• Dr. Mulugeta Mengist

የችግሩ ምክንያት ምንድን ነው?

Updated: Nov 17, 2019


“አሁን ያለዉ ሁኔታ ወይም ችግር” ይሉታል። እስካሁን ስም አልወጣለትም። ልማቱ የወለደው፥ ልማቱ የወለደዉ የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች፤ ተደማሪ ፍላጎቶች፥ የከንአንን ማርና ወተት ለማየት መጓጓት፥ የሚሉ አባባሎች ችግሩን/ሁኔታዉን ከመግለጽ ይልቅ ለችግሩ/ሁኔታው ምክንያት ናቸዉ ተብለዉ የታሰቡትን ነገሮችና መፍትሄዎች የሚያመለክቱ ናቸዉ። የችግሩ ምክንያት፥ የበፊት ፍላጎቶች ሲሟሉ አዲስ የተፈጠሩ ፍላጎቶች ናቸዉ የሚል ነው። ከዚሁ ጋር የሚያያዘዉ፥ የእስካሁኑ የልማት ፍጥነት የፈጠረው ከዚህም በላይ መሄድ እንችላለን የሚል መተማመን ነዉ። ወይም፥ ከችግሮች አየወጣን ስንሄድ፥ የተስፋዋ ምድር አየቀረበች ስትሄድ፥ በፍጥነት ደርሶ ማርና ወተት የሚፈስበትን አገር ለማየት መጓጓት ነዉ። ተቀራራቢ ናቸዉ። መፍትሄዉም ፍጥነት መጨመር ነው በሚል ይገለጻል።

የችግሩን ምክንያቶች በዚህ መልክ ሲቀርቡ፥ በመንገዱና በመጓጓዣዎቹ ምርጫ ፍጹም እምነት እንዳለን ያሳያል። መንገድ ተሳስተናል ወይም ሌላ የተሻለ መጓጓዣ ሊኖር ይችላል የሚል የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል ጥርጣሬ እንደሌለን ያሳያል። ለምን? መጠራጠር ፍጥነትን ስለሚቀንስ? ስለምርጫዉ ትክክለኛነት የማያወላዳ ማስረጃ ስላለን ነው?

የፓሊሲ ምርጫና ትግበራ የሃይማኖት ጉዳይ አይደለም። ስለምርጫችን ዶግማቲክ መሆን፥ የስኬት ሳይሆን የዉድቀት ግብአት ነው። ሳይንሳዊ አሰራር ዶግማቲክ አይደለም። የሳይንስ ግኝት ሁልጊዜ ጊዜያዊ ነዉ። ተቃራኒ ማስረጃ ከመጣ፥ የቀደመዉ ድምዳሜ ውድቅ ይደረጋል። ተቃራኒ ማስረጃ እስኪመጣም ዝም አይባልም። ድምዳሜው በተደጋጋሚ በሚሰበሰቡ መረጃዎች ይፈተናል። ስለዚህ የፓሊሲ ጉዳይም እንዲሁ ነዉ መሆን ያለበት።

የፓሊሲና የመሳሪያ ምርጫችን ለዘመናት አይደለም። መረጃዎች ሌላ የተሻለ ፓሊሲና መሳሪያ እንዳለ እስከሚያሳዩ ድረስ ነዉ። እስከዛ ድረስ ይተገበራል። አተገባበሩን አስመልክቶ መረጃ ይሰበሰባል። መረጃዉም ይተነተናል፥ ምርጫችን አሁንም ትክልል ስለመሆኑ ለመመርመር። ከምን አንጻር ነዉ የሚመረመረዉ? ስራ ስንጀምር የታለሙ ግቦች/ዉጤቶች እየተገኙ ስለመሆኑ ወይም በተባለዉ ወቅት የታሰቡት ዉጤቶች ይገኙ እንደሆነ? መረጃዎቹ የዉጤት ጉድለት ካሳዩ፥ የጉድለቱ ምንጭ ሊለይ ይገባል? እንዲሁም የተሻለ ሌላ ፓሊሲና መሳሪያ ስለመኖሩ ምርመራ ማድረግ ይገባል። ምንም እንኳን ጉድለት ባይኖርም፥ የተገኙ ዉጤቶችን የሚያሳድጉ ለዉጦች ስለመኖራቸዉ የማያቋርጥ ምርመራ ያስፈልገዋል። እኛ ግን የፓሊሲ ችግር የለብንም እያልን ነው። ችግሩ ያፈጻጸም ነው እያልን ነው። እንዴት ነዉ ነገሩ እንዴት አዉቀነዉ ነው? የምንገነባቸዉና የገነባናቸዉ ግድቦች ላይ ብዙ የዲዛይን ለዉጥ እያደረግን (ያላሰብነዉ ነገር አጋጥሞን፥ ወይም የተሻለ መረጃ ስለተገኘ ወይስ ስህተት መስራታችንን ስለደረስንበት) እንዴት ነዉ ታዲያ የፓሊሲ ትክክለኛነት ላይ ሙሉ ለሙሉ እርገጠኛ የሆነው? ባይሆን ፕሮጀክትን አስመልክቶ ነበር የበለጠ እርግጠኝነት የሚጠበቀዉ።

አሁን ስለፓሊሲያችን ትክክለኛነት ያሉ ጉዳዮችን ለጊዜው ተወት አድርገን፥ ስለችግሮች ምርመራ ትንሽ ልበል። ለማንኛዉም ችግር፤ በተለይ ደግሞ አገራዊ ለሆኑ፥ አንድ ምክንያት ብቻ ከመፈለግ መጠንቀቅ አለብን። ላንድ ችግር ምክንያቶቹ ብዙ ሊሆኑ ይችላሉ። በእርግጥ አያንዳንዱ ምክንያት በራሱ ችግሩን ላያመጣዉ ይችላል። ነገር ግን የብዙ ጉዳዩች መስተጋብርና ቁርኝት አያንዳንዱ ጉዳይ ሊያመጣዉ ከሚችል የበለጠና የሰፋ ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል። እያንዳንዱ ብጥስጣሽ ገመድ ካንድ ነጥብ ወደ ሌላ ነጥብ ላይደርስ ይችላል። ገመዶቹን አስረን ከዘረጋናቸዉ ግን ከመድረሻዉ ነጥብም ሊያልፍ ይችላል። በተለይ ደግሞ ችግሩ የሚመለከተዉ ስርአት ኮምፕሌክስ የሚባል ከሆነ (በተለያዩ ስርአቶች የተገነባ አብይ ስርአት ወይም የተለያዩ መስተጋብር ባላቸዉ ክፍሎችና ሂደቶች የተገነባ ስርአት ከሆነ፥ አንዲሁም የስርአቱ አካባቢያዉ አድማስ ሰፊ ከሆነ)።

ሁለተኛ፥ ችግሮቹን ስንለይ ስለእይታ አድማሳችን ሁለት ነገሮችን ማስተዋል ይኖርብናል። አንደኛ፥ ምርመራችን ችግሩ ያጠቃዉን ወይም የሚመለከተዉን ስርአትና ክፍሎች በሚገባ የሚያዳርስ መሆን አለበት። ሁለተኛ፤ ወደ ሗላ የምናደርገው ምርመራ በሰሞኑ ክስተቶች ላይ ብቻ የታጠረ መሆን የለበትም። እስከቻልን ድረስ ወደ ሗላ መሄድ ይኖርብናል። ችግሩ የተገለጠው ዛሬ ቢሆን፥ እይታችን ግን ወደ ሗላ ብዙ አመታትን ሊጨምር ይችላል። እንዲሁም ችግሩ የተገለጠው እዚህ ቢሆንም፥ እይታችን ግን ስርአቱ የሚያዳርሳቸዉን ሁሉንም ቦታዎችን ሊያካትት ይገባል። ከላይ እንዳልነዉ ኮምፕሎክስ ስርአቶችን አስመልክቶ፥ የችግሩ ነገረ ምክንያቶች፤ እርስ በርስ የሚስተጋበሩ ብዙ ነግሮች ሊሆኑ ይችላል። አንዱ ሌላዉን አየነካና እያባሰ የተለየዉን ችግር ለማስከሰት፥ ጊዜ ይወስድባቸዋል።

ሶስተኛ፥ ችግሮችን ስንለይ፥ ባንድ ወቅት የችግር ሳይሆን የስኬት ምክንያት የሆኑ ነገሮችንም በምርመራችን መጨመር ይኖርብናል። ነገሮቹ ባንድ ወቅት የስኬታችን ምንጭ በመሆናቸው ብቻ ሙሉ እምነት ልናሳድርባቸዉ አንችልም። አሁን ደግም የችግራችን ምንጭ ሊሆኑ ስለሚችል። ይህ “ልማቱ  የወለደዉ ነዉ” ከማለት የተለየ ነዉ።

አራተኛ፤ ለችግሮች የምናስቀምጣቸው መፍትሄዎች ዋና ዋና የሚባሉ ነገረ ምክንያቶችን እና የእርስበርስ ግንኙነቶችን መሸፈን ይኖርባቸዋል። ለዚህ ደግሞ ባንድ መፍትሄ ብቻ መተማመን አይቻልም በብዙ ምክንያቶች። አንደኛ፥ የችግሩ ነገረምክንያቶች ብዙ ስለሆኑ እና የእርስ በርስ መስተጋብራቸዉም ስለሚበዛ። ሁለተኛ፥ አንድ መፍትሄ ስለመስራቱ ፍጹም እርግጠኛ መሆን ስለማንችል፥ እንደኛዉን አስመልክቶ የነበረን ምርጫ ስህተት ቢሆን፥ ሌሎቹ ስለሚረዱን። ሶስተኛ፥ መፍትሄዎቹ የነገረምክንያቶቹን እና የስርአቱን ባህሪ ላይ ተመስርተዉ የተቀረጹ ከሆነ፥ የመፍትሄዎቹ የእርስ በርስ መደጋገፍ፥ ውጤቱን ያልቀዋል።

ስለችግሮቹ ነገረምክንያትም ሆነ ስለመፍትሄዉ ዶግማቲክ መሆን የለብንም። በእርግጥ መፍትሄዎቹን ወደ መተግበር ከመግባታችን በፊት ዉጤት ስለማምጣታቸዉ መዋቅራዊ ትንተና ላይ የተመሰረተ በቂ እርገጠኝነት ሊኖረን ይገባል። ስራ ከተጀመረ በሗላ ግን፥ ስለ መፍትሄዎቹ አተገባበር በቋሚነት መረጃ በመሰብሰብ፥ ምርመራችን እና እየወሰድን ያለዉ መድሃኒት ተገቢ ስለመሆኑ በየወቅቱ መፈተሽ ይኖርብናል። ለዚህ ፍተሻ የሚያስፈልጉ የመረጃ አይነቶች አስቀድመዉ ተለይተዉ የሚሰበሰቡበት ሁኔታና የሰብሳቢዉ ማንነት ሊለይ ይገባል። ያላበለዚያ በጨለማ መቶኮስ ነዉ። በየጊዜዉም ልምድ መረጃና ትንተና ላይ የተመሰረቱ ለዉጦች ማከናወን ይኖርብናል።

ከዚህ በላይ በተጠቀሱ ጉዳዮች ላይ (የፓሊሲና መሳሪያ ትክክለኛነት፥ የችግሩ ምክንያቶችና መፍትሄዎች) ከጅምሩ ጀምር ፍጹም እርግጠኛ ሆኖ መገለጽ፥ ለትምህርት እንቅፋት ነው። ለአስፈላጊ ለዉጥ ጋሬጣ ነዉ። እይታን ይጋርዳል። ትንታኔን ያሳስታል። ከዚህ በፊት ስለማንነት ግጭት በሰፊዉ ግልጫለሁ።

extracted from a book

….everything appears fine, with the system capably absorbing even severe but anticipated disruptions as it was intended to do. The very fact that the system continues to perform in this way covers a sense of safety…and then a critical trhehold is breached, often by a stimulus that is itself rather modest, and all hell breaks loose….

And in the wake….we end up resorting to simplified, moralistic narratives, featuring cartoon-like villains, to explain why they happened. In reality, such failures are more often the result of the almost imperceptible accretion of a thousand small, highly distributed decisions—each so narrow in scope as to seem innocuous—that slowly erode a system’s buffer ones and adaptive capacity….

1 view
  • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.