• Dr. Mulugeta Mengist

ከተፈጥሮ አይበገሬነት ሰዉና ፍጡሩ ምን ይማራሉ?

Updated: Nov 17, 2019


ለውጥ የነበረ ያለና የሚኖር ነው። ሰውነታችንም የለውጥ ውጤት ነው። ተፈጥሮ በጥቅሏ ራሷን ከለውጥ ጋር አጣጥማና ተለማምዳ ልግስናዋን ትቀጥላለች። ነገር ግን ተፈጥሮ ራሷን በምን ያህል ስኬት እንደምታለማምድ በለዉጡ ፍጥነት ይወስናል። ድንገተኛ፥ አብዬተኛ፥ ፈጣን ለውጥ ተፈጥሮን ትንፋሽ ይነሳል። የአየር ንብረት ለውጥ ምሳሌ ነው። ወግ አጥባቂዋች፥ ፀረ ለውጦች ስለሆንን አይደለም። የለውጡ ፍጥነት ግን ያፍናል። የልምምድ ጊዜ አይሰጥም።

ባንፃሩ ሰውና ሰው ሰራሽ ስርአቶች ለለውጥ ያላቸው አይበገሬነት ውስን ነው። የተፈጥሮን ያህል አይደለም። በተለይ ሰዉ ራሱን የተፈጥሮ አካል አድርጎ ማሰቡን ሲያቆም። ለአስር ሺ አመታት ለቅመን እና አድነን ስንኖር የህልውናችን ምንጭ የነበሩ ባህሪያት አሁንም የሙጥኝ እንዳልን ነው። የእድገታችን ምንጩ የተፈጥሮን ብዝሃነት በማቆርቆዝ ነው። የፓለቲካ ስርአታችን ለፈጣን ለውጥ ምላሽ የለውም። እስካሁን ጠንቁ ትንሽ ነበር። አሁን ግን ለውጡ ፈጣን እና ሰፊ እየሆነ ነው። ሰውና ሰው ሰራሽ ስርአቶች እየተፈተኑ ነው።

ከተፈጥሮ ምን እንማራለን? ለዛሬ አንዱን እንመልከት፤ የተፈጥሮ አይበገሬነት ምንጩ የተፈጥሮ ብዝሃነት ነው። የሰው ልጅ ይህን ብዝሃነት እጅግ አስደንጋጭ በሆነ ፍጥነትና ስፋት እየደረመሰው ነው። ብዝሃነት ስንል ምን ማለታችን ነው? ሁለት ዋና ሃሳባችን ይጨምራል። አንደኛ በእያንዳንዷ ስርቻ/ካሬ ሴንቲሜትር ብዙ የህይወት ዘሮች ታገኛለህ። አንድ ሺ ኪሎሜትር ስኮየር አንድ አይነት የበቆሎ ዘር፥ ቀጥሎ አንድ አይነት የባቄላ ዘር፥ ቀጥሎ ባለው ቦታ ደግሞ አንድ አይነት የዝሆን ዘር…. ብታገኝ ብዝሃነት የጥቅሉ መገለጫ ሊሆን ይችላል እንጂ የእያንዳንዱ ክፍልፋይ መገለጫ አይደለም። የተፈጥሮ ብዝሃነት በጥቅሉም በክፍልፋዩም ነው የሚገለፀው። አሁን ይህም እየተሸረሸረ ፓርኮችና ቦታኒካል ገርደኖች ብቻ ናቸው በጥቅሉም በክፍልፋዩቻቸውም ብዝሃነትን የሚገልጡት። እነሱም በቁጥርና ስፋት ውስን ናቸው።

ሁለተኛው ሃሳብ እነዚህ ባይነትና በቅርፅ የበዙ የህይወት ዘርፎች እርስ በርስ ከፍተኛ መስተጋብር አላቸው። የተፈጥሮ እያንዳንዷ ክፍልፋይ ብዝሃነትን ማሳየቱ የእርስ በርስ መስተጋብሩ የፈጠረው እውነታ ነው። የእርስ በርስ መስተጋብሩም ለብዙሃኑ ህልውና እና እድገት መሰረት ነው። መስተጋብሩ ምርጫ ብቻ አይደለም። መሆን ያለበት የህልውና እና የእድገት ስትራቴጂ ነው። ሁሉንም ብዝሃ ህይወት የሚጠቅም ነው።

የተፈጥሮ አንድነት በጥቅልና በክፍልፋይ ብዝሃነትና የእርስ በርስ መስተጋብር ላይ የተመሰረተ ነው። ሰውና ሰው ሰራሽ ስርአቶች ከዚህ ምን እንማራለን?

  1. ሁለገብነት ተመልሶ ፋሽን ይሆናል። የህልውና ስትራቴጁም ነው። የህክምና እውቀት ለሃኪሙ ብቻ የሚተው አይደለም… ብዙ ቋንቋ ተናጋሪነት የአይበገሬነትና የእድገት ምንጭ ነው።

  2. እያንዳንዷ ክፍልፋዮቻችን (መንደሮቻችን ከተሞቻችን) ብዝሃነታችንን ሊገልጡ ይገባል።

  3. ብዝሃነታችን በእርስ በርስ መስተጋብር ማህበራዊ ኤኮኖሚያዊ ፓለቲካዊ ሊታገዝ ይገባል።

  4. ፓሊሲዎቻችን ብዝሃነትን ሊገልጡ ይገባል። ያልተማከለ አስተዳደር ለዚህ ምቹ ነው። ፌዴራሊዝምን የዴሞክራሲ ቤተ ሙከራ ያሉት እኮ ለዚህ ነዉ። ወጥነት ከመጣም፥ የሚመጣዉ ከታች ወደ ላይ ቀስ በቀስ ነዉ እንጂ በማእከላዊ ድንጋጌ አይሆንም። በዚህ መልኩ የመጣ ወጥነት ዘላቂና ተፈላጊም ይሆናል። በማእከላዊ ወጥነት፤ ትምህርት በቅደም ተከተል በሚደረጉ ሙከራዎች ላይ የተመሰረተና አዝጋሚ ነዉ። የፓሊሲ ብዝሃነት ባንዴ ብዙ እንድንሞክርና በፈጣኑ እንድንማር ያደርጋል። እድገትን ያፋጥናል። ልማታዊነት ከፌዴራል ስርአቱ ጋር እንደማይጣጣም ባንድ ወቅት ኢትዮጲያን የጎበኙ የሕገመንግስትና የፓለቲካ ምሁር ተናግረዉ ነበር። ከብዝሃነት አንጻር ካየነዉ ግን፥ ፈጣን እድገት ፈጣን የመማር ብቃትን ይጠይቃል፥ በማእከላዊ አስራር ትምህርት ዘገምተኛ ነዉ፥ ከገበያም ሊያዘግም ይችላል። የፓሊሲ ብዝሃነት ፈጣን ተማሪዎች ያደርገናል። ስለዚህ የፓሊሲ ብዝሃነት እና ፈጣን ልማት የጆሮ ጉትቻ ያንገት ሃብል ናቸዉ። የፓሊሲ ብዝሃነት ባንድ አይነት የፓሊሲ መሳሪያ አለመተማመንን ያካትታል።

  5. ብዝሃነት በድርጅቶቻችን አይነትና ቁጥር መገለጥ አለበት።

  6. ብዝሃነት በሃሳቦች ብዝሃነት ሊገለጥ ይገባዋል። ወጥ አስተሳሰብ፥ አንድ ልኡል ሃሳብ ሳይሆን፥ ብዙ ሃሳቦችን ስርአቶቻችን ማስተናገድ ይገባቸዋል። ትምህርት ስርአቱ፥ የምርምር ስርአቱ፥ ሜዲያው፥ የፓለቲካ ስርአቱ የሃሳብ ብዝሃነትን ማስተናገድ ይገባቸዋል።

  7. ካንድ ትልቅ፥ ቁርኝትና ተመጋጋቢነት ያላቸዉ ብዙ ትንንሾች ይሻላሉ።

  8. እያንዳንዳችን፥ በጥቅላችን፥ መንግስታችን ሰርክ ተማሪ መሆን ይገባናል። አስራ ሰባት ወይም ስምንት ወይም ሃያ አራት አመታት ተምሮ ለእድሜ ልክ የሚሆን እውቀትና ክህሎት መገብየት ፋሽኑ ሊያልፍበት ትንሽ ቀርቶታል። ትምህርት ቤቶቻችን ልጆቻችንን ለማድረስና ለመውሰድ እና በአመት አንድ ጊዜ ለወላጆች ቀን የምንሄድባቸዉ ቦታዎች ሳይሆኑ፥ ወላጆችና ልጆች ለመማር ሁልጊዜ የሚሄዱባቸዉ ስፍራዎች ይሆናሉ። ባምና በሬ አይታረስም ይባል ነበር፥ አሁን ደግሞ በጧቱ በሬ አይታረስም በሚል መተካቱ አይቀርም።

  9. ሁላችንም የመረጃ ሸማቾች የመረጃ አምራቾች መሆናችን የግድ ይሆናል። እየሆንም ነዉ በተወሰነ መልኩ። ይህ ደግሞ ብቃትን ይጠይቃል። የመረጃን ጥራት የመገምገም ብቃት። መረጃን የመገምገም የዜጎች ብቃት፤ የሃያአንደኛዉ ክፍለዘመን ወሳኝ ክህሎት የሚባለዉም ለዚህ ነዉ። ትምህርት ቤቶቻችን፥ መገናኛ ብዙሃኖቻችን፥ ምርምር ድርጅቶቻችን፥ የፓለቲካ ስርአታችን የሃሳብ ብዝሃነትን የማያስተናግዱ ከሆኑ፥ ይህ የሃያአንደኛዉ ክፍለዘመን ወሳኝ ክህሎት አይዳብርም። ብዝሃነት የመገምገምና የመምረጥ ብቃትን ያሳድጋል። ስለዚህ ብዝሃነትን በየቀኑ በየቦታዉ፥ ከልጅ አስከ አዋቂ ልንለማመደዉ ይገባል።

የቶማስ ፍሪድማንን የቅርብ መጽሃፍ ካነበብኩ በሗላ፥ አንዳንድ ሃሳቦቹን በመወጠር፥ ቦታ በማሻገር፥ የሃሳቦቹን ጥንካሬ ለመፈተሽ እየሞከርኩ ነዉ። ይህም ጽሁፍ የዚሁ ሙከራ አካል ነው። ሲወጠር፥ ስፍራ ስታሻግረው፥ መልእክቱ ትርጉም ካለዉ የሃሳቡን ጥንካሬ ሊያሳይ ይችላል በሚልና ውይይት ለመጫር ነዉ። ትርጉም አለዉ? ጨምሩበት።

  • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.