• Dr. Mulugeta Mengist

የሽግግር መንግስት ህገመንግስታዊ ነው?

የዶር መሃሪ ታደለን ፅሁፍ አነበብሁት። https://meharitaddele.info/2020/05/the-limits-of-legal-solutions/

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው ለመንግስት ተጨማሪ ስልጣን በመስጠትና መብቶችን በመገደብ በሽታውን ለመዋጋትና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ ከሆኑ ብቻ ነው። መንግስትም ለራሱ የሚሰጣቸው ስልጣኖችና የሚገድባቸው መብቶች ለዚህ አላማ አስፈላጊ ሲሆኑና በዚሁ ልክ ብቻ ነው።

እንደ ነገሩ ሁኔታ ምርጫን ማገድ አስፈላጊ ሊሆን ይችላል ባይ ነኝ።

ዶር መሃሪ፤ አስፈላጊ እስከሆነ ድረስ ተጨማሪ ስልጣንን ለመንግስት የመስጠትና መብትን የማገድ ውጤት እንጂ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምርጫን የማገድ ውጤት የለውም ባይ ነው። ስለዚህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታዉጆ የምክር ቤቱ የስራ ዘመን ቢያበቃ፤ ምክር ቤቱ ተበትኖ መንግስት ኬርቴከር መንግስት ብቻ ይሆናል ባይ ነው።

ይህማ ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን አላማና መንፈስ ጋር አብሮ አይሄድም። በሽታ መብትን የሚገድብና ስልጣንን የሚጨምር ውጤት ካለው (በሽታውን ለመከላከልና ህዝብን ለመጠበቅ) በሽታው ሳይጠፋ የምክር ቤት የስራ ዘመን ማለቅ መንግስትን የኬርቴከር መንግስት ካደረገው እኮ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተገደቡ መብቶችና የተገኙ ስልጣኖች ሊጠፉ ነው፥ እንደውም ከዛ በፊት የነበረውንም ስልጣን ሊያጣ ነው። በሽታው ያላመጣውን ጉዳይ የስራ ዘመን ማለፉ እንዲያመጣው መፍቀድ ይሆናል። ለኔ ይህ ተቀባይነት የለውም።

ለኔ ዋናው ነገር ምርጫውን ማራዘም በሽታውን ለመከላከልና የህዝብን ደህንነት ለማረጋገጥ አስፈላጊነት ጉዳይ ነው። ህገመንግስታዊነት ሙግት የሚነሳው መንግስት ይህን አስፈላጊነት አላረጋገጠም በሚል ብቻ ነው።

ምርጫው ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ የሚራዘምበት እድል ስለመኖሩ በሃሳብ ብንለያይም፤ ዶር መሃሪ እስካሁን በሚገባ ያልተዳሰሰን ጉዳይ ማንሳቱን ጥሩ አንስቷል። አስፈላጊ ስለመሆኑ ማስረዳት የሚገባው አሜሪካ፥ ቻይና፥ ጣሊያን፥ ብራዚል እና የመሳሰሉ ሃገራት በሽታው ያለውን ሁኔታ በመጥቀስ ሳይሆን ሃገራዊ ሁኔታው ጋር በማያያዝ ብቻ ነው። ይህ ትኩረት ያላገኘን ሃሳብ ዶር መሃሪ በፅሁፉ አንስቷል።

በተጨማሪም ዶር መሃሪ ታደለ በፅሁፉ ማጠናቀቂያ እንዲህ ይላል There are two ways to address the legitimacy deficit: establishing a broad transitional government of national unity that brings together the pockets of dispersed legitimacy and power centres together. Many political forces and others have demanded this for a long time. However, it is unconstitutional, as the constitution under Article 60 stipulates that the caretaker should elected representatives.

የፅሁፉ መነሻም ይህ ነው።

የፌዴራልና የክልል ምክር ቤቶች የስራ ዘመን ከማለቁ በፊት ምርጫ ማከናወን ካልተቻለ፤ መፍትሄው የህግ ሳይሆን የፓለቲካ እንደሆነ ይነገራል። የፓለቲካ መፍትሄን አስመልክቶ ከዚህ በፊት ያለኝን እይታ ለማብራራት ሞክሬያለሁ። ባጭሩ ለማስቀመጥ ያህል የሚከተለው ነው። የፓለቲካ መፍትሄም ቢሆን በህግ ማእቀፍ የሚከወን ነው። የፓለቲካ መፍትሄ የሀገሪቱን ህግጋት፤ በተለይ ደግሞ ህገመንግስቱን ባልተፃረረ መልኩ መተግበር አለበት። ይህ አንደኛው ነው። ሁለተኛ፤ የፓለቲካ መፍትሄን እንደ መብት ወይም ግዴታ የሚወሰድ አይደለም። ቃሉ እንደሚጠቁመው ስሌቱ ፓለቲካዊ ነው። የፓለቲካ ድርጅቶች በፓለቲካ መፍትሄው መሳተፋቸውና አለመሳተፋቸው፤ ከተሳተፉ ደግሞ የተሳትፎው ቅርፅና ይዘት የሚወስኑት ፓለቲካዊ በሆነ የተናጥል ስሌት ነው። “እንዲህ አይነት ቅርፅና ይዘት ባለው መፍትሄ ብሳተፍ፤ የሚያስገኝልኝ ፓለቲካዊ ጥቅም ምንድን ነው?” የሚለውን ያሰላሉ። ከእነ እገሌ ጋር እንዲህ አይነት ቅርፅና ይዘት ባለው ፓለቲካዊ ትብብር ብሳተፍ የማገኘው ፓለቲካዊ ጥቅም የለም ብሎ የሚያምን ድርጅት አይሳተፍም። እንዲሳተፍም ማስገደድ አይቻልም።

***መነጋገርና መመካከር እንደ ፓለቲካዊ መፍትሄ***

ለመሆኑ ፓለቲካዊ መፍትሄ ተብሎ የሚቀርበው ምንድን ነው?

ብዙ ጊዜ ግልፅ አይደለም። አንዳንዶቹ ፓለቲካዊ መፍትሄ ሲሉ፤ መመካከርን፥ መነጋገርን የሚጠቁሙ ይመስላሉ። ታዲያ አሁን ስልጣን ላይ ያለው ብልፅግና ፓርቲና እርሱ የሚመራው የፌዴራል መንግስት ከተለያዩ የፓለቲካ ድርጅቶች ጋር ቢመካከሩ፥ ቢነጋገሩ የትኛውን የሀገሪቱን ህግ ይጥሳሉ?

የትኛውንም የሀገሪቱን ህግ አይጥሱም። እንደውም ህገመንግስቱ የተመሰረተበት የህዝቦች ሉአላዊነት መርህ፤ የሀገሪቱ መንግስት በህዝብ የተመረጠና አሳታፊ መሆን አለበት። ስለዚህ መንግስት ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር ቢመካከር፥ ቢነጋገር የህዝቦችን ሊአላዊነት ያከብራል እንጂ አይጥስም።

በምክክሩና ንግግሩ የተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎችንና ድርጅቶችን ምክንያታዊ ባልሆነ መልኩ እንዳይሳተፉ ቢያደርግ እኩልነትንና የህዝቦችን ሊአላዊነትን የሚቃረን ይሆናል።

አሳታፊነት፥ መመካከር ህጉም የሚጠይቀው ነገር ነው። በእርግጥ ለተሳትፎና ምክር ጠሪው አካል፤ መንግስት፤ የተሳትፎው ጥሪውን እና መንገዱን የሚወስነው በፓለቲካዊ ትርፉ ነው። ይህ ፓለቲካዊ ትርፍ ስሌት ህጉን እስካልተቃረነ ድረስ ችግር የለውም።

ግልፅ መሆን ያለበት ግን በንግግርና ምክክር የተደረገ የህገመንግስት ጥሰት ኢህመንግስታዊ ከመሆን አይድንም። በንግግርና በምክክር ህገመንግስታዊ በሆነ መልኩ ህገመንግስቱ ካልተሻሻለ በስተቀር።

***የሽግግር መንግስት እንደ ፓለቲካዊ መፍትሄ***

የሽግግር መንግስት አንደኛው ፓለቲካዊ መፍትሄ እንደሆነ ይነገራል። የሽግግር መንግስት ማለት ምንድር ነው?

ፓርላማውን በማፍረስ የሚቋቋም መንግስት ነው? ፓርላማውን ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ ማፍረስ ይቻላል። ይህ ሲሆን ግን ምርጫ በስድስት ወር ውስጥ መከወን አለበት። ለስድስት ወር ምርጫ ሲከወን ግን የመንግስትን ስልጣን ይዞ የሚቆዬው በስልጣን ላይ የነበረው ፓርቲ ነው። ይህ ፓርቲ ዋና ስራው ምርጫን ማከናወን ሆኖ፤ አስተዳደራዊ ስራዎችን ብቻ እየሰራ ይቆያል። አዲስ ህጎችን ማውጣት አይችልም።

በስልጣን ላይ የነበረው ፓርቲ ለስድስት ወር የእለት ተእለት ስራዎችን ብቻ እየሰራ ይቆያል ማለት ምንድር ነው? የተለያዩ መስሪያ ቤቶች እየመሩ ያሉ የፓለቲካ ተሿሚዎች፥ ሚኒስትሮችና ሌሎች ባለስልጣኖች፥ ይቀጥላሉ ማለት ነው። ፓርቲው ከወሰነም እነዚህ ተሻሚዎች በአዲስ ተሿሚዎች ሊተኩ ይችላሉ፤ ለስድስት ወሩ። ሚኒስትሮቹም እንዲሁ። ሌላው ቢቀር የፓለቲካ ፓርቲው ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሁሉ ሊቀይር ይችላል ማለት ነው። ዋናው ጉዳይ ፓርቲውና አዲሶቹ ተሿሚዎች የመንግስት የእለት ተእለት ስራ ከመከወን ሌላ፤ አዳዲስ ህጎችን ማውጣት አለመቻላቸው ነው።

ይህ የስድስት ወር መንግስት የሽግግር መንግስት ሊባል ይችላል። ብዙ ጊዜ ግን የሽግግር መንግስት የሚባለው የተለያዩ የፓለቲካ ድርጅት መሪዎች የተሳተፉበት ነው። ታዲያ ይህ የስድስት ወር የሽግግር መንግስት የተለያዩ የፓለቲካ ድርጅት መሪዎች የተሳተፉበት ሊሆን ይችላል?

መልሱ፤ አዎ ሊሆን ይችላል ነው። ምንም የሚከለክል ነገር የለም። ስልጣን ላይ የነበረው ፓርቲ፤ በራሱ የፓለቲካ ትርፍ ስሌት፤የስድስት ወሩን መንግስት ሌሎቹን ፓርቲዎች ባሳተፍ መልኩ ላከናውነው ቢል የሚከለክለው ነገር የለም። ዋናው ነገር፤ ይህ የሽግግር መንግስት ስድስት ወር ማለፍ አይችልም። እንዲሁም ምርጫን ከማከናወን እና የእለት ተእለት ስራን ከመስራት ውጭ አዲስ ህግ ማውጣት አለመቻሉ ነው።

አንዳንድ ሰዎች እንደ መፍትሄ የሚያቀርቡት የሽግግር መንግስት ይህን አይነቱን መንግስት ለመጠቆም ከሆነ፤ ከህገመንግስቱ ጋር የሚቃረን መፍትሄ አይደለም። ዋናው ነገር፤ በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ የሚሰራው የፓለቲካ ትርፍ ስሌት ነው።

ፓርላማው ሳይፈርስና ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ እየቀጠለ፤ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት የሽግግር መንግስት ማቋቋም ይችላል? እንደ የሽግግር መንግስቱ አይነት ይወሰናል። በሽግግር መንግስት ስም የተለያዩ ድርጅት መሪዎችን ፓርላማ ውስጥ እንደ ውሳኔ ሰጪ እንዲሳተፉ ማድረግ ከሆነ፤ ህገመንግስቱን ይፃረራል።

ነገር ግን የሽግግር መንግስት ሲባል፤ የተለያዩ የፓለቲካ ድርጅት መሪዎችን በተለያዩ የሚኒስቴርና ሌሎች መስሪያ ቤቶች አባላት አድርጎ መሾም ከሆነ፤ ህገመንግስቱ ይህን አይከለክልም። ዋናው ነገር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፓርላማ አባል የነበሩና የሆኑ መሆናቸው ነው።

የፓለቲካ ድርጅት መሪዎችን ፓርላማ ማስገባት የማይቻል ነገር ቢሆንም፤ ኢመደበኛ የሆነ የምክክር ምክር ቤት ከፓለቲካ ድርጅት መሪዎች ጋር ከማቋቋም ስልጣን ላይ ያለውን ፓርቲ የሚከለክለው ነገር የለም። ዋናው ነገር የእንዲህ አይነት ምክር ቤት ውሳኔ አስገዳጅ አለመሆኑ ነው።

**

ከዚህ በላይ ከዳሰሱኳቸው ውጭ የሆኑ የሽግግር መንግስት ሃሳቦች ሊኖሩ ይችላሉ። ከላይ የጠቀስኳቸውን በተመለከተ ግን ዋናው ነገር ህገመንግስቱን በስምምነት መጣስ ኢህገመንግስታዊ ከመሆን አይድንም። ነገር ግን ህገመንግስታዊ የሆኑ የሽግግር መንግስቶች ሊቋቋሙ ይችላሉ። ዋናው ነገር ስልጣን ላይ ያለው ፓርቲ የፓለቲካ ትርፍ ስሌት እና በሽግግር መንግስቱ የሚሳተፉ ሌሎች ድርጅቶች ያላቸው የፓለቲካ ትርፍ ስሌት ነው።

ከዚህ በላይ ያለው ፅሁፍ፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ ምርጫው ሲራዘም ስለሚኖረው ሁኔታ አይመለከትም።

ህገመንግስታዊ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆ፤ ምርጫው ህገመንግስታዊ በሆነ መንገድ ከተራዘመ፤ ከዚህ በላይ ስለ ሽግግር መንግስት ያልሁት ነገር ለዚህም ይሰራል።

38 views
  • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.