• Dr. Mulugeta Mengist

የታሪክ እግረሙቅ

Updated: Nov 17, 2019


መግቢያ

የታሪክ ወሳኝነትን ፕሮፌሰር አንድሪያስ አሸቴ፤ ታሪካችን ያስረናል በሚል ይገልጹታል። አሳሪነቱ ጠቃሚ ወይም ጎጂ ሊሆን ይችላል።  ይህንን ጉዳይ፥ በተለይ ደግሞ የታሪክ አሳሪነትን ጎጂ ገጽታ አስመልክቶ ቡድሃ ሲናገር፤ “በአንድ ወቅት የጠቀሙንን መንፈሳዊ ልምምዶች የሙጥኝ ማለት፥ ወንዙን ከተሻገሩ በሁዋላ፥ ጀልባዉን ተሸክሞ የመጓዝ ያህል ነዉ”። የማይጠቅም ሸክም ጉዞ ይገድባል፥ ጉልበት ያንጠፈጥፋል። ሲከፋም፤ ያስብንበት ሳንደርስ፤ ሰብሮ ይጥለናል። ለምን ታዲያ ተሸክመን እንጓዛለን?

የታሪክ ወሳኝነት፤ በግለሰብ፥ በቡድን፥ እና በሃገር ደረጃ ሊታይ ይችላል። ዛሬ የምንወስደዉ ዉሳኔ፤ ትናንት በወሰድነዉ ዉሳኔ ጫና/ተጽእኖ ዉስጥ ይወድቃል። የዛሬ ዉሳኔያችን፤ ነገ ልንወስደዉ በምንችለዉ ዉሳኔ ላይ ጥላዉን ያጠላል።

የምጣኔሃብት ሳይንስ ባለሙያዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የታሪክን ወሳኝነት የተጠቀሙት የቴክኖሎጂ ስርጭትን ለማብራራት ነዉ። ምንም እንኳን አንጻራዊ ብልጫ ባይኖራቸውም፤ አንዳንድ ቴክኖሎጂዎች፤ ቀድመዉ በመሰራጨታቸዉ የተነሳ፤ ተከታይ የቴክኖሎጂ እድገት ላይ ተጽእኖ ያደርጋሉ። ለምሳሌ QWERTY የተባለዉ ኪቦርድ የዚህ ማሳያ ነዉ። ሌላ ቅርጽ ያለዉ ኪቦርድ የተሻለ ቢሆንም፤ QWERTY ኪቦርድ ቀድሞ ስለተሰራጨ ብቻ የተሻለ ኪቦርድ እንዳይሰራጭ ሆኗል። በሃገራት መካከል የሚስተዋልን የብልጽግና ደረጃ ልዩነትን ለማብራራት፤ ለማስረዳት፥ የታሪክ ወሳኝነት ይጠቅማል።

በወቅቱ የበላይነት/ልዕልና የነበረዉ የምጣኔሃብት ሞዴል “የራሽናል ተዋናይ ሞዴል” የሚባለዉ ነበር። በዚህ ሞዴል መሰረት ግለሰቦች ዉሳኔ ሲሰጡ፥ አማራጮችን ግልጽ መመዘኛዎችን በመጠቀም ገምግመዉ፥ የተሻለዉን በመምረጥ ነዉ። አንድ አማራጭን፤ ትናንት ወይም ዛሬ ስለመርጥነዉ ብቻ፤ ዛሬ ወይም ነገ ደግመን እንመርጠዋለን ማለት አይደለም። የሚመረጠዉ፥ ዉሳኔ ለመስጠት በተደረገው ሳይንሳዊ ግምገማ በልጦ ሲገኝ ብቻ ነዉ።

የታሪክ ወሳኝነት ጽንሰሃሳብ፤ ይህን ልዕልና ያገኘዉን የትንተና ሞዴል ይገዳደራል። ዉሳኔዎች በታሪክ ተጽእኖ ስር ሊወድቁ ይችላሉ። በሳይንሳዊ ግምገማ ብልጫ ያገኘዉ ወይም ማግኘት የነበረበት አማራጭ እያለ፤ ትናንት አወንታ ያገኘዉ አማራጭ በተግባር ሲዉል ይታያል። የታሪክ ወሳኝነት አዎንታዊና አሉታዊ ገጽታዎች አሉት። በዚህ ጽሁፍ ትኩረት የሚደረገዉ በአሉታዊ ገጽታዎቹ ላይ ነዉ። በዚህ ገጹ ሲታይ፤ ታሪክ ያስረናል፤ ያዉረናል፤ ምርጫችን ያጠብብናል፤ ግምገማችን ነጻ እንዳይሆን ጥላዉን ያጠላብናል። ለመሆኑ እንዴት ነዉ ታሪክ የሚያስረን?

በተደራሽ መረጃ ላይ ተመስርቶ መምረጥ፥ መወሰን

በ“ራሽናል ተዋናይ ሞዴል” መሰረት ግለሰቦች ራሽናል ናቸዉ። ይህ አባባል ሶስት ነገሮችን ይጠቁማል። አንደኛ፤ ሰዎች የሚፈልጉትን ያውቃሉ፤ ከግለሰቡ በላይ ስለግለስቡ የበለጠ የሚያውቅ የለም። ሁለተኛ፤ ግለሰቦች ፍላጎቶቻቸውን በላቀ ደረጃ ለማሟላት አማራጮችን ይለያሉ፥ ይገመግማሉ፥ ከዛም ይመርጣሉ። አማራጮች መብዛት የግለሰቡን ምርጫ ያልቀዋል። ሶስተኛ፤ ግለሰቦች ራሳቸዉን መቆጣጠር ይችላሉ። ሞግዚት አያስፈልጋቸዉም።

ሰዉ ማለት እንዲህ ነዉ? ከባለፉት በርካታ አመታት ጀምሮ፤ የስነባህሪ የጥናት ግኝቶች፤ ይህን ሞዴል የሚሞግቱ ናቸዉ። ሞዴሉን ሙሉ ለሙሉ ጠርገዉ ለማስወጣት አቅም ገና ባያገኙም፤ ዉስንነቶቹን በመለየት፤ የምጣኔሃብት ትንተናዎችም ወደ እዉነታው ለማቅረብ ይረዳሉ። ከእነዚህ ግኝቶች መካከል availability heuristics የሚባለዉ ነዉ። በተደራሽ መረጃ ላይ ተመስርቶ መወሰን፥ መምረጥ፤ ማለት ነዉ።

እንደ “ራሽናል ተዋናይ ሞዴል” ከሆነ፤ ሰዎች አማራጮችን ለመለየትና ለመገምገም መረጃን ይሰበስባሉ። ምን አይነት እና ምን ያህል መረጃ? ምን አይነትና መጠን ያለዉ ግምገማ? ለእነዚህ የሚሰጠዉ የተለመደዉ መልሱ ይህ ነዉ፤ “ተጨማሪ መረጃ ለመሰብሰብና ለመገምገም የሚያስውጣዉ ወጪ፤ መረጃዉን በመጠቀም ከሚያስገኘዉ ወጪ ጋር ተነጻጽሮ እኩል እስኪሆን ድረስ፤ ተጨማሪ መረጃ ይሰበስባሉ፥ ተጨማሪ ግምገማ ያካሂዳሉ”። እያንዳንዱን ተጨማሪ መረጃ ለመሰብሰብ የሚወጣዉ ወጪ እየጨመረ፥ በዚህ የሚገኘዉ ተጨማሪ ጥቅም ደግሞ እየቀነሰ የመሄድ ባህሪ አላቸዉ።

ከዚህ ተቃራኒ በሆነ መልኩ፥ የስነባህሪ ተመራማሪዎች፥ የሰዎች ዉሳኔ የሚመሰረተዉ በተደራሽ መረጃ ላይ ነዉ። በርሜል ዉስጥ ያለች እንቁራሪት፥ የሰማዩ ስፋት የበርሜሉ አፍ ያህል ነዉ እንዲሉ። መረጃዉ በአካል ቢኖርም፥ ለአይምሮ ግን ተደራሽ ካልሆነ፥ ዉሳኔ ሰጪዉ አይጠቀምበትም። ሰማዩ ከበርሜሉ አፍ ቢሰፋም፥ እንቁራሪቷ ካላወቀችው (ካልተረዳችዉና ካላስታወሰችው) የበርሜሉ አፍ ያህል ነው። ተደራሽ መረጃ ማለት በቀላሉ ሊረዱትና ሊያስታዉሱት የሚችሉት አይነቱ ነዉ።

ለምሳሌ አንድን ችግር ለመፍታት አራት አማራጮች አሉ እንበል። ዉሳኔ ሰጪዉ ስለ አራተኛዉ አማራጭ፤ መኖር፥ ወጪና፥ ጥቅም መረጃዉ የለዉም እንበል። ስለመኖሩ ካላወቀ እንዴት ለመሰብሰብ ሊወስን ይችላል። “መኖርና አለመኖሩን እስካዉቅ ድረስ ልፈልግ” ቢልም እንኳ መቼ ፍለጋዉን ማቆም እንዳለበት ማወቅ አይችልም። ስለዚህ አማራጩ የሌለ ያህል ነዉ።  መረጃዉን በአካል አግኝቶት ነገር ግን በእንግዳ ቋንቋ ወይም ቴክኒካል ዘይቤ ተጽፏል እንበል። በዚህ ጊዜም መረጃዉ በአካል ቢገኝም በአይምሮ ግን ተደራሽ አይደለም፤ ዉሳኔ ሰጪው አይረዳዉም። ስለዚህ መረጃዉ የሌለ ያህል ነዉ።

አዲስ ነገር ለመሞከር ያለን ዝግጅት

የተቀሩትን ሶስት አማራጮችን ያለዉን ሁኔታ እንመልከት። ከእነዚህ ዉስጥ፤ አንደኛዉ ከዚህ በፊት ሌላ ወይም ተቀራራቢ ችግርን ለመቅረፍ አስቦ ዉሳኔ ሰጪው ሲተገብረዉ ነበር። ቀሪዎቹን ሁለት አማራጮች በተመለከተ ያሉት መረጃዎች ተደራሽ ቢሆኑም፤ በተግባር ሞክሯቸው አያውቅም። በአጭሩ ስለሶስቱም አማራጮች ዉሳኔ ሰጪዉ ተደራሽ መረጃዎች አሉት።  ነገር ግን ሶስቱ አማራጭ መፍትሄዎች ችግሩን የመፍታት እድላቸዉ ላይ ሙሉ አርግጠኝነት የለም እንበል። ከዚህ በፊት የተሞከረዉ አማራጭ፥ ከሌሎቹ ተሞክረዉ ከማያዉቁት ጋር ሲነጻጸር፤ የመሳካት እድሉ አነስተኛ እንደሆነ መረጃዎቹ ያሳያሉ። ያለመሳካት እድሉ የበለጠ እያለ፤ የመመረጥ እድሉ ግን ካልተሞከሩት ይበልጣል።

የዉሳኔዉ ሙሉ ተጠቃሚም፥ ተጎጂም ዉሳኔ ሰጪዉ ከሆነ፤ ምርጫዉ በአማራጮቹ የመሳካት እድል ይወሰናል። ዉሳኔ ሰጪዉ የመንግስት ሰራተኛ ወይም ባለስልጣን ከሆነ፥ ምርጫዉ ያለመሳካት ጠንቁን ለመሸከም ባለዉ ዝግጁነት ይወሰናል። ይህ ዝግጁነት ደግሞ፤ አማራጮቹ ባይሳኩ፤ የዉሳኔ ሰጪዉ ተጠያቂነት በሚገመገምበት ሂደትና መመዘኛዎች ይወሰናል። ሂደቱ እና መመዘኛዎቹ ያልተለመዱ ሃሳቦችን የማያበረታታ ከሆነ፥ ዉሳኔ ሰጪዉ ከሚገባዉ በላይ እንዲጠነቀቅ የሚያደርግ ከሆነ፥ ሶስቱን አማራጮች የሚመለከትበት አግባብ ተጨባጭ መረጃዎች ላይ የተመሰረተ አይሆንም። ለተለመደው የበለጠ ዋጋ ይሰጣል። ተሞክሮ ባይሳካም፤ “የተለየ ነገር አላደረኩም፥ ትናንት ያደረግነዉን ነዉ ዛሬም ያደረኩት” የሚል መከራከሪያ ማቅረብ ስለሚችል። በተለይ ደግሞ እንግዳዎቹ ሁለቱ አማራጮች፥ ከዚህ በፊት የተለመዱት ጠላቶቻችን ወይም ወዳጆች አይደሉም ተብለዉ በሚታሰቡት ከሆነ፤ በታሪክ የመታሰር እድላችን ይጨምራል።

የመጣረስን ግላዊ ስሜት ለማስወገድ የማንፈነቅለዉ ድንጋይ የለም

ስለመጣረስ ስሜት ወይም የማንነት ግጭት ከዚህ በፊት ጽፌያለዉ። የታሪክ አሳሪነት ከዚህ ጋር ይያያዛል። በዚህ አግባብ መሰረት ምንም ትናንት ከሀ እና ለ መካከል ለን ከመረጥን፥ ዛሬ በሌላ ዉሳኔ አሁንም ሀ እና ለ እንደ አማራጭ ቢቀርቡ ለን የመምረጥ እድላችን ሰፊ ነዉ። በተለይ ደግሞ ትናንት ለን የመረጥንበትን መንገድ ስናስረዳ ከሀ ይልቅ ለ ስላለዉ ብልጫ በግልጽና በአደባባይ ካወራን።

አልማጭነት፤ ዳተኝነት

ሌላዉ የታሪክ አሳሪነት ሊያብራራን የሚችለዉ የዉሳኔ ሰጪዎች አልማጭነትና ዳተኝነት ነዉ። አዲስ አማራጭን ከመመርመርና ለመተግበር ከመሞከር ይልቅ ትናንት የመረጥነዉን ደግመን መሄድ ልንመርጥ እንችላለን።

በእጅ የያዙት መዳብ ከወርቅ ይበልጣል

በእጃችን ያለን ማንኛዉንም ነገር ከሚገባዉ መጠን በላይ ዋጋ እንደምንሰጠዉ የተለያዩ ጥናቶች ያሳያሉ። ስለዚህ በሁለት አማራጮች መካከል ዛሬ የሚደረግ ምዘና ላይ፥ ለአማራጮቹ የምንሰጠዉ ዋጋ ከአማራጮቹ ጋር ባለን የቀደመ ግንኙነት ይወሰናል።

የተለያዩ ጥናቶችና ግንጥል-ታሪኮች[1] እንደሚያሳዩት ሰዎች በእጃቸዉ ላለ ነገር የሚሰጡት ዋጋ/ቦታ/ግምት፥ ነገሩ ባይኖራቸዉ ኖሮ ከሚሰጡት ዋጋ ይበልጣል። ሰዎች የሚፈልጉትን ያዉቃሉ፥ ፍላጎታቸዉ ደግሞ ሙሉ፥ ወጥ፥ እና ተሻጋሪ ነዉ ይሉናል የክላሲካል የምጣኔሃብት ምሁሮች፨ በእነሱ አባባል ለአንድ ነገር የምንሰጠዉ ዋጋ ተመሳሳይ ነዉ፥ ነገሩ በእጃችን ሲኖርና ሳይኖር፨ በዚህ ረገድ፥ በእጅ የያዙት ወርቅ ከመዳብ ይቆጠራል፥ በጉዋሮ ያለ ጸበል ልጥ መንከሪያ ይሆናል፥ ደብተራ ባገሩ አይከበርም፤ አወኩሽ ናኩሽ ከሚሉት ያገራችን አባባሎች ጋር ይጣረሳል፨ በእነዚህ አባባሎች መሰረት፥ በእጃችን ላለ ነገር የምንሰጠዉ ዋጋ ነገሩ ባይኖረን ከምንሰጠዉ ዋጋ ያንሳል።[2] ለእነዚህ ምጣኔሃብት ምሁሮች ግን፥ ዋጋዉ ተመሳሳይ ነዉ፥ ወይም መበላለጥ የለበትም።

እነዚያ የምጣኔሃብት ምሁሮች ከሚሉት ተቃራኒ በሆነ መልኩ፤ በእጃችን ላለ ነገር የምንሰጠዉ ዋጋ፥ ሳይኖረን ከምንሰጠዉ ዋጋ ይለያል ብቻ ሳይሆን ይበልጣልም። ይህ የሚሆነዉ መቼ እና ለምንድን ነዉ የሚለዉን እንመልከት።

ይህን ጉዳይ የመታደል ዉጤት/ተጽእኖ[3] ይሉታል፣ የታደልንበትን ነገር ባንታደለዉ ኖሮ ከምንሰጠዉ በላይ ዋጋ እንሰጠዋለን። ለምንድን ነዉ ቢሮዋችን እና ቤታችን የማይፈለግ ወረቀት የሚበዛዉና ለማቃጠልም ሆነ በሌላ መልኩ ለማስወገድ (ለምሳሌ ለሸቀጥ መጠቅለያ በመሸጥ) የሚያዳግተን? ለምንድን ነዉ የማንጠቀማቸዉ ልብሶቻችንን ለማስወገድ የማንደፍረዉ? ለምንድን ነዉ ለረጅም ጊዜ አብሮ የቆየን አቁዋም ለመቀየር የምንቸገረዉ፤ ምንም እንኩዋ የማይረባ ስለመሆኑ አሳማኝ ምክንያት ቢቀርብልን እና ብናምንበትም? በሌላ አነጋገር የማናምንበትን የቆየ አስተሳሰብ ለምን ይዘነዉ እንጉዋዛለን? እንደ አቁዋም የምንይዘዉ የምናምንበትን ብቻ አይደለም፤ አንዳንዴ የማናምንበትንም የሙጥኝ እንላለን።

ልብ በሉ ነገሩ በእጃችን በመቆየቱ የተነሳ ብቻ የሚመጣ ሁኔታ አይደለም። ለአፍታም ቢሆን የቆየዉ፥ የዋጋ ልዪነት ይኖራል። በእጃችን የቆየዉ ብዙ ጊዜ ከሆነ ደግሞ የዋጋዉ ልዩነት ሊበዛ ይችላል። ለነገሩ ጥያቄዉ፤ በእጃችን ለቆየ ነገር ለምን ትልቅ ዋጋ እንሰጣለን የሚል አይደለም። ጥያቄዉ ሳይኖረን በፊት የምንሰጠዉ ዋጋ፥ ለምን ከኖረን በሁዋላ ጨመር የሚል አይደል። የተለያዩ ጊዜዎችን እያወዳደርን አይደለም። በተለያየ ጊዜ ያሉ ዋጋዎችን እንዳሉ በቀጥታ ማወዳደር አይቻልም። ያማ ዱባን እና ዱባለን ማወዳደር ይሆናል፨ በተለያየ ጊዜ ያሉ ዋጋዎችን ለማወዳደር፥ የግድ አንደኛዉን በወለድ መጠን አስልተን ወደ ሌላኛዉ ጊዜ መለወጥ ስላለብን። ጥያቄዉ የሚመለከተዉ ተመሳሳይ ጊዜን ነዉ። ነገሩ በእጃችን እያለ የምንሰጠዉ ዋጋ፤ ነገሩ ባይኖር ኖሮ ከምንሰጠዉ ዋጋ ለምን ይለያል ነዉ ጥያቄዉ።

ለምሳሌ አምስት ብር የገዛነዉ እስክርቢቶ ወዲያዉ እንደገዛነዉ ካምስት ብር የበለጠ የሙጥኝ የምንለዉ። ምናልባት ዋጋዉ እምስት ብር ካምስት ሳንቲም ነዉ ብንባል ኖሮ ላለመግዛት የምንወስን ሰዎች፥ እስክርቢቶዉን ባምስት ብር ከገዛነዉ በሁዋላ ግን የምንሰጠዉ ዋጋ ካምስት ብር ወድ አስር ብር ከፍ ይላል፤ ምሳሌ ነዉ (በዚህ ምሳሌ በሁለቱ ሁኔታዎች የጊዜ ልዩነት የለም ብለን እናስብ፥ ለዛ ነዉ ወዲያዉ የሚለዉን ቃል የተጠቀምኩት)። ሰዎች በእጃቸዉ ላለ ነገር የሚሰጡት ዋጋ ቀድሞ ከሚሰጡት ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ያሁኑ ዋጋ ይበልጣል፤ ይህ የሚሆነዉ ጊዜ በማለፉ የተነሳ የሚመጣ አይደለም፤ እንዳልኩት በተለያየ ጊዜ ያሉ ሁለት ዋጋዎችን በቀጥታ ማወዳደር የለብንም፥ ወደ ተመሳሳይ ጊዜ ማምጣት አለብን። ይህን የምናደርገዉ ደግሞ የቀድሞዉ ዋጋ ወደ አሁን በመለወጥ ወይም ያሁኑን ዋጋ በፊት ቢሆን ኖሮ ወደሚኖረዉ ዋጋ በመቀየር ነው፥ በገበያ ያለዉን የገንዘብ ዋጋን (ወይም የወለድን መጠንን) ግምት ዉስጥ በማስገባት። ነገር ግን ያነሳሁት ጉዳይ በተመሳሳይ የጊዜ ሰሌዳ ዉስጥ፤ ሲኖረን እና ሳይኖረን የምንሰጠዉ ዋጋ ለምን ተለያየ የሚል ነዉ። ለምሳሌ የጊዜ ልዩነትን ለማስተካከል፥ የወለድ መጠን አባዝተነዉም ቢሆን ተመሳሳይ መሆን አለበት ይሉናል የክላሲካል ምጣኔሃብት ምሁሮች። የሙከራ ጥናቶች ያነሱት ጉዳይ ደግሞ በተግባር ግን ዋጋዉ ይለያያል፥ ምንም የጊዜ ልዩነት ሲኖር (ወደተመሳሳይ ጊዜ ተለዉጦም) እና ሳይኖር። ይህ ለምን ሆነ? የጊዜ ልዩነት የገንዘብ የመግዛት አቅምን ስለሚቀይር ነዉ የሚለዉ ምክንያት ሊሆን አይችልም፥ ምክንያቱም ያንን ግምት ዉስጥ አስገብተነዋልና።

የምጣኔሃብት ባለሙያዎች ሰዎች የሚፍልጉትን ያዉቃሉ፤ ስለፍላጎታቸዉ ከነሱ በላይ ያወቀ ቡዳ ነዉ ይሉናል። እንዲሁም ፍላጎታቸዉ ሙሉ ነዉ። ሁለት ምርጫ ብንሰጣቸዉ፥ ፍላጎታቸዉ ከሶስት አማራጮች ዉጭ አይወጣም። ለምሳሌ የተሰጣቸዉ ምርጫ እንድ ኪሎ ሙዝ ወይስ እንድ ኪሎ ገንፎ የሚል ይሆናል። ስለዚህ አንድ ሰዉ ፍላጎቱ ከሶስት አንዱ ነዉ የሚሆነዉ። ሙዝን ይመርጣል፥ ወይም ግንፎን ይመርጣል፥ ወይም ሁለቱንም በተመሳሳይ መልኩ ሊሆን ይችላል የሚያያችዉ። እንዲሁም ሰዎች የሚፈልጉትን ያዉቃሉ ሲባል፥ በተመሳሳይ ጊዜ አንዴ ሙዝን፥ አንዴ ደግሞ ገንፎን ሊመርጥ አይችልም። ከላይ እንዳልኩት ደግሞ፥ ሙዝን መርጦ፥ ወዲያዉ ደግሞ ገንፎን ሊመርጥ ይችላል።

ይህን ለመተንተን/ለማስረዳት እንድርድሪት[4] የሚባለዉ ክስተት ወይም ጽንሰሃሳብ ይጠቅመናል። በአዉቶብስ ቆሞ የሚሄድ ሰዉ ድንገት መኪናዉ ቢቆም፥ ሰዉየዉን ወደ ፊት ያንደረድረዋል። ልክ መቆም እንዳልፈለገ ሰዉ፥ ጉዞዉን መቀጠል እንደፈለገ ሁሉ (ምንም እንኩዋን አዉቶብሱ እንዲቆምለት የጠየቀዉ እሱ ቢሆንም)። በተመሳሳይ መልኩ መኪናዉ ቆሞ ከነበረና፥ መንቀሳቀስ ሲጀምር በዉስጡ ያሉት ውደ ሁዋላ እንደሚንደረደሩት ሁሉ።

ሁለተኛዉ ማብራሪያ፥ በተለይ ደግሞ የጊዜ ልዩነት ካለና በወለድ በማስላት ወደ ተመሳሳይ ጊዜ ለዉጠነዉም የዋጋን ልዩነት ካየን፥ መላመድ የሚፈጥረዉ ስሜታዊ ዋጋ ሊሆን ይችላል። በወለድ ለማጣጣም ሲሞከር፥ መላመድ የሚፈጥረዉን ስሜታዊ ዋጋ ግምት ዉስጥ አናስገባም። እናም ልዩነቱ የተፈጠረዉ በመላመድ ነዉ ሊባል ይችላል። ይህ ከእንድርድሪት ማብራሪያ የተለየ ነዉ።

ሶስተኛ ሰዎች እንዴት ነዉ ለእንድ ነገር የሚሰጡትን ዋጋ የሚተምኑት የሚለዉን ማወቅ ተገቢ ነዉ። እንደ አንዳንድ ምሁሮች አባባል ሰዎች ለማንኛዉም ነገር የፍላጎታቸዉን ልክና ደረጃ መወስን ይችላሉ። ነገር ግን የተለያዩ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሰዎች የፍላጎታቸዉን ልክ ለመወስን ባብዛኛዉ በንጽጽር ነዉ የሚያሰላስሉት። ይህ በመሆኑ የተነሳ የቀረበላቸዉ ንጽጽር ፍላጎታቸዉን ይወስነዋል።

በመሆኑም ሰዎችን በምክር፥ በጥቅምና፥ በዱላ ብቻ አይደለም መቆጣጠር የሚቻለዉ። የምናቀርብላቸዉን ንጽጽር በመቀየር ወደ ምንፈልገዉ ምርጫ እንዲያዘነብሉ ማድረግ ይቻላል።[5] ለዛ ነዉ ልታማልላት ወደምትፈልገዉ ሴት ስትሄድ፥ ፉንጋ ጉዋደኛህን አስከትል፥ እጅግ ቆንጆ ነህ ብላ ታስባለች፥ ቆንጆ ጉዋደኛህን አስከትል፥ ፉንጋ ነህ ብላ ታስባለች። ስለዚህ አንተ እንዳስከተልከዉ ሰዉ አይነት፥ ወይ ቆንጆ ወይ ፉንጋ ትሆናለህ ለልጅቱዋ። ተመሳሳይ ሰዉ አይደለህም፥ ያንተ ማንነት እንደ ሁኔታዉ ይለያያል። እስስትን ያስታዉሱዋል። እስስትስ እየተቀያየርች ነዉ።

በተመሳሳይ ሁኔታ የእስክርቢቶዉን ምሳሌ ስንወስድ፥ ሁለት ሁኔታዎችን ማየት እንችላለን። አንደኛዉ እስክርቢቶዉ የራስህ ሲሆን እና ሁለተኛዉ እስክርቢቶዉ የእኔ ሲሆን። እስክርቢቶዉ የእኔ ሲሆን፥ ለእክስርቢቶዉ የምትሰጠዉ ዋጋ አምስት ብር ነዉ፥ ከዛ አምስት ሳንቲም አይጨምርም። በመሆኑም ከእስክርቢቶዉና ከአራት ብር ሲባል እስክርቢቶዉን ትመርጣለህ። ነገር ግን እስክርቢቶዉ የራስህ ሲሆን፥ ለእስክርቢቶዉ የምትሰጠዉ ዋጋ ወዲያዉ ወደ ስድስት ብር ያሻቅባል፤ በመሆኑም ከስድስት ብር በላይ ካልሆን በሰተቀር አትሸተዉም። ይህ ለምን ሆነ ቢባል፥ በሁለቱ አማራጮች ያሉት እስክርቢቶዎች የተለያዩ ናቸዉ የሚል ነዉ። የንጽጽሮቹ ልዩነት የማንነት (የአይነትና የጥራት) ልዩነት ያመጣል። አንተ ከፉንጋ ጉዋደኛህ ጋር ስትሆን እና ከቆንጆ ጉዋደኛህ ጋር ስትሆን የተለያየህ ነህ (በአይነትና በጥራት)።[6] ያለህን ታዉቀዋለህ፥ ስለዚህ የምትሰጠዉ ዋጋ ከፍ ይላል። በእጅህ ያለዉ አምስት ብር ካምስት ሳንቲም ሲሆን፥ እና እስክርቢቶዉ በእኔ እጅ ሲሆን፥ ያለህ ነገር ይበልጥብሃል፥ ስለዚህ አምስት ብር ካምስት ሳንቲም ይበልጥብሃል። ነገር ግን እስክርቢቶዉ ባንተ እጅ ሲሆን እና በእኔ እጅ ያለዉ አምስት ብር ካምስት ሳንቲም ሲሆን፥ አሁንም ያለህ ይበልጥብሃል፥ ስለዚህ እስክርቢቶዉ ይበልጥብሃል።

ከማያዉቁት መላእክት የሚያዉቁት ሰይጣን ይባላል። ይህ ከጉዳዩ ጋር ተመሳሳይ አይደልም። በዚህ አባባል መሰረት ሁልጊዜ የለመድከዉን፥ የምታዉቀዉን ትመርጣለህ ሰይጣንም ቢሆን። በዚህ ሶስተኛ ማብራሪያ መስረት ግን፥ ሁልጊዜ የለመድነዉን የምናዉቀዉን እንመርጣለን ሳይሆን፥ የምርጫዎቹ አቀማመጥና ልዩነት ለተመሳሳይ ነገር የምንሰጠዉን ዋጋ ያለያየዋል። ጥያቄዉ ሰይጣኑ አንድ ቢሆንም ስናዉቀዉና ሳናዉቀዉ ግን አንድነቱ ይቆማል። ያ ማለት ስናዉቀዉ ሁልጊዜ እንመርጠዋለን ሳይሆን፥ አንጻራዊ ዋጋዉ ግን ይለያል።

አንድ ሰዉ እራቱን መብላት ፈልጎ ሚዳቆ ተኩሶ ገደለ እና ምላሱን ጠብሶ በላ። ጡዋት ደግሞ ሲነቃ ያደረ ሚዳቆ ከምበላ ብሎ ሌላ ሚዳቆ ገድሎ ቁርሱን ዱለት በላ፨ ስለዚህ ድርጊት ተገቢነት ጥያቄ ቢነሳ፥ መልስ መስጠት እንደሚያዳግት ጋሬት ሃርዲን የተባለ ጸሃፊ ይናገራል። ነገር ግን ይህ የሆነዉ በሁለት አማራጭ ሁኔታዎች ነዉ ብለን እናስብ። አንደኛዉ ሚዳቆ ከሚገባዉ በላይ በዝቶ በሚያስቸግርበት ወቅት እና ሚዳቆ ተመናምኖ ሊጠፋ በደረሰብት ሁኔታ። በሃርዲን እምነት በእነዚህ ሁለት አማራጮች ድርጊቱ ተመሳሳይ ነዉ ብለን መናገር ይከብደናል፥ ባንደኛዉ ሁኔታ ድርጊቱን ኮንነን፥ በሌላኛዉ ሁኔታ ደግሞ ድርጊቱን እንደግፋለን። ሃርዲን ይህን ምሳሌ በመጥቀስ አትግደል፥ አታመንዝር የሚሉት አይነት ትእዛዞችን ለመቀበል ያስቸግራል ይለናል። መግደል ሁሉ አንድ አይነት አይደለም፥ አንደኛዉ ነፍስ ማጥፋት ሲሆን ሌላኛዉ ነፍስ ማዳን ነዉ። ዋናዉ አንጻጻሪዉ ነዉ።

የዛሬ አቅማችን በትናንቱ ዉሳኔ፥ የነገ አቅማቸን በዛሬው ዉሳኔ ይገደባል

አማራጮችን ከምንገመግምበት መለኪያ አንዱ፤ ያለን አቅም ነዉ፥ አማራጮቹን ለመተግበር በሚያስፈልገዉ አቅም እና እኛ ያለንን አቅም በማነጻጸር ነዉ። ትናንት አንድን አማራጭ መርጠን ስንተገብር፥ አማራጩን አስመልክቶ ልምድ እናገኛለን። አቅማችን ይዳብራል። ዛሬ ላይ ሆነን ምርጫ ስናከናዉን ትናንት የመረጥነዉ አማራጭ አንደኛው ተወዳዳሪ ከሆነ ከዚህ አንጻር የመመረጥ እድሉ ከፍተኛ ነዉ። በመሆኑም በዚህ መልኩ ታሪካችን ሊያስረን ይችላል።

የተለያዩ አማራጮች በተለያዩ ቡድኖች የሚያስከትሉት ጥቅምና ጉዳት፤ እና ቡድኖቹ ያላቸዉ የተጽእኖ ፈጣሪነት አቅም መለያየቱ

ማንኛዉም ምርጫ አሸናፊና ተሽናፊ አለዉ። አሸናፊዎቹ ትንሽ ከሆኑ፥ የነፍስ ወከፍ ጥቅማቸዉ ከፍተኛ ነዉ። እንዲሁም የመደራጀት ወጪያቸዉ ዝቅተኛ ነዉ። ስለሆነም፥ ራሳቸዉን አድራጀተዉ ይህን ጥቅማቸዉን ለማደራጀትና ለማስፋት ይሰራሉ። ባንጻሩ የተሸነፉት ብዙ ከሆኑ የነፍስ ወከፍ ጉዳታቸዉ ዝቅተኛ ነዉ። እንዲሁም በብዛታቸዉ የተነሳ የመደራጀት ወጪያቸዉ ከፍተኛ ነዉ። በመሆኑም፥ በተበታተነ መልኩ የሚደርስባቸዉ ይደርስባቸዋል።

ከዚህ አንጻር ስንመለከተዉ የትናንት ዉሳኔያችን አሽናፊዎች በቁጥር ትንሽ ከሆኑ፥ ዛሬ ላይ ሆነን በምናደርገዉ ሌላ ዉሳኔ ትናንት የተመረጠዉ አማራጭ አሁንም ተቀባይነት እንዲኖረዉ የትናንት አሸናፊዎች የተደራጀ ተጽእኖ ያደርጋሉ። በእርግጥ ይህ አይቀሬ ዉጤት አይደለም። የፓለቲካ ስርአቱ መዋቅርና አስራር ይወስኑታል። ይህን ለሌላ ቀን እናቆየዉ።

የከፈልነዉ እና የምንከፍለዉ መስዋእትነት አይነትና መጠን

ለትናንት ዉሳኔ የከፈልነዉ መስዋእት ዉሳኔዉን እንድንደጋግመዉ ሊያደርግ ይችላል። በተለይ ደግሞ መስዋእቱ፤ ካይምሮ የማይጠፋ ከሆነ ወይም ከፍተኛ ከሆነ። መስዋእቱን የሚያስታዉሱ ነገሮችን፤ ከወቅታዊ ዋጋቸዉ የበለጠ የሙጥኝ እንላለን። ጀልባዉን ለመስራት ከፍተኛ መስዋእት ከከፈልን፥ ምንም እንኩዋን ወንዙን ከተሻገርን በሁዋላ የጀልባዉ ዋጋ ትንሽ ቢሆንም፥ የምንስጠዉ ዋጋ ግን መስዋእቱን በምናስታውሰዉ ልክ ነዉ።

ቀሊጥ ወጪ

ወንዙን ያሻገረን ጀልባ ወንዙን ከተሻገረን በሗላ በሰልባጅነት እንኳን ምንም ያህል ዋጋ የማያወጣ ከሆነ፥ እንዲህ በቀላሉ ጥለነዉ አንሄድም። ቀሊጥ ወጪ የምንለዉ አንዴ ከወጣ በሁዋላ፥ መልሶ ሊሽጥ የማይችል አይነት ወጪ ነዉ፥ ወይም ሊመለስ የማይችል ወጪ።

እንዲህ አይነት ወጪዎች ሰዎች ወደ አንድ የኢኮኖሚ ዘርፍ እንዳይገቡ ወይም ከገቡ በሁዋላም እንዳይወጡ መሰናክል የሚሆኑ ናቸዉ። ምክንያቱም እንዲህ አይነት ወጪ፥ ባገለገል እቃ ገበያም እንኩዋን የረባ ዋጋ ስለሌለዉ ነው።

ለምሳሌ፥ ነገሩን ለማግኝት አንድ ሰዉ ከከፈለዉ ገንዘብ በተጨማሪ ያወጣዉ ቀሊጥ ወጪ ካለ፥ እንደ ቀሊጥ ወጪዉ መጠን ለነገሩ የሚሰጠዉ ግምት/ቦታ ይጨምራል። ምንም እንኩዋን ቀሊጥ ወጪዉን መልሶ ማግኝት ባይችልም፥ ነገሩን አብዝቶ ዋጋ በመስጠት፥ ቀሊጥ ወጪዉን ባያወጣ ኖሮ ሊኖረዉ ከሚችለዉ የበለጠ ግምት ይሰጠዋል።

ሚስትህን ሳታገባ፥ ሳትተዋወቃት፥ ካገባህ በሁዋላ፥ አብራቹ ከኖራቹ በሁዋላ የምትሰጣት ቦታ ይለያያል። ያወጣህዉ ቀሊጥ ወጪ በበዛ መጠን የምትሰጠዉ ዋጋም ይጨምራል። ለምሳሌ፥ እሷን የበለጠ ለማወቅ የምታጠፋዉ ጊዜ፥ አብረህ ያሳለፍከዉ ጊዜ ተመልሶ ተሽጦ ዋጋ አያወጣም። ልብ ማለት የሚገባዉ በዚህ አብሮ ቆይታ የተማርከዉና ያዳበርከዉ ችሎታ ካለ እና ሌላ ሴት ወይም ወንድ ወይም ንግድን አስመልክቶ በሙሉ የሚጠቅምህ ከሆነ እንደ ቀሊጥ ወጪ ሊቆጠር አይገባም።

መምህሩ ወጣቱን ተማሪ ጠየቀው፤ “በየአመቱ ይህን ፎቶ ታሳየኛለህ፥ ሁሌም አስተያየቴ አንድ ነው፥ አይረባም። ይህን ያህል ፎቶዉን ለምን ወደድከው?”

ወጣቱ መለሰ፤ “ምክንያቱማ፤ ይህን የተፈጥሮ ገጽታ ለመፎተት በጣም ትልቅ ተራራ በእንፉቅቅ መዉጣት ስለነበረብኝ ነዉ”።

የወጣቱ ተማሪ መልስንም ከዚህ አንጻር ማብራራት ይቻላል። ልብ ይሉዋል፥ ይህ ማብራሪያ የማርክስ የዋጋ መላምት[7] እየተባለ ከሚጥራዉ ይለያል፥ እንዴት ማለት ጥሩ ነው፥ ማለቴ ጥሩ የቤት ስራ። ዉሃ ከአልማዝ ይልቅ ለህይወታችን አስፈላጊ ነዉ፥ ታዲያ ይህ ሆኖ እያለ ለምን አልማዝ ከዉሃ የበለጠ ተወደደ? የማርክስ መልስ የፈሰሰበት ጉልበት የሚል ነዉ። ጃንሆይ ብሄራዊ ትያትር በር ላይ ያለዉን አንበሳ ሲመርቁ አሉ እንደተባለዉ፥ ‘ምንም እንኩዋ ይህ በፊታችን የቆመዉ ሃዉልት በምንም መልኩ አንበሳ ባይመስልም፥ የወጣበት ወጪ ግን አንበሳ አስመስሎታል’። ዉድ ዋጋ ተከፍሎበታል።

መደምደሚያ

ለዚህ ነዉ፥ የችግር ትንተናን አስመልክቶ ከዚህ በፊት በጻፍኩት አጭር ማስታወሻ ላይ የሚከተለዉን የጠቀስኩት፤ “ችግሮችን ስንለይ፥ ባንድ ወቅት የችግር ሳይሆን የስኬት ምክንያት የሆኑ ነገሮችንም በምርመራችን መጨመር ይኖርብናል። ነገሮቹ ባንድ ወቅት የስኬታችን ምንጭ በመሆናቸው ብቻ ሙሉ እምነት ልናሳድርባቸዉ አንችልም። አሁን ደግም የችግራችን ምንጭ ሊሆኑ ስለሚችል”።

የታሪክ አሳሪነት መገለጫዎችን እና የታሪክ አሳሪነትን ለመቀነስ መወሰድ ስላለባቸዉ እርምጃዎች በሌላ ጊዜ እመለስበታለዉ።

[1] Anecdotes

[2] የአገራችን አባባሎች መሰረታቸዉ ምንድን ነዉ? ነገሩ በእጃችን ከገባ በሁዋላ ለምንድን ነዉ የምንሰጠዉ ዋጋ የሚቀንሰዉ? ነገሩ እንደ ልባሽ/ያገለገለ ስለሚቆጠርና መልሰን ልንሸጠዉ ብንሞክር ስለሚቀንስ ነዉ? ነገሩ በገበያ የማይሸጥ ቢሆንስ? ስለነዚህ አባባሎች ለማዉጋት አይደለም። እንዲህ አይነቱን አባባሎች ለማጣጣልም አይደለም። ምሳሌያዊ አባባሎች መቼና በምን ሁኔታዎች የዉሳኔ ምክንያት ይሆናሉ፥ መቼ እንደ መሪና መካሪ መቁጠር አለብን ወይስ ወግ የማሳመሪያ ዉብ አባባሎች (የቁዋንቁዋ ቀለማት) ብቻ ናቸዉ? ጊዜ ያለፈባቸዉ፥ ብስባሽ ቅሪቶች ናቸዉ? ይህን ለሌላ ጊዜ እናቆየዉ።

[3] Endowment effect

[4] Inertia

[5] ካስ ሳንስቴይን እና ታለር ይህን በተመለከተ ሲጽፉ፤ መንግስት ነጻነትን የማይሸረሽር የአባትነትን (libertarian paternalism) ሚና መጫወት ይችላል፥ ይገባልም ይላሉ።

[6] ጉዋደኛህን ንገረኛና ማንነትህን ልንገርህ፥ ወይም ከአህያ ጋር የዋለች ጊደር ፈስ ተምራ መጣች ከሚለዉ አባባል ይለያል።

[7] Marx’s labor theory of value

2 views
  • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.