• Dr. Mulugeta Mengist

ከአገልጋይነት ወደ ጌትነት/ጣኦትነት!

Updated: Nov 17, 2019


በአዲሱ አመት ዋዜማ ለጓደኞቼ የአዲስ አመት ምኞቴን ገልጬ ነበር። አዲሱ አመት መሳሪያዉን ከስራዉ የምንለይበትና መሳሪያዉን አንደ መሳሪያ፥ ስራዉን እንደስራ የምናይበት ይሁን ብየ ነበር። ይህ የአዲስ አመት ምኞት የመነጨዉ፥ ብዙ ጊዜ የግለሰቦችን፥ ቡድኖችን ህይወት የሚያቆረቁዘዉ መሳሪያዉን ከስራዉ ካለመለየት ነዉ ከሚል እሳቤ ነዉ።

ገንዘብን መዉሰድ እንችላለን። ገንዘብ የመጣዉ የግብይት ስርአትን ለማሳለጥ ነዉ። ለምሳሌ አንድ ሰዉ ትርፍ በቆሎ ቢኖረዉና በዚህ ትርፍ በቆሎ ምትክ፥ የሚያስፈልገዉ/የሚፈልገዉን አንድ ጋቢ ማግኘት ቢፈልግ፥ ተገቢዉን ተገበያይ ማግኘት አለበት። ተገቢዉ ተገበያይ ማለት፤ ትርፍ ጋቢ ያለዉና በቆሎ የሚፈልግ መሆን አለበት። ትርፍ ጋቢ ኖሮት የሚፈልገዉ ግን በግ ከሆነ ይህ ተገቢ ተገበያይ አይደለም።

ነገር ግን የግብይት ስርአት በገንዘብ ሲደገፍ፥ የግድ ተገቢዉን ተገበያይ ማግኘት አይጠበቅበትም። ትርፉን በቆሎ በገንዘብ ለዉጦ፥ ጋቢዉን በገንዘብ መግዛት ይችላል። ጋቢ ያለዉ ሰዉ ነገር ግን በቆሎ የማይፈልግ ሰዉ የግድ ጋቢዉን በበቆሎ ለዉጦ፥ ከእንደገና በቆሎዉን በበግ ለመለወጥ መፍጋት የለበትም። ስለዚህ የገንዘብ ጥቅም ግብይትን ማሳለጥ ነዉ። በቆሎዉን በገንዘብ ስንለዉጠዉ፥ ገንዘብ ከፋዩ በቆሎዉን ላይበላዉ ይችላል፥ እንደዉም ከበቂ በላይ በቆሎ ያለዉ ይሆናል። ነገር ግን በቆሎዉን ወስዶ በሌላ ነገር (ገንዘብን ጨምሮ ሊለዉጠዉ) ይችላል። እንዲሁም በቆሎዉን በገንዘብ የለወጠዉ ግለሰብ፥ ገንዘቡን ፈልጎት አይደለም። የሚፈልገዉ ጋቢ ነዉ። ገንዘቡን ሊለብሰዉ፥ ሊጎናጸፈዉ አይችልም። ነገር ግን በገንዘቡ የሚፈልገዉን ጋቢ ሊለዉጥበት ይችላል። ስለዚህ ገንዘብ የግብይት ወጪን በመቀነስ፥ ግብይትን ያሳልጣል። ግብይት ሲሳለጥ፥ አምራቾች በተወሰነ የኤኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ብቻ እንዲተጉ ያደርጋል (specialization)። በዚህም ምርት ይጨምራል።

ስለዚህ ገንዘብ መሳሪያ ነዉ። በራሱ ትርጉም የለዉም። አይበላም፤ አይጠጣም፥ አይለበስም። የሚበላዉ፥ የሚጠጣዉ፥ የሚለበሰዉ ግን ዋናዉ ጉዳይ ነዉ፥ ስራዉ። መሳሪያዉ ለስራዉ ያገለግላል። ነገር ግን በጊዜ ሂደት መሳሪያዉ፥ መሳሪያነቱ ተረስቶ ልክ እንደ ዋናዉ ስራ ሊቆጠር ይችላል። ለአንድ ተግባር የሚቀርበዉ ምክንያት፥ የተግባሩ ምርት/ዉጤት ሊሆን ይችላል። ለምን ታርሳለህ ቢባል፥ ጤፍ ማምረት ፈልጎ ይሆናል። ጤፉን ሊበላዉ ወይም በሌላ ነገር ሊቀይረዉ ይችላል። በዚህ ሂደት ገንዘብ አጋዥ ነዉ፥ መሳሪያ ነዉ። ለምን ታርሳለህ የተባለ ሰዉ፥ መልሱ ገንዘብ ማግኘት ፈልጌ የሚል ከሆነ፥ ይህ ሰዉ መሳሪያዉን እና ስራዉን አምታቶታል ማለት ነዉ።

ለምንድን ነዉ በጊዜ ሂደት መሳሪያዎች መሳሪያነታቸዉን የሚያጡት የሚል ጥያቄ ይነሳል? ለዚህ ብዙ ምክንያት ሊቀርብ ይችላል። ከላይ ከተቀመጠዉ ምሳሌ አንጻር ግን፥ ጥያቄዉ ገንዘብ ከአገልጋይነት ወደ ጌትነት ሊሻገር ለምን ይችላል የሚል ቅርጽ ይይዛል።

ገንዘብ ከአገልጋይነት ወደ ጌታነት እንዲሻገር ያስቻለዉ የገንዘብ ባህሪ ነዉ። ገንዘብ ግብይነትን ለማሳለጥ ያስቻለው አቅሙ፥ በአይነታቸዉ የተለያዩ በሆኑ ነገሮች መካከል እኩልነት መፍጠሩ ነዉ። ስለዚህ ምንም ስራ ምንም፥ ዋናዉ ምን ያህል ገንዘብ ታገኛለህ ነዉ ጥያቄዉ። ገንዘቡ ከታወቀ ምን ያህል በቆሎ ወይም ጋቢ ልትገዛበት እንደምትችል ይታወቃል።

ምርትና አገልግሎቶች ምንም እንኳን በአይነት የተለያዩ ቢሆኑም፥ በገንዘብ አማካኝነት ይወዳደራሉ። ጋቢ እና በቆሎ አይነታቸዉ የየቅል ነዉ። ነገር ግን በገንዘብ አማካይነት አንድ ጋቢ ከስንት በቆሎ ጋር እኩል እንደሚሆን ማወቅ ይቻላል። ለምሳሌ ጋቢዉ 100 ብር ቢሆን፥ እና በመቶ ብር አስር ኪሎ በቆሎ መግዛት ቢቻል። አንድ ጋቢ ከአስር ኪሎ በቆሎ ጋር እኩል ነዉ እንላለን። ስለዚህ ገንዘብ በአይነት የተለያዩ ነገሮችን በቁጥር/መጠን አማካይነት እኩል ያደርጋቸዋል። በዚህም ግብይት ይሳለጣል።

ነገር ግን ገንዘብ ግብይትን ከማሳለጥ አልፎ፥ ያልታሰቡ ዉስንነቶችን ወይም ጠንቆችን አምጥቷል። አሁን ገንዘብ ከግብይት ማካሄጃነት አልፎ፥ የግብይት እና የስራ ምክንያት ሆኗል። ለምን ትቆፍራለህ ሲባል አሁን ምክንያቱ ገንዘብ ሆኗል። ወይም ለምን ከእከሌ ጋር ግብይት ፈጸምክ ሲባል አሁን መልሱ ገንዘብ ሆኗል። ይህ የሆነበት ምክንያት፥ ገንዘብ በስራዎችና ነገሮች መካከል ያለዉን አይነታዊ ልዩነት ማጥፋቱ ነዉ። በመሆኑም ከምርቶቹና ስራዎቹ በላይ፥ ገንዘብ ትልቅ ቦታ እንዲሰጠዉ ሆኗል።

ሌላኛዉ ምክንያት የገንዘብ መምጣትን ተከትሎ የመጡ የስራ መስኮች ናቸዉ። ጋቢ የሚፈልግ ሰዉ፥ ሌላ ተፈላጊ ነገር ሊኖረዉ ይገባል ለምሳሌ በቆሎ። ስለዚህ በቆሎዉን በማምረት ብቻ ነዉ ጋቢዉን ሊያገኝ የሚችለዉ። ስለዚህ ፍላጎት ያለዉ ሁሉ በምርት ሂደት ይሰማራል። ነገር ግን ገንዘብ ሲመጣ፥ ፍላጎት ያለዉ ሁሉ ምርታዊ እንዲሆን አይገባዉም። ዋናዉ ጉዳይ ይዞ መገኘቱ ነዉ፥ ገንዘቡን። በምንም ያምጣዉ በምንም። ስለዚህ ምርታዊ ባልሆኑ ስራዎች በመስማራት ገንዘቡን ሊያገኘዉ ይችላል። እነዚህ አማራጭ ምርታዊ ያልሆኑ ስራዎች ምንድን ናቸው፥

  1. ስርቆት፥ ማታለል፥ እና ዘረፋ። ምንም እንኳን ስርቆት፥ ማታለል እና ዘረፋ የመጣዉ በገንዘብ ነዉ ማለት ባንችልም፥ ገንዘብ እነዚህን ድርጊቶች ያግዛል። ገንዘብ ሳይኖር መስረቅ፥ ማታለል እና መዝረፍ የሚፈልግ ሰዉ፥ ብዙ ወጪዎች ይጠብቁታል። አጋጣሚዉን ሲያገኝም ሊወስደዉ የሚችል በቆሎ ወይም ጋቢ ብዛት ዉስን ነዉ። ነገር ግን ገንዘብ ሲመጣ፥ የሚሰርቀዉ መጠን ብዙ ይሆናል። አንድ ኩንታል በቆሎ በሚሰርቅበት አቅም፥ አንድ ጆንያ ሙሉ ገንዘብ ሊሰርቅ ይችላል። ይህን ያህል ገንዘብ ደግሞ የመቶ ኩንታል በቆሎ ያህል ሊሆን ይችላል። ገንዘብ በድርጊቶች መካከል ያለዉን አይነታዊ ልዩነቶች በማጥፋቱ የተነሳ እና ገንዘብ በመስረቅ የሚገኘዉን ጥቅም በማብዛት፥ እነዚህን ተግባሮች ያበረታታል።

  2. ሌላኛዉ አማራጭ ንግድ ነዉ። ጋቢ የሚፈልግ ሰዉ የግድ በቆሎ በማምረት መሰማራት የለበትም። ትርፍ ጋቢ ካላቸዉ ጋቢ በመግዛት፥ ጋቢ ለሚፈልጉ በትርፍ ይሸጠዋል። ወይም ትርፍ በቆሎ ካላቸዉ ትርፍ በቆሎ በመግዛት፥ በቆሎ ለሚፈልገዉ ይሸጣል። ንግድ ስለዚህ ገንዘብን በመጠቀም አምራችን እና ሽማችን ያገናኛል። የድለላ ስራ ነዉ ማለት ነዉ። ደለላዉ ግን የግድ አንድ አምራችን ከአንድ ሸማች ጋር በአካል ማገናኘት የለበትም። ዋናዉ በመንፈስና በጥቅም መገናኘታቸዉ ነዉ። በድርጊቶች መካከል ያለዉ አይነታዊ ልዩነት በገንዘብ ምክንያት በመጥፋቱ የተነሳ፥ በቆሎ አመረትክ ወይስ ጋቢ ወይስ የንግድ ስራ ሰራህ ለዉጥ የለዉም። ከምርታዊ ስራዎች በተለየ መልኩ፥ በንግድ ስራ ላይ በመሰማራት የሚገኘዉ ጥቅም ብዙ ነዉ። ስለዚህ በዚህ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች ብዙ ገንዘብ ያገኛሉ። በቆሎ ቢያመርቱ ኖሮ በአመት 100 ኩንታል ብቻ ሊያመርት የሚችለዉ ሰዉ፥ አሁን ንግድ ላይ በመሰማራቱ የተነሳ 100፥000 ኩንታል በቆሎ ሊገዛበት የሚችለዉን ገንዘብ በንግድ ስራ ላይ በመሰማራት ያገኛል። ችግሩ የጥቅም መለያየቱ አይደለም። በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች፥ ጥቅማቸዉ የሚከበረዉ ብዙ ምርት ሲመረት እና ለግብይነት ሲቀርብ ነዉ። ስለዚህ ምንም እንኳን በአንድ ኤኮኖሚ ዉስጥ የሚኖሩ ሰዎች በድምር የሚፈልጉት የበቆሎ መጠን አንድ ሚሊዮን ኩንታል ብቻ ቢሆንም፥ ነጋዴዎቹ ግን አስር ሚሊዮን ቢመረትላቸዉ እና በእነሱ አማካይነት ለግብይት ቀርቦ ለፍጆታ ቢዉል ተጠቃሚዎች ናቸዉ። ስለዚህ ይህን ለማድረግ በተናጥል እና በቅንጅት ሊሰሩ ይችላል። ምን ለማድረግ? ብዙ በቆሎ እንዲመረት እና ብዙ በቆሎ ፍጆታ ላይ እንዲዉል። ለዚህም ሲሉ ብዙ ነገር ሊፈጥሩ ይችላሉ። ለምሳሌ እያንዳንዱ ሰዉ በአመት አንድ ኩንታል በቆሎ በማቃጠል ለፈጣሪዉ ምስጋና ማቅረብ አለበት የሚል አሰራር። እንዲህ ያደረገ በፈጣሪዉ ይባረካል። ያላደረግ ይቀሰፋል። እንዲህ አይነት እምነት ስር ቢሰድ ስለሚጠቀሙ ለዚህ ይሰራሉ። ከዚህ በላይ ያሉት ነጥቦች ይህን አዝማሚያ እና ለዚህ አዝማሚያ መጠናከር ሌሎች አምራቾችም እንዲተጉ ያደርጋል።

ከዚህ በተጨማሪ ገንዘብ ሌላም አላስፈላጊ ዉጤት አለዉ። የተወሰኑ አይነት ስራዎች እና ግብይቶች በዚህ ምክንያት ይታፈናሉ። ለስራዉ ወይም ግብይቱ ያለን ተነሳሽነት ከገንዘብ ወይም ቁስ አካላዊ ጥቅም ዉጭ ሲሆን፥ ስራና ግብይት በገንዘብ በመሆኑ የተነሳ፥ ተነሳሽነቱም ይቀንሳል።

ለምሳሌ፥ በከተማዉ ዉስጥ የምትንቀሳቀሰዉ በግል መኪና ነዉ እንበል። መኪናዉ ካንተ በተጨማሪ ሌሎች አራት ሰዎችን መጫን ይችላል እንበል። አራት ሰዎች በመጫንህ ደግሞ የሚደርስብህ ተጨማሪ ኪሳራ ትንሽ ነዉ እንበል። እናም ባዶየን ከምሄድ እያልክ ለሰዉ ራይድ ትሰጣለህ። የትራንስፓርት ችግርም ስላለ፥ ብዙ ተሳፋሪ ታገኛለህ። በዚህም ሰዎች ትረዳለህ እንበል። አንተም ሰዎች ትተዋወቃለህ፥ ከተሳፋሪዎቹ ትማራለህ እና የመሳሰሉት። እንበልና አሁን የትራንስፓርቱን ችግር ለመፍታት ሲባል፥ ማንኛዉም ሰዉ የታክሲ ፈቃድ ሳያወጣ በግል መኪናዉ ሰዎችን እየጫነ እንዲያስከፍል፥ መንግስት ፈቀደ እንበል። ይህን አጋጣሚም ሰዎች የተወሰነ ገንዘብ እንዲያገኙ እድል ፈጠረ። የትራንስፓርት ችግርም እየቀነሰ መጣ እንበል። ነገር ግን ከዚህ በፊት በነጻም ቢሆን ሰዎችን እየጫንክ ነበር። አሁን ጥያቄዉ፥ መንግስት ይህን ከፈቀደ በኋላ፥ አንተስ እያስከፈልክ ትጭናለህ ወይ? መልሱ ላይሆን ይችላል። እንደዉም በነጻ የምጭነዉን ነገር ትቼ ብቻየን ልጓዝ እችላለሁ፥

  1. ለምሳሌ አንድ ብር ለእኔ እና ለሌላ ሰዉ እኩል ዋጋ የለዉም።መኪና ላለው ሰዉ ብቻዉን ከመንዳት፤ ሃያ ብር አስከፍሎ ሁለት ሰዉ ቢጭን፥ ተጨማሪ ሃያ ብር አገኘ ማለት ነዉ። የቀን ደመዎዙ 100 ብር የሆነ ሰዉ እንደ ትልቅ ገቢ ሊቆጥረዉ ይችላል፥ ነገር ግን መኪና ያለዉ እና የቀን ገቢዉ 500 ብር የሆነ ሰዉ ሁለት ሰዎችን በማሳፈር የሚገኝ 20 ብር ብዙም ላያነሳሳዉ ይችላል።

  2. ሁለተኛ፥ ይህ አሰራር ባለበት ሁኔታ በነጻ እንኳን ማሳፈር የሚፈልግ ሰዉ ከማሳፈር ይቆጠባል። ምክንያቱም ለሱ 20 ብር ብዙም ዋጋ የለዉም። ሁለተኛ በነጻ እንኳን ማሳፈር የሚፈልግ ሰዉ በነጻ ማሳፈሩን ሊያዉቅ የሚችለዉ ተሳፋሪዉ ብቻ ነዉ። ሌላ ሰዉ ግን አስከፍሎ የሚያሳፍር ነዉ ብሎ ሊያስብበት ስለሚችል ላለማሳፈር ሊወስን ይችላል።

  3. ሶስተኛ መኪና በሚሰጠዉ አገልግሎት መጠን ነዉ ዋጋዉ የሚተመነዉ። ነገር ግን በተግባር ምርትና አገልግሎቶችን የምናየው ከሚሰጠዉ አገልግሎት አንጻር ሳይሆን ከገንዘቡ አንጻር ነዉ። ምክንያቱም በገበያ የሚታወቀዉ የአይነት ጥራት ሳይሆን የዋጋ መጠን ስለሆነ። ግብይትም ከጥራቱ እና ከሚያስገኘዉ ዘርፈ ብዙ ጥቅም አንጻር ሳይሆን የምናየዉ ከሚያስገኘዉ ገንዘብ አኳያ ነዉ።

ከዚህ በላይ ያሉት ምክንያቶች የተነሳ፥ አንዳንድ ግብይቶች፥ ምርትና፥ አገልግሎቶች በሚገባዉ መጠን አይቀርቡም። የገበያ ስርአት የሚያበረታታዉ ግላዊ እና ቁሳዊ ጥቅሞችን እና ግብይቶችን ነዉ።

ገንዘብ ከግብይት ማሳለጫነት አልፎ የስራና ግብይቶች ምክንያት ሆኗል። ከመሳሪያነት አልፎ ግብ ሆኗል። ከአገልጋይነት ወደ ጌታነት ተሽጋግሯል። ከቁሳዊ ጥቅሞች ዉጭ ያሉ መሰረታዊ የምርትና አገልግሎትና ግብይት ምክንያቶችን፥ ብዙ አይነት ገንዘቦችን በመፍጠር እና በማበረታታት መቀነስ ይችላል። በገንዘቦች መካከል አይነታዊ ልዩነት አሁን የለም። በዶላር እና በብር መካከልም ቢሆን ያለዉ ልዩነት አይነታዊ ሳይሆን የመጠን ነዉ። ነገር ግን ማህበረሰብ፥ ተጨማሪ አይነት ገንዘብ ያስፈልጋል። ለምሳሌ፥ የፍቅር ገንዘብ የሚባል ቢኖር ብለን እናስብ። ስለዚህ አሁን ያለን ብር የቁስአካላዊ ገንዘብ ነዉ እንበል። ቁስአካላዊ የምንለዉ የምገዛበት ነገር ሁሉ ቁስአካል ብቻ ነዉ ለማለት ሳይሆን፥ ይህን ገንዘብ ለመቀበል እና ለመስጠት የሚፈልገዉ ለቁስአካላዊ ምክንያቶች ነዉ። ስለዚህ ቁስአካላዊ ተነሳሽነት እስካለ ድረስ፥ ያለን ገንዘብ ዉስን እስካልሆነ ድረስ የማንገዛዉ አይነት ምርት ወይም አገልግሎት የለም። በገንዘብ ጓደኝነትም እንኳን እንገዛለን። ባንድ ወቅት ትንሽ ብር በመክፈል፥ የፌስቡክ ጓደኞችን መርጠን መግዛት እንችል ነበር።

የገንዘብ የመግዛትን አቅም የሚገድበዉ፥ የተገበያይ ወገኖች ተነሳሽነት የመጣዉ ቁስ አካላዊ ካልሆነ ነዉ። ለምሳሌ፥ መረዳዳት፥ መተባበር፥ ፍቅር ከሆነ። ገንዘብ እነዚህ የመግዛት አቅሙ ዉስን ነዉ። እንደዉም ገንዘብ እነዚህ ጉዳዮች የማጥፋት አቅም አለዉ።

እንዲሁም ገንዘብ የግብይት ወጪን በመቀነስ፥ specialization ያበረታታል። specialization ጠቃሚ ነገር እንደሆነ ብዙዎችን ያስማማል። ጠንቁንም ግን መዘንጋት የለብንም። specialization ሰዎች ለጥቃትና ብዝበዛ ያጋልጣል። ለዛም ነዉ አንዳንዴ specialization ስንፈልግ ነገር ግን ሰዎች specialization የሚያመጣዉን ጠንቅ ፈርተዉ እንዳይርቁ፥ ሌሎች ማበረታቻዎችን የምንጠቀመዉ። ለምሳሌ፥ specialization የመቀጠር እድልን ይቀንሳል። በአስገድዶ መድፈር የወንጀል ሕግ specialize ያደረገ ሰዉ የመቀጠር እድሉ specialize ካላደረግ ሌላ የሕግ ባለሙያ ጋር ሲነጻጸር ዝቅተኛ ነዉ። በሌላ መልኩ ለምሳሌ የሕግ አስተማሪዎች specialize ቢያደርጉ ጥቅሙ ብዙ ነዉ። ለዚህ ነዉ specialize ላደረጉ አስተማሪዎች፥ የስራ ዋስትናን እንደ ማበረታቻ የሚቀርበዉ። በሌሎች ሃገራት ፕሮፌሰር ለመሆን ሰፊ የ specialization ስራ መስራትን ይጠይቃል። ይህን ያደረገ ሰዉ ምንም እንኳን የመቀጠር እድሉ ቢቀንስም፥ ፕሮፌሰር በመሆኑ የተነሳ የስራ ዋስትና ያገኛል፥ ማለትም እጅግ ልዩ በሆነ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር ስራዉን አያጣም። specialization በህይወታችንም ቢሆን አላስፈላጊ ጠንቆችን ያረገዘ ስለመሆኑ መዘንጋት የለብንም። አዳም ስሚዝ እንዳለዉ፥ ምንም እንኳን specialization የምርት አብዮትን ለማምጣት ቢረዳም፥ ሰራተኛዉን ግን ለጥቃት እና ብዝበዛ ያጋልጠዋል። specialization የግላዊ ነጻነት ጸርም ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ይህ ማለት specialization አያስፈልግም፥ ገንዘብ አያስፈልግም ሳይሆን፥ አደጋቸዉን መለየትና አደጋዉን ለመቀነስ ግን መሞከር ያስፈልጋል ለማለት ነዉ።

ከዚህ በታች የጠቀስኩት አማራጭ ገንዘብ፥ የለመድነዉን የገንዘብን ዉስን የመግዛት ፍላጎት ከመደገፍ አልፎ፥ ፍቅርን፥ መተባበርን እና የመሳሰሉትን ጉዳዮች ከመጥፋት ይጠብቅልናል።

ከዚህ በላይ ገንዘብን አስመልክቶ የቀረበዉ መግለጫ፥ ገንዘብን ብቻ አይመለከትም። ሌሎች ብዙ መሳሪያዎችንም ይመለከታል። ይህ ማለት መሳሪያዎቹ አያስፈልጉም ለማለት አይደለም። እንደዉም መሳሪያ መጠቀም የሰዉ ልጆች ልዩ ችሎታ ነዉ፥ የሰዉ ልጆችን የህይወት ብልጽግና ያመጣዉ ይህ ነዉ። ሰዎች ወደ ማርስ መንኮራኩርና ሮቦት ሲልኩ፥ ዝንጀሮዎች ግን ከዛፍ ዛፍ ይዘላሉ። ይህ የሆነበት ምክንያት አንድ ሰዉ ከአንድ ዝንጀሮ የተለየ አቅም ኖሮት ሳይሆን፥ ሰዎች እርስ በርሳቸዉ እጅግ መጠነ ሰፊ ትብብር ማድረግ በመቻላቸዉም በጋራ ሊያደርጉት የሚችሉትን ነገር እና የጋራ አቅማቸዉን ማሳደግ መቻላቸው ነዉ። ይህን እንዲያደርጉ ደግሞ መሳሪያዎች ትልቅ አስተዋእጾ አድርገዋል። ዝንጀሮዎች አይተባበሩም ማለት አይደለም። ዝንጀሮዎች ይተባበራሉ። ነገር ግን የሰዉ ልጆች የሚያደርጉትን አይነት ዉስብስብ፥ መጠነ ሰፊ፥ እና ተቀያያሪ ትብብሮችን ግን አያደርጉም።

ዝንጀሮዎች እነዚህን መሳሪያዎች መፍጠር፥ መጠቀም አይችሉም። በዚህም የትብብር መጠናቸዉ ዝቅተኛ ነዉ። መሳሪያዎች ስንል ዶማ እና አካፋ አይነቱን አይደለም። እሱንማ ምናልባትም ሰዎች መስራት ከሚችሉት የተሻለ ዶማ እና አካፋ ዝንጀሮዎች ሊሰሩ ይችላሉ። መሳሪያ ስንል እንዲህ አይነቱን መሳሪያ ሳይሆን፥ ገንዘብ የመሰሉትን ነዉ።

እንሰሶች ሁለት አይነትን እዉነታዎችን ይገነዘባሉ። እሱም ተጨባጭ እዉነታ ነዉ። ለምሳሌ አንድ ዝንጀሮ ፊት ለፊቱ ያለዉን ሙዝ ይገነዘበዋል። ተጨባጭ ሁኔታ ነዉ። ሙዝ ከመሆኑ እሱ ባያምንበትም፥ ሙዝንነቱን ግን አይለዉጠውም። ሰዎች ስንባልም እንዲሁ ነን።

ሁለተኛዉ ግላዊ እዉነታ ነዉ። አንድ ዝንጀሮ ሊርበዉ፥ ሊናደድ ይችላል። ርሃቡ እና ንዴቱ ግን ሌሎች ዝንጀሮዎች ስላልተገነዘቡት ብቻ ርሃብ ወይም ንዴት መሆኑ አይቆምም። ምክንያቱም ይህ ግላዊ እዉነታ ነዉ። ሰዎች ስንባልም እንዲሁ ነዉ።

ነገር ግን ሰዎች ከእንሰሳቶች በተለየ መልኩ፥ በስምምነት የሚፈጥሩት እዉነታ አለ። ይህ እዉነታ መስረቱ፥ ልምድ፥ ስምምነት፥ እምነት ሊሆን ይችላል። እንዲሁም እዉነታነቱ ሊቀየር የሚችል ነዉ። በአንድ ሰኮንድ። በስምምነት የተፈጠር እዉነታ ከምንለዉ ዉስጥ ገንዘብ ይገኝበታል። አንድ ወረቀት ይዤ ይሄ አስር ብር ነዉ። ሁለት ዳቦ ይገዛል ብል፥ ሌሎች ሰዎች እስካላላመኑበት ድረስ፥ ይሄ እውነት ሊሆን አይችልም። በዚህም ምክንያት እንዲህ አይነቱ ነገር ሶስተኛዉ አይነት እውነታ ልንለዉ እንችላለን።

ገንዘብን ለመሰሉ እንዲህ አይነት እዉነታዎች መፈጠርና መጠናከር፥ ቋንቋ፥ የጽሁፍ፥ እና የመገናኛ ቴክኖሎጂዎች አስተዋእጾ ያደርጋሉ። አንዲህ አይነት አዉነታዎች፥ እንሰሳቶች እርስ በእርስ መተባበር ከሚችሉት በላይ፥ በሰዎች መካከል መጠነ ሰፊ እና የተረጋጋ ትብብር እንዲፈጠሩ ያደርጋሉ። ስለዚህ አስፈላጊ ናቸዉ።

ነገር ግን ዋናዉ መልእክት እነዚህ አይነት መሳሪያዎች፥ ትብብርን በማስቻል የሰዉ ልጆችን ኑሮ ለማበልጸግ እንደሚዉሉ ሁሉ፥ ለብዘበዛ እና ጭቆና እና ሰቆቃ ሊዉሉ ይችላሉ። ይህ የሚሆነዉ አገልጋይነቱን ረስተን እንደ ጌታ ከቆጠርነዉ ነዉ። የዛን ጊዜ ጥያቄ ይቆማል፥ ማሻሻል፥ መቀየር የሚባሉ ነገሮች አይታሰቡም።

አገልጋይነታቸዉ ተረስቶ ወደ ጌትነት የተለወጡ ብዙ መሳሪያዎች እና እዉነታዎች አሉ። በግላዊ ሆነ አገራዊ፥ እና አካባቢያዊ ኑሯችን። እነሱን እንፈትሽ። ራሳችንን ነጻ እናዉጣ። ጣኦቶቻችንን እንለይ፥ እንካዳቸው።

  • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.