• Dr. Mulugeta Mengist

የመርህ እና የጥቅም ጉድኝት

Updated: Nov 17, 2019


አንድ ሰዉ ደዉሎ “የሆሳዕና ዘንባባ አድርገህ፤ ከሆኑ ልጆች ጋር ፎቶ ተነስተህ የለጠፍከዉን አየሁት። እኔ እኮ ሃይማኖትህን የቀየርክ መስሎኝ ነበር….” አለኝ። ይህ ንግግር ምክንያት ሆኖኝ እንደሚከተለዉ ተቆላጨሁ።

ሃይማኖትን፥ እምነትን፥ እሴትን ብቻ ማዕከል ያደረግ ጉድኝት መሞገት ይገባናል። ጉድኝታችን የተለያዩ ሃይማኖት፥ ሙያ፥ ባህል፥ አስተዳደግ፥ ፓለቲካ፥ ፍልስፍና ካላቸዉ ሰዎች ጋር ቢሆን ጥሩ ነዉ። በሁሉም ነገር ከሚመስለን ወይም ባብዛኛዉ ነገር ከሚመስለን ጋር ከሆነ ጉድኝታችን ከምናገኘዉ ጥቅም ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል። “አበጀህ ጓዴ” እየተባባልን፤ አንዱ የሌላዉ የገደል ማሚቶ እየሆነ፥ አስተሳሰባችንን አያከረርን ተቻችሎ የመኖርና የመስራት አቅማችንን አያሟሸሽን፥ በስህተት ጎዳና ግራ ቀኙን ባግባቡ ሳንመረምር እንድንነጉድ ይሆናል።

ጥቅምን መስረት ያደረጉ ጉድኝቶች ሁሉ መጥፎ አይደሉም። እርስ በርሳቸዉ የሚጣረሱ አይደሉም። ከብዙ ሰዎች ጋር ጥቅምን ያማከሉ የተለያዩ ጉድኝቶች ልንመሰርት እንችላለን። ወሰኑ አድማስ ይሻገራል። በእርግጥ እኚህ አይነት ጉድኝቶች፤ ዘላለማዊ አይደሉም። ጥቅሙ ከወጪዉ ካነሰ የጉድኝቱ ዘርፍና ጥንካሬ ይቀንሳል። በኋላም ይጠፋል። ችግር የለዉም። ሟች ሆነን ዘላለማዊ ጉድኝት ለምን እንፈልጋለን?

ዋናዉ ነገር የጉድኝቱ አባሎች በዉስንነት ልክፍት ስለማይያዙ፤ የቅናት መንፈስ ተጠቂ አይሆኑም። “ለምን ከሌላ ሰዉ ጋር ጉድኝት መሰረትህ” የሚሉ አቤቱታዎች የተለመዱ አይሆኑም። “ትቶኝ ይሄዳል” የሚል ፍራቻ ስር አይሰድም ወይም ቦታ አይኖረዉም።

በሌላ መልኩ እምነትን፥ እሴትን፥ አስተሳሰብን ማዕከል ያደረገ ጉድኝት የመለየት ፍርሃትን ይፈጥራል። ጉድኝትን እንደ አላቂ ሃብት ስለሚቆጥረዉ። ስለዚህ ዉስን የጉድኝት መረቦችን ብቻ ነው የሚያስተናግደዉ። በዚህ ውስን መረብ ያለዉ ጉድኝት ዘርፈ ብዙ እና ሁሉን የህይወት መስኮች አዳራሽ ነዉ የሚሆነዉ። የግል የሚባሉ ጉዳዮች እየጠበቡ ይሄዳሉ።

ዘላቂ ሊመስል ይችላል። ግን የዉሸት ነዉ። ደህንነትን ዋስትናን የሚስጥ ይመስላል፥ ግን የዉሸት ነዉ። ይልቅስ ፍርሃትን ነዉ የሚያጠናክረዉ። እየተጠናከረ የሚሄደዉ ፍርሃት ደግሞ መጠኑ እየሰፋ የሚሄድ የግል ህይወታችን በጉድኝቱ እንዲገዛ ያደርጋል።

በአሜሪካ የዉጭ ጉዳይ ፓሊሲ ታሪክ እነዚህን ሁለት አይነት ጉድኝቶችን የሚያራምዱ የተለያዩ አካላት ታይተዋል። አንዳንዶቹ ከሰይጣንም ጋር ቢሆን ለጋር ጥቅማችን መስራት አለብን ይላሉ። ሌሎቹ ደግሞ አለም ሁሉ የእነሱን እሴት እምነት ካልተቀበለ ፍርሃት የሚያርዳቸዉ ናቸው። ደህንነት/ዋስትና የሚያገኙት ከሚመስላቸዉ ጋር ሲጎዳኙ ነዉ። ለራሳቸዉ ጥቅም ሲሉ ጥቅምን ያማከለ ጉድኝት በእሴት፥ እምነት፥ ፍልስፍና ከማይመስላቸዉ ጋር ቢመሰርቱም ለጊዜዉ ነዉ። በእርግጥ ይህ ችግር የለዉም። ግን ዉስጥ ዉስጡን ይህን ጉድኝት በሌላ በሚመስላቸዉ ስዉ ለመተካት ይባዝናሉ፤ የመጀመሪያዉን ጓደኛቸውን በስዉር በመሸርሸር።

ተመሳሳይ እሴት፥ እምነት፥ ፍልስፍና ላይ የተመሰረተ ጉድኝት በመሰረቱ ኢዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብን፥ አክራሪነትን የሚያጠናክር፥ ግጭት ከሳች፥ ቻይነትና አብሮነትን የሚሸረሽር ፀረ ብዝሃነት ነዉ።

መገለጫቸዉ እና አመጣጣቸዉ ቢለያይም በፍሬያቸዉ ግን ተመሳሳይ ናቸዉ። መጽሃፍ ቅዱስ የእዉነትና የሃሰት አስተማሪዎች ተመሳሳይ ትምህርት ያስተምራሉ፥ ተመሳሳይ አመጣጥና መገለጫዎች (ለምሳሌ ታምራትን ማድረግ) ይኖራቸዋል ይላል። ሁሉም በእኔ ስም ነዉ የሚመጡት ይለናል። “ታዲያ እንዴት ነዉ እዉነተኞቹን ከሃሰት አስተማሪዎች የምንለያቸዉ” ለሚለዉ፥ መጽሃፉ ሲመልስ፤ “በፍሬያቸዉ ይለያሉ” ይለናል። ከመገለጫዉ፥ ከአመጣጡ፥ ከይዘቱ፥ ራስህን አሻግረህ ፍሬዉን ገምግም። ግምገማዉ ድህረ ወይም ቅድመ ይሆናል። በእርግጥ እንዲህ አይነት ግምገማ ለመንፈሰ ሰነፎች አይሆንም። ምክንያቱም ከባድ ነዉ። ጊዜ ይወስዳል። አይምሮን ያደክማል። ምክሩ፤ ከሃሰትና ከእዉነት ትምህርት ይዘላል። በማንኛዉም ጉዳይ አማራጮችን ስትገመግም ፍሬን ማዕከል ያደረገ ይሁን።

እሴት/እምነት ወይስ ጥቅምን ያማከለ ጓደኝነት? በምርጫ መልክ እንዲህ ማቅረብ በራሱ እሴት/እምነትን ብቻ ያማከለ ጉድኝትን ከመመስረት አይለይም። ብዙ ጉድኝቶች ሊኖሩን ይችላል።  ሁሉም ተመሳሳይ ጥንካሬ ሊኖራቸዉ አይገባም። አንዳንዱ መርህን ማዕከል ያደርጋል። ሌላዉ ጥቅምን ያማክላል። አንዱ ሌላዉን ለማጥፋት መሞከር ግን የለበትም።

እምነትም፥ ጥቅምም ይቀያየራል። ምን የማይቀየር ነገር አለ ሁሉን አይነት ለዉጥ ለማስቀረት መሞከር፤ የሞት መንገድ ነዉ። ከአስር ሺ አመታት በፊት አድነንና ለቅመን ስንኖር፥ ራሳቸዉን ከለዉጥ ጋር ማጣጣም ያቃታቸዉ ብዙ ሰዎች፥ ምንም እንኳን እጅግ ጥሩ ዘረመል ቢኖራቸዉም፥ ከለዉጥ ጋር መሄድ ስላቃታቸዉ ብቻ ከዘረመሉ ባንክ እንደወጡ ቀርተዋል። ህልዉናቸዉ የሚረጋገጠዉ የጠንካሮቹ አይደለም፥ ይልቅስ ራሳቸዉን ከለዉጥ ጋር ማጣጣም የቻሉት እንጂ። ራስን ከለዉጥ ጋር አያጣጣሙ ለመሄድ ሁለቱም አይነት ጉድኝቶች ያስፈልጋሉ።

በግላዊና ድርጅታዊ ህይወትና ስራዎች የሚለወጥና የማይለወጥ ይኖራል። ነገር ግን የማይለወጠዉ በጣም እጅግ ጥቂት ሊሆን ይገባል። አብዛኛዉን ነገራችን ለመለወጥ ዝግጁ ልንሆን ይገባል። ከዘረመሉ ባንክ እንዳንወጣ። ዘመን ተሻጋሪ እንድንሆን። ዝግጁ ብቻ ሳይሆን እንደዉም አስፈላጊ ለዉጦችን አፈንፍነን መለየትና መተግበር ይገባናል።

በእርግጥ አንዳንድ ድርጅቶች ከአባሎቻቸዉ የሚጠብቁት ዶግማቲክ እምነት ነዉ። ለምሳሌ፤ አንዳንድ የሃይማኖት ድርጅቶች። ስለዚህ አባሎቻቸው እምነትን ማዕከል ባደረጉ ዉስን ግንኙነቶች ብቻ እንዲጠመዱ ይፈልጋሉ። ለዚህም ያስተምራሉ። በዚህም የአባሎቻቸው እምነት እየጠነከረ፤ ጫፍ እየረገጠ፥ ለድርጅቱ ያላቸዉ ታማኝነት፥ ጽናት፥ ተሳትፎ፥ እና መስዋእት ፍጹምና ከፍተኛ ይሆናል።

የጥቅም ጉድኝት ስል፥ ቁሳዊ ወይም ገንዘባዊ ጥቅምን ብቻ እያሰብኩ አይደለም። እንዲሁም ጥቅሙን እና ወጪውን ስንገመግም እይታችን ጠቅላላ ሊሆን ይገባል፥ ማለትም የግልና ማህበራዊ ጥቅምና ወጪዎችን አካቶ። የተደራጁ የወንጀለኞች ቡድኖችም ጥቅምን ያማከለ ጉድኝት ይመሰርታሉ። ጥቅም ብቻዉን ግን የወንጀለኛ ቡድኑን ዘላቂነት ስለማያረጋግጥ፥ በጥቅም የተጀመረን ይህን ጉድኝት፥ እሴት/እምነትን ባማከለ እንዲተካ ወይም እንዲታገዝ በሰፊዉ ይሰራሉ።

Recent Posts

See All

የሽግግር መንግስት ህገመንግስታዊ ነው?

የዶር መሃሪ ታደለን ፅሁፍ አነበብሁት። https://meharitaddele.info/2020/05/the-limits-of-legal-solutions/ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው ለመንግስት ተጨማሪ ስልጣን በመስጠትና መብቶችን በመገደብ በሽታውን ለመዋጋትና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ ከሆኑ ብቻ ነው። መንግስ

  • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.