• Dr. Mulugeta Mengist

የአዲስ አበባ ሚኒባስና የፈረንጅ ላም! አንዳንድ ጉዳዮች ስለግብርና እድገት

Updated: Nov 17, 2019

1.   መግቢያ

ነጋዴዎች፣ ባላሃብቶች፣ ኢንቨስተሮች ልዩነታቸዉ ምንድን ነዉ?

ይሄንን ለመመለስ አይደለም። ይሄን መነሻን አድርጌ ስለሌላ ላወጋ ነው። ወሬን ወሬ ያነሳዋል እንዲሉ።

በልማት ወደ ኋላ በቀሩ ሀገራት፣ የገንዘብ ካፒታል ችግር እንዳለ ይታመናል። እድገታቸዉን ከገደቡት ነገሮች አንዱ፣ የገንዘብ ካፒታል እጥረት እንደሆነ ይታመናል። አለም አቀፍ ተቋማት ገንዘብ በማቅረብ እና የዉጭ ኢንቨስትመንትን በማበረታታት ሊያግዧቸው ይሞክራሉ። እነሱም በዚህና ሌሎች የገንዘብ ካፒታል ማከማቻ ስራዎች (ለምሳሌ የዉጭ ንግድን እና ቁጠባን በማበረታታት) ይተጋሉ።

ችግሩን የሚያብሰው ደግሞ ያላቸውም ትንሽ ካፒታል፣ ከምርትና ከአምራች ይልቅ በግብይትና በነጋዴዎች መያዙ ነዉ። በተለምዶ ነጋዴ ስንል ገንዘብ ያለዉን ሁሉ ይጠቁማል። ለጊዜውና እነዚህ ሀገራት ላይ ገንዘቡ ያለው እነሱ ጋር በመሆኑ ነዉ እንጂ፤ ነጋዴ ማለት አምራች ሳይሆን ምርትን ከአምራቹ ተቀብሎ ለሸማቹ የሚያቀርበዉ ወይም በዚህ ሂደት የሚሰማራዉ ማለት ነዉ። ስለዚህ ገንዘቡ ያለዉ በአምራቹ ሳይሆን በነጋዴዉ ነዉ።

የገንዘብ ካፒታልን ከዉጭ ከማግኘት አስቀድሞ፤ ይህ በግብይትና በነጋዴዉ ታፍኖ የተያዘዉ ገንዘብ ወደ ምርት እንዲገባ ማድረግ ያሰፈልጋል። ይህ ግን፤ የግብይት ስርአቱ የገንዘብ ካፒታል አያስፈልገዉም ማለት አይደለም። ነገር ግን ከበቂ በላይ ሊኖረዉ አይገባም። ከበቂ በላይ ቢኖረዉማ እኮ፤ ትርፉ ገንዘብ ምርት ዉሰጥ ይገባ ነበር? በፍፁም። ትርፍ ገንዘብ ሲኖረዉ፣ ንግዱን ያሰፋበታል ወይም መኪና እና መሬት ይገዛበታል፥ ፍጆታዉን ይጨምርበታል እንጂ ምርት ዉስጥ አይገባም። በዚህም የመሬት/ቤት ዋጋ ይጨምራል። የመኪና ዋጋ ይጨምራል። የፍጆታ ሸቀጦች ዋጋ ይጨምራል።

ሌላዉ ቢቀር ቡና ላኪዎቻችንን እንመልከት። ቡና በመላክ ብዙ ትርፍ ለማግኘት አይፈልጉም። ዋናዉ ዶላሩ ነዉ። የሚያተጋቸው የቡናዉ ትርፍ ቢሆንማ ቡናዉን ከመላክ አገር ዉስጥ ቢሸጡት ይሻላል። ዋናዉ ዶላሩን ማግኘታቸዉ ነዉ። ከዶላሩ ውስጥ የተወሰነዉን መንግስት እቃ እንዲያስገቡበት ይፈቅድላቸዋል። ስለዚህ ሸቀጥ ገዝተዉ ያሰገቡበታል። በዚህ ከ200 ፕርሰንት በላይ ትርፍ ያገኙበታል። የሸቀጥ ዋጋ ከፍተኛ ይሆናል። ቡና ልከዉ ከ200 ፕርሰንት በላይ ትርፍ ቢያገኙ፤ ትርፉ ግን ከቡናዉ ሳይሆን ከሸቀጡ ነዉ፣ በዶላር በተገዛዉ። እነዚህ የቡና ላኪዎች የቡናን ጥራት ለመጨመር ምንም ተነሳሽነት የላቸዉም። የቡና አምራቹም ቢሆን ተነሳሽነቱ ትንሽ ነዉ። በመንግስትና የእርዳታ ድርጅቶች ድጋፍ፣ ፕሪሚየም ፕራይስ እንዲያገኙ እየተሞከር፣ በህብረት ስራ ማህበራት በኩል ከሚሰራዉ ውጭ። በተለይ ደግሞ በኛ አገር፤ ቡና ምርት ላይ የተሰማራዉ የግል ዘርፍ ዉስን መሆኑ ችግሩ ያከፋዋል።

ይህን ለመቀየር (ገንዘብን ወደ ምርት ለማስገባት) ምን ተሰራ? ኢህአዴግ ይህን ለመቀየር እንደ ዋና መሳሪያ የተጠቀመዉ ትርክትና ቃላትን ነዉ። መጀመሪያ ጥገኛ፤ ቀጥሎ ኪራይ ሰብሳቢ የሚሉ ቃላትን ተጠቀመ። እነዚህ ቃላት ከጥቅማቸዉ ጉዳታቸዉ በዛ። ለስራ ጉዳይ ቢሸፍቱ የተላከ የመንግስት ሰራተኛ ስለስራዉ ጉዳይ ሲል በየቀኑ በግል ስልኩ እየደወለ ወጪዉ ቢበዛበት፣ የስልክ ካርድ ይሞላልኝ ብሎ አለቃዉን ጠየቀዉ። መልካሙ አለቃ፣ “ይቅርብህ በኪራይ ሰብሳቢነት ትገመገማለህ” ብሎ መከረዉ።

ከቃላት ትርክቱ በመቀጠል፣ መንግስት የኪራይ ገቢ ላይ ግብር በመጣል፣ ነጋዴዎች ገንዘባቸዉን ከግብይት ይልቅ ወደ ምርት እንደዲቀይሩ ሞከረ። የተሳካላት አልመሰለኝም።

ልመና መሰል አደራም ተሞከረ። እናንተ ወደ ምርት መግባት ስላልፈለጋችሁ፣ ቻይና ህንድና ቱርክ ለምነን እያመጣን ነዉ። ምርት ላይ ብትገቡ፣ እድገቱ ወሰን የለዉም በሚል መምከር ተሞከረ።

ቀጥሎ ኢንዱስትሪ ፓርክ እንደ መፍትሄ ቀረበ። በኢንዱስትሪዉ ፓርክ ቀደመዉ የገቡት ግን የዉጭ ባለሃብቶች ናቸው። የሃገራችን ባለሃብቶች እንዲገቡ አሁንም የማባባል ስራ እየተሰራ ነው።

ዋናዉ ጉዳይ ኢህአዴግ፣ ችግር ሁሉ የፍላጎት ማነስ፣ የህዝባዊነት ማነስ አድርጉ ማየቱ ነዉ። ወጣት የህዝብ ጥቅም ተቆርቋሪን፣ ደፋርን፣ ፈሪን፣ የደርግ ጭካኔያዊ ሰርአትን የሸሸን፣ ወንጀለኛን፣ እረኛን፣ አስተማሪን፣ ሃኪምን፣ ቄስን፣ የዩኒቨርስቲን ተማሪን፥ ከተሜን በሙሉ ወስዶ፣ ፅኑ ራስአልባ የነፃነት ታጋይ ያደረገዉ ድርጅት አሁንም በትርክትና ቃላት፣ ነጋዴዉን ወደ አምራች ለመቀየር ሞከረ። አልተሳካም። “ባንድ ወቅት የጠቀሙንን መንፈሳዊ ልምምዶች የሙጥኝ ማለት፣ ወንዙን ከተሻገሩ በኋላ ጀልባውን ተሸክሞ የየብሱን ጉዞ መቀጠል ነዉ”።

መጀመሪያ መደረግ ያለበት፣ ከንግድ ሰራ የሚገኘዉ ትርፍ ለምን አንዲህ ከፍተኛ እንድሆነ መርምሮ አግባብነት ያለዉን ተቋማዊ እርምጃ መዉሰድ ያስፈልጋል።

ቀጥሎ፣ ከንግድ የሚገኘዉ ትርፍ፣ ከቤት ህንፃና መኪና ሆቴል ካፌ ይልቅ ምርት ላይ እንዲዉል፣ ለምን የነዚህ አማራጮች ትርፍ ከፍተኛ እንደሆነ መመርምርና አግባብነት ያለዉን ተቋማዊ እርምጃ መዉሰድ ያስፈልጋል።

ሶሰተኛ ነጋዴዉ አምራች የማይሆነዉ ፍላጎት ሰለሌለዉ ብቻ አይደለም። አቅምም ይጠይቃል። እድሜ ልኩን ነጋዴ የሆነ ሰዉ ያለዉ አቅም የነጋዴነት ነዉ። ገንዘብ አገኘሁ ብሎ ዘሎ አምራች አይሆንም። ልምምድ ይጠይቃል። እንኳን የሌሎቹ አማራጮች አጓጊ ሆኖ ይቅርና። አዲስ አበባ ዉስጥ ሚኒባስ በመግዛትና በሹፌር በማሰራት የምታገኘው ገቢ፣ የፈረንጅ ላም ብትገዛበት የተሻለ ትርፍ ታገኝበታለህ። ያም ሆኖ ግን ሰዉ፤ ከላም ይልቅ ሚኒባስ ይገዛል። ስለዚህ ዋናዉ ነገር አቅም ነዉ። አቅም ደግሞ የልምምድ ጉዳይ ነዉ። በሚኒባስ ሹፊርነት ሲሰራ የቆየ ሰው፥ ገንዘብ ስላገኘ ብቻ የፈርንጅ ልም አርቢ አይሆንም። ምርት ሲባል ግብርና እና ኢንዱስትሪ ናቸዉ። ለልምምድ ግብርና ይቀላል። ስለዚህ በነጋዴዎች የተያዘዉ የገንዘብ ካፒታል ወደ ግብርናዉ እንዲገባ ከዛ በኋላ ወደ ኢንዱስትሪ እንዲገባ መስራት ይገባል።

ከላይ ካሉት ሶስት መፍትሄዎች አንፃር የመንግስት ስራ ሲገመገም ዜሮ ከመቶ ነዉ ማለት ይቻላል። ለፀባይ ያለዉ ዉጤት ግምት ዉስጥ ሳይገባ። እንኳን ነጋዴዉ አምራች ይሁንና፣ በመንግስት የግንባታ ዉል የተገኘ ትርፍ እንኳን ምርት ዉስጥ አይገባም።

2.   ነጋዴዉን በማበረታታት አርሶ አደሩን እና ግብርናን ማበረታታት

በንግዱ ሴክተርና በነጋዴዉ ያለው የገንዘብ ካፒታል ስለምን በዛው ይቀራል? ስለምንስ ገንዘብ ወደ ንግዱ ያመራል? እነዚህን ጥያቄዎች እንመልከታቸው።

ብዙ ማብራሪያዎች ለእነዚህ ጥያቄዎች እንደ መልስ ሊቀርቡ ይችላሉ። ለምሳሌ፥ የንግድ ኢንቨስትመንትን (መዋእለ ንዋይን) ለመጠበቅና ለማስተዳደር ቀላል መሆኑ፥ ከግብርና እና ኢንዱስትሪ አምራችነት ጋር ሲነጻጸር። ንግድን ማስተዳደር ሸቀጦችን መዝግቦ መያዝ፥ ሽያጭን እና ግዢን መቆጣጠር ይጠይቃል። ለዚህ የሚያስፈልገው የሰው ሃይል ውስን መሆኑ ብቻ ሳይሆን፥ የሰዉ ሃይሉን ትጋትና ታምኝነት እና ውጤት መቆጣጠር ቀላል ነው።

በሌላ መልኩ የግብርና እና ኢንዱስትሪ ምርት የሚጠይቀው የሰው ሃይልና የሚያስፈልገው ሙያ የተለያየ ነው። ትጋትን፥ ታማኝነትን፥ እና ውጤትን መቆጣጠር ግብአትን እና ምርትን መዝግቦ ከመያዝ ባለፈ ይከብዳል። እንዲሁም የሚያስፈልጉ ቴኬኖሎጂዎች እንደ ግብይት ቴኬኖሎጂዎች በቀላሉ አይገኙም። የግብርና እና ኢንዱስትሪ የምርት ግብአቶች ተደራሽንትም እንዲሁ በአንጻራዊነት ዝቅተኛ እና ከባድ ነዉ። ይሄ አንደኛው ምክንያት ሊሆን ይችላል።

ሁለተኛ፥ በንግድ ስራ የሚገኝን ገቢና ትርፍ ከታክስ ለመሰወር፥ የግብርናን እና ኢንዱስትሪን ገቢና ትርፍ ከመሰወር በአንጻራዊነቱ ይቀላል። መንግስት እንዲህ አይነት ምክንያት ያቀርብ ነበር። ለዚያም ነው የቤትና ሕንጻ ገቢ ግብርን መስብሰብ፥ ምርትና ለማበረታታት እንደ መፍትሄ የተወሰደዉ።

በዚህ ክፍል ግን እንደ ምክንያትነት የምወስደው የመረጃ መበጣጠስ ነው። መረጃ፤ በጠባዩ በእያንዳንዱ ግብይት እና ተዋንያን በተበጣጠሰ ሁኔታ ይገኛል። በተለይ ደግሞ ምርቱም እንዲሁ የተበጣጠሰ ከሆነ፥ እነዚህን መረጃዎች መበጣጠስ በተወሰነ ደረጃ ማገናኘት የሚችል አካል፥ እና ምርትን ከየቦታዉ እየገዙ በገፍ ለማከማችት የገንዘብ አቅም እና ምርቱን ካንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ የማዘዋወር አቅም (የገንዘብ) ያላቸው ሰዎች በዚህ ስራ (ነጋዴነት) ይሰማራሉ። በዚህም እጅግ ከፍተኛ ትርፍ ያገኛሉ።

የመጨረሻዉ ሸማች ከከፈለው ዋጋ ውስጥ ወደ አምራቹ ኪስ የሚገባው ዝቅተኛ ነው። ለምሳሌ በቅርብ ጊዜ የገበያን መረጃ አስመልክቶ ጥናት ያደረገ አንድ ሰዉ ሲያጫውተኝ፥ አንድ ገበሬ ጤፍን በኩንታል ጎጃምና ጎንደር 800 ብር ሲሸጥ፥ ነጋዴዉ አንዱን ኩንታል ለሰማች አዲስ አበባ ላይ 2000 ብር ይሸጠዋል። ለትራንስፓርትና መጋዘን በኩንታል 200 ብር ቢያወጣ፥ ይህ ሰው በኩንታል አንድ ሺ ብር እያገኘ ነው ማለት ነው። ይህ ሰዉ እንዴት ብሎ በግብርና ስራ ይሰማራል። ከዚህ በተጨማሪ የዚህ ሰዉ የገንዘብ አቅም በጊዜ ሂደት እየፈረጠመ፥ በአንዴ የሚገዛው ምርት መጠን እየጨመረ፥ በዛውም የገንዘብ ካፒታሉ እየፈረጠመ ይሄዳል። እንዲህ አይነት ነጋዴዎች ምርትን በመግዛትና በማከማቸት ስራ ከሚያወጡት ገንዘብ የሚተርፋቸው ካለ ለግል ፍጆታ፥ ቤትና መኪና ለመግዛት፥ አራጣ ለማበደር፥ ወይም ሆቴልና ህንጻ ለመስራት ያዉሉታል። እንዲሁም ተወዳዳሪን ለማስቀረት የግዢና ትራንስፓርት መረባቸውን ከሌላ ተወዳዳሪ ለመቆለፍ ያዉሉታል። የግበያዉ በር ላይ ደናቃራ ለማቆም ይዉሉታል።

ነጋዴዎች እንዲህ የሚያታረፉ ቢሆን ኖሮ፥ ሌሎች ሰዎች በንግድ ስራ አይገቡም ነበር? ቢገቡ መልካም ነበር። አንደኛ፥ ከመጨረሻው ምርት ለአምራቹ የሚደርሰው ድርሻ ይጨምር ነበር። በዚህም ለምርት ይበረታታ ነበር። ሁለተኛ፥ እርስ በርስ ዉድድር ሸማቹ የሚከፍለው ዋጋ ይቀንስ ነበር። በዚህ ሁሉ በንግድ ስራዉ ላይ የተሰማራዉ ሰዉ ትርፍ ይቀንሳል። ሶስተኛ፥ እርስ በርስ በሚያደርጉት ዉድድር፥ወደ ዘመናዊ ወጪ መቀነስና ተያያዥ ስራዎች ይገቡ ነበር። ለምሳሌ፥ እሴት መጨመር፥ ዘመናዊ የግብይት ስርአት መረብ መዘርጋት እና የመሳስሉት። በዚህ ዋነኛ ተጠቃሚዉ ሸማቹ ይሆናል። አራተኛ፥ እርስ በርስ በሚያደርጉት ዉድድር የአምራቹን ደንበኝነት ለመያዝ ሲሉ፥ ለአምራቹ የሚያቀርቡት አገልግሎት ይኖራል። ለምሳሌ፥ ምርት የሚጨምሩ ጥራትና እውቀቶች አቅርቦት፥ ብድር (ከምርት በፊት ምርትን መግዛት)፥ ወይም ምርትን ወደፊት ለመግዛት የሚደረግ ዉል (ቀብድ)። እና የመሳስሉት። አምስተኛ በግብርና እና ሌሎች ምርት ውስጥ መግባት (የንግዱ ትርፍ ሲቀንስ በአምራችነት መሰማራት ማዋጣት ይጀምራል።

እና መፍትሄዉ ምንድን ነው?

የግብይት ወጪ እና ሰዎች ወደ ግብይት እንዳይገቡ የሚያደርጋቸውን ደንቃራ መቀነስ። የግብይት ወጪን ለመቀነስ የሚያስፈልገው ስራ (አንደኛው ስራ)፥ የግብይት መረጃን በመላው ኢትዮጲያ በመሰብሰብ (እያንዳንዱ ምርት የተሸጠበትን ዋጋ፥ የትራንስፓርት ዋጋን፥ የመጋዘን ዋጋን መሰብሰብ፥ ማደራጀት) የፈለገው ሁሉ እንዲያገኘው ማድረግ። በዚህም ብዙ ነጋዴዎች፥ አጓዦች፥ እና ባለመጋዘኖች ወደ ስራዉ እንዲገቡ ያደርጋል። ሁለተኛ፥ ሰዎች ወደ እነዚህ ስራ እንዳይገቡ የሚያደርጉ ደናቃራዎችን መቀነስ። ለምሳሌ፥ የፈቃድና ምዝገባ ስርአቱን ቀላልና ከሙስና የጸዳ እንዲሆን ማድረግ። እንዲሁም የገንዘብ ችግር ቢኖርም እንኳን፥ የገንዘብ አቅርቦት በገንዘብ ድርጅቶች እንዲቀርብ ወይም በአክስዮን ድርጅቶች በኩል እንዲሰበሰብ ማድረግ። ልብ ሊባል የሚገባው እነዚህ ስራዎች በሙሉ ንግድን እና ነጋዴዉን የሚያበረታቱ ናቸው። ብዙ ሰው ወደ ንግድ ስራ ሲበረታታ፥ ብዙ ነጋዴ ይኖራል፥ ብዙ ገንዘብ ምርትን ማሳደድ ይጀምራል። በዚህም የአምራቹና የሸማቹ ድርሻ ይጨምራል፥ የነጋዴዉ ይቀንሳል፥ ዘመናዊ የንግድ ስርአት ይፈጠራል። በዚህ ሁሉ የተወሰነ ገንዘብ ከንግድ ወደ ምርት መግባት ይጀምራል። ከላይ እንደተብራራዉ።

እንቆቅልሽ ይመስላል። ግን እውነታው ይህ ነው። ምርትን ለማበረታታት ግብይትን ማበረታታት ይጠይቃል። ግብይትን አላበረታታም፥ እኔ ምርትን ነው የማበረታታዉ በሚል ግብይትን መዘንጋት፥ የግብይትን ትርፍ እጅግ በማላቅ ያለችው ትንሽ ገንዘብም በግብይት፥ በቤትና ህንጻ፥ መኪና፥ እና ፍጆታ እንዲዉል ያደርጋል።

በአንድ አገር ኤኮኖሚ የግብርናው ድርሻ በፈጣን ሁኔታ እንዲቀንስ፥ የግብርናው ምርታማነት በፈጣን ሁኔታ ማደግ አለበት። እንቆቅልሽ፥ እርስ በርሱ የሚጣረስ ይመስላል። ለዛ እኮ ነው፤ ኢንዱስትሪዉ ለማደግ ግብርናው በፈጣን ሁኔታ ማደጉ ቅደመሁኔታ ነዉ የሚባለውና “ግብርና መሩ የኢንዱስትሪ እድገት” የሚባለው ፓሊሲ። በተመሳሳይ ሁኔታ፥ የገንዘብ ካፒታል ከግብይትና ነጋዴዉ ወደ አምራቹና ምርት እንዲሄድ፥ ግብይትን በማበረታታት ብዙ ሰዎች አይናቸው በግብይት ስራ ላይ እንዲያርፍ ማድረግ ያስፈልጋል። የግብይት ወጪን በመቀነስ (ለምሳሌ መረጃን በመሰብሰብ፥ በማደራጀትና፥ ተደራሽ እንዲሆን በማድረግ፥ እና የበሩ ላይ ደንቃራዎችን በመቀነስ)።

መንግስት አምራቹን በመደገፍና ምርትን ለመጨመር የሚሰራዉ ስራ እጅግ ብዙ ከመሆኑ የተነሳ፥ አንድ አካል ብቻውን የሚሰራዉ አይደለም። ቢሞከርም እንኳ፥ አምራቹን አይጠቅምም። የሚጠቅመዉ ነጋዴውን ነዉ። ከዚህ ጋር ሲነጻጸር ብዙ ሰዎች ወደ ንግዱ እንዲበረታቱ ለማድረግ የሚሰራዉ ስራ ቀላል ነው። በአጭር ጊዜና ሃብት ብዙ መስራት ይቻላል። ይህን መስራት የሚጠቅመው በዋናነት አምራቹን እና ሸማቹን ነዉ። ነጋዴዎችን ማበረታታት አምራቹን ይጠቅማል፥ ምርትን ይጨምራል።

ችግሩ፤ ዋናዉን አምራች ክፍለ ኤኮኖሚ (ግብርና እና ኢንዱስትሪ) የሚመራዉ ማን ነው የሚለውን ማየቱ ጠቃሚ ነው። የግብርና ባለሙያና እና ኢንጂነሮች ናቸው ወይስ የምጣኔሃብት ባለሙያዎች? ወደ ሶስተኛው ክፍል ከመሄዳችን በፊት የግብርናን ክፍለ ኤኮኖሚ እንደ ምሳሌ እንድውሰድ። በሃገራችን ዘመናዊ ከፍተኛ ትምህርት ሲጀመር ከተከፈቱት ሁለት ዩኒቨርስቲዎች መካከል አንደኛው ግብርና ላይ ያተኮረ ነው። በዚህ ተቋም የሰብል፥ እንሰሳት፥ አፈርና፥ የግብርና ምህንድስና ባለሙያዎች ለረጅም አመታት ሲያስተምርና ሲያስመርቅ ቆይቷል። በቅርብ ጊዜ የከፍተኛ ትምህርት በስፋት  ከመሰራጨቱ  በፊት ሀገራችን ካሏቸው የዶክትሬት ዲግሪ ባለቤቶች አብዛኞቹ የግብርና ምሁሮች ናቸው። በግብርና ሳይንቲስቶች ደረጃ፥ ከአፍሪካ አልፈዉ በአለም ደረጃ እውቅና ያገኙ ምሁሮች አገሪቱ አፍርታለች። ታዲያ እንዴት ነዉ፥ ለረጅም አመታት የግብርናው ክፍለኤኮኖሚ ባለበት የሚረግጠው። እነዚህን ባለሙያዎች በግብርና ሚኒስቴር በማሰባሰብና መስሪያ ቤቱን እንዲመሩ ብናደርግ፤ ግብርናው በፈጣን ሁኔታ እንዲያድግ ማድረግ አይቻልም ነበር? እነዚህ ባለሙያዎች ግብርናውን ሲመሩ የሚያተኩሩት፥ እንዴት ብለው የተሻሻለ ዝርያ፥ ግብአት፥ መስኖ፥ የግብርና ማሺነሪዎች በማቅረብ ላይ  ነዉ። የሚያዉቁት የተማሩት የተለማመዱት ይህን ነዉ። ይህን ደግሞ እስካሁንም ስንሰራዉ የቆየነው ነገር ነው። በሶስተኛው ክፍል እንደሚብራራዉ ዋናዉ መሰራት ያለበት የግብርና ግብይትን በማበረታታት ነዉ።

3.   የግብርና እድገትና የመንግስት ሚና

3.1.      ጠቅላላ

ግብርና የሃገራችን ወሳኝ የኤኮኖሚ ዘርፍ ነው። ምጣኔ ሃብት ምሁሮች እንደሚሉት፥ በቅጥርና አገራዊ ምርት የግብርናው ድርሻ እንዲቀንስ (በሌሎች ዘርፎች እንዲተካ)፥ ግብርናው በፍጥነት ማደግ አለበት። ለማነስ፤ በፍጥነት ማደግ።

የግብርና እድገት ምን ይጠይቃል? የመስኖ መሰረተልማት። የተሻሻለ ግብአት፥ ምርጥ ዘርና ዝርያ፥ ማዳበሪያ፥ አረም ማጥፊያ። የምርት ገበያ። መሬት። ጉልበት። እውቀት። የገጠር መንገድ። የአርብቶ እና አርሶ አደሮች ትምህርት። የገጠር የጤና አገልግሎት። የገጠር የመጠጥ ውሃ አገልግሎት። የገጠር ሃይል አቅርቦት። የገጠር ሰላምና ደህንነት ማስከበር። የግብርና ግብይቶችን እና ድርጅቶችን መጠበቅ።

እነዚህን ሁሉ ማነው የሚያቀርበው? አሁን ባለበት ሁኔታ እነዚህን ሁሉ በዋናነት የሚያቀርበው መንግስት ነው። የፌዴራሉ መንግስት፥ የክልሎች መንግስታት፥ እና አካባቢያዊ መስተዳድሮች ። የእነዚህ ሁሉ ዋና አቅራቢ መንግስት ሆኖ፥ እንዴት ነው ታዲያ ግብርናውን በፍጥነት ማሳደግ የሚቻለው? መንግስት እኮ ከግብርናው በተጨማሪ ሌሎች ሃላፊነቶችም አሉበት።

“እንደሚቻልማ እኮ የባለፊት አስራ አምስት አመታት የግብርናው እድገት ምስክር ነው” ሊባል ይችላል? “ሪፓርት የተደረገውና በእርግጥ የታየው እድገት ተመሳሳይ ናቸው ወይ” የሚል ጥያቄ ይነሳል። እሱን እንተወውና፤ የፓሊሲ ለውጥ በማድርግ ግብርናው እስካሁን ካደገበት በላይ እንዲያድግ ማድረግ አይቻልም ወይ?[1] ይሄን ለመመለስ አማራጭን መሞከርና ማወዳደር ይጠይቃል። በሙከራ የሚረጋገጥ ጉዳይ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፤ የተለየ አማራጭ የተሻለ ውጤት ሊኖረው እንደሚችል ግን መገመት ይቻላል።

ገንዘብ ከግብይት ወደ ግብርና ምርት እንዲሄድ፥ የግብይት ወጪን መቀነስ ይጠይቃል። ይህም የመሬትና ግብርና ግብይቶችን ማበረታታት ይጠይቃል። የመሬት ፓሊሲን እና ህግን ማሻሻል ይጠይቃል።

በክፍል አንድ እንደተገለፀው፥ ሁለት አይነት የምርት ሂደቶች (ግብርና እና ኢንዱስትሪ) በልማት ወደ ሁዋላ በቀሩ ሃገራት፥ በተለይ ደግሞ የገንዘብና የሌላ አይነት ካፒታል ችግር ባለበት አገር፥ የአገር ዉስጥ ገንዘብ የመጀመሪያዉ ምርጫ መሆን ያለበት ግብርና ነው። ከዚህ በላይ ከተገለፁት ምክንያቶች በተጨማሪ፥ ካፒታል ወደ ኢንዱስትሪ ከመሄዱ በፊት የግብርና ምርት በፈጣን ሁኔታ ማደግ ይኖርበታል።

የግብርናዉ ፈጣን እድገት የኢንዱስትሪን እድገት በሚከሉት መንገዶች ያግዛል። አንደኛ፥ ግብርናዉ ሲያድግ የአርሶ አደሩ የመግዛት አቅም ይጨምራል። ይህ ደግሞ አርሶ አደሩ ሊሸምታቸው የሚፈልጋቸውን የኢንዱስትሪ ምርቶች እድገት ያበረታታል። እነዚህ የኢንዱስትሪ ምርቶች የግብርና ግብአቶችና የፍጆታ ሸቀጦችን ይጨምራል።

ሁለተኛ፥ የግብርናው ምርታማነት ሲያድግ፥ ከግብርና ስራ ነፃ የሚወጣ የሰዉ ሃይል ይኖራል። ይህ የሰዉ ሃይል በኢንዱስትሪ እድገት ግብአት ሆኖ ያገለግላል።

ሶስተኛ፥ የግብርናው ምርታማነት መጨመር፥ ትርፍ ገንዘብ ወደ ኢንዱስትሪዉ እንዲሄድ ያደርጋል። ይህ ትርፍ ገንዘብ የዉጭ ምንዛሬን ይጨምራል።

አራተኛ፥ የግብርናዉ እድገት፥ ለኢንዱስትሪ ምርት ግብአቶች ሆነው የሚያገለግሉ የግብርና ምርቶች እድገት እንዲኖራቸው በማድረግ፥ እነዚህን ግብአቶች የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች እድገትን ያግዛል።

አምስተኛ፥ ለኢንዱስትሪ ምርት እድገት የሚያግዙ የሰብአዊ ካፒታል እና ቴክኖሎጂ እጥረት ይኖራል። ከኢንዱስትሪ አንጻር ለግብርና ምርት እድገት የሚያስፈልጉ ካፒታሎች እና ቴኬኖሎጂዎች በቀላሉ ተደራሽ ናቸው። እንዲሁም የግብርና ልምምድና እድገት፥ ለኢንዱስትሪዉ የሰብአዊ ካፒታልና ቴክኖሎጂ ግብአቶች አቅርቦች ይሆናሉ። እነ ኖኪያ ወይም ኤሪክሰን (እርግጠኛ ስላልሆንኩ ነው) ሲጀምሩ ጣዉላ ቤት ነበሩ። እንደ ሞሪሽየስ ያሉ አገራት በሸንኮራ አገዳ ጀምረው አሁን የኮጀነሬሽን ቴኬኖሎጂ እውቅ አቅራቢዎችና ምንጮች ሆነዋል። በግብርናው ያልታመነ ያገሬ ነጋዴና ሃብታም እንዴት በኢንዱስትሪዉ ይታመናል?

ስድስተኛ፥ ለኢንዱስትሪዉ እድገት፥ የምግብ ዋስትና መረጋገጥ ያስፈልጋል። ያለበለዚያ በኢንዱስትሪ ተቀጥረዉ የሚሰሩ ሰራተኞች ደመወዛቸውን በአብዛኛዉ በምግብ ወጪ ያዉሉታል። የግብርናው እድገት ደግሞ የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ የኢንዱስትሪ እድገትን ያግዛል።

በመሆኑም ከዚህ በላይ ባሉ ምክንያቶች፥ በነጋዴዉ እና በግብይት ስርአቱ የተያዙ ትርፍ ገንዘቦች የመጀመሪያዉ መዳረሻቸው መሆን ያለበት ግብርናው እንደሆነ ተገልጿል። ይህ ትርፍ ገንዘብ ወደ ግብርናዉ እንዲገባ ለማገዝ ግን መሰራት ያለባቸው ስራዎች አሉ። አንደኛው፥ ገንዘቡ ወደ ግብርና እንዳይገባ የሚያደርጉ ደንቃራዎችን መቀነስ ያስፈልጋል። እነዚህ ደንቃራዎች ባብዛኛዉ የፓሊሲና የሕግ ደንቃራዎች ናቸው። ሁለተኛ፥ ገንዘቡ ወደ ግብርና እንዲያገባ የሚያደርጉ የግብርና ግብይቶች እንዲበረታቱ የግብይት ወጪን መቀነስ ያስፈልጋል።

አሁን ባለበት ሁኔታ፥ የሃገራችን ፓሊሲና ህግ ይህን ሃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም። የአርሶ አደሩን ጥቅም ያስጠብቃሉ ተብለዉ የታሰቡት የሃገራችን ህጎች፥ እንኳን የአርሶ አድሩን ጥቅም ሊያስከብሩ ቀርቶ፥ የእውቀት፥ መረጃ፥ ገንዘብ፥ እና ቴክኖሎጂ ወደ ግብርናዉ ዘርፉ በቀላሉ በሚጠበቀው መጠን እና ፍጥነት እንዳይፈሱ ደንቃራ በመሆን፥ የግብርናዉን እድገት፥ የአርሶ አደሩን ጥቅም የሚጎዱ ናቸው። ከዚህ በላይ ባለው ክፍል እንደተገፀዉ፥ የግብርናዉን ምርት ለመጨመር መንግስት ሁለት አይነት ስራዎችን ሊስራ ይችላል። አንደኛው ስራ ለግብርናዉ ግብአት የሚያስፈልጉ የተለያዩ ግብአቶችን ራሱ በማቅረብ ነው። እነዚህ ግብአቶች የተሻሻሉ ዘርና ዝርያዎች፥ የመስኖና ዉሃ፥ ማዳበሪያ፥ አረም መከላከያ፥ እውቀት፥ ቴክኖሎ/ማሺነሪዎች፥ ገንዘብ፥ መሬት፥ የአፈርና ዉሃ ጥበቃ አገልግሎት፥ ጤና አገልግሎት፥ ትምህርት፥ እና የመሳሰሉት ናቸው። እነዚህ ግብአቶች በበቂዉ መጠን እና ጥራት ለአርሶ አደሩ በማቅረብ የግብርናን ምርት መጨመር ይችላል። ይህኛው አማራጭ ቀጥተኛው አማራጭ ነው። ሁለተኛው አማራጭ፥ የግብይትን ወጪ በመቀነስ፥ እነዚህ ግብአቶች በግል ዘርፉ በብዛት እንዲቀርቡ ማድረግ ነው። እነዚህ ግብአቶች በሁለቱም አማራጮች ከአስራ አምስት ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ አርሶ አደሮች ይቀርባል። መንግስት የመረጠው አማራጭ የመጀመሪያዉን ነው። ይህ አማራጭ ብዙ ገንዘብ የሚጠይቅና የሚፈለገውን ዉጤን ለማግኘት ብዙ ጊዜ የሚወስድ ነው። እንዲሁም በነጋዴውና በግብይት ስርአቱ ያለው ገንዘብ ወደ ግብርናዉ እንዲገባ የሚያደርግ ነው። ግብርናዉ በፈጣን ሁኔታ ካላደገ እንዱስትሪዉ አያድግም (የዉጭ ገንዘብ ለኢንዱስትሪዉ ቢገኝም)። እንዲሁም ወደ ግብርናዉ ያለው የገንዘብ ፍሰት ስለተገደበ ብቻ፥ ይህ ገንዘብ ወደ ኢንዱስትሪዉ ይፈሳል ማለት አይደልለም። በግብርናዉ ሳይለማመድ፥ ወደ ኢንዱስትሪዉ አይሄድም።

የግብርና ግብይትን የማፈን እና ወደ ግብርናዉ የሚደረግ የገንዘብ ፍሰትን የመግታት ዉጤት ያላቸውን የሃገራችን ፓሊሲዎችን ከዚህ በታች ባሉ ክፍሎች እንመለከታቸዋለን።

3.2.      የግብርና እውቀት

ለምሳሌ እውቀትን እንውሰድ። ለእድገት የሚያስፈልጉ ግብአቶችን ምሁሮች በተለያየ መልኩ ይከፋፍሏቸዋል። መሬት፥ ጉልበትና፥ ካፒታል የሚለው ክፍፍል የቆየ ነው። ካፒታል የሚለው አባባል የገንዘብና የማምረቻ መሳሪያዎችን ይጨምራል። እየቆየ መሬት የሚለው አባባል ራሱ ሙሉ አንዳልሆነ እና የተፈጥሮ ካፒታል በሚል ተቀይሯል። የተፈጥሮ ካፒታል የሚባሉት የተለያዩ ታዳሽና የማይታደሱ የተፈጥሮ ሃብቶች መሬትን ጨምሮ፥ እና የስነምህዳር አገልግሎቶችን ያካትታል። ጉልበት የሚለው አባባልም ሙሉ አይደለም። ይልቅስ ሰብአዊ ካፒታል በሚል ቢገለጽ የተሻለ ይሆናል። ሰብአዊ ካፒታል የሰው ጉልበትን እና እውቀትን ይጨምራል። ድሮ ካፒታል በሚል የሚገለጹት አሁን የገንዘብ ካፒታልና ፍብሩክ ካፒታሎች ተብለው ይታወቃሉ። ከእነዚህ ግብአቶች በተጨማር ማህበራዊ ካፒታል (መደበኛና ኢመደበኛ ተቋማት)፥ ዲፕሎማቲክ ካፒታል (በአለም አቀፍ ግንኝነቶች የሃገርን ጥቅም የማራመድ አቅም)፥ እና የፓለቲካ ካፒታል (ቅቡልነት) ሊጨመሩ ይችላል። በአጭሩ ለእድገት የሚያስፈልገው ካፒታል ነው። ካፒታል የተለያየ ቅርፅ ይኖረዋል። የእድገትን ጥራትና መጠን የሚወስኑት ያሉንን ካፒታል በጥራትና በመጠን የመጨመርና ለላቀ ዉጤት የመጠቀም አቅማችን ነው። ከገንዘብ፥ የተፈጥሮ ካፒታል፥ እና ፍብሩክ ካፒታል ይልቅ፥ ለእድገት እጅግ ከፍተኛ አስተዋእጾ የሚኖረው ሰብአዊ ካፒታል ነው። ከጥሬ ጉልበት አልፎ እውቀትን ከጨመረ። የተፈትሮ ካፒታል አላቂ ሊሆን ይችላል። የማያልቀው እውቀት ነው። በተፈጥሮ ሃብት የታደሉ ሆነው አንዳንዶቹ ክፍተኛ የኤኮኖሚ እድገትና ትራንስፎርሜሽን ሲያሳዩ አንዳንድ ሃገሮች ግን በማያቋርጥ ድህነትና ግጭት ይማቅቃሉ። በእነዚህ ሃገሮች መካከል ያለው ልዩነት የተፈጥሮ ሃብታቸውን የተጠቀሙበት አግባብ ነው። የተፈጥሮ ሃብታቸውን ለማያቋርጥ እድገት የተጠቀሙ ሃገራት፥ በእውቀት ላይ ከፍተኛ ስራ ስርተዋል። እውቀት ለእድገት ያለው አስተዋእጾ፥ የማይነጥፍ ነው። ስለዚህ በፈጣን ሁኔታ ማደግ የሚሻ ሃገር እውቀትን በፍጥነት ማስራጨት፥ መጠቀምና አዲስ አውቀትን በፈጣን ሁኔታ ማምረትና መለማመድ አቅም ሊኖረው ይገባል። ስለዚህ ስለግብርናው ፈጣን እድገት ስናቅድ፥ እንዴት በአለም ላይ ያለውን የግብርና እውቀት በፈጣን ሁኔታ ማሰራጨትና ለላቀ ውጤት መጠቀም እንደምንችል አብረን ልናቅድ ይገባል።

ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ ከነበረው ባህላዊ እውቀት ውጭ፥ የገበሬው ብቸኛ የዘመናዊ እውቀት ምንጭ መንግስት ነው።[2] መንግስት ይህን እውቀት በልማት ሰራተኞችና በግብርና ኤክስቴንሽን ፓኬጆች አማካይነት ያቀርባል።

ገበሬው የግብርናን ባለሙያን በስራተኝነት ወይም በአማካሪነት የመቅጠር አቅም የለውም። አንድ አካል በሌላ አካል ያለን እውቀት ሊያገኝ የሚችለው በሶስት መንገድ ነው። አንደኛው ባለእውቀቱን እንደ ሰራተኛ መቅጠር። ሁለተኛ ባለእውቀቱን አማካሪ አድርጎ መቅጠር። በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ስራተኛ በቀን ተቀን ስራው በቀጣሪው ቁጥጥርና መመሪያ የሚሰራ ሲሆን፥ አማካሪ ግን ለተወሰነ ስራ ተብሎ የሚቀጠርና ከቀጣሪው ቁጥጥርና መመሪያ ውጭ ሆኖ ራሱን ችሎ የሚሰራ መሆኑ ነው። በሶስተኛ ደረጃ ባለእውቀቱ እውቀቱን በመጠቀም የሚሰራቸውን ሸቀጦች በመግዛትና በመጠቀም ነው። ለምሳሌ እውቀቱን በመጠቀም መድሃኒት፥ ማሽን ሊሰራ ይችላል። ወደ ግብርናው ስንመጣ፥ በሃገራችን እውቀታቸውን በመጠቀም የግብርና ግብአቶችና ማሽኖችን የሚሰሩ መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እዚህ ግቡ የሚባሉ አይደለም። ከእጽዋት ፈሳሽ ማዳበሪያ አየሰራ የሚሸጥ ሃገር በቀል ድርጅት እንዳለ አውቃለሁ። ስለሃገራችን ግብርና ስናወራ 18ሚሊዮን የሚገመት ባለትንሽ ማሳ የገበሬ አባና እማ ወራዎች ነዉ የምናወራው። አማካኝ የማሳ መጠን አንደ ሄክታር አካባቢ ነው። እነዚህ ገበሬዎች የግብርና ባለሙያን በሰራተኛነት እና አማካሪነት ቀጥሮ የማሰራት የገንዘብ አቅም የላቸውም። ገንዘቡ ቢኖራቸውም እንኳን፥ የመክፈል ፈቃደኝነታቸው ውስን ይሆናል። እውቀት ክፍሎ ለመግዛት፤ የምትገዛውን እውቀት ጥራት መገምገም መቻል አለብህ። እውቀትን መገምገም ይከብዳል። የምርቱ ጥራትና መጠን፤ ሙሉ ለሙሉ በተጠቀምከው እውቀት ስለማይወሰን።

በዚህም ምክንያት ዋነኛው የግብርና ባለሙያዎች ቀጣሪ መንግስት ሆኗል። መንግስት ብቸኛው የግብርና ባለሙያ ቀጣሪ መሆኑ ምን ችግር ያመጣል? አንድ ብቻ ገዢ ያለበትን ገበያ በአምራችነት መቀላቀል ይከብዳል። ምክንያቱም የምርትህን ዋጋ የሚተምነው ገዢው ስለሆነ። በዚህ ላይ አንተ ሚና ስለሌለህ። ስለዚህ መጀመሪያውኑ መርጦ የሚገባ አይኖርም። በሆነ አጋጣሚ ብትቀላቀልም እንኳን፥ የአምራችነት አቅምህን ለመገንባት በየጊዜው የምታፈሰው መዋእለ ንዋይ ሌላ ገዢ ስለማያገኝ፥ የምርት አቅምህን ለማበልጸግ ሃብትህን አታወጣም። ይልቅስ ይህን ገበያ ለመልቀቅና ሌላ ገበያን ለመቀላቀል ጥረት በማድረግ ትጠመዳለህ። አማራጭ ስታገኘ፥ በተቻለ ፍጥነት ለቀህ ትወጣለህ።

የግብርና ባለሙያ ብቸኛ ቀጣሪ መንግስት መሆኑ፥ የሚኖረው ውጤት ተመሳሳይ ነው። ወደ ግብርና ሙያ የሚያስገባውን በር እንዲጠብና ከፍ እንዲል አድርጎታል። የመንግስት የቅጥር ቅድመሁኔታ ከፍ በማለቱ አይደለም። ይልቅስ የግብርና ሙያን በመማርና በዚህም በመስራት የምታጠፋውን የህይወት ጊዜ፤ እንደ ቀሊጥ ወጪ የመቆጠር እድሉን ከፍ ስለሚያደርገው ነው።  ስለዚህ በሆነ አጋጣሚ ግብርና የተማረ ሰው፥ በግብርና ሙያ ቢጀምርም እንኳን፥ በዚህ ሙያ እስከመጨረሻው የመቀጠል ፍላጎቱን ይቀንሰዋል። አንድ ዋና ቀጣሪ ያለው ሙያ በመሆኑ። ስለዚህ ኮምፒዩተር፥ ወይም አካውንቲንግ እና ሌላ ትምህርትና ሙያ በፍጥነት በመቅሰም፥ ከግብርናው ለመውጣት ይሞከራል። በእርግጥ የግብርና ባለሙያዉ እውቀቱን ከመሸጥ ይልቅ፥ እውቀቱን ተጠቅሞ በግብርና ስራ ላይ ሊሰማራ መቻሉ እንደ አማራጭ ገዢ ሊወሰድ ይችላል። አማራጮች መኖራቸው የግብርና ባለሙያዎች በሙያቸው እንዲቆዩና እንዲያዳብሩ ያደርጋል። ነገር ግን ይህኛው አማራጭ በሃገራችን እጅግ ጠባብ ነው።

የግብርና እውቀት ብቸና አቅራቢዉ መንግስት መሆኑ ወደ ግብርና ሙያ የሚገቡ ሰዎችን ፍላጎት ከመቀነሱ በላይ የሚከፋው ደግሞ፤ መንግስት የሚያቀርበው የግብርና እውቀት አቅርቦት በማእከል የሚዘጋጅ መሆኑ ነው። በመሆኑም በገበሬውና በገበያ የሚፈለገው እውቀት ሳይሆን የሚቀርበው፤ የመንግስት ባለሙያዎችና አመራሮች ያስፈልጋል ብለው የሚያምኑት እንጂ። እንዲሁም አንድ ድርጅት ሊያስተናግደው የሚችለው የስራና ቴክኖሎጂ ብዝሃነት ውስን ነው። ስለዚህ ለሁሉም አይነት ተፈላጊ እውቀት ኤክስቴንሽን ፓኬጅ ይዘጋጅለታል ማለት አይደለም። ዝንጅብል ተመርቶበት በማያውቅ አካባቢ የሚኖር ገበሬ፥ ዝንጅብል ከፍተኛ ዋጋ እንዳለው ቢያውቅና ዝንጅብል ማምረት ቢፈልግ፥ የዝንጅብል ፓኬጅ ይኖራል? የሮዝሜሪ ፓኬጅ ይኖራል? የቀይ ስር ፓኬጅ ይኖራል? የለውዝ ፓኬጅ ይኖራል? መንግስት ብቻ የእውቀት አቅራቢ በሆነበት ሁኔታ ተፈላጊው እውቀት በሙሉ በሚገባ ጥራት፥ መጠን፥ እና ፍጥነት አይቀርብም።

መንግስት በፓኬጅና በልማት ሰራተኞች አማካይነት ከሚያቀርበው በተጨማሪ፥ የተሻሻሉ አስራሮችን የማስፋፊያ ስትራቴጂ አለው። እንደውም የልማት እቅዶቹ የሚቃኙት የተሻሻለ አሰራርን በማዛመት ነው። የተሻሻለን አሰራር የማዛመት ስልት፥ ዋነኛዉ የግብርና ቴኬኖሎጂ ማስፋፊያ ስትራቴጂ ነዉ። ከወጪ አንጻርና የቴኬኖሎጂ ልምምድ እስኪስፋፋ ድረስ በሚል። ለምሳሌ ከአስሩ የቡና አምራቾች ዉስጥ አንዱ በሄክታር አማካይ አስር ኩንታል ቢያመርትና ሌሎቹ ዘጠኙ ግን አማካይ አምስት ቢያመርቱ፥ ይህ ገበሬ እንደ ሞዴል ገበሬ ተወስዶ፥ እና በሚቀጥሉት አምስት አመታት ከተቀሩት ዘጠኙ ዉስጥ ቢያንስ አምስቱ እንደሞዴሉ ገበሬ ቢያመርቱ በሚል፤ ምርትን ከ55 ኩንታል ወደ 80 ኩንታል የማስገባት እቅድ ይወጣል። ምን በማድረግ? ሞዴል ገበሬዉ የተጠቀመዉን የተሻሻለ አሰራር ሌሎቹ አምስት ገበሬዎች እንዲጠቀሙ በማድረግ? እንዴት? አንድ ለአምስት በሚባለው አስራር። ይሄ አስራር ብዙ ስሞታ ይቀርብበታል። ከያዝነው ጉዳይ ግን የሚያያዝዉ ትልቁ የአስራሩ ችግር፥ ከእውቀት ማነስ የሚመጣ ስልት መሆኑን ነዉ። እንዲሁም የተሻሻለው አስራርን በፈጣን እና በስፋት ለማሰራጨት አይጠቅምም። ከዚህ ሁሉ ሞዴሉ ገበሬ የተጠቀመዉ የተለየ አሰራር ምንድን ነዉ የሚለዉን መለየትና ይሄን አሰራር በአንድ አምስት አሰራር የታቀፉት ብቻ ሳይሆን በጣም ብዙ ሰዎች እንዲከተሉት ማድረግ ይቻል ነበር። መንግስት እራሱ የተሻሻሉ አሰራሮችን ከራሱ የምርምር ድርጅቶች ከሚያገኘዉ ዉጭ፥ ተራማጅ ገበሬዎች የሚከተሏቸውን አሰራሮችን የሚለይበት ፕሮግራም የለዉም።

የግብርና እውቀት (በተለይ ደግሞ ለእኛ ሁኔታ የሚያስፈልገው እውቀት) በቀላሉ የሚገኝ ነው። በጽሁፍ፥ በቪዲዮ፥ በድምፅ። ችግሩ እነዚህ እውቀቶች በውጭ ቋንቋ መሆናቸው ነው። ሁለተኛ፥ እነዚህን እውቀቶች በቀጥታ መተግበር ያስቸግራል። ከመሬቱ አይነት፥ ከአየር ጸባዩ ጋር ማስማማት ያስፈልጋል። ስለዚህ በዚህ ረገድ በፈጣን ሁኔታ ያለውን እውቀት ለመጠቀም የሚያስፈልገው፤ በፈጣን ሁኔታ የእውቀት ድለላና ማጣጣም ስራን መስራት ነው። ይህ ደግሞ በመንግስት ብቻ በማእከል ሊሰራ አይችልም። የተለያዩ ድርጅቶች (በትርፍና ያለትርፍ የሚሰሩ) በዚህ ስራ እንዲገቡ ማድረግ ይቻላል። “ግን እኮ ገበሬው ከእነዚህ ድርጅቶች እውቀትን የመግዛት አቅም የለውም” ሊባል ይችላል። እውነት ነው። አንዱ አማራጭ፥ የቃና ቴሌቪዥን ሞዴልን መከተል ነው። ቃና መዝናኛን ዴሞክራታይዝ እንዳደረገው ሁሉ፥ ተመሳሳይ ሞዴል የግብርናን እውቀት አቅርቦት ዴሞክራታይዝ ሊያደርገው ይችላል። ቃና ቴሌቪዥን ገቢ የሚያገኘው ከተመልካች ክፍያ ሳይሆን ከማስታወቂያና ስፓንሰር ስለሆነ። በዚህ ረገድ የመንግስት ሚና የግብርና ቴሌቪዥን መሰረተልማትን በመዘርጋት፥ የግብርና እውቀትን የሚያሰራጩ ድርጅቶች ክፍት በማድረግ፤ እሱ በኤክስቴንሽን ፓኬጅ ከሚያቀርበው እውቀት በላይ ገበሬው ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል።

3.3.      የመስኖ አቅርቦት

የመስኖ አቅርቦትን መውሰድ ይቻላል። በዝናብ ዉሃ ብቻ ግብርናን በሚፈለገው መጠን እና ፍጥነት ማሳደግ አይቻልም። የግብርናው ክፍለ ኤኮኖሚ በተከታታይ አመታት በአማካይ 8 ከመቶ አድጓል እየተባለ እንኳን፥ በመስኖ የሚለማው ማሳ መጠን ውስን ነው። የመስኖ ቴክኖሎጂን እና መሰረተልማትን የሚያቀርበው ማን ነው? መንግስት፥ ልክ እንደ ግብርና እውቀት። በተለይ ደግሞ የጥልቅ የዉሃ ጉድጓድን እና የገጸምድርን ግድብ በመጠቀም የሚከናወን። በእጅ የሚቆፈር ጉድጓድ በገበሬው የሚሰራ ነው። ይሄም ቢሆን ሙሃ ማቆር በሚል ዘመቻ፥ ሲመራ የነበረው በመንግስት ነው።

ገበሬው የመስኖ መሰረተ ልማትን የሚጠበቀው ከመንግስት በሆነበት በአሁኑ ጊዜ እንዴት ነው አስፈላጊው መሰረተልማት በሚፈለገው መጠን እና ጥራት በፍጥነት ሊቀርብ የሚችለው? ከብዙ ጊዜ ስራ በኋላ አሁንም የመስኖ ተደራሽነት እጅግ ዝቅተኛ ነው። መንግስትም በማእከል ሲስራ ትንንሽ የመስኖ ቴክኖሎጂዎች ሳይሆን የሚታዩት ግዙፎቹ ናቸው። እነሱ ደግሞ ብዙ ጊዜና ገንዘብ ይወስዳሉ። በታቀደላቸው ጊዜና ወጪ አያልቁም።

ገንዘቡና አቅሙ ያላቸው፥ የመስኖ ዉሃን ለገበሬው በክፍያ ቢያቀርቡስ? ወይም አርሶአደሮች ገንዘብ በመበደር የሚያስፈልጋቸውን የመስኖ ቴክኖሎጂ ቢገበዩስ? እነዚህ ላይ በብዛት በመስራት የመስኖ ዉሃ በብዛትና በፍጥነት እንዲቀርብ ማድረግ አይቻልም? የመስኖ ዉሃ እና የግብርና አርቦት ጉዳይ ከመሬት ህግና ከግብርና ግብይት ጋር ስለሚያያዝ ከዚህ በታች እንመለስበታለን።

3.4.      የመሬት መበጣጠስ

የመሬት አቅርቦትን መመልከት ይቻላል። አቅራቢው መንግስት ነው። በተለይ በተለምዶ ቅይጥ ግብርና በሚከተሉ የሃገራችን ከፍተኛ ቦታዎች፥ የመሬት ዉስንነት ችግር እንዳለ ይታመናል። የመሬት መበጣጠስ ይስተዋላል። ባደኩበት አካባቢ የገበሬው ቦታ በሶስት ወይም አራት ቦታዎች ተበጣጥሶ የተለያየ አካባቢ ይገኛል። አንድ ገበሬ ግማሽ ኳስ ሜዳ የምታክል ቦታ በጓሮው ይኖረዋል። ከዛ እሷን የምታክል ቦታ ከመኖሪያው ሶስት ኪሎሜትር ርቆ ሊኖረው ይችላል። እንዲሁም በሌላ አቅጣጫ በተመሳሳይ ርቀት ሌላ ተመሳሳይ ቦታ ይኖረዋል። ለምን እንዲህ ተበጣጠሰ? የአፈሩ አይነት የተለያየ ስለሚሆን ለሁሉም ከሁሉም የአፈር አይነት እንዲደርሰው ለማድረግ ሲባል። ለፍትሃዊ የመሬት ክፍፍል ሲባል።

እንዲህ መሆኑ ምን ያመጣል? ገበሬ በመሬቱ ላይ የሚያስፍልገውን መዋእለ ንዋይ በበቂ ሁኔታ እንዳያፈስ ያደርገዋል። እንዲህ ባይበጣጠስ ኖሮ፥ ሁሉም መሬት አንድ ቦታ ተያይዞ የሚገኝ ቢሆን ኖሮ፥ አንድ ገበሬ ለምሳሌ የጉድጓድ ውሃ በማሽን ሊያስቆፍር ይችል ይሆናል። አሁን ግን ሶስቱን የተለያዩ ቦታዎች በማሽን ለማስቆፈር አይችልም። ስለዚህ በቀላሉ የሚያደርገው በእጅ የጉድጓድ ውሃ መቆፈር ነው። ያም ቢሆን በጓሮው እንጂ በሌሎቹ መሬቶች ላይ አይሞክረውም። ማን ሊጠብቅለት? ለዛውም በትንሽ እርቀት የጉድጓድ ዉሃ ከተገኘ ነው።

መሬት በዚህ መልኩ መበጣጠስ፤ የመሬት ለምነትን ለመጠበቅ አያነሳሳም። አንድ ገበሬ ብቻውን በዛ ትንሽ መሬት የአፈርን ለምነት ለመጠበቅ የሚሰራው ስራ ምንም ያህል ውጤት አያመጣም። ለምሳሌ የችግሩ ምንጭ መነሻው የሱ መሬት ሳይሆን ከሱ በላይ የሚገኝና በሌሎች ገበሬዎች የተያዘ ቦታ ሊሆን ይችላል። እንዲሁም የዘር አይነትን በመምረጥ፥ ግብአትን በመጠቀም የሚያመጣው ውጤት ውስን ነው። ምክንያቱ የመሬቱ ማነስ ሳይሆን መበጣጠስም ነው። በአንዱ መሬቱ ምርጥ የበቆሎ ዘር ቢዘራና ማዳበሪያ ቢጠቀም፥ የሚገኘው ውጤት በስራውና ባፈሰሰው መዋእለ ንዋይ ብቻ ሳይሆን፥ መሬቱ ባለበት ተፋሰስ ያሉ ሌሎች ገበሬዎች በዘሩት ሰብል እና በስራቸው መጠን እና ጥራት ነው።

አሁን ባለበት ሁኔታ፥ በመሬት መበጣጠስ ያለውን እንዲህ አይነት ችግር ለመፍታት የተሞከረው፤ ገበሬዎች በማህበራት እንዲደራጁ በማድረግና የአፈር ጥበቃ ስራን በጋርዮሽ በመንግስት በዘመቻ እንዲሰራ ማድረግ ነው። ስለዚህ የመንግስት ፓሊሲ የሚያመጣውን ችግር ለመፍታት የተሞከረው ለመንግስት ተጨማሪ ሚና በመስጠት ነው። የአፈር ጥበቃ ስራን በማእከል እንዲመራ በማድረግና ገበሬዎች በማህበራት እንዲደራጁ በማድረግ። በዘመቻ የሚሰራ አፈር ጥበቃም ሆነ ማህበራት በራሳቸው ሰፊ የተነሳሽነት፥ የትጋትና የማስተዳደር ችግር ያለባቸው ናቸው።

3.5.      የመሬት ግብይት

ገበሬው መሬቱን መሸጥ አይችልም። በተወሰነ ደረጃ ማውረስና ማከራየት ብቻ ይችላል። ለምሳሌ መሬትን ለሌላ ሰው ለተወሰነ ጊዜ (እንደ ክልሎቹ ሕግ የሚለያይ) ማከራየት ይችላል። ነገር ግን ተከራዩ መሬቱን የሚፈልገው ለግብርና መሆን አለበት። ለሌላ አላማ የሚፈለግ ሰዉ፤ መሬትን ከገበሬ መከራየት አይቻልም።

እንዲሁም እንደ ክልሉ ሕግ፤ ገበሬው መሬቱን ሙሉ ለሙሉ ማከራየት አይችልም። የተወሰነውን ብቻ ነው። መሬቱን አስይዞ መበደር አይችልም። እንዲህ አይነት ድንጋጌዎች በግብርናው ዘርፍ የሚደረጉ ግብይቶችን ይቀንሳሉ። የብድር ምንጭን ይቀንሳል። የክራይ ዋጋ እንዲወድቅ ያደርጋል። መሬቱን ለሌላ አላማ የሚፈልጉ ተከራዮችን ከገበያው በማስወጣት። ተበጣጥሶ ያለን መሬት በመከራየትና በመሰብሰብ፥ የተሻሻሉ የግብርና ግብአቶችን መጠቀም፥ ጠንክሮ መስራት ውጤት እንዲኖራቸው ለማድረግ ያለው እድል ዝቅተኛ ነው። እንዲሁም ባለገንዘቦች ጥልቅ የጉድጓድ ዉሃን ብዙ ገንዘብ በማውጣት አስቆፍረው፥ የመስኖ አገልግሎትን ለገበሬው ለማቅረብ፥ ወይም ባለሃብቶች ከገበሬዎች ጋር በመዋዋል፥ በገበሬው መሬት ላይ የማዘዝ መብትን ባለሃብቱ በኪራይ ወይም ደግሞ በትርፍ ድርሻ በመውሰድ የተሻሉ ግብአቶችን በመጠቀም፤ የግብርና ምርትን ለመጨመር ያለው እድል ዝግ ወይም እጅግ ጠባብ ነው።

መሬት ላይ ያሉት ገደቦችን ለመሞገት የሚቀርቡ ሁለት ዋና ዋና ምክንያቶች እነዚህ ናቸው። አንደኛ፤ ገበሬው በጊዜያዊ ችግር መሬቱን ሙሉ ለሙሉ አከራይቶ ስራ አጥ የከተማ ኗሪ እንዳይሆን። ሁለተኛ፤ መሬት የህዝብ ስለሆነ መሸጥና በእዳ መያዝ የለበትም።

የመጀመሪያውን ሙግት እንመልከት። ገበሬው መሬቱን ሙሉ ለሙሉ እንዲያከራይ ቢፈቀድ፥ በእርግጥ ከግብርናው ሙሉ ለሙሉ የሚወጣ ጉልበት ይኖራል። ይህ ጉልበት ግን በሌላ የኤኮኖሚ መስክ ላይ በማሰማራት ምርታማ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል። ሁለተኛ የመሬቱ ተከራይ ራሱ ጉልበት ይፈልጋል። ስለዚህ ገበሬው ከኪራይ በተጨማሪ በቅጥር ደመወዝ ሊያገኝ ይችላል።

ሁለተኛውን ሙግት እንመልከተው። መሬት የሕዝብ መሆኑ፥ መሬትን በእዳ ከማስያዝ የሚከለክል አይሆንም። ዞሮ ዞሮ ገበሬዉ በእዳ የሚያስይዘው የመሬቱን ባለቤትነት ሳይሆን በመሬት የመጠቀም መብቱን ነው። መሬቱን ለአስርም ይሁን ለሃያ አመት የመጠቀም መብት እስካለው ድረስ፥ ለምን ይህን መብቱን በእዳ እንዲያስይዝ አይፈቀድለትም።

ገበሬው መሬቱን ሙሉ ለሙሉ እንዲያከራይ ብቻ ሳይሆን መፈቀድ ያለበት፥ አሁን ያለውን “መሬትን ለግብርና ስራ ብቻ ነው ማከራየት የሚቻለው” የሚለው ገደብ ራሱ መነሳት አለበት። ያለበለዚያ መሬቱን በሙሉ ማከራየት መቻሉ ብቻ የሚያመጣው፤ የኪራይ ዋጋ መውደቅን ነው። ብዙ መሬቶችና ጥቂት ተከራዮች እንዲኖሩ በማድረግ።

በተጨማሪ በመሬት አስተዳደር ያሉ ቅሬታዎችን እና ብልሹ አስራሮችን ለማጥፋት ይረዳል። አሁን ባለው አሰራር፥ መሬትን ከግብርና ውጭ ላሉ ስራዎች የሚፈልግ አካል፥ ይህን መሬት ማግኘት የሚችለው በሊዝ ከመንግስት በመከራየት ነው። መንግስት ደግሞ ይህን መሬት የሚያገኘው ከገበሬው በመውረስ ነው። ከገበሬው ወርሶ ለባለሃብቱ በሊዝ ያከራየዋል። የሕዝብ ጥቅም የሚያስከብር እስከሆነ ድረስ። ለገበሬው ካሳ እስከከፈለ ድረስ።

አንድ ገበሬ መሬቱን በማረስ በአመት መቶ ሺ ብር ያህል ይጠቀማል እንበል። ይህን መሬት መከራየት የሚፈልግ ሰው ቢያንስ በአመት መቶ ሺ ብር በኪራይ መክፈል መቻል አለበት። ይህ የሚሆነው ደግሞ መሬቱን በመከራየት ከመቶ ሺ በላይ ጥቅም ማግኘት ሲችል ነው። እንበልና መሬቱን ቢከራይ ይህ ሰው በአመት የተጣራ ሁለት ሚሊዮን ብር ያገኛል እንበል። በዚህ ጊዜ ይህን መሬት በመቶ ሃምሳ ሺ ቢከራየው ያዋጣዋል። ገበሬውም ቢያከራየው ያዋጣዋል። በዚህ ግብይት ሁለቱም ወገኖች ተጠቃሚዎች ናቸው። ሃገርም እንዲሁ። መሬት የላቀ ውጤት ባለው ስራ እንዲውል ያደርጋል። ይህ ክራይ ሕጋዊ የሚሆነው ግን አንደኛ ተከራዩ መሬቱን የፈለገው ለዘመናዊ ግብርና ከሆነ ነው። ሁለተኛ አከራዩ ከዚህ ከሚያከራየው መሬት በተጨማሪ ሌሎች መሬቶች ሊኖሩት ይገባል፤ ሙሉ መሬቱን ማከራየት ስለማይችል። በእነዚህና ሌሎች ችግሮች ምክንያት የተነሳ ይህ ኪራይ የማይፈቀድ ነው እንበል።

ታዲያ ፈላጊው ይህን መሬት በሌላ በምን መልኩ ሊያገኝው ይችላል? መሬቱን ከመንግስት በሊዝ ሊያገኘው ይችላል። ሊዙ ከ40 እስከ 99 አመታት ሊሆን ይችላል። መንግስት ደግሞ ከገበሬው በመውረስ። ለገበሬው የሚከፈለው ካሳ፥ መሬቱን እንዲያከራይ ቢፈቀድለት ኖሮ ከሚያገኘው ጥቅም ጋር ተቀራራቢ ነው? ገበሬው ይህን መሬት እያረሰ በአመት የተጣራ መቶ ሺ ብር ካገኘ፥ ይህ አመታዊ ገቢ መሬቱ በሊዝ በሚቀርብበት አመታት ተባዝቶና ዲስካውንት ተደርጎ የሚገኘው ያህል በካሳ ይከፈለዋል? አይከፈለውም። እንደውም የሚባለው፥ ባለሃብቱ በሜትር ካሬ ብዙ ሺ ብር እየከፈለ፥ ለገበሬው ግን በሄክታር ከሃምሳ ብር እጅግ ባነሰ ተመን ተስልቶ ካሳ ይከፈለዋል። ኪራይ ወርሃዊ ወይም አመታዊ ሲሆን፥ ካሳ ግን አንዴ የሚከፈል ነው። ታዲያ በዚህ የሚጠቀመው ማን  ነው? በመሬት ኪራይ ላይ የተጣሉ ገደቦች፥ ገበሬው በመሬቱ በመስራት የሚያገኘውን ጥቅም መቀማት አይደለም ወይ? መሬትን በነፃ እንዲያከራይ መፍቀድ ነው ወይስ መሬትን ካሳ እየከፈሉ በመውረስና ለባለሃብት በመስጠት፤ የትኛው ነው ገበሬዎች ገጠርን አየተው ስራ አልባ የከተማ ነዋሪዎች እንዲሆኑ የሚያደርገው?

የሚከፋው ደግሞ፥ በመሬት መውረስ አስራር፥ መሬት የሚወረሰው ለሕዝብ ጥቅም ነው ቢባልም፥ “የሕዝብ ጥቅም ያስከብራል ወይ” የሚለው ጉዳይ እንደ ተወረሰው መሬት የሚታይ ነው። ይህን የሚወስነውም መንግስት ሲሆን፥ በፍርድ ቤት በይግባኝ የማይፈተሽ ነው። ይህ በሆነበት ሁኔታ እና የካሳው መጠንም ገበሬው መሬቱን ከመወረሱ በፊት ከመሬቱ ከሚያገኘው ገቢ ጋር የማይመጣጣን በሆነበት ሁኔታ እና ካሳውን የሚከፍለው ባለሃብቱ ሳይሆን መንግስት በሆነበት ሁኔታ፥ የመሬቱ መወረስ ሕዝብን እንደሚጠቅም እንዴት መተማመን እንችላለን?

ከላይ ባለው ምሳሌ ገበሬው ከመሬቱ የሚያገኘው አመታዊ ጥቅም መቶ ሺ ሲሆን ባለሃብቱ ግን ከተመሳሳይ መሬት የሁለት ሚሊዮን ያህል ምርት ያግኝበታል። ይህን ሕዝባዊ ጥቅም ልንለው እንችላለን (ይህም ቢሆን ሙግትሊቀርብበት ይችላል)። እንበልና ባለሃብቱ መሬቱ ቢሰጠው ከመሬቱ የሚያገኘው አመታዊ ምርት፥ ሃምሳ ሺ ብር ብቻ ነው። እንዲህ አይነት ሰው መሬቱን እንዲከራይ ቢፈቀድለትም፥ ገበሬው ሊጠይቀው የሚችለውን ኪራይ መክፈል አይችልም። ስለዚህ በኪራይ መሬቱን አያገኝም። ማግኘትም የለበትም፥ ከሕዝብ ጥቅም አንጻር። ነገር ግን በኪራይ ማግኘት የማይችለውን መሬት፥ መንግስት ወርሶ በሊዝ መልክ ለባለሃብቱ እንደማይሰጠው እንዴት እርግጠኛ መሆን እንችላለን?

መሬትን ከግብርና ውጭ የሚፈልጉ አካላት መሬትን ማግኘት የሚችሉት ከመንግስት ብቻ መሆኑ፥ እነዚህ አካላት ምርጫ እንዳይኖራቸው፥ በተለይ ደግሞ የመንግስት አስራር ብልሹ ከሆነም፥ መሬት ማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ የተነሳ መዋእለ ንዋያቸውን እንዳያፈሱ የሚደረጉ ይኖራሉ። ስለዚህ ገበሬዎች በመሬታቸው ያላቸውን የግብይት ነጻነት መጨመር፥ ገደቦችን ማንሳት፥ ለባለሃብቶች አማራጭ በማቅረብ፥ የተሻለ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴዎችና ምርታማነት (ከግብርናው ውጭ) እንዲኖር ያደርጋል።

ባጭሩ ግብርናን ለማሳደግ የሚያስፈልጉ ግብአቶች፥ ገበያዎች፥ እውቀቶች፥ መሬትና የመሳሰሉት ጉዳዮችን መንግስት በብቸኝነት እያቀረበ፥ ግብርናው እያደገ እንደሆነ ሪፓርት ይደረጋል። በእነዚህ አቅርቦቶች በትርፍና ያለትርፍ የሚሰሩ ድርጅቶች ቢሰማሩ ደግሞ፤ ግብርናው እስካሁን ካደገበት በላይ በሆነ ፍጥነት፤ ሊያድግ ይችላል። ይህ ግን በዋናነት የመሬት ሕጉን እና የግብርና ግብይቶችን የሚገዙ ሕጎችን መቀየርና ማዳበር ይገባል። ሃሳቡን አንድ ጊዜ በመላው አገር ባንተገብረውም፥ በተወሰኑ ቦታዎች ግን መሞከር አይገባም ወይ?

በግብርና እና መሬት ግብይቶችን በማበረታታት፥ መንግስት ለግብርናው ዘርፍ ማደግ ያለበትን እጅግ ሰፊ ሃላፊነት መቀነስ ይቻላል። እውቀትና መዋእለ ንዋይ በግብርናውና በገጠሩ ክፍለኤኮኖሚ በሰፊው በተለያዩ ድርጅቶች እንዲፈስ ያደርጋል። በዚህም የመንግስት ሚና ይቀንሳል። በተወሰኑ ስራዎች (ለምሳሌ እጅግ ግዙፍ የመስኖ መስረተ ልማቶች) ላይ በማተኮር፥ የተሻለ ውጤት እንዲያመጣ ያደርጋል። የተሻለ የመሬትና የአፈር ጥበቃ ውጤቶችን ማስመዝገብ ይቻላል። በእርግጥ ገበሬዎች መሬታቸው እያከራዩ ከተማ እንዲሰበሰቡ ሊያደርግ ይችላል። ያም ቢሆን ኪራይ አንዴ እንዳይከፈል፥ ወርሃዊ ወይም በየሶስት ወሩ እንዲከፈል በሕግ በመደንገግ፥ በአካባቢዉ አማራጭ የኤኮኖሚ እድሎች ለገበሬዎች በመፍጠር፥ እና በመሳሰሉት የሚፈሩ አሉታዊ ዉጤቶችን መቀነስ ይቻላል። አሁንም ገበሬዎች መሬታቸውን በማከራየት በአካቢያቸው በሚገኙ ትንንሽ የገጠር ከተሞች ቢሰበሰቡም፥ የስራ እድል በመፍጠር ምርታማ እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል። ከሁሉም ግን መሬትን ከገበሬዎች ተከራይተው ለሚሰሩ ሰዎች እንደቀድሞው ሁሉ የመጠጥ ውሃ፥ ጤና፥ ሃይል፥ እና የመሳሰሉትን አገልግሎቶች የማቅረብ ሃላፊነት ላይኖርበት ይችላል። ቢኖርበትም በመጠን ትንሽ ይሆናል። መሬታቸውን ላከራዩ ሰዎች እነዚህን አገልግሎቶች ማቅረብ ቢኖርበትም፥ በትንንሽ የገጠር ከተሞች ስለሚሰበሰቡ፥ አገልግሎት የማቅረብ ወጪዉን ይቀንስለታል። አሁን በየመንደሩ ትንንሽ የመጠጥ ዉሃ ጉድጓዶችን በመቆፈር የሚያወጣውን ወጪ፥ ገበሬዎች ተሰብስበው በሚገኙባቸው ትንንሽ የገጠር ከተሞች ላይ አንድ ጥልቅ የዉሃ ጉድጓድ መቆፈር ወጪ ይቀንሳል።

3.6.      መሬትን ለረጅም ጊዜ መከራየት

አሁን ባለው የመሬት የሕግ ማእቀፍ መሬትን ለረጅም ጊዜ መከራየት የሚቻለው ለዘመናዊ እርሻ ነው። ከእርሻ ውጭ መሬትን ከገበሬ መከራየት እንደማይቻል ከላይ ተገልጿል።  ለእርሻም ቢሆን መሬትን መከራየት የሚቻለው ለሁለት አመታት ብቻ ነው። ከዛ በላይ ከሆነ ተከራዩ መሬቱን ለዘመናዊ እርሻ ማዋል አለበት። በዚህ አግባብ መሰረት አንድ ገበሬ ከሌላ ገበሬ መሬት መከራየት ከፈለገ ለሁለት አመት መከራየት ይፈቀድለታል። ከዚያ በላይ አይችልም። ምክንያቱም እሱም ገበሬ፥ ያኛውም ገበሬ። ከዛኛው ገበሬ በተለየ መሬቱን በዘመናዊ መልክ ካልተጠቀመበት። ዘመናዊ እርሻ የሚባለው ማሽን እና የተለያዩ ዘመናዊ ግብአቶችን የሚጠቀም ነው ብለን አስበን። አንድ አማካኝ ገበሬ እንዲህ የማድረግ አቅም የለውም። እንዲህ አይነት አቅም ያለው የመሬት ተከራይ ካለ፥ መሬቱን በረጅም ጊዜ የኪራይ ዉል ሊያገኘው ይችላል። ችግሩ እያንዳንዱ ገበሬ መሬቱን በሙሉ ማከራየት ሳይፈቀድለት፥ እንዲሁም የእያንዳንዱ ገበሬ እርሻ ከዚህ በላይ እንደተገለጸው ባንድ ቦታ የሚገኝ ሳይሆን ተበጣጥሶ በተለያየ ቦታ በሚገኝበት ሁኔታ፥ ምን አይነት ዘመናዊ እርሻ ነው መሬትን በመከራየት ማካሄድ የሚቻለው የሚል ጥያቄ ያስነሳል? አሁን ባለበት ሁኔታ መሬትን በረጅም ጊዜ የኪራይ ዉል አግኘተው ዘመናዊ እርሻ ያካሂዳሉ የሚባሉት የአበባ አምራቾች ናቸው። ከእነሱ ዉጭ አሁን ባለው የሕግ ማእቀፍ መሬትን ከገበሬ መከራየት የሚችለው እዛው አካባቢ ያለ ገበሬ ሲሆን፥ እሱም በአጭር ጊዜ ዉል ነው። ከዚህ የምንረዳው እውቀት፥ ገንዘብና፥ ቴኬኖሎጂ ወደ ገጠሩ ክፍል በመሳብ የግብርናን እድገት በማፋጠን ረገድ፤ አሁን ያለው የመሬት የሕግ ማእቀፍ ሚና እና አቅም ዜሮ ነው ማለት ይቻላል። በዚህ የሕግ ማእቀፍ የመሬት ኪራይ ፍላጎት እጅግ ትንሽ፥ ነገር ግን አቅራቢው ብዙ በሆነበት ሁኔታ፥ የኪራይ ዋጋ ዝቅተኛ ስለሚሆን፥ ገበሬዎች መሬታቸውን የማከራየት ፍቃዳቸው ዝቅተኛ እንዲሆን እና የመሬት ኪራይ ገበያ አገራዊ፥ ክልላዊ አድማስ እንዳይኖረውና በመንደር እንዲወስን ያደርገዋል።

3.7.      ሰፊ መሬትን ከብዙ ገበሬዎች በኪራይ የማግኘት ችግር

ከዚህ በላይ ባሉት ክፍሎች፥ የመሬት ኪራይን አስመልክቶ የተቀመጡ ገደቦች (ለእርሻ ብቻ መከራየት እና ሙሉ መሬትን ማከራየት አለመቻሉ) ያለባቸውን ችግሮች በማመላከት እነዚህ ገደቦች መነሳት እንዳለባቸው አሳይተናል። እነዚህ ገደቦች ቢነሱ፤ ካፒታል ያላቸው ሰዎች በበርካታ ገበሬዎች ተይዘው ያሉ መሬቶችን በመከራየትና በመጠቅለል ዘመናዊ እርሻ በማከናወን ግብርናው በፈጣን ሁኔታ እንዲያድግ ያስችላል። እነዚህ ካፒታል ያላቸው ሰዎች፥ እውቀትን፥ ግብአትን፥ ገበያን ከመንግስት የሚጠበቁ አይሆንም። በመሆኑም የመንግስትን ሃላፊነትም የሚጋሩ ይሆናሉ። የተበጣጠሱት ተያያዥ መሬቶች በአንድ ዉሳኔ ሰጪ አካል (ሰው ወይም ድርጅት) ሲሰበሰቡ፥ መታረስ የሌለበት ተዳፋት ቦታ ከእርሻ ይልቅ ዛፍ ይተክሉብታል። ምክንያቱም እንዲያ ባያደርጉ በመሬት መሸርሸር፥ ጎርፍ የተነሳ ከተዳፋቱ ታች የሚገኘው የራሱ መሬት አፈር ስለሚጎዳ። እንዲሁም በራሱ ወጪ ጥልቅ የዉሃ ጉድጓድ በመቆፈር ወይም ሌላ መንገድ ዉሃን በመያዝ፥ የመስኖ እርሻን መጠቀም ይጀምራል። መሬት በተበጣጠሰ ሁኔታ እንዲህ አይነት መዋእለ ንዋይን ለጥበቃና ግንባታ ስራዎች ማዋል አያዋጣም። አሁን ባለው አስራር ትልልቅ የመስኖ መሰረተ ልማቶችን እና የጥበቃ ስራዎችን ማካሄድ የሚችለው መንግስት ብቻ ነው።

ይህ እንዲሆን ግን ከዚህ በላይ ያሉ ገደቦችን ማንሳቱ ብቻ በቂ አይደለም። ምክንያቱም መሬት በተበጣጠስበት ሁኔታ መሬትን በኪራይ ለመሰብሰብ ከብዙ ገበሬዎች ጋር መዋዋልን ይጠይቃል። ከአርባ ገበሬዎች ጋር ተከራዩ ተስማምቶ፤ መሃል ላይ ያሉ ሁለት ገበሬዎች አንስማማም ሊሉ ይችላሉ። በዚህ ጊዜ የኪራይ ድርድሩ ላይሳካ ይችላል። ከብዙ ሰዎች ጋር በሚደረግ ድርድር እና ለድርድሩ መሳካት ሁሉም ሰዎች መስማማት ያለባቸው ከሆነ፥ እያንዳንዱ ሰዉ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ስለሚኖረው፥ ይህን በመጠቀም ከሚገባው በላይ ኪራይ በመጠየቅ፥ ከነአንካቴው ድርድሩ እንዲፈርስ ሊያደርግ ይችላል። ኪራዩ ሁሉን የሚጠቅም ሆኖ እያለ በዚህ ምክንያት ሊፈርስ ይችላል። ይህን ችግር መፍታት ያስፈልጋል።

መፍትሄዉን ግን እኛው ሃገር ካለ ሌላ ሕግ መማር እንችላለን። የንግድ ሕጉ መጽሃፍ አምስት የኪሳራ ሕግ ይባላል። ይህ ሕግ የሚጠቅመው አንድ ነጋዴ ለብዙ ባለገንዘቦች ባለ እዳ በሚሆንበት ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ ይህ ነጋዴ እዳውን ለመክፈል የገንዘብ ችግር ቢያጋጥመው፥ እያንዳንዱ ባለገንዘብ ገንዘቡን ለማስመለስ በሚያደርገው የተናጥል ክስ፥ ንብረት የማሳገድና የመሸጥ ሩጫና ውድድር የተነሳ፥ ንብረት ይባክናል። ተስፋ ያለው ነጋዴም (አገግሞ ሊወጣ የሚችል ቢሆንም) ከገበያው ተገፍቶ ሊወጣ ይችላል። ይህ አይነት ሁኔታ ሃገርንም፥ ባለገንዘቦቹንም፥ ባለእዳውንም አይጠቅምም። ተመሳሳይ እዳ ኖሮበት፥ ባለገንዘቡ ግን አንድ ቢሆን፥ የገንዘብ ችግር ስላለበት ብቻ ንብረቱ ላይሸጥ ይችላል። እዳውን እና አከፋፈሉን አስመልክቶ ከባለገንዘቡ ጋር በመስማማት፥ ንብረቱ ሳይሸጥ የንግድ ስራዉን ሊቀጥል ይችላል። ባለገንዘቡም ቢሆን ገንዘቡን ማግኘቱ አይቀርም። እንዲህ የሚሆነው ግን ነጋዴው ተስፋ እንዳለው ባለገንዘቡ ሲያምን ነው። ባለገንዘቦቹ ብዙ ሲሆኑ ግን ነጋዴዉ ተሰፋ ያለዉ ቢሆንም፥ ባለገንዘቦቹ በሚያደርጉት ሩጫና ውድድር ንግዱ ያከትማል። ንብረት ይባክናል። የኪሳራ ሕግ አንደኛው አላማ ይህን ማስቀረት ነው። ስለዚህ አንድ የገንዘብ ችግር ያጋጠመው ነጋዴ በፍርድ ቤት ቀርቦ ንብረቱ ከመሸጡ በፊት ንግዱ ተስፋ ያለው እንደሆነ በማስረዳት፥ የእዳውን አከፋፈል አስመልክቶ ሃሳብ እንዲያቀርብ እድል ይሰጠዋል። ማንም ባለገንዘብ በተናጥል ንብረትን ለማሳገድ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ይታገዳል። ባለገንዘቦቹ ይጠሩና ስለ እዳው አከፋፈል የቀረበውን ሃሳብ ሰምተው፥ ተወያይተው ድምጽ ይሰጣሉ። ሙሉ ለሙሉ ከተቀበሉት ችግር የለውም። ግን ላይቀበሉት ይችላሉ። በዚህ ጊዜ ፍርድ ቤቱ አብዛኞቹ ባለገንዘቦች በቀረበው ሃሳብ ከተስማሙ እና በፍርድ ቤቱ ግምገማ የቀረበው ሃሳብ ምክንያታዊ እና ሁሉን የሚጠቅም ነው ብሎ የሚያስብ ከሆነ፥ ምንም እንኳ ጥቂቶች ባይስማሙበትም ሊጸድቅና ሁሉም ላይ ተግባራዊ ሊሆን ይችላል። ከጠቀማቸውማ እንዴት እንቢ ይላሉ? ሁሉም መስማማት አለበት ማለት፥ እያንዳንዱ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት አለው ማለት ነው። ይህን መብቱን ተጠቅሞ የግል ድርሻውን ለመጨመር ስለሚሞክር፤ ስምምነቱ እንዳይሳካ ይሆናል። በዛ ላይ እያንዳንዱ ሰው በስምምነቱ እኩል ተጠቃሚ ላይሆን ይችላል። ለምሳሌ አንድ ሰው ከሃምሳ ገበሬዎች መሬትን በኪራይ መውሰድ ቢፈልግ፥ እነዚህ ሃምሳ ገበሬዎች ያላቸው መሬት በመጠንም በጥራትም እኩል ላይሆን ይችላል። ስለዚህ በኪራይ ዉሉ እኩል አይጠቀሙም። በድርድሩ መፍረስ ሁሉም እኩል አይጎዳም። በዚህ ጊዜ እያንዳንዱ መስማማት አለበት ማለት እኩል መሬት ለሌላቸው ሰዎች እኩል መብት መስጠት ነው።

ለመደምደም ያህል፥ መሬት ላይ የተጣሉት ገደቦች መነሳት ብቻውን አይጠቅምም። በኪሳራ ሕጉ ላይ እንዳሉት አይነት ድንጋጌዎችም በመሬት ኪራይ ሕጉ መካተት አለባቸው። ይህ ሲሆን፥ መሬትን ለእርሻና ለተለያዩ ስራዎች በሰፊው ከበርካታ ገበሬዎች ባንዴ በመከራየት ግብርናውን ማዘመን ይቻላል። ከገበሬዎች በመውረስ ለባለሃብት የመስጠት አስራር ያለበትን ችግር ይፈታል።

4.   ተጨማሪ ሃሳቦች ስለ ግብርና እድገትና የመሬት ፓሊሲና ሕግ

ከዚህ በፊት ባለው ጽሁፍ የሚከተሉትን ሃሳቦች አቅርቤ ነበር። በዋናነት የእነዚህ ሃሳቦች ተግባራዊነት ዉጤት፤ አሁን ተበጣጥሶ የሚገኘውን በገጠር መሬት ላይ የግብርና ውሳኔ መብት በአንጻራዊነት እንዲማከል ማድረጉ ነው። የግብርና ውሳኔ ማለት፥ በአንድ እርሻ ላይ ምን ላምርት? መቼ ላምርት? ምን አይነት እና መጠን ያለው ማዳበሪያ ልጠቀም? ምን አይነት የውሃ ቴኬኖሎጂ ልጠቀም? ምን አይነት ማረሻ፥ ማጨጃ፥ እና መውቂያ ልጠቀም? ምን አይነት የመሬትና አፈር ጥበቃና አስተዳደር አሰራሮችን ልከተል? እና የመሳሰሉት ናቸው። ከግብርና ውሳኔዎች ጋር የሚገናኙ የገበያ ውሳኔዎች ይኖራሉ። ለምሳሌ፤ ምን ያህል ምርቴን፥ መቼ፥ ለማን ልሽጥ? ምን ያህል ገንዘብ፥ ከማን፥ በምን ያህል ወለድ ልበደር? እነዚህና የመሳሰሉት ገበያ ነክ ውሳኔዎች ካነሳኋቸው ነጥቦች ጋር በቀጥታ አይገናኙም። እኔ ያነሳሁት የግብርና ውሳኔዎችን ነው።

አሁን ባለው ሁኔታ ሁለት አይነት መበጣጠሶች ይታያሉ። አንደኛው በቀደመው ጽሁፍ እንዳብራራሁት የመሬት መበጣጠስ አለ። በእርግጥ የመሬት መበጣጠሱ ሁኔታ እንደቦታው ይለያያል። እኔ ያደኩበትን አካባቢ ኢህአዴግ ከደርግ ነጻ እንዳወጣና ደርግን ተክቶ የሕዝብ አስተዳደር ሃላፊነትን ሲወስድ ካደረጋቸው ነገሮች አንደኛው መሬትን መልሶ ማከፋፈል ነው። ለምን? ምክንያቱም ጥቂት ‘አድሃሪያን’ ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ጥሩ ጥሩ መሬቱን በብዛት ስለያዙት። እኔ በበኩሌ የመሬት ክፍፍልና ራሱን አልቃወምም። የኔ ነጥብ የዚህ መሬት ክፍፍልና የክፍፍሉ ስልት ስለፈጠረው የመሬት መበጣጠስ ነው። እንደገለጽኩት አንድ ገበሬ ከግማሽ ኳስ ሜዳ ያነሱ፥ ሶስትና አራት እርሻዎች ይኖሩታል። አንደኛው የጓሮ መሬት ሲሆን ሌሎች ከመኖሪያ ጎጆዉ በተለያየ አቅጣጫ በተለያየ እርቀት ይገኛሉ።  የመሬት መበጣጠስ የምለው ይሄን ነው። ሁለተኛው አይነት መበጣጠስ፥ የግብርና ውሳኔዎችን የመስጠት መብት መበጣጠስ ነው።

4.1.      ኤኮኖሚ ኦፍ ስኬል (economy of scale)

የሁለት አይነት መበጣጠሶች፥ መጠን/ስኬል ከሚያስገኘው ጥቅም መጠቀም እንዳንችል ሆኗል። ብዙ አይነት የስኬል ጥቅሞች አሉ። አንደኛው ስኬል የሚባለውና ብዙ የሚታወቀው፥ ‘ኤኮኖሚ ኦፍ ስኬል’ ነው። ‘ኤኮኖሚ ኦፍ ስኬል’ ማለት በብዛት በማምረት የሚገኝ የነፍስ ወከፍ ወጪ መቀነስና የምርት መጨመር ነው።

ለምሳሌ አንድ መፅሃፍን በ200 እና በ2000 ቅጂዎች ስናሳትመው፥ የነፍስ ወከፍ ወጪው ይለያያል። 200 መፅሃፍ ሲታተም የአንዱ መፅሃፍ ወጪ 800 ብር ሊሆን ይችላል። በሌላ መልኩ 2000 ሲታተም ግን የነፍስ ወከፍ ወጪው 80 ብር ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አንድን ምርት በብዛት በማምረት የሚገኝ ጥቅም ነው። ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል? በብዙ ምክንያቶች።

አንደኛ ለምርቱ የሚያስፈልጉ ቋሚ ወጪዎች (fixed costs) ይኖራሉ። ትንሽ ቢመረትም፥ ብዙ ቢመረትም ቋሚ ወጪው ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ ቋሚ ወጪዎችን በሚገባ በመጠቀም፥ ምርትን ማላቅ ይቻላል። ሁለተኛው፥ በብዛት ማምረት ስፔሻላይዜሽንን ያበረታታል። ስፔሻላይዜሽን ደግሞ ምርትን ይጨምራል። ስፔሻላይዜሽን ምርትን የሚጨምረው ልምምድ በሚያመጣው የአቅም መዳበር፥ ከአንድ ስራ ወደ ሌላ ስራ በተደጋጋሚ በመዞር/በመቀያየር የሚባክን ጊዜና የትኩረት መባከንን ይቀንሳል። እንዲሁም ስፔሻላይዜሽን ለስታንዳርዳይዤሽንን ያመቻል። ይህ ደግሞ ምርታማነትን ይጨምራል። የአስተዳደርና የግብይት ወጪን በመጨመር።

ወደ ግብርናው ስንመጣ፥ መሬትና የግብርና ውሳኔ በተበጣጠሰበት ሁኔታ፥ “ከኤኮኖሚ ኦፍ ስኬል” መጠቀም እንዳንችል  ያደርጋል። ለምሳሌ አንድ ጥልቅ የዉሃ ጉድጓድ በመቆፈር፥ ብዙ መሬትን በመስኖ ማምረት ቢቻልም፥ መሬቶች ተበጣጥሰው እያለ እንዲህ ማድረግ ግን አይቻልም። ለምሳሌ 500 000 ብር ወጪ በማውጣት፥ አሁን በ100 ገበሬዎች ተይዘው ያሉ መሬቶችን በመስኖ ለሚቀጥሉት 20 አመታት ማምረት ይቻላል እንበል። በዚህ ደግሞ እጅግ ምርትን መጨመር እንችላለን እንበል። አሁንም አንበልና እነዚህ መቶ ገበሬዎች ከመሬቱ የሚያገኙት አመታዊ አማካኝ ምርት 50 ኩንታል ነው እንበል። ማለትም እነዚህ መቶ ገበሬዎች በጠቅላላው ከመሬቱ በአመት 5000 ኩንታል ያመርታሉ። ነገር ግን ይህ ጉድጓድ ቢቆፈር በእነዚህ ገበሬዎች ተይዞ ካለው መሬት በጠቅላላው መስኖ በመጠቀም ብቻ (ሌላ የተሻሻለ ግብአት ሳንጠቀም) 15000 ኩንታል ለሚቀጥሉት ሃያ አመታት ማምረት ይቻላል። ከኤኮኖሚ አንፃር ይህ የመስኖ መሰረተ ልማት መገንባት አለበት። ግን ማን ይገንባው?

መቶ ገበሬዎች ያላችው የዉሳኔ መብት በራሳቸው ትንሽ መሬት ላይ ነው። ስለዚህ እያንዳንዱ ገበሬ “ጉድጓድ ልገንባ አልገንባ” የሚለውን ሲያስብ፥ የሚያሰላው ብጣሽ መሬቱን ነው። ከዚህ አንጻር ደግሞ እያንዳንዱ ገበሬ “ጥልቅ ጉድጓድ አያዋጣኝም” ብሎ ያስባል። የመስኖ ውሃን ለምሳሌ አነሳን እንጂ ሌሎች ቴክኖሎጂዎችን “ልጠቀም አልጠቀም” የሚለውም በዚህ ይወሰናል። ማዳበሪያ፥ ማሽነሪዎች፥ አረም ማጥፊያ፥ እንዲሁም የግብርና ባለሙያ “ልጠቀም አልጠቀም” የሚለው በዚህ ይወሰናል።

የዉሃ ቴክኖሎጂ ሲታሰብም የሚታሰበው በገበሬው ጉልበት ሊሰሩ የሚችሉ ናቸው። ችግሩ “በኤኮኖሚ ኦፍ ስኬል” መጠቀም አለመቻላችን ብቻ ሳይሆን፥ የሚባክነውን ሃብት ይጨምራል። እነዚህ 100 ገበሬዎች የዉሃ ማቆሪያ በጉልበታቸው ቢገነቡ፤ በዚህ መሬት ላይ መቶ የዉሃ ማቆሪያ ጎድጓዶች ይቆፈራሉ ማለት ነው። ለምርት ሊውል የሚችል ሰፊ ቦታ ጉድጓድ ይቆፈርበታል። 100 ጉድጓድ ለመቆፈር የሚወጣው ጉልበትና ገንዘብ ሲደመር ብዙ ነው። ከዚህ ሁሉ አንድ ትልቅ ጉድጓድ ይበቃ ነበር።

ባጭሩ መሬትና የግብርና ውሳኔ መበጣጠስ “ከኤኮኖሚ ኦፍ ስኬል” እንዳንጠቀም ያደርጋል። የዚህ መገለጫ ስፔሻላይዜሽን አለመኖሩ ነው። እያንዳንዱ ገበሬ ባሉት ሶስትና አራት ትንንሽ መሬቶች ለመኖር የሚያስፈልጉትን የተለያዩ ሰብሎች ያመርታል። እንዲሁም ከብት ያረባል። ይህ ትልቅ ምርታማነት መጨመር እድልን ይቀንሳል። በዚህም የገጠር ኤኮኖሚ የግብይት ኤኮኖሚ ሳይሆን፥ ከእጅ ወደ አፍ እንዲሆን ያደርጋል። በዚህ ደግሞ ምርታማነት አይጨምርም።

4.2.      ባዮሎጂ ኦፍ ስኬል (biology of scale)

ሁለተኛው አይነት ስኬል “ባዮሎጂ ኦፍ ስኬል” ነው። ስኬል የኤኮኖሚ ጥቅም ብቻ አይደለም ያለው። ተፈጥሮ አንድ ነች። ተፈጥሮን በመከፋፋል የባዮሎጂ ፍራግመንቴሽን ያመጣል። ግብርና የተፈጥሮ ሃብት ላይ የተመሰረተ ነው። ለምሳሌ እነዚህ መቶ ገበሬዎች በያዙት መሬት ላይ፥ ባብዛኛው ባቄላ በመዝራት፥ እና ተዳፋት የሆኑ መሬቶችን ከማረስ ይልቅ የፍራፍሬ ወይም የሌላ አይነት ዛፎች መትከል ይቻላል። በዚህ ትልቅ ጥቅም ማምጣት ይቻላል። የአፈር መሸርሸርን በመቆጣጠር የአፈር ለምነትን ማሻሻል ይቻላል። ፍርቲላይዘር ብንጠቀም፥ በውሃ ተጠርጎ አይሄድም። ስለዚህ ምን ያህል ማዳባሪያ መጠቀም እንዳለንብን እርግጠኛ መሆን እንችላለን። የንጥረነገርና የማዳበሪያ የአፈር ዉስጥ ዝውውር ቢኖርም እንኳን እዛው ነው። ባቄላ ናይትሮጅንን በአፈር ዉስጥ የማመቅ ብቃት አለው። ስለዚህ በሚቀጥለው አመት ባቄላ ተዘርቶበት በነበረው መሬት፥ ስንዴ ቢዘራ ምርት ይጨምራል።

ከዚህ ጋር የሚያያዛው የፓሊኔሽን “የኤኮኖሚ ኦፍ ስኬልም” ይኖራል። ንቦችና ተመሳሳይ ነፍሳት ለግብርና ምርታማነት እስከ 50 ከመቶ አስትዋዕፆ ይኖራቸዋል (የማስታወስ ችሎታየ ካልከዳኝ)። በመሆኑም ለሁሉም መሬት በሚል ንብ በጎን ማነብ እንችላለን።

እንዲሁም ጠቅላላው መሬት ላይ አንድ አይነት ሰብል በመዝራት ይህ አዋጭ እንዲሆን ያደርጋል። ‘ባዮሎጂ ኦፍ ስኬል’ ማለት በሰፊ ቦታ አንድ አይነት ሰብል መዝራትን ብቻ አይመለከትም። በተመሳሳይ ቦታ የተለያየ ነገር ብንዘራም፥ ሰብሎቹ በባዮሎጂ አርስ በርስ መስተጋብር ያላቸው ከሆነ ይህን በማድረጋችን የተነሳ ምርት ሊጨምር ይችላል። ሰብሎች ብቻ አይደሉም የእርስ በርስ መስተጋብር ያላቸው። ስለዚህ የዶሮና አሳማ ምርትን ከበቆሎ ጋር አብሮ በማከናወን የሁሉንም ምርት መጨመር ይቻላል። አሁን ባለው የመሬትና የግብርና ውሳኔ መበጣጠስ፥ ‘ከባዮሎጂ ኦፍ ስኬል’ እንዳንጠቀም ያደርገናል።

እነዛ መቶ ገበሬዎች መሬቱን እና የመወሰን ስልጣኑን ተበጣጥሰውት ስለሆነ የያዙት፥ ከኤኮኖሚ ኦፍ ስኬል እና ከባዮሎጂ ኦፍ ስኬን ተጠቃሚ እንዳንሆን ሆነናል። በዚህ ደግሞ እነሱ ብቻ ሳይሆን እንደ አገርም እንጎዳለን።

4.3.      ችግሩ የእውቀት ጉዳይ አይደለም

ልብ ሊባል የሚገባው ይህ ችግር የእውቀት ችግር አይደለም። በእርግጥ የእውቀት ችግር አለብን። ነገር ግን ይህ የእውቀት ችግር አይደለም። የኢንሰንቲቭ/የጥቅምና የትጋት ጉዳይ ነው። የመሬት መበጣጠስ ትጋትን ይበጣጥሳል። ስለዚህ ገበሬዎችን በማስተማር አይፈታም። የትጋት ችግርን በመፍታት ብቻ ነው የሚፈታው። አንዳንዴ መንግስት የእውቀት እና የትጋት ችግርን በሚገባ ሲለይ አይስተዋልም።

4.4.      የግብይት ወጪ መናር

ገበሬዎች በጋራ ተነጋግረው፥ ተወያይተው፥ የግብርና ውሳኔዎችን በጋራ ሊወስኑ ይችላሉ። በሌላ አገር ንቦቻቸውን የሚያከራዩ አንቢዎች አሉ። ንብ አንቢዎች ማር ብቻ አይደለም የሚያመርቱት። የፓሊኔሽን አገልግሎትም ያቀርባሉ። ለዚህም ይከፈላቸዋል። ስለዚህ የንብ ቀፏቸውን በመኪና እየጫኑ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወሩ ይህን አገልግሎት በክፍያ ይቀርባሉ። ለንቦቻችውም ምግብ ያገኛሉ። በእነዚህ ሃገሮች አንድ ገበሬ በጣም ሰፊ መሬት ስላለው፥ ድርድር ወይም የግብይት ወጪው አነስተኛ ነው። በኛ አገር ቢሆን ይህ ንብ አንቢ ንቦቹ ሊሄዱበት በሚችሉ እርሻዎች ካሉ ገበሬዎች ጋር ሊደራደርና ሊስማማ ይገባል ማለት ነው። ከብዙ ሰዎች ጋር ድርድርና ስምምነት መፈፀም ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ከዚህ በፊት ባለው ፅሁፍ አሳይቻለሁ። 100 ገበሬዎቹ ተስማምተው በጋር የግብርና ውሳኔዎችን ማከናወን ከባድ ነው። የግብይት ውጪው ከፍተኛ ነው። ይህ ደግሞ በመሬትና በውሳኔ መበጣጠስ የመጣ ነው።

4.5.      የተወሰደው መፍትሄ

የተወሰደው መፍትሄ መንግስት ብዙውን የግብርና ውሳኔ ከገበሬው መውሰድ ነው። ለምሳሌ የመስኖ መስረተ ልማትን ማቅረብ። የግብርና ባለሙያና ማቅረብ። የተሻሻሉ ዘሮችን ማቅረብ። የአፈር ጥበቃ ስራን በዘመቻ ማከናወን። ችግሩ፤ የግብርና ውሳኔ መተላለፍ ያለበት እዛው ማሳ ላይ እንጂ፥ ግብርና ሚኒስቴር ቢሮ አይደለም። ስለዚህ የፍላጎትና የአቅርቦት አልተገናኝቶ ይመጣል።

ሁለተኛ፥ መንግስት ሁሉንም ነገር ለሁሉም በበቂ ሁኔታ ማቅረብ አይችልም። ስለዚህ መንግስትም ስራዉን ካመት አመት በቁጥ ቁጥ እየሰራ ይገኛል። ሶስተኛ የአፈር ጥበቃን ስንመለከት፥ እዛ መቶ ገበሬዎች ላይ የሚሰራው የአፈር ጥበቃ ሁሉንም እኩል ስለማይጠቅምና እኩል ወጪ ስለማያስወጣ፥ የተሰራዉ እርከን ባጭር ጊዜ ውስጥ ይፈርሳል።

የግብርና ዉሳኔ መበጣጠስን በህብረት ስራ ማህበራት ማከናወን ቢቻልም፥ የግብርና ውሳኔን በሙሉ በማዕከልበመጠቅለለ አይከናወንም። ገበያን ወይም ግብአትን መሰረት ያደረጉ አይደሉም። እንዲሁም የሕብረት ስራ ማህበራትን አስመልክቶ ሰፊ የአስተዳደር ችግሮች አሉ።

4.6.      ምን ይሻላል?

የመሬት ግብይትን በማበረታት የግብርና ውሳኔን መጠቅለል ቢቻልም፥ የመሬት ፓሊሲና ሕግ ግን ይህ እንዳይሆን አድርጓል። የሚከተሉት ለውጦች ያስፈልጋሉ

 1. ገበሬው መሬቱን አስይዞ ገንዘብ እንዲበደር ሊፈቀድ ይገባል። ዞሮ ዞሮ የሚያስይዘው ባለቤትነቱን አይደለም። በመሬት የመጠቀም መብቱን ነው። ለዚህ ደግሞ “አንድ ገበሬ ለምን ያህል ጊዜ በመሬቱ የመጠቀም መብት” እንዳለው ግልጽ ሊሆን ይገባል። ምክንያቱም የመሬቱ ዋጋ የሚወሰነው ገበሬዉ መሬቱን ምን ያህል አመታት ወደ ፊት መጠቀም ይችላል በሚለው ነው። አሁን ባለበት ሁኔታ መሬት ሙት ካፒታል ሆኗል።

 2. ገበሬው መሬቱን ሙሉ ለሙሉ እንዲያከራይ መፍቀድ። አሁን ያለውን ከግማሽ በላይ ማከራየት አይችልም የሚለውን ድንጋጌ ማንሳት።

 3. ገበሬው መሬቱን ለግብርና ብቻ ሳይሆን ለማንኛውም አገልግሎት እንዲያከራይ መፍቀድ።

 4. ገበሬው ለምን ያህል ጊዜ መሬቱን ማከራየት ይችላል የሚለው የግብርና እና ሌላ አይነት ኢንቨስትመንት በሚያበረታታ አኳኋን መወሰን።

 5. መንግስት ከገበሬዎች እየወረሰ ለባለሃብቶች የሚሰጠውን አስራር ማስቀረት። መንግስት ሊወርስ የሚችለው ለሕዝብ ጥቅም ሲሆን ብቻ መሆን አለበት። የሕዝብ ጥቅም የሚለው ደግሞ እጅግ በጠባቡ ሊተረጎምና በፍርድ ቤት ሊፈተሽ ይገባል። የካሳው መጠንም ገበሬው በመሬቱ ሲያገኝ ከነበርዉ ጥቅም ጋር ተመጣጣኝ መሆን አለበት።

 6. የመሬት ግብይትን የሚያግዝ የመረጃ ስርአት መንግስት በማደራጀት ማቅረብ አለበት።

 7. በብዙ ሰዎች ተበጣጥሶ ያለን ቦታ መከራየት የሚፈልግ ሰዉ፤ ከኪሳራ ሕግ ጋር የሚመሳሰል የጋርዮሽ የድርድር ስርአት መፍጠር። በዚህም የቀረበውን የኪራይ ሃሳብ አብዛኛው የገጠር መሬት ባለይዞታ ከደገፈና፥ አገርን ይጠቅማል ተብሎ ሲታሰብ፤ በሁሉም ላይ ተግባራዊ የሚሆንበት አስራር መዘርጋት። ለዚህም አስተማማኝ መመሪያና የቁጥጥር ስርአት መዘርጋት።

እነዚህ የለውጥ ሃሳቦች እንዴት እንደሚጠቅሙ ከላይ እና ከዚህ በፊት በወጣው ጽሁፍ ቀርቧል። በዚህ ጽሁፍ ደግሞ ሌላኛው አማራጭ ይቀርባል።

4.7.      የእርሻ ኩባንያዎች

የግብርና ውሳኔን መጠቅለል የሚቻለው በኪራይ ብቻ አይደለም። ከላይ በተቀመጠው ምሳሌ መቶዎቹ ገበሬዎች መሬታቸውን አዋጥተው አንድ ኩባንያ ድርጅት ሊመሰርቱ ይችላል። በርጅቱ የሚኖራቸው ድርሻ እንዳዋጡት መሬት ይሆናል። በዚህም በድርጅቱ አክስዮን ይኖራቸዋል። ባለቤቶች ይሆናሉ። ነገር ግን ድርጅቱ የሚተዳደረው በባለሙያዎች ይሆናል። ማለትም በባለቤትነትና በአስተዳደር መካከል ልዩነት ይኖራል። በእርግጥ እንደ ባለ አክስዮን ቦርድ በመምረጥና አስተዳደሩን በመቆጣጠር ሚና ይኖራቸዋል። ድርጅቱ በራሱ ስም ገንዘብ መበደር ይችላል። ንብረት ማፍራት ይችላል። ውል ይዋዋላል። የገበሬዎች ሃላፊነት የተገደበ ነው። ገበሬዎች በምርት ሂደት ከተካፈሉ እንደ ባለይዞታ ሳይሆን በድርጅቱ ተቀጥረው ነው። በዚህም ደመወዝ ያገኛሉ።

የተዋጣው መሬት የድርጅቱ ይዞታ ይሆናል። ስለዚህ የግብርና ውሳኔ በድርጅቱ ይሰጣል። ይህን በማድረግ ከላይ የተጠቀሱትን የኤኮኖሚ እና የባዮሎጂ ስኬል ጥቅሞች ማግኘት ይችላል። በኪራይም ተመሳሳይ ጥቅም ማግኘት ቢቻልም፥ ገበሬዎቹ ኪራይ ብቻ ነው የሚያገኙት። ተከራዩ በመሬቱ ምንም ያምርት ምንም ኪራያቸውን ያገኛሉ። ስለዚህ ሪስኩን የወሰደው ተከራዩ ነው። መሬቱን በኩባንያ በመጠቅለል፥ ገበሬዎቹ የሚያገኙት ከትርፍ እንደ አክስዮናቸው መጠን መከፋፈል ነው። ገበሬዎቹ ሪስኩን ይካፈላሉ። ቢከስር ግን ሃላፊነታቸውን የተገደበ ነው።  ትልቁ ችግር አስተዳደሩን የመቆጣጠር ነው።

የተለመደ የግብርና ግብይት የእኩል ማረስ የሚባለው ነው። መሬትህን በሌላ በማሳረስ፥ ከሚገኘው ምርት እኩል ወይም በሌላ መልኩ መካፈል ነው። በዚህ ሪስኩንም አራሹና ባለይዞታው ይካፈሉታል።

ይህኛውን አማራጭ ለማበረታታት፥ ለግብርናው ልዩ ጸባይ በሚመች መልኩ የድርጅት ሕግ ማዳበር ሊጠይቅ ይችላል። ለሌሎች ንግዶች የሚውለው የንግድ ድርጅቶች ሕግ ለግብርና ላይስማማ ይችላል።

በአማራጮቹ መካከል ውድድር በመፍጠር፥ ለገበሬዎቹ አማራጭ በመስጠት፥ ምርትን ማላቅ ይቻላል። እንዲሁም የተለያዩ ቦታዎች ላይ ሁለቱ አማራጮች እኩል ተመራጭ ላይሆኑ ይችላሉ።

4.8.      የግብርና ባለሙያ ቀጣሪን ማብዛት

ከዚህ በፊት ባለው ጽሁፍ መንግስት ብቸኛው የግብርና ባለሙያ ቀጣሪ መሆኑ የሚያመጣውን ችግር አይተናል። ከዚህ በላይ ያሉትን ሁለቱን አማራጮች መተግበር፥ ለግብርና ባለሙያዎች አማራጭ ቀጣሪ መፍጠር ነው። በዚህ ደግሞ ሰዎች መርጠው ወደ ግብርና ሙያ እንዲገቡና እንዲቆዩ ያደርጋል።

ከዚህ በተጨማሪ፥ የፌዴራል መዋቅሩ የሰጠንን የዴሞክራሲ ላብራቶሪነት ተስፋ በሚገባ ቢተገበር፥ ለግብርና ባለሙያዎች ተጨማሪ እድል ይፈጥራል።

4.9.      አተገባበር

ከዚህ በላይ ያሉትን ሃሳቦች በሙሉ በሃገሪት መተግበር አያስፈልግም። በተወሰኑ አካባቢዎችና የተወሰኑ ምርቶችን ለማበረታት በሚል በሙከራነት ተግብሮ ፍሬውን መገምገም ያስፈልጋል። ሲያዩት፥ ሲሰሙት፥ ሲያነቡት ሎጂካል ስለመሰለን ብቻ በሃገር ደረጃ አንድን መፍትሄ መተግበር ሃብት ማባከን ነው። መጀመሪያ በሙክራ መተግበር፥ መረጃ መሰብሰብና መገምገም ያስፈልጋል።

5.   የግብይት ወጪ በግብርና

የግብይት እና የምርት ወጪ የሚባሉ ሁለት መሰረታዊ ወጪዎች አሉ። የምርት ወጪ የምትለው፥ አንድን አገልግሎት ወይም ሸቀጥ ወይም ነገር ለማምረት የምታወጣው ነው። ቋሚ እና ተቀያያሪ ወጪ ሊሆን ይችላል። ቋሚ የሚባለው ወጪ መጠን፥ በምርትህ መጠን አይወሰነም እስከተወሰነ ደረጃ ድረስ። ስለዚህ አንድም አመረትህ ሺተሚሊዮን ቋሚ ወጪዉ ተመሳሳይ ነው። ስለዚህ ብዙ ማምረት ከመጠን እንድትጠቀም ያደርግሃል። ነገር ግን ምን ታመርታለህ? ምንድን ነው ፍላጎትህ? ያመረትከውንስ ለማን እና በምን ያህል ትሸጣልህ? ግብይት ከማን ጋር ትፈጽማለህ? በድርድር ሂደት ያኛው ተዋዋይ ወገን የሚነግርህን መረጃ እንዴት ታረጋግጣለህ? ያኛው ሰውየ ያልነገረህ መረጃ ስለመኖሩ እንዴት ታረጋግጣለህ? እንዴት ትደዳደራለህ? ስምምነት ከገባህ በዃላ ያኛው ሰው ግዴታውን ለመወጣቱ ምን ማረጋገጫ አለህ? ግዴታውንስ በተባለው መጠን እና ጥራት ስለመወጣቱ እንዴት ትከታተላለህ? እነዚህ ሁሉ የግብይት ወጪ ይባላሉ።

ሁለቱ አይነት ወጪዎች ይገናኛሉ። የግብይት ወጪ መናር፥ ግብይት እንዲቀንስ ያደርጋል። ግብይት አነስተኛ ሲሆን፥ ምርት ይቀንሳል። ምክንያቱም ምርት የሚጨምረው ስፔሻላይዜሽን ሲኖር ነው። ነገር ግን የግብይት ወጪ መናር ስፔሻላይዤሽን እንዲቀንስ ያደርጋል። አንድ ምርት ላይ ብቻ አተኩረህ፥ በዚህም ምርትህን በጣም ልትጨምር ትችላለህ። ነገር ግን ሁሉንም ምርት ለግል ፍጆታህ ላትፈልገው ትችላለህ። እንዲሁም፥ የአንተ ፍላጎት አይነት በአንድ ምርት ብቻ ላይገደብ ይችላል። ሌሎች ብዙ የምትፈልጋቸው ነገሮች ይኖራሉ። ችግር የለውም፥ ትርፍ ምርትህን ሸጠህ፥ አንተ ያላመረትከውን ነገር ግን የምትፈልጋቸውን ነገሮች ከሌላ ትገበያለህ። ይህን የምታደርገው ግን የግብይት ወጪዉ አነስተኛ ከሆነ ነው። የግብይት ወጪዉ ከፍተኛ ከሆነ፥ የምትፈልገውን ወጪ በሙሉ ራስህ ለማምረት ትሞክራለህ። በዚህም ሁሉም ፍላጎትህ በመጠኑ ይሟላል። ነገር ግን በአይነትና በመጠን የማይሟሉ ፍላጎቶች ይኖርሃል።

የግብርና ክፍለኤኮኖሚ ባብዛኛው ከእጅ ወደ አፍ ነው።  አብዛኛው አርብቶ እና አርሶ አደር ከብትም ያረባል፥ ከሰብል ምርትም ከሁሉም አይነት ለማምረት ይሞክራል። ጥያቄው ምርትን እንዴት እንጨምር የሚል ነው?

ባብዛኛው ትኩረታችን እንዴት አድርገን የምርት ወጪውን እንቀንስለት የሚል ነው። አርሶ አደሩ የሚፈልገውን ግብአት በሚፈለገው መጠን እና አይነት እና ጥራት ማቅረብ። ስለዚህ የግብርና እውቀት፥ መስኖ፥ ጤና፥ የመጠጥ ዉሃ፥ ማዳበሪያ፥ ምርጥ ዘር፥ ትራክተር፥ ማጨጃ፥ መውቂያ፥ ሰውሰራሽ የከብት እርባት ቴክኖሎጂ፥ የከብት ህክምና አገልግሎት፥ የአየር ሁኔታ ትንበያ፥ እና የመሳሰሉትን የምርት ወጪ መቀነሻ ወይም የምርት መጨመሪያ ግብአቶችን ማቅረብ እንደ መፍትሄ ተወስዶ እየቀረበ ነው።

ልብ በሉ በሃገራችን ያለው አርብቶ እና አርሶ አደር ቤተሰብ ወደ አስራአምስት ሚሊዮን ይገመታል። ለዚህ ሁሉ ማነው አቅራቢው? ባብዛኛው መንግስት። የሚያቀርበው ነገር ፍላጎትን መሰረት ስለማድረጉ እንዴት እናወቃለን? ወይስ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ያመነውን ነው የሚያቀርበው? የአቅርቦቱን ዋጋ የመቀነስና ጥራትን የማሻሻል፥ አይነትን የመጨመር ተነሳሽነት ይኖረዋል? አቅራቢው ተወዳዳሪ ከሌለው እና ሸማቹ ደግሞ አማራጭ ከሌለውና መረጃው ከሌለው እንዴትንስ ብሎ አቅራቢዉ ዋጋን በመቀንስና ጥራትና አይነትን በማሻሻል ይደክማል?

በግብርናው ህይወቱን የመሰረተዉ ህዝብ 80 ሚሊዮን ይቆጠራል። ሃገራችን የውጭ ምንዛሬ የምታገኘው አብዛኛውን ከግብርና ምርቶች ነው። ለዚህ ወሳኝ ሴክተርን ለማሳደግ ያለንን ስልት ባብዛኛው የምርት ወጪን የመቀነስ አማራጭ ነዉ። በዚህ አማራጭ መቅረብ ያለበት የግብአት መጠን አይነት፥ እና የአቅርቦቱ ተጠቃሚ ብዛት እና የምህዳር ልዩነትን ግምት ወስጥ ስናስገባ፥ እንዴት ለዚህ ከባድና ወሳኝ ሃላፊነት የተማመንነው አንድ መንግስትን ይሆናል? ግብርናው እኮ አድጓል ይህም ሆኖ በተከታታይ ላስራ አምስት አመታት። የአቅራቢዉን ማንነት እና ቁጥር እጅግ ብናበዛው ምን ያህል ከዚህ በላይ ግብርናው ሊያድግ እንደሚችል እናስበው።

የምርት ወጪ ላይ ከመስራት በተጨማሪ፥ የግብይት ወጪን በከፍተኛ መጠን መቀነስ ሌላው መፍትሄ ነው። የግብይት ወጪን ስንቀንስ፥ ግብይት አትራፊ ይሆናል። ግብይት አትራፊ ከሆነ፥ እያንዳንዱ ገበሬ ከብትም ዶሮም አርቢ፥ ንብ ናቢ፥ በቆሎ፥ ማሽላ፥ ስንዴ፥ ባቄላ፥ በርበሬ፥ ኑግ እና ሌሎች የሚፈልጋቸውን ነገሮች አምራች መሆን የለበትም። ለዛውም በዛች ትንሽ መሬትና ከሷ ብሶ ሶስት ቦታዎች ላይ ተራርቃ በተበጣጠሰች መሬት። ከዚህ ሁሉ አንዱን ቢመርጥስ? አንዱን መምረጡ ፍላጎት መገደብ ማለት አይደለም። የመረጠውን ሰብል ምርት እጅግ ከፍተኛ በሆነ መጠን ያሳድገዋል። ስፔሻላይዝ አድርጓል ማለት ነው። ከሰብሉ ወስጥ የሚያስፈልገውን ያህል አስቅርቶ፥ የተቀረውን ሽጦ፥ በሚያገኘው ገንዘብ እርሱ የሚፈልገውን ነገር ግን እራሱ ያላመረተውን ምርት ይገበያል። ነገር ግን ግብይት ወጪ አለው። ይህ ወጪ ማለት በስፔሳላይዜሽን የተገኘን ተጨማሪ ምርት የሚቀነስ ነዉ። መጠኑ ሲጨምር፥ ስፔሻላይዜሽን ይቀንሳል። ሁሉንም ላምርት ይላል። በዚህ ምርቱ ይቀንሳል።

ልብ ሊባል የሚገባው ይህ ችግር ከእውቀት ማነስ የሚመጣ አይደለም። ይህ የጥቅም፥ ወጪ፥ ትጋት፥ እና ሪስክ ጉዳይ ነው። ጥያቄው ግብርናውን ለማሳደግ ምን ያህል ግብይት ወጪን የመቀነስ ስራ ሰርተናል? የሃገራችን አማካይ ገበሬ አሁንም የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ በተቻለው መጠን ራሱ ለማምረት ይሞክራል። የእጅ ወደ አፍ የሆነውም በዚህ ነው። ይህን ችግር ለመቀንስ የምርት ወጪን ለመቀነስ መስራት ብቻውን በቂ አይደለም። እንደውም የምርት ወጪን መቀነስ፥ ከስራው ከባድነትና ብዙነት እንዲሁም ከሃገሪቱ ስፋትና የአርሶና አርብቶ አደሩ ህዘብ ብዛት አንጻር፥ እና ለዚህም ሃላፊነቱን የወሰደው በዋናነት መንግስት መሆኑ አኳያ፥ ምናልባት የግብይት ወቺን በመቀነስ ላይ ብንሰራ አያዋጣም ወይ የሚል ጥያቄ ይነሳል?

መንግስት የጫትን ምርት ወጪ ለመቀነስ ሲል የሰራው የምርጥ ዘር ጥናት፥ መስኖ እና የመሳሰሉት ስራዎች የለም። ግን እንደ ጫት ምርት የተንሰራፋ የለም። በአይነት፥ በመጠን፥ እና ጥራት እየጨመረ ነው። ምክንያቱ ምንድን ነው? መንግስት የጫትን የምርት ወጪ ለመቀነስ የሰራው ስራ ባይኖርም፥ ስራው ግን አልተሰራም ማለት አይደለም። መንግስት ባይሰራውም ሰሪ ግን አላጣም። ይህ የሆነው ደግሞ የግብይት ወጪውን በመቀነስ አምራች የበለጠ ተጠቃሚ በመሆኑ ነው።

አሁንም የሚገርመው የጫትን የግብይት ወጪን ለመቀነስ በሚል በመንግስት የተሰራ ስራ አለመኖሩ ነው። ዋናው መልእክቴ፥ የግብርና ግብይት የሚባሉት እነማን ናቸው? እነዚህ ግብይቶች ጋር ተያይዘው ያሉ ወጪዎች ምንድን ናቸው? እነዚህ ግብይቶች በመጠን ምን ያህል ናቸው? ወጪያቸውስ? ወጪውን ቢቀንስ ግብይት በምን ያህል መጠን ይጨምራል? ግብይት በዚህ ያህል መጠን ሲጨምር ምርትስ በምን ያህል ይጨምራል? የግብይት ወጪን አይነትና እያንዳንዱን ግብይት ወጪ እንዴት መቀንስ እንደሚቻል፥ በዋናነት ከግብርና ውጭ ያሉ ምሳሌዎችን በመጠቀም ወደፊት አብራራለሁ? የግብይት ወጪ ከፍተኛ በመሆኑ የተነሳ፥ ግብይትና ምርት ይቀንሳል። በዚህ እንደ አገር እንጎዳለን። ሁላችንም ግን አንጎዳም። አንዳንዶቻችን እንጎዳለን። የጉዳት መጠናችንም ተመሳሳይ አይሆንም።

ሶስት ነገር ግን ላይ እርግጠና እንሆናለን። አንደኛ፥ የምንጎዳው አብዛኛው ህዝብ ነው።ሁለተኛ ነገር በዚህ እጅግ የሚጠቀሙ ይኖራሉ። በቁጥር ትንሽ ናቸው። ሶስተኛ፥ ችግሩ አብዛኛው ተጎድቶ ትንሹ መጠቀሙ ሳይሆን፥ ትንሹ ጥቅሙን ለመጨመር፥ አብዛኛው ደግሞ ጥቅሙን ላለማጣት በመከላከል እና በማጥቃት ስራ መጠመዳቸው ነዉ።

ክፍል ሁለት በሚቀጥሉትጉዳዮች ላይ ያተኩራል

 1. ገንዘብን ከከተማ መሬት፥ ቤት፥ መኪና፥ ፍጆታ፥ እና አገልግሎት ማውጣት

 2. በመጨረሻም ገንዘብን ከግብይት፥ ግብርና እና መሬትና የመሳሰሉት ወደ ኢንዱስትሪዉ መሳብ

 3. ኢህአዴግ የአርሶና የአርብቶ አደር ፓርቲ ነዉ?[1] በዚህ ረገድ “የአፈጻጸም እንጂ የፓሊሲ ችግር የለብንም” የሚለውን አነጋገር ልብ ይሏል። አሁን ያለውን ፓሊሲ ተከትለን፥ በአማካኝ 10 ከመቶ በላይ በሚሆን መልኩ አድገናል። ነገር ግን ያደግነው በፓሊሲው የተነሳ ነው ወይስ ፓሊሲውም እያለ ነው እንዲህ ያደግነው? በፓሊሲዉ ነው ከተባለ፤ አፈፃፀማችንን በማላቅ የተሻለ እድገት ልናስመዘግብ እንችላለን። ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ፓሊሲው ላይ ማስተካከያ በማድረግ ከዚህም በላይ ማደግ እንደማንችል በምን አወቅን። የፓሊሲ ችግር የለብንም ብሎ መጀመር ከልምድ የመማርን እድልን ያጠባል። ፓሊሲን የሃይማኖት ያህል ቦታ ይሰጣል። በመሆኑም ይህ ሊስተካከል ይገባል። ፓሊሲን በጥብቅ መከታተልና ልምድና መረጃን መሰረት ያደረገ ማስተካከያዎች መውሰድ ያስፈልጋል።

ከዚህ በተጨማሪ አሁን ያሉንን ዋና ዋና ፓሊሲዎች እንኳን ብንወስዳቸውና እንዴት እንደወጡ ብንመረምራቸው፥ የፓሊሲ ችግር የለብንም ብለን አፍ ሞልተን ለመናገር ያዳግታል። በተለይ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ህልፈት ህይወትን ተከትሎ ሁሉንም ፓሊሲዎች ይፅፏቸው የነበሩት እሳቸው እንደነበሩ ጓዶቻቸው ነግረውናል። (እሳቸው ይህን ሲፅፉ እናንተ የት ነበራችሁ? በምን የሞራል ልእልና ነው የእሳቸውን ሌጋሲ እናስቀጥላለን የምትሉት? እንዲህ ብለን እንኳን እልነገርናቸውም።) እንደውም አምስት የሚሆኑ የፓሊሲ ሰነዶች በመለስ ዜናዊ ፋዉንዴሽን የመለስ ዜናዊ ድርሰቶች በሚል ታትመው ለገበያ ቀርበዋል። በእነዚህ ሰነዶች ላይ የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች ሲወያዩ፤ የዉይይቱ አላማ ሰነዶቹን ለማበልፀግ ግብአት መሰብሰብ እንደሆነ ቢነገርም፥ አሁንም ድረስ ሰነዶቹ በመጀመሪያ ህትመታቸው የያዙትን ቅርጽ ይዘው አሉ። እነዚህ የፓሊሲ ሰነዶችስ እውነት ፓሊሲዎች ናቸው? መቼ ነው ለመንግስት ቀርበው (በሚኒስትሮች ምክር ቤትና ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት) የፀደቁት? ሌሎች ፓሊሲዎቻችንስ እንዴት ነው የሚዘጋጁት? እነዚህን ጥያቄዎች ስናነሳ፥ “የፓሊሲ ችግር የለብንም” የሚለው አነጋገር ተቀባይነት ሊኖረው እንደማይገባ ግልፅ ይሆናል።

[2] መንግስታዊ ያልሆኑ እና ያለትርፍ የሚሰሩ ጥቂት ድርጅቶች እየሰሩ ያሉትን ስራ ሳንዘነጋ።

#Agriculturalpolicyandlaw #Ethiopialandpolicyandlaw #RuralDevelopmentPolicyandLaw #Ethiopia #Landrentals #capitalanddevelopment

0 views
 • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.