• Dr. Mulugeta Mengist

የድርጅት መበስበስና መታደስ

Updated: Nov 17, 2019ገብረጉራቻ ነበርሁ። በሰሜን ሸዋ ዞን ላሉ ዳኞች በተዘጋጀዉ ስልጠና ላይ በመገኘት የሕግ የበላይነትና የፍርድ ቤቶች ሚናን አሰመልክቶ ሃሳቤን አካፍየ ተመለስሁ። ወደ አዲስ አበባ ስመለስ መንገድ ላይ፣ እንደሚከተዉ ተቆላጨሁ!

*****

ድርጅት ማለት የሰዎች ስብስብ ነዉ። ነገር ግን ድርጅቱ፤ ከሰበሰባቸዉ ሰዎች የተለየ፤ ሰዉነት አለዉ። የድርጅት ሰዉነት፤ ሕግ ለሰዉ ልጆች እድገት ካበረከታቸዉ ጠቃሚ ልብወለዶች፤ አንደኛዉ ነዉ።

****

ድርጀቱ እንደ ሰዉ ይከሳል፥ ይከሰሳል። የንብረት መብት ይኖረዋል። ዉል ይዋዋላል። የደርጅቱ ንብረትና ዉል ከሰበሰባቸዉ ሰዎች ንብረትና ዉል ይለያል። ሰዉ ይሞታል። ድርጅትም ሊፈርሰ ይችላል። ነገር ግን ስለ ሰዉ ሞት እርግጠኛ እንደምንሆነዉ፤ ሰለድርጅት መፍረሰ እርግጠኛ መሆን አንችልም። በአለም ረጅም እድሜ ያስቆጠረዉ ድርጅት የትኛዉ እንደሆነ ባላዉቅም፤ ድርጅቶች ረጅም ጊዜ የመቆየት እድል እንዳላቸው ግን እርግጠኛ ነኝ።

በሰዎች ሞት ምክንያት የሚመጣን የንብረት መበጣጠስና የኤኮኖሚያዊ፥ ማህበራዊና፥ ፓለቲካዊ እንቅስቃሴዎች መቋረጥን፣ ድርጅታዊ አሰራር ይቀርፈዋል። ****

በሚገባ የተደራጀና የሚመራ ድርጅት ያለዉ አቅም በማንኛዉም ጊዜ ከሰበሰባቸዉ ግለሰቦች አቅም ድምር በላይ ነዉ። እንደዉም ደርጅት የሰዎችን አቅም የማባዛት አቅም አለዉ። ይህን ለማድረግ የሚከተሉትን ስልቶች ይጠቅማሉ

 1. ሰዎችን በስራ ቡደኖች ማደራጀት። እያንዳንዱ ቡድን በግልፅ በተለየ ስራ ላይ ማተኮር። በዚህም አቅም ይበዛል። ምርት ይጨምራል። ስፔሻላይዜሽን ምርትን ይጨምራል።

 2. እያንዳንዱ ቡድን በራሱ ብቻዉን የሚያመርተዉ ምርትና አቅርቦት የለም። የድርጅቱ ምርቶች የሚመረቱት እነዚህ የስራ ቡድኖች በሚያደርጉት ትብብርና ቅብብሎሽ ነዉ።

 3. ለዚህ ትብብርና ቅብብሎሽ ዉጤታማነት የመረጃ ፍሰቱ ነፃነት ትልቅ አስተዋእፆ አለዉ።

 4. የእያንዳንዱ ቡድን ስራ በዝርዝር መመሪያዎችና ማኑዋሎች ያገዛል። የላቀ እዉቀትና ልምድ ያላቸዉን ሰዎች በጥራት ቁጥጥርና በተቋም ግንባታ ላይ ማሰማራት።

 5. በሰራ ሂደት የሚገኙ የተሻሻሉ አሰራሮችና መረጃዎችን ተቋማዊ ማድረግ። በመሆኑም በድርጅቱ ሰርቶ ያለፈ ሁሉ ልምዱን ለቀጣዩ ትዉልድ ጥሎ ያልፋል።

 6. አንዳንድ ቡድኖች የድርጅቱ ማእከሎች ናቸዉ። ለምሳሌ የሃብት አሰተዳደር፥ እቅድ፥ ክትትል ቡድኖች። የእነዚህ መጠናከር ድርጅቱን ያልቀዋል።

 7. የድርጅቱ ሰራተኞችና ቡድኖች የአላማ አንድነት ሊኖራቸዉ ይገባል።

 8. እና የመሳሰሉት

ስለድርጅት ጥቅም ስናወራ አደጋዎቹንም መርሳት የለብንም

 1. ጣኦት አምላኪነት። ድርጅቱን እና የተዘረጉ አሰራሮችን በጊዜ ሂደት እንደ መሳሪያ ሳይሆን እንደ ግብ መዉሰድ።

 2. የመበስበስ አደጋ። ራስን ከለዉጥ ጋር አብሮ አለማስኬድ።

 3. አክራሪነት። በአንድ ድርጅት የተሰበሰቡ ሰዎች የሚጋሯቸዉ የጋራ እምነቶች አሉ። በጊዜ ሂደት እነዚህ ሰዎች በእምነታቸዉ አክራሪ ይሆናሉ። ይህም እይታቸዉን እና ዉሳኔዎቻቸዉን ይገድበዋል፥ ይጋርደዋል።

እነዚህን ችግሮች መፍታት ያሰፈልጋል። እንዴት?

 1. የድርጅቱን ማንነት የሚወስነዉን ጉዳይ መለየት። ይሄ ከተቀየረ የድርጅቱ ማንነት ተቀየሯል የሚያስብለዉን መለየት። በመጠን ትንሽ መሆን አለበት። መጠኑ በበዛ ቁጥር የመበሰበሰ አደጋዉ ይጨምራል። ከዚህ የተረፈዉ በሙሉ የሚቀየር መሆን አለበት።

 2. ድርጅቱ ማንነቱን ለመጠበቅ፣ ሌላዉን ደግሞ ለመለወጥ የሚያሰችሉ አሰራሮችን መዘርጋትና መተግበር። የድርጅቱ ማእከሎች በዚህ ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። አስፈላጊ ለውጦችን አነፍንፎ የሚተገብር ቡድን እና አስራር ያስፈልጋል። እንዲሁም የድርጅቱን ማንነት ጠብቆ ለመቆየት የሚያስችሉ አሰራሮች ያስፈልጋሉ።

 3. ድርጅቱን ከአክራሪነት የሚጠብቅ “የሰይጣን ጠበቃ” አሰራርን መተግበር። ይህ አስራር ዋናው ሚናው በድርጅቱ ተቀባይነት ያገኙ ጉዳዮችን ሆን ብሎ መሞገት ነው።

 4. ዋና ዋና የፓሊሲ ዉሳኔዎች ፍሬን ተኮር ባደረገ ግምገማ መታገዝ አለባቸው። የድርጅቱ ዉሳኔዎች ሙሉ ለሙሉ መልክ ተኮር ከሆኑ ድርጅቱ የመበስበስ አደጋ ተጋርጦበታል።

 5. የድርጅቱ ሰራተኞች በወጣት ሰራተኞች የሚተኩበት አሰራርን መዘርጋት። በተለይ ድርጅቱ የተሰማራበት መስክ በፈጣን ለዉጦች የሚታወቅ ከሆነ፣ ነባር ሰራተኞች ቶሎ ቶሎ መቀየር አለባቸዉ። በተለይ ራሳቸዉን ለመለወጥ ፈቃደኛ ያልሆኑትን። የፈቃድ ጉዳይ ብቻም አይደለም። የአቅምም ጭምር እንጂ። “ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” ይባላል። ፈቃደኛ ስላልሆነች ብቻ አይደለም። አመሏን መርሳት ብትፈልግም ስለማትችል ነዉ። መተካካት ለወጣቱ እድል የመስጠት ጉዳይ ብቻ አይደለም። መተካካት የህይወት መንገድ ነዉ። ሌላዉ የመበስበስና የሞት ነዉ።

ይህን ስጨርስ አዲስ አበባ ቤቴ ደረስሁ። ከመታደስና መበስበስ ጋር የተያያዘ ነገር ግን ስለድርጅት ሳይሆን ስለ ሰዉ የፃፍኩትን ደሞ ከዚህ በታች ታገኙታላቹ።

መታደስና መበስበስ

******

መታሰቢያነቱ፣ እንዴት ነው በተወሰኑ ወራት ከቦርጮ ወደ ቀጮ የተሸጋገርኽው ብላቹ  ለጠየቃችሁኝ!

ሚስጥሩን “እናስከሳለን። ጆሮም አንበሳለን። ስቴሽነሪም እናቀርባለን።” በሚል መሪ ቃል፥ ቢዝነስ ልከፍትበት አስቤ ነበር። በኋላ አዲስ የተሻለ የንግድ ሃሳብ ስለተከሰተልኝ፥ “ሚስጥሩን አደባባይ ይሙቀው” በሚል ሌላ መሪ ቃል እዚህ ለጥፌዋለሁ።

*********

ሰው በሴሎች ተዋቅሯል። ሴሎች ይፈጠራሉ፥ ያረጃሉ፥ ይወገዳሉ። አርጀተው ካልተወገዱ ካንሰር ወይም ሌላ በሽታ ያመጣሉ። ማነው የሚያስወግዳቸው? ያረጁ ሴሎችን የሚያስወግድ ስርአት አለ። ማነው አዲስ ሴሎችን የሚፈጥረው? አዲስ ሴሎችን የሚፈጥር ስርአት አለ።

የማስወገዱም ሆነ አዲስ ሴል የመፍጠር ስርአቱ፥ 24 ሰአት የሚሰራ ስርአት አይደለም፥ ልክ እንደ አተነፋፈስ ስርአት። ሰው ሁሌ መተንፈስ አለበት። ሳይተነፍስ ሊቆይ የሚችለው  ትንሽ ወቅት ብቻ ነው። ስለዚህ የአተነፋፈስ ስርአታችን 24 ሰዓት መስራት አለበት። ነገር ግን 24 ሰአት አዳዲስ  ሴሎች መፈጠር ያረጁ ሴሎች ደግሞ  መወገድ የለባቸውም። ነገር ግን በየወቅቱ ይህ ሊከናወን ይገባል። በዛ ላይ 24 ሰዓት መስራት ያለባቸው የሰውነት ስርአቶች ብዙ አሉ። ሁሉም የሰዉነት ስርአቶች 24 ሰዓት ቢሰሩ ግን ልንግል፥ ልንጨስ እንችላለን። ብዙ ጊዜ ሻወር መውሰድ የግል ይል ነበር።  ስገምት ነው። በዛ ላይ የምንፈጀውን ምግብ አስቡት።

ጥያቄው፤ ሰውነታችን እንዴት ነው የሚያውቀው? አሁን አዲስ ሴል መፍጠር እንዳለበት? አሁን ደግሞ ያረጁትን ማስወገድ እንዳለበት? የተለያዩ የስውነት ስርአቶችና ብልቶች መረጃ፥ ትእዛዝ፥ ግብረመልስ የሚቀባበሉት በሆርሞኖች ነው። ምግብ ስትበላ፥ ቆሽትህ የሚያመነጨው ሆርሞን (ኢንሱሊን) አለ። ይህ ሆርሞን ሲመነጭ፥ ሰውነትህ ምግብን ወደ ግላይኮጅን መቀየር ይጀምራል። በቂ ግላይኮጅን ካለ፥ የተረፈውን ወደ ስብ ይቀይረዋል።

ስብ ማለት በረዶ ቤት በለው። ግላይኮጅን ደግሞ ማቀዝቀዣ። በቅርብ የማትፈልገውን ስጋ፤ በረዶ ቤት እንደምታስቀምጠው። ስለዚህ ግላይኮጅኑን ሳይጨርስ ወደ ስብ ማቃጠል አይሄድም። ታዲያ እንዴት ነው ስፓርት መስራት ቦርጭ የሚቀንሰው? ስፓርት ስትሰራ ሃይል ትፈልጋለህ። ሰውነትህ ሃይሉን ከማቀዝቀዣው ይወስዳል። እሱ ሲያልቅ ወደ በረዶ ቤት ይገባል። ስለዚህ ስፓርት ቦርጭ የሚቀንሰው፥ ስብ የሚያቃጥለው ማቀዝቀዣ ቤት ያለውን ግላይኮጅንን እንዲጨርስ አድርገኽው ወደ በረዶ ቤት እንዲሄድ ስታደርገው ብቻ ነው።

ስለዚህ ኢንሱሊን መልእክት/መረጃ ነው ለሰውነትህ። ኢንሱሊን መጠንህ ዝቅ ካላለ፥ ስብ አይቃጠልም።  ኢንሱሊን መጠንህ ዝቅ እንዲል ደግሞ ማቀዝቀዣ ያለው ግላይኮጅን ሲያልቅ ነው። ኢንሱሊን የሚመነጨው ምግብ ስትበላ ነው። ሲመነጭ ምግብን ወደ ግላይኮጅን መቀየር ይጀምራል። ግላይኮጅን ሲያልቅ ኢንሱሊን ይቀንሳል።  ኢንሱሊን ሲቀንስ ደግሞ ሰውነትህ ስብ ማቃጠል ይጀምራል። ችግሩ ስብ እና ጡንቻን መለየት አይችልም። ስለዚህ ሁለቱንም ሊያቃጥላቸው ይችላል። ጡንቻህ መቃጠል እንደሌለበት መልእክት ካልተላፈለት። ይህኛው መልእክት የሚተላለፈው ጡንቻህን በመጠቀም ነው። ጡንቻ የሚጠይቁ እንቅስቃሴዎች በማድረግ።

የኢንሱሊን መጠን ስብ የማቃጠል ሂደትን ብቻ አይደለም የሚያነሳሳው። አርጌ ሴሎችን የማስወገድ ስርአትንም መልእክት ያስተላልፋል። ኢንሱሊን መጠን ከፍ ባለበት ሰአት አሮጌ ሴሎችን የማስወገድ ስርአቱ ስራ አይጀምርም። ኢንሱሊን መጠኑ ዝቅ ማለት አለበት። ምክንያቱም የሴል ማስወገድ ስርአቱን የሚያስጀምረው ሌላኛው ሆርሞን የሚመነጨው፤ የኢንሱሊን መጠን ዝቅ ባለበት ጊዜ ብቻ ነው። አሮጌ ሴሎችን የምናስወግድበት ሁለት መንገድ አለ። አንደኛው እንደ ማንኛውም ቆሻሻ ማስወገድ ነው። ሁለተኛው አሮጌ ሴሎችን ሰውነታችን አቃጥሎ ሃይል ሊያመነጭባቸው ይችላል። ልክ እንደ ረጲ ከቆሻሻ ሃይል ማመንጫ ፕሮጀክት።

አዲስ ሴሎች የሚፈጠሩት በፕሮቲን ነው። ስለዚህ ፕሮቲን መብላት ያስፈልጋል። ከሆርሞናል መረጃዎቹ በተጨማሪ። ባጭሩ ስብ ለመቃጠል፥ አሮጌ ሴሎችን ለማስወገድ፥ አንዳንዴ ከምግብ ራሳችንን ማቀብ አለብን። ጨጓራችንን እረፍት መስጠት። አዲስ ሴል ለመገንባትም ቢሆን ጨጓራችንን እረፍት መስጠት ያስፈልጋል። አዎ አዲስ ሴል ለመገንባት ፕሮቲን ያስፈልጋል። ነገር ግን ጊዜ የለኝም፥ አዲስ ሴል መገንባት የህልውና ጉዳይ ነው፥ ያለበለዚህ ይህ ሰውነት እርስ በርሱ ይባላል፥ ይበታተናል በማለት በላይ በላዩ ፕሮቲን ብትበላ፥ ዉጤቱ አዲስ ሴል ይሁን ቦርጭ እርግጠኛ መሆን አትችልም። አዲስ ሴል ቢሆንም እንኳ፥ ያረጀው ሳይወጣ አዲስ ሴል መገንባት ትርጉም አይኖረውም። ያረጀው ሴል ካንሰር ከሆነ፥ በሱ ልክ አዲስ ሴል ብትገነባም፥ የካንሰሩን እኩይ ጎን ባዲሱ ሴል ልታጠፋው አትችልም። ባሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይን መክተት ነው የሚሆነው። አቁማዳው ይቀደዳል። ጊዜ የለኝም በሚል ፍሬኑን አውልቆ የጣለ ሹፌር፥ አድራሻው ገደል ይሁን ከፍታ እርግጠኛ መሆን አይቻልም። እረፍት፥ መረጋጋት፥ ከምግቡ ላላ ማለት ወሳኝ ነው።

 • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.