊዜዉ እየተነሳ ሊወሰን ይገባዋል።

ታዲያ ምን ሆነን ነዉ? በተዘሩ የአረም ዘሮች የተነሳ እና የፌዴራል መንግስቱ ስንፈት ነዉ።

አንደኛ የክልሉ ባለቤቶች እያሉ በህገመንግስታቸዉ ሲደነግጉ ሕገመንግሰቱን የማሰከበር ሃላፊነቱን አለመወጣቱ።

ሁለተኛ የመሬትና የተፈጥሮ ባለቤትነት የእከሌ ብሄር ነዉ እያሉ ክልሎች ሲያዉጁም ጭምር የፌዴራል መንግስቱ በዝምታ አልፎታል።

ሶሰተኛ፣ የወሰን ጥያቄን የማንነት ጥያቄ ነዉ በሚል አብሮ አስተሳሰብ ማደፍረሱ።

አራተኛ፣ ማንነት የግለሰብ ምርጫ ሳይሆን በድምፅ ብልጫና በጥናት የሚወሰን ይመስል አብሮ አሰተሳሰብና አሰራር ማደፍረሱ።

አምሰተኛ፣ ህዝብ አሰተዳደር ማለት የግለሰቦችና የቡደኖችን ደህንነት ማሰጠበቅ፣ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ ነዉ። ምን አይነት አገልግሎትና በምን ያህል ጥራትና መጠን እና ዋጋ? እንደ አካባቢዉ ይለያያል። ለዛ ነዉ ያልተማከለ ዴሞክራሲያዊ አሰተዳደር የሚያሰፈልገዉ። በዚህ ቋንቋና ባህል ብዙም ግንኙነት የለዉም። ታዲህ ህዝብን ለማሰተዳደር በብሄር መደራጀት ምን አመጣዉ?

ባህልና ቋንቋ ለጭቆና ዉሏል። የሰዉ ልጆች ታሪክ ይህን ያሳያል። ጨቋኞቹ ብቻቸዉን አቅም ሰለሚያጡ፣ በመደብ የማይመሰሏቸውን ነገር ግን በቋንቋ እና ባህል የሚመስሏቸዉን ያሰልፉበታል። ቢርብህም እንኳ የበላይ የሆነ ታሪክ ቋንቋና ባህል አለህ! ተጨባጭ ጥቅሙ ግን የጨቋኙ መደብ ብቻ ነዉ። ከጨቋኙ ጋር የጋራ ቋንቋና ባህል ቢኖራቸዉም በመደብ ግን የሚለዩት አንደኛዉ ተጨቋኝ ነዉ። ሁለተኛዉ፣ በመደብ ብቻ ሳይሆን በቋንቋና ባህልም የሚለዩ ተጨቋኞች ናቸዉ። ሁለተኛዉ ጨቋኝ ከዋናዉ ጨቋኝ ጋር የመደብ አንድነት ቢኖረዉም፣ የቋንቋና የባህል አንድነት የለዉም። ነገር ግን በጊዜ ሂደት፤ በትምህርትና ልምምድ የቋንቋና ባህል አንድነትን ሊያገኙ ይችላሉ። የመደብ አንድነታቸዉ ግን የመጠን አንድነትን አያሳይም።

በዚህ መሃል ተጨቋኞች ትግል ይጀምራሉ። ትግሉ በመደብ ከተመሰረተ ሁለቱንም ተጨቋኞች ያቅፋል፣ ሁለቱንም ጨቋኞች እንደ ጠላት ይቆጥራል።

ትግሉ በቋንቋና ባህል ላይ ከተመሰረተ፣ አንደኛዉ ተጨቋኝ አንደኛዉን ጨቋኝ ብቻ ይታገላል።

የዚህ ዉጤት ሁለት ታጋዮች። አንደኛዉ፤ በመደብ ተመሰርቶ ሁለት ጨቋኞችን የሚታገል። ሁለተኛዉ፤ በባህልና ቋንቋ ተመስርቶ አንዱን ጨቋኝ ብቻ የሚታገል። ይህኛዉ ሁለት አይነት ነዉ። አንደኛዉ የኛም ባህልና ቋንቋ አያንስም። ሁለተኛዉ እንደዉም ይበልጣል የሚል ነዉ። ጭቆና ሳይሆን የጨቋኙ ማንነት ነዉ ወሳኙ ነገር። ሰለዚህ እድል ሲቀናዉ ይህኛዉ ታጋይ ጨቋኝ ሊሆን ይችላል።

ትግሉ በመደብ አንድነት ላይ ቢመሰረት ዘላቂ ዋሰትና ያለዉ ለዉጥ ይመጣል። በባህልና ቋንቋ አንድነት የተመሰረተ ትግል ዉጤታማ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ከድል በኋላ መሰረቱን ወደ መደብ ማስፋት ይኖርበታል።

ሁለቱም ታጋዮች ሊተባበሩ ይችላሉ። ነገር ግን መሰረታቸዉን ሳይቀይሩ የሚደረግ ትብብር የታክቲክ ነዉ። ከትግሉ ማዶ ግን የተለያየ መሰረት ይዞ መቀጠል አይቻልም። ወደ መደብ መሰረትነት መምጣት ይኖርባቸዋል። የሆነዉ ግን እንደዉም መደብን መሰረት አደርጎ የታገለዉ፤ ከድል በኋላ የሌላዉን ታጋይ መሰረት በጉዲፈቻነት መዉሰዱ ነዉ። በዚህ ጊዜ አንድነታችን የመደብ ነዉ የሚለዉ ማሰመሰያ ነዉ። የገበሬ ፓርቲነት፣ አብዮታዊነት፣ ዴሞክራሲያዊነት፣ ልማታዊነት እነዚህ ሁሉ ባዶ ቃላት ይሆናሉ።

ባህልን እና ቋንቋን የሙጥኝ ማለት የድሮዉን ጨቋኝ በአዲሰ መተካት ነዉ። በዚህ መሃል የቋንቋን እና ባህል አንድነትን እንደ ግላዊና የጋርዮሽ ኑሮ መመሪያ ካደረከዉ፣ አንተ የጭቆና መሳሪያ ነህ ማለት ነዉ። የሌላ መደብ መጠቀሚያ። በወኪል የምትረካ ሰዉ። Public administration that satisfies vicariously. የተኛችው እያለች ያዳመጠችዉ አረገዘች።

እና የመሳሰሉት የታሪክ እግረሙቆች፣ ጣኦቶች፣ አሰራሮችና አመለካከቶች ማሰተካከያ ይፈልጋሉ። ራስን ከነዚህ አሰተሳሰቦች ነፃ ማዉጣት ግን ለሌላዉ ብለህ የምታደርገዉ አሰተዋእፆ አየደለም። ለራስህ ብለህ እንጂ። መሳሪያ እንዳትሆን። የራስህን ወኪልነት፣ ሰዉነት ላለማጣት። የራሰህን ወኪልነት ሰታረጋገጥ፣ ለሌላም ትተርፋለህ።

Recent Posts

See All

የሽግግር መንግስት ህገመንግስታዊ ነው?

የዶር መሃሪ ታደለን ፅሁፍ አነበብሁት። https://meharitaddele.info/2020/05/the-limits-of-legal-solutions/ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው ለመንግስት ተጨማሪ ስልጣን በመስጠትና መብቶችን በመገደብ በሽታውን ለመዋጋትና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ ከሆኑ ብቻ ነው። መንግስ

  • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.