• Dr. Mulugeta Mengist

ያልተላመጡ ሃሳቦች ስለሰንደቅ ዓላማ

Updated: Nov 17, 2019


ሕገመንግስቱ የሃገራችንን ሰንደቅ ዓላማ አስመልክቶ እንዲህ ይላል።

የኢትዮጲያ ሰንደቅ ዓላማ ከላይ አረንጓዴ፥ ከመሐል ቢጫ፥ ከታች ቀይ ሆኖ በመሐሉ ብሔራዊ ዓርማ ይኖረዋል። ሦስቱም ቀለማት እኩል ሆነው በአግድም ይቀመጣሉ።

ከሰንደቅ ዓላማው ላይ የሚቀመጠው ብሔራዊ ዓርማ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች እና ሃይማኖቶች በእኩልነትና በአንድነት ለመኖር ያላቸውን ተስፋ የሚያንጸባርቅ ይሆናል።

ምንም እንኳን የዓርማው አይነት በሕገመንግስቱ ባይገለጽም፥ የዓርማው ትርጉም ግን ተቀምጧል። ይህም በእኩልነትና በአንድነት የመኖር ተስፋ ነው።

ዓርማዉን መቃወም የግድ በእኩልነትና በአንድነት የመኖር ተስፋን መቃወም ተደርጎ ሊወሰድ አይገባም። እኩልነትና አንድነትን በሌላ ዓርማ ልንወክላቸውን እንችላለን። እንዲሁም ዓርማውን መቃወም ሕገመንግስቱን መቃወም ተደርጎ ሊወሰድ አይችልም፥ አይገባም። ከላይ እንደተገለጸው ሕገመንግስቱ ስለዓርማው መኖርና ትርጉም እንጂ ስለዓርማው አይነት አይደነግግም።ሕገመንግስቱን ሳይቀይሩ የዓርማውን አይነት ግን መቀየር ይቻላል።

ዓርማ አይኑርበት ብሎ መቃወም ይቻላል። ነገር ግን በመንግስት የሚሰቀሉ፥ የሚያዙ፥ የሚቀመጡ ሰንደቅ ዓላማዎች ሕገመንግስቱ እስካልተቀየር ድረስ የግድ አርማ ሊኖርባቸው ይገባል። እንዲሁም አሁን ያለው አርማ በሕጋዊ መንገድ እስካልተቀየረ ድረስ፥ በመንግስት የሚሰቀሉ፥ የሚያዙ፥ የሚቀመጡ ሰንደቅ ዓላማዎች ሊኖራቸው የሚገባ ዓርማ አሁን ያለው ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳል፥ በግለሰቦች የሚያዙ፥ የሚሰቀሉ፥ የሚቀመጡ፥ የሚውለበሉ ባንዲራዎች ዓርማ ሊኖራቸው ይገባል ወይ? ካላቸው ደግሞ የአሁኑን ዓርማ ብቻ እንዲጠቀሙ ይገደዳሉ ወይ? ይህን አስመልክቶ የወጣ አዋጅ፥ አሁን ያለውን ዓርማ የማካተት ግዴታ ይጥላል። ስለዚህ በሕግ ደረጃ አስገዳጅ ነው።

ጉዳዩ ግን የዚህ ሕግ አግባብነት ነው? አንደኛ ሃሳብን በነጻነት ከመግለጽ የግለሰቦች ነፃነት ጋር ይጋጫል። ሕገመንግስቱ እንዲህ ይላል። ማንኛውም ሰው ያለምንም ጣልቃ ገብነት የመሰለውን አመለካከት ለመያዝ ይችላል። ማንኛውም ሰው ያለምንም ጣልቃ ገብነት ሀሳቡን የመግለጽ ነፃነት አለው። ይህ ነፃነት በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ወሰን ሳይደረግበት በቃልም ሆነ በጽሑድ ወይም በሕትመት፥ በሥነ ጥበብ መልክ ወይም በመረጠው በማንኛውም የማሰራጫ ዘዴ፥ ማንኛውንም ዓይነት መረጃና ሀሳብ የመሰብሰብ፥ የመቀበልና የማሰራጨት ነጻነቶችን ያካትታል። ሰንደቅ አላማ፥ የአላማ መግለጫ ነው። ሃሳብ መግለጫ ነው። ምንም ሰው ደግሞ የመሰለውን ሃሳብ መያዝ ይችላል። ይህን ሃሳቡን ደግሞ በተለያየ መልኩ የመግለፅ ነፃነት አለው።

ሁለተኛ፥ በሕግ አርማ የሌላቸውን ሰንደቅ ዓላማዎችን በማፈን፥ ባለዓርማውን ሰንደቅ አላማ የበላይነት እንዲኖረው ማድረግ አይቻልም። እንደውም ዓርማ የለሹ ባንዲራ የብዙ ተቃውሞዎች አጭር መግለጫ ተደርጎ እንዲወሰድ ያደርጋል።

ሶስተኛ፥ በታሪክ ሂደት ብዙ አይነት ሰንደቅ ዓላማዎች ታይተዋል። ዓርማ የሌላቸውና ያላቸው። ዓርማ የሌላቸውን እና የተለየ ዓርማ ያላቸውን ሰንደቆች መከልከል፥ ታሪክን የመሰረዝ ያህል ነው። ከታሪካችን ልንቆራረጥ አንችልም። አይገባም። ታሪካችን ትምህርት ነው። ታሪካችን ግን ሊያስረን አይገባም። አዲስ ጅምር፥ ታሪክን በመርሳት ወይም በማጥፋት አይመጣም። የሰውነታችን መገለጫ እኮ ታሪካችን ላይ እየጨመርን መሄዳችን እንጂ፥ ሁልጊዜ እንደ አዲስ መጀመራችን አይደለም። የዝንብ ኑሮ የማይሻሻለው እያደር አዲስ መሆኗ ነው። ከባለፈው የዝንብ ትዉልድ ልምድ በመነሳት፥ እሱ ላይ ጨምራ አትሄድም። እያንዳንዷ ዝንብ እንደ አዲስ ትጀምራለች። በሃገራችን የዝንባዊነት አዝማሚያ በብዙ መልኩ ይገለጣል።

አራተኛ፤ የሰንደቅ አላማ ትርጉሙና ጥቅሙ፥ ሰንደቁ ላይ ሳይሆን ዓላማው ላይ ነው። ዓላማው ደግሞ በተግባር በወረቀት ብቻ ሳይወሰን በተግባር ሲፈጸም፥ ጥበቃ ሲደረግለት፥ ሰንደቅ ባይኖረውም ደጋፊዎችን ያፈራል። ዓላማው በወረቀት ብቻ ከተወሰነ፥ ጥበቃ ካልተደረገለት፥ አላማውን ለማስፈፀም በየጊዜው ተጨባጭና ዉጤታማ እርምጃዎች ካልተተገበሪ፥ ለአላማው ወኪል ሰንደቅ ብታቆምለትም፥ የሰንደቅ ዓላማውን ተቀባይነትን ግን አያረጋግጥም።

እኔ ብዙም በዚህ ጉዳይ መጨነቅ አልፈልግም። ዋናው ጉዳይ በሕገመንግስቱ የተካተቱ መብቶችና አሰራሮችና አደረጃጀቶችን በተግባር ማዋል ነው ዋናው ቁም ነገር።

Recent Posts

See All

የሽግግር መንግስት ህገመንግስታዊ ነው?

የዶር መሃሪ ታደለን ፅሁፍ አነበብሁት። https://meharitaddele.info/2020/05/the-limits-of-legal-solutions/ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው ለመንግስት ተጨማሪ ስልጣን በመስጠትና መብቶችን በመገደብ በሽታውን ለመዋጋትና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ ከሆኑ ብቻ ነው። መንግስ

  • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.