• Dr. Mulugeta Mengist

ከራሳችን ጋር ላለመጣረስ የምከፍለው ዋጋ

Updated: Nov 17, 2019


አየርማረፊያ ነኝ። ወደ ማስተናገጃዉ ጠረጴዛ ተጠግቼ ‘ትኬቴን’ እና ‘ፓስፓርቴን’ ላስተናጋጁ ሰጠሁት። ሁልጊዜ ወደ አውሮፕላን ውስጥ ይዤው የምገባውን ትንሽ ሻንጣ፥ በስህተት ሚዛኑ ላይ አሰቀመጥኩት። ጉዞ ሲኖረኝ፥ ትንሽ እረበሻለሁ። እቃ የረሳሁ ይመስለኛል። የዘገየሁ ይመስለኛል። በኋላ ያደረግኩትን ሳውቅ፥ አስተናጋጁ ሻንጣየን ሳይልከው በፊት፥

“በስህተት ነው፤ ይዤው ነው የምገባው” አልኩት።

“ይሄማ ትልቅ ነው፤ አይገባም” አለኝ። “ኪሎው ትንሽ ነው፤ ግን ሻንጣው ረጅም ነው”

“ሁልጊዜ እኮ ይዤው የምሄደው ነው” ብዬ ተከራከርኩ።

አይ አውሮፕላኑ ትንሽ ነው” ሲለኝ፥ ምንም እንኳን ሁሌ የምጓዝበት አውሮፕላን መሆኑን ባውቅም፥ በእሱ ሃሳብ ተስማማሁ ።

ለምንድን ነው ሻንጣየን አውሮፕላን ውስጥ ማስገባት ያልፈለግኩት። ብዙ ሰው የተለያየ ምክንያት አለው። የአየር መንገዱ ሰራተኞች ካንዱ ወደ አንዱ ሲያስተላልፉ በሻንጣው እና በውስጡ ባሉ ነገሮች ላይ ጉዳት እንዳያደርሱበት፥ ወይም እቃቸው እንዳይጠፋ፥ እንዳይሰረቅ በመፍራት። ወይም መድረሻቸው ላይ ቶሎ ብለው ከአየር ማረፊያው ለመውጣት። ሻንጣው ከአውሮፕላን ወርዶ እንስኪመጣላቸው ድረስ ጊዜ ይወስዳል፤ በተለይ ብዙ መንገደኞች እና በረራዎች ካሉ። የኔ ምክንያት ይህኛው ነው። ቶሎ መውጣት እፈልጋለሁ። ለነገሩ የበረራው ርዝመት ካንድ ሰዓት ትንሽ ነው የሚበልጠው።  የ16 ሰዓት በረራ አይደለም። ቢሆንም እንደ ብዙ በራሪዎች፥ አንዴ አዉሮፕላኑ ካረፈ በኋላ ያቁነጠንጠኛል።  ለአጭር ጊዜ ቢሆንም እንኳን፥ ታፍኖ የመቆየት ስሜት ቶሎ ለመውጣት ያጣድፋል።

ዞሮ ዞሮ ምንም ያህል ቶሎ መውጣት ብፈልግም፥ እንዲሁም ከዚህ በፊት ይዤው የተጓዝኩት ሻንጣ ቢሆንም፥ አስተናጋጁ ሻንጣው መግባት አለበት ሲለኝ፥ ያለውን እሺ ብየ ተቀበልኩ። አንዳንድ ሰዎች ይዤ እገባለሁ አትገባም ጭቅጭቅ ውስጥ ሲገቡ ከዚህ በፊት አጋጥሞኛል። ምናልባት በልቤ ለምን ያካብዳሉ ሳልል አልቀረሁም። እኔም አካባጅ እንዳልባል፥ ‘የገባው ነው’፥ ‘ኩል ነው’ ለመባል ይሆናል ወይም ከራሴው ጋር ላለመጣላት፥ ብቻ እሺ አልኩኝ።

ቀጥሎ የመሳፈሪያ ‘ትኬቱን’ ሲሰጠኝ “ይቅርታ የመጨረሻ አካባቢ ያለ ወንበር ነው የሰጠሁህ” አለኝ። እኔ ደግም የመጀመሪያዎቹ አካባቢ ነው መሳፈር የምፈልገው። ለምን? ብዙ ጊዜ የመጀመሪያዎቹ ወንበሮች ለ‘ቪአይፒ’ ተብሎው ይያዛሉ። አዘውትረው የሚበሩ የአየር መንገዱ ድንበኞች በተለይ የ‘ፕላቲኒየም’ እና ‘ጎልድ’ ደረጃ የደረሱትም፥ የፈለጉት ቦታ ለመቀመጥ ቅድሚያ ያገኛሉ ። አንዳንድ ጊዜ የ‘ትኬት’ ዋጋ እንደወንበሩም ሊለያይ ይችላል። ከዚህ በፊት ሁልጊዜ ፊት ለፊት እና የመስኮት ወንበር አጠገብ መቀመጥ እንደምፈልግ እናገራለሁ። ብዙ ጊዜም ይሰጡኛል። ‘ጎልድ’ ደረጃ ከደረስኩ በኋላ ግን፥ የአባላት ቅጽ ላይ የወንበር ምርጫየን ስለተናገርኩ ነው መሰለኝ፥ ሳልናገር እንኳን የምፈልገውን ወንበር አገኛለሁ። ለዛም ይመስለኛል አሁን አስቀድሜ ያልተናገርኩት።

ግን ለምን የተለየ የወንበር ምርጫ ኖረኝ? ‘ቪአይፒ’ አጠገብ ለመቀመጥ ወይስ ‘ቪአይፒ’ መስሎ ለመታየት? መልሱ ከዚህ በፊት ከጠቀስኩት ጋር ይገናኛል። ቶሎ መውረድ ስለምፈልግ። ከበረራው ይልቅ ከአውሮፕላን ለመውረድ ያለው ጊዜ ረጅም መስሎ ይታየኛል። ኮሪደር አጠገብ (‘አይል’ መቀመጫ) የምፈልገው ደግሞ ወፍራም ስለሆንኩና መስኮት አጠገብ መቀመጥ ስለሚያጣብበኝ ነው።

አሁን ግን ፍላጎቴን ነግሬ መቀየር የሚችል እንደሆነ ጠየኩት። የፈለኩትን ሰጠኝ። ሻንጣየን ከመላኩ በፊት ሻንጣውን በአየር መንገዱ የገመድ ቁልፍ መቆለፍ ጀመረ። እኔ ደግሞ ብዙ ጊዜ ሻንጣየን ይዤው አውሮፕላን ውስጥ በማላስገባበት ጊዜ እንኳን አልቆልፈውም። አንደኛ እቃ ጠፍቶብኝ አያውቅም። የአክስቴ ልጅ ግን አንድ ጊዜ ከውጭ ሲመጣ ሻንጣው ተከፍቶ፣ ደህና ጫማው ጠፍቶ፣ በሱ ምትክ ያረጀ ጫማ እንዳገኘ አጫውቶኛል። ይሄ ግን አጭር የአገር ውስጥ በረራ ነው። ያም ሆነ ይህ፥ መጥፎ ነገር አጋጥሞኝ ባያውቅም፥ ውድ ነገሮችን ስለማላስገባ አልቆልፍም። ። ሻንጣየ ተረስቶ፥ መደረሻ ቦታየ ላይ ሁለት ጊዜ አጥቼዋለሁ። በሌላ ቀን እስኪመጣልኝ ድረስ፥ ሌላ ልብስ መግዛት ነበረብኝ። እቃቸውን ያስጫኑ መንገደኞች ብዙ ጊዜ ቀላል ምትክ ልብስ በእጃቸዉ በሚይዙት ሻንጣ እንዲከቱ ይመከራል፥ ካላስፈላጊ ወጪ፥ በተለይ በውጭ ሀገር ላይ፥ ያድናል።

አኔ ደግሞ አስተናጋጁን “አትቸገር እኔም ራሴ ቆልፌ አላዉቅም” አልኩት። ‘እንኳን በሀገር ውስጥ በረራ ብዙ ጊዜ ከውጭ ስመጣም…’ ልለዉ ፈለኩኝ እና ካፌ መለስኩት። ‘ደግሞ የማን ነው አካባጅ፥ ውጭ ሀገር እመላለሳለሁ ለማለት ነው?’ እንዳይለኝ በሚል። ደግሞ አስቀድሜ ሻንጣውን መጫን አስመልክቶ አካባጅ እንዳልሆንኩ እና ‘ኩል’ እንደሆንኩ ለማሳየት ሞክሬአለሁ።

 1. •••••••

በኋላ፥ ትንሽ ጊዜ ስለነበረኝ፥ ወደ ‘ጎልድ ላውንጅ’ ገባሁ።   የ‘ጎልድ’ ላውንጅን ለምን እጠቀማለሁ? ብዙ ጊዜ ነጻ እና ፈጣን ኢንቴርኔት ስላለ እና ጊዜ እስኪደርስ ለመገልገል። አንዳንዴ በጣም ከራበኝ ለመብላት። ወደ ማታ ከሆነ ደግሞ ትንሽ በነጻ ለመጠጣት። የተለያዩ አይነት ውስኪዎች፣ ቮድካ እና ሌሎችም መጠጦች ተቀምጠዋል። ብዙዎቹ ገና አልተከፈቱም። ተከፍቶ ያገኘሁት ‘ሬድ ሌብል’ ውስኪ ነበር። ምንም እንኳን ሌሎቹ ትንሽ የሚሻሉ ቢሆንም፥   እኔ ግን ‘ሬድ ሌብል’ ቀዳሁ። በላውንጁ ውስጥ ሌላ መንገደኛ የለም። ትንሽ ቆይቶ አንድ ወንድ የአየር መንገዱ አስተናጋጅ ገብቶ መንጎራደድ ጀመረ። የእንግዳ ተቀባዩዋ ቦታዋ ላይ ናት። በአፍታ በኋላ ጭማሪ ለመቅዳት ስነሳ ‘ሬድ ሌብል’ ጠርሙሱ የለም። የት ሄደ? ገረመኝ። “እንዴ እንዳይሰክር ብለው አነሱት እንዴ?”  ብዬ አሰብኩ። ሌሎቹ ያልተከፈቱትን ለምን አላነሷቸውም? በኋላ የቅድሙ ወንድ ስራተኛ ከእቃቤት ውስጥ ብቅ ብሎ ትንሽ ከተንጎራደደ በኋላ፥ ማቀዝቀዣውን ከፍቶ የቆርቆሮ ለስላሳ መጠጦች ይዞ ተመለሰ። ምን አልባት እሱ ይሆን የወሰደው? ስራውን ጨርሶ ሊወጣ ሲል ትንሽ ዘና ለማለት ነው ወይስ ስራ ላይ እያለ ነው የሚጠጣው?

ዋናው ጥያቄ ግን ምንም እንኳን ከ‘ሬድ ሌብል’ ውጭ ያሉት መጠጦችን፥ ለምሳሌ ‘ብላክ ሌብል’ ብመርጥም ለምን ከፍቼ አልጠጣሁም? የጀመርኩት ‘ሬድ ሌብል’ ሲወሰድ እንኳን ለምን እንደዛ አላደረግኩም? አስቀድሞ ከሻንጣው ጉዳይ ጀምሮ ‘እኔ አካባጅ አይደለሁም’፥ በሚል ስሜት ተንቀሳቅሻለሁ። እና ክፍት መጠጥ እያለ ሌላውን መክፈት ከዚህ ስሜት ጋር መጣላት ይሆን? ወትሮም አዲስ መጠጥ መክፈት እንደ ትልቅ ክስተት ስለሚቆጠር ይሆን? ስንጋበዝ እኮ፥ ‘ለኔ ብለህ አትክፈተው’፣ ‘ትንሽ ነው የምጠጣው’፣ ‘የተከፈተ ካለ እሺ ያለዚያ እንቢ’፣ እንላለን። ለምን? መጠጡ መከፈቱ አይቀርም አይደል? በተመሳሳይ መልኩ ‘መቶ ብሩን አትመንዝረው እኔ ዝርዝር አለኝ’ እንላለን። ክፍያ የሚቀበለው ሰው፥ ምንዛሬ እንዳያጣ አይደለም። የከፋዩ መቶ ብር እንዳይመነዘር እንጂ። ግን ለምን? መመንዘሩ አይቀርም እኮ። አሰብኩበት፤ ምናልባት ተጋባዡ ውለታ/ብድር ፈርቶ ነው? ለትንሽ መለኪያ ሲባል ከከፈተልኝ፥ እኔ ጠጥቼ ባልጨርሰውም፥ በሌላ ጊዜ እኔም ውስኪ እንድከፍትለት እንዳይጠብቅ ወይም መክፈት እንዳለብኝ እንዳይሰማኝ። ለካስ ግብዣ፥ የእከክልኝ ልከክልህ ጉዳይ ነው። ወይስ ያልተከፈተ ውስኪ፥ ጌጥ ነው?፥ ለሌላ ትልቅ እንግዳ ሊከፈት ይችል ነበር፤ ስለዚህ ጋባዡን ይህን እድል ላለመንፈግ ነው? ግብዣ ስንቀበል፥ እዳም እየወሰድን ነው ማለት ነው? የእዳው መጠን ደግሞ በተጠቀምነው ልክ አይደለም ማለት ነው? ማለትም የጠጣሁት አንድ መለኪያ ቢሆንም፥ አዲስ ጠርሙስ ከተከፈተ፥ ምንም እንኳን ከአንዱ መለኪያ ውጭ ያለውን በሙሉ የጠጣው ጋባዡ እና ሌሎች ሰዎች ቢሆኑም፥ እኔ ግን የምወስደው፥ የአንድ መለኪያ ውስኪ ሳይሆን የሙሉ ጠርሙስ እዳ ነው ማለት ነው? ለሶስት ብር ታክሲ ክፍያ ግብዣ፥ ጋባዡ መቶ ብር ሲመነዝር፥ የምወስደው እዳ የሶስት ብር ሳይሆን የመቶ ብር ነው ማለት ነው? ስለዚህ ይቅርብኝ አይነት መልስ ለራሴው አስቤ እንጂ ለጋባዡ አይደለም ማለት ነው? እንዲሁም፥ ጋባዡ አዲስ ጠርሙስ ለመክፈት፥ ለእኔ አስቦ ሳይሆን፥ ሙሉ እዳዉን ለእኔ አስተላልፎ፥ ከአንድ መለኪያ ውጭ ያለውን በዛ አጋጣሚ ለመጠጣት ነው። እቃህን ለሌላ ሰው አበድረህ/ሸጠህ እያለ፥ እንዳሻህ መጠቀም ይሉሃል ይህ ነው። ይሄ ጥርጣሬየ ትክክል ከሆነ፥ ከአንዳንድ የኤኮኖሚክስ ባለሙያዎች እምነት ጋር ይጋጫል ማለት ነው። አንዳንድ ኤኮኖሚስቶች ስጦታ፥ ሃብት ያባክናል ይሉናል። ለዚህ ምክንያታቸው፥ ስጦታውን አስመልክቶ ስጦታ ተቀባዩ እና ስጦታ ሰጪው፥ ለስጦታው እኩል ዋጋ አለመስጠታቸው ነው ። በአንዳንድ ጥናቶች መሰረት ስጦታ ተቀባዩ ለስጦታው የሚስጠው ዋጋ፥ ሰጪው ከከፈለበት በአማካኝ 20 ከመቶ ያንሳል ይላሉ። ስጦታ፥ በአለም አቅፍ ደረጃ በየአመቱ ሰዎች ብዙ ብር የሚያወጡበት ጉዳይ ነው። አመታዊ ዝውውሩ በቢሊየኖች የሚቆጠር ነው። ስለዚህ፥ የዚህ ከፍተኛ መጠን 20 ከመቶ የሚሆነው የባከነ የጠፋ ሃብት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ለምንድን ነው እንዲህ የሆነው? ዋናው ምክንያት ስጦታ ስንመርጥ የተቀባዩን ፍላጎት ካለማወቃችን የተነሳ ነው። ከሱ በላይ ፍላጎቱን የሚያውቅ ስለሌለ። ሌላው ብዙ ጊዜ ስጦታ እና ግብዣ አይነቱን የሚወስኑት ጋባዡ እና ሰጪው ናቸው። ስለዚህ ‘ተጋባዤ ምን ይፈልጋል? የት ቦታ፥ በምን አይነት ሁኔታ?’ ሳይሆን፥ ‘እኔ ምን አፈልጋለሁ?፥ እኔ ምን እወዳለሁ?’ በሚል ነው። ስለዚህ ሽሮ ቢበላ የሚመርጥ ሰው፥ ጥሬ ስጋ ሲጋበዝ እሺ ይላል። ጋባዡም አሰቀድሞ ምን ይፈልጋል የሚለውን ለማወቅ አይሞክርም። ተጋባዡም፥ ግብዣ እና ስጦታ አይነቱ ላይ ምርጫ ሊኖረኝ አይገባም ብሎ ያምናል። ይህ እንዲህ ከሆነ ከባድ ችግር ነው። ለዚህም ይመስላል፥ ይህን ብክነት ሊቀንስ ይችላል በሚል፥ በውጭ አገር አዲስ ተጋቢዎች ፍላጎታቸውን በአደባባይ በተለያየ መንገድ ያሳውቃሉ። ። እንዲሁም ስጦታን በገንዘብ መልክ መስጠት ይበልጥ እየተለመደ ነው። ሌላው ብክነት የሚመጣው ስጦታ ሰጪዎቹ ብዙ ሲሆኑ ነው። ባለመቀናጀታቸው የተነሳ፥ የሃብት ብክነት ይመጣል። ለምሳሌ አዲስ ሙሽሮች ከሚፈልጉት በላይ ጋቢ፥ ብርጭቆ፥ ሸሚዝ፥ ተመሳሳይ የባህል ልብስ በስጦታ መልክ ይቀበላሉ። አንድ ጓደኛየ ከብዙ አመት በፊት ስንመረቅ፥ በዚያ ጊዜ የተለመደ አይነት ሸሚዝ በብዙ ቁጥር ከተለያዩ ሰዎች በስጦታ ተቀብሏል። ያኔ፥ ብዙ ጊዜ የሚደረገው፥ ወይ መልበስ፥ አሊያም   አስቀምጦ ለሌሎች ሰዎች በስጦታ ማቀበል ነው ። ቢሆንም ብክነት መሆኑ አይቀርም። ወይም ለባለሱቆች በርካሽ ዋጋ እንሸጠዋለን። ይህም ብክነት ነው።

‘ስጦታ ሃብትን ያባክናል’ የሚለው ግኝት፥ ከላይ ከጠቀስነው ጋር ይጋጫል። እላይ እንዳየነው፥ ውስኪው እንዳይከፈት የፈለግነው የአንድ መለኪያ እዳ ለመውስድ ፈርተን ሳይሆን የሙሉ ጠርሙስ እዳ እንዳንወስድ ከሆነ፥ ታዲያ እንዴት ነው ስጦታ ተቀባዮች ለተቀበሉት እቃ ከወጣው ወጪ በ20 ከመቶ ያነሰ ዋጋ የሚሰጡት? የሙሉ ጠርሙስ እዳ የምወስድ ከሆነ፥ በተቻለኝ መጠን የሚገባውን ዋጋ መስጠት የለብኝም እንዴ? ለነገሩ ይህንን የአንዳንድ ኤኮኖሚስቶች እምነት የሚሞግቱ ሃሳቦችም አሉ። በዚህ መሰረት፥ የስጦታ ጥቅም (ለሰጪው) ለስጦታው በተከፈለው ዋጋ አይወስንም ይላሉ። የስጦታ አላማ እዳ፥ ብድር መስጠት አይደለም። ይልቅስ፥ ለተቀባዩ ማስተላለፍ የምንፈልገው መልእክት ስላለ ነው። ማለትም፥ ታማኝ፥ አሳቢ፥ አፍቃሪ የመሳሰሉት መሆናችንን ለማሳየት ነው። ስለዚህ ዝም ብሎ ከሱቅ በአንድ ሺህ ብር ከተገዛ ስጦታ ይልቅ፥ የተቀባዩን ፍላጎት በተለይ ደግሞ እንዲህ በቀላሉ ሊታወቅ የማይችልን ፍላጎት ፈልጎ ለይቶ፣ ረጅም ጊዜ አጥፍቶ፣ ይህን ፍላጎት መሰረት አድርጎ፣ ደግሞም እንዲሁ ጊዜ ፈጅቶ፥ ከብዙ አማራጮች መካከል በ100 ብር የተገዛ ስጦታ ለሰጪው የበለጠ ጥቅም (ወደ ፊት ከ100 ብር በላይ የሆነ ጥቅም የሚያስገኝ)፥ ለተቀባዩ ደግሞ የበለጠ እዳ (ከ100 ብር በላይ) ያመጣል ። ዞሮ ዞሮ የስጦታ አላማ እዳ፥ ብድር ማስተላለፍ፥ መረጃ መስጠት ነው። ስለዚህ ስጦታ አዋጭ ኢንቨስትመንት ሊሆን ይችላል። የስጦታውን አይነት እና ሁኔታ በጥንቃቄ እስከመረጥን ደርስ። 100 ብር አውጥተን 1000 ብር ማግኘት። በዚህኛው አስተሳሰብ ግን፥ የገንዘብ ስጦታ፥ እንኳን የሃብት ብክነትን ሊያድን የስጦታውን አላማ ላያሳካ ይችላል።

ስጦታን እና ሌሎች ጉዳዮችን አስመልክቶ፥ የኤኮኖሚክስ እና የስነባህሪ/ሰው ተመራማሪዎች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በከፍተኛ ፍጥነት በጥናት የሚያገኟቸውን ግኝቶች ሳነብ፥ ሁልጊዜ የማስበው ይሄ ግኝት፥ ማብራሪያ የሀገራችንን ሁኔታ ይገልጽ ይሆን? ስጦታ፥ ግብዣ ምንድን ነዉ? የስጦታ ጥቅም ለሰጪዉ፥ እና ለተቀባዩ በወጣበት ዋጋ ወይስ በሌላ በምን ይወሰናል? የገንዘብ ስጦታ የተለየ ጥቅም አለዉ? እያልኩ እጠይቃለሁ።

 1. ••

ለምን ግን ብላክ ሌብሉን አልከፈትኩትም? የአየር መንገዱን እዳ ፈርቼ ነው? ነው ወይስ ነጻ ነገር ላይ መንቀባረር፥ ውዱ መጠጥ እያለ ርካሹን መምረጤ ‘አካባጅ አይደለሁም፤ ኩል ነኝ’ ከሚለው ስሜት ጋር ለመጣጣም ነው? ምክንያቱም ለአንድ መለኪያ ሲባል ሙሉ ጠርሙስ መክፈቴ፥ ርካሽ እያለ ዉዱን መምረጤ፥ አይቶ የማያዉቅ፥ ነጻ ስለሆነ ውስኪ የምጠጣ ያስመስለኛል? ለነገሩ እኮ እዚህ ልታየኝ የምትችለው የላዉንጁ እንግዳ ተቀባይ ናት። ቅድም የነበረውን ክስተት ያየው ደግሞ፥ ሻንጣየን ልኮ የመሳፈሪያውን ፓስ/የይለፍ ወረቀት የሰጠኝ አስተናጋጅ ነው። የተለያዩ ሰዎች ናቸው።

 1. ••

የሚገርመውም እሱ ነው። ከቀድሞ ባህሪያችን፥ ውሳኔያችን፥ እምነታችን፥ ሃሳባችን መጣጣም የምንፈልገው ሰው ምን ይለናል ብለን ሳይሆን፥ ‘እኔ’ ምን ይለኛል ብለን ነው ። ባጭሩ የማይጣጣም ነገር መስራት አንፈልግም። በተፈጥሮ። በአንድም ወይም በሌላ ምክንያት ብናደርገውም እንኳን፥ ‘ያልተጣጣመ ነገር አደረግኩ’ ከማለት፥ አንዱን መርጠን አውቀን ለመርሳት፥ ወይም ወደ ኋላ በመሄድ ለመከለስ እንሞክራለን። ከዚህ ጋር የሚያያዝ አንድ ጥያቄ አለ። ድርጊት ከእምነት ይመነጫል፥ ወይስ እምነት ከድርጊት ይመነጫል? የሚል ነው።

 1. ••

በደቡብ እና ሰሜን ኮሪያ መካከል በተደረገው ጦርነት የአሜሪካን ወታደሮች በደቡብ ኮሪያ ወገን ተሰልፈዋል። የቻይና ወታደሮች ደግሞ በሰሜን ኮሪያ ጎን። በዚህ መካከል በቻይና የተማረኩ የአሜሪካን ወታደሮች ነበሩ። እነዚህ ወታደሮች፥ ህይወታቸውን ለሀገራቸዉ እና የህዝባቸው ጥቅም ሲሉ አሳልፈው ለመስጠት የተዘጋጁ ነበሩ። ነገር ግን አብዛኞቹ ወደ ሀገራቸዉ ሲመለሱ፥ ይዘውት ከሄዱት እምነትና አቋም በተለየ መልኩ ጸረ-አሜሪካን እምነት እና አቋም አንጸባረቁ። ይሄ እንቆቅልሽ የሆነባቸው ወታደራዊ ባለስልጣኖች እና ባለሙያዎች እነዚህ ወታደሮች በቻይና ቆይታቸው ያሳለፉት ሁኔታ ሊሆን ይችላል አቋማቸውን የቀየረው በሚል፥ የቀን ተቀን ኑሮዋቸው ምን ይመስል እንደነበር ማናገር ጀመሩ። ያገኙት ይህንን ነው።

በጦር ምርኮኞች መካከል የተለያዩ ውድድሮች ይካሄዱ ነበር። ከእነዚህ ውስጥ የጽሁፍ ውድድር አንዱ ነው። ሽልማቱም ሲጋራ ነው። ወታደሮቹ ባብዛኛው አጫሾች ነበሩ። አጫሽ ላልሆኑትም ቢሆን ሲጋራ ትልቅ ዋጋ ነዉ ያለው ። ምክንያቱም በእስር ቤቱ እንደ መገበያያ ገንዘብ ያገለግላልና ። ቻይናዎቹ ወታደሮቹ ከውድድር ውጭ በሌላ መልኩ ሲጋራ እንዳያገኙ አድርገዋል። ከዚህ በስተቀር ያደረሱባቸው ስቃይ አልነበረም። እናም አብዛኛው ምርኮኛ ቀኑን ሙሉ ይጽፍና በኋላ በውድድሩ ወቅት፥ ለሌሎቹ ምርኮኞች እና ለዳኞቹ ያነብባል። ገንዘብ የማግኛ መንገዱ ይህ ነበር። ሲጋራ ደግሞ ውድ ገንዘብ ነበር፥ ለአጫሹም ለማያጨሰውም። የጽሁፎቹ ማጠንጠኛ እንዴት የአሜሪካ መንግስት ጨቋኝ ኢምፔሪያሊስት እንደሆነ መሞገትና ማስረዳት ነው። እነዚህ ወታደሮች በዚህ አያምኑበትም። ሀገራቸውን ለቅቀው የሄዱት ተቃራኒ እምነት ስላላቸው ነው። ይልቅስ ጽሁፉን ለይስሙላ፣ ዳኞቹን ለማስደሰት እና ሽልማቱን ለማግኘት ነበር የሚጽፉት።

ድርጊት ከእምነት ይቀዳል? ወይስ እምነት ከድርጊት ይቀዳል የሚለው ክርክር የቆየ ነው። ይህ ታሪክ ለዚህ ጥያቄ ውስን ምላሽ ይሰጣል። ዋናው መልእክቱ ግን ባለሙያዎች ‘የማንነት ግጭት’ (cognitive disonance) ብለው ስለሚጠሩት ጉዳይ ነው።  ጉዳዩ እንዲህ ነው። ምንም እንኳን ጊዜ ቢያልፍም፥ የሰው ልጆች በእምነታቸው እና ድርጊታቸው አለመጣረስ ይፈልጋሉ። የእምነት፥ የድርጊት፥ የንግግር መጣረስ የማይመች ስሜት ውስጥ ይከታቸዋል። ስለዚህ በተቻለ መጠን መጣረስን ያስወግዳሉ። ስለዚህ ከነበረ እምነታቸው፥ ድርጊታቸው፥ ንግግራቸው ጋር የሚጣጣም እምነትን፥ ድርጊትን፥ ንግግርን ይመርጣሉ። ምርጫው እስካላቸው ድረስ። ይህን የሚመርጡት እምነቱን፥ ድርጊቱን፥ ንግግሩን ለብቻው መርምረው፥ “ይጠቅመኛል፥ መልካም ነገር ነው” ብለው አይደለም። ይልቅስ መጣረስን ለማስወገድ ነው። ምን ያህሉ ድርጊቶቻችን እና እምነቶቻችን በዚህ መልኩ የተቃኙ ይሆኑ? አውቀነው፥ መርምረነው ሳይሆን መጣረስን ለማስወገድ ስንል፥ ምን ያህል በድርጊትና በእምነት ተጠምደናል? ። ጉዳዩን አሰደናቂ የሚያደርገው ይህን የሚያደርጉት ሰው ምን ይለኛል ብለው ሳይሆን፥ ራሳቸውን ፈርተውና ለራሳቸው ነው። ምክንያቱ ውስጣዊ ነው። ሰዎች እንዲህ የሚያደርጉት በግላዊ ኑሮዋቸው ብቻ አይደለም፥ በቡድን በሚያደርጉት ዉሳኔም ጭምር እንጂ፥ ይህኛዉን ፓዝ ዲፔንደንስ ይሉታል (ፕሮፌሰር አንድሪያስ እሸቴ ‘ታሪካችን ያስረናል’ በሚል ይገልፁታል)።

በተለያየ ምክንያት እንኳን ራሳቸውን ተጣርሰው ካገኙት፥ በተለያየ መንገድ ይህን መጣረስ ለማስተካከል ይሞክራሉ። አሁንም ለራሳቸው ሲሉ። በምን አይነት መንገድ? አንደኛው፥ ከተጣረሱት መካከል አንደኛውን መልሶ በመከለስ፥ እንዳይጣረስ ማድረግ ነው። ሁለተኛው ደግሞ በሁለቱ መካከል መሰረታዊ ልዩነት እንዳለ እና የተለያዩ ነገሮች ደግሞ እንደማይጣረሱ አድርጎ ማቅረብ ነው። ከላይ ባለው ምሳሌ፥ ወታደሮቹ ከቀደመ እምነታቸው በተለየ መልኩ አሜሪካን የሚያጥላላ ጽሁፍና ንግግር ሲያደርጉ ነበር። ይህን ያደረገ ወታደር፥ መጣረሱ የሚያመጣበትን ውስጣዊ መረበሽ እና እረፍት ማጣት ማስተካከል የሚችለው መልሶ በመከለስ ነው። የጻፈውን ጽሁፍ እና ንግግር ሊከልሰው አይችልም። ስለዚህ ቀላሉ መንገድ መጀመሪያ የነበረውን እምነት መከለስ ነው።   ከመጀመሪያዉኑ ጀምሮ አሜሪካን እንደሚጠላ ራሱን ማሳመን ነው። ከተሳካለት፥ ከምርኮ ከወጣም በኋላም እንኳን አሜሪካን ያለመውደድ፥ የመጥላት፥ እምነት እና ድርጊት ማንጸባረቅ ነው። ይህ ምሳሌ ‘የማንነት ግጭት’ ከሚባለዉ በተጨማሪ፥ አንዳንዴ ድርጊት እንዴት ከእምነት ሊቀድም እንደሚችል ነው። ወይም እምነትን በምክንያት እና ሙግት መቀየር ሳያስፈልገን፥ ከምንፈልገው ድርጊት ጋር የሚጣጣም እና ግለሰቡ ከነበረው እምነት ጋር በሚጣጣም ድርጊት በተለያዩ ማበረታቻዎች እንዲሰማራ በማድረግ እምነቱንም መቀየር እንደሚቻል ያሳያል።

ምንም እንኳን በዚህ ዙሪያ የተጻፉ ብዙ ማብራሪያዎችና ጥናቶች ቢኖሩም፥ ባጭሩ ግን “የማንነት መጣረስ” ይህ ነው።

 1. ••

አሁን ወደ አውሮፕላን ውስጥ አየገባን ነው። የመረጥኩት እና የተሰጠኝ መቀመጫ ተይዟል። አስተናጋጆቹ ደግሞ በሰአቱ ለመነሳት እየተሯሯጡ   ነው። በዚህ ጊዜ አንዱን አስተናጋጅ ቦታየ ተይዟል አልኩት። እሱም ከኋላ ቦታ አለ አለኝ። መልሼ ቦታየ ተይዟል ስለውዉ ያለቦታው የተቀመጠውን መንገደኛ አስነሳው። መልእክቱ ለእኔ በሚመስል መልኩ፥ መንገደኛውን “ከኋላ ብዙ ባዶ ቦታ አለ፥ የፈለግከው ጋር መርጠህ መቀመጥ ትችላለህ” አለው። ደስ አላለኝም። አንዳንድ መንገደኞች ቀና ብለው ተመለከቱኝ። አስተናጋጁን ጨምሮ፥ ያ መንገደኛ፥ እና ቀና እያሉ የተመለከቱኝ ሰዎች አካባጅ እያሉኝ ይሆን? አካባጅ እንዳልሆንኩ በሚያሳይ መልኩ ለምን ዝም ብየ ከኋላ አልተቀመጥኩም? ለምንድን ነው ደስ ያላለኝ? የአስተናጋጁ እና የአንዳንድ መንገደኞች ምላሽ ነው ወይስ እነሱ ዝም ቢሉም እንኳን ተመሳሳይ ስሜት ይሰማኝ ነበር?

የቅድሙን የባህሪና ውሳኔ ማብራሪያ ከተከተልን፥ ማንም ምንም ባይለኝም እንኳን፥ አካባጅ ያለመሆን እና እንደዛ ላለመቆጠር ያደረግኩት የቀደሙ ሁለት ውሳኔዎች ጋር እየተጣረስኩ ስለሆነ ነው ደስ ያላለኝ? ለመሆኑ አካባጅ ላለመሆን ነው ወይስ አካባጅ ተብየ በሌሎች እንዳልቆጠር ነው? የትኛው ነው የሰዎች ባህሪ እና ውሳኔ ላይ ተጽእኖ ያለው። ይሄን ወደኋላ እመለስበታለሁ። አሁን ግን ሌላ ያልጠቀስኩትን ነገር ልጥቀስ? ወንበሬን ሳስቀይርም እኮ ‘አካባጅነት’ ከሚለው ጋር ተጣርሻለሁ። አሱን ግን ወንበሩን ለምን እንደምፈልገዉ በማብራራት መልሶ ለማጣጣም ሞክሬ ይሆናል። እናም አሁን ኋላ ወንበር ዝም ብየ ሄጄ ብቀመጥ ኖሮ፥ ራሴን እየተጣረስኩ ነው። ስለዚህ ወንበሬን ማስለቀቄ ከራሴ ጋር ላለመጣረስ ያደረኩት ሙከራ ሊሆን ይችላል። እዚህ ጋር አንድ ምቾት የማይሰጥ ጉዳይ ልጥቀስ። በዚህ ጽሁፍ ለምን ሻንጣየን ይዤ መግባት እንደምፈልግ፥ ለምን ደግሞ ፊት ለፊት እና ‘አይል’ መቀመጫ እንደምመርጥ የጻፍኩት ነገር አለ። እውነት ነው? ወይስ መጣረስ የሚያመጣውን የማይመች ስሜት ለመቀነስ ድህረ ክስተት ምክንያት ነው። ድህረ ክስተት ምክንያቶች የውሸት የመሆናቸው እድል ሰፊ ነው። ለዚያ ይመስለኛል፥ በግላዊ ኑሯችን ለነገሮች ሁሉ ያለንን ፍላጎት፥ አላማ አስቀድመን እንድንመረምርና እንድንለይ የሚመከረው። በተለይ ወሳኝ በሆኑ ጉዳዮች። ያለዚያ ከጉዳዩ በኋላ የምንፈጥረው ምክንያት ራሳችንን ለማታለል ልንጠቀምበት እንቻላለን። እንዲሁም መንግስት በሚስራቸው ስራዎች ለዚህ ነው አላማዎቹን እና ምክንያቶቹን አስቀድሞ እንዲያሳውቅ የሚጠበቀው። ለመስኖ ተብሎ የተገነባዉ ግድብ፥ ለምሳሌ ህዝብን በማማከር እና በማሳተፍ፥ ውጤታማ መሆን እየቻለ፥ በንድፍ እና በጥናት ችግር፥ ውሃ ማጠራቀም ባለመቻሉ የተነሳ፥ ለመስኖ ባይውል፥ በኋላ ላይ ግድቡ የአካባቢውን የጉድጓድ ውሃ ለማደስ በማዋሉ ውጤታማ ነው ማለት ራስን እና ሌሎችን ማሞኘት ነው። ጅምላ ጨራሽ መሳሪያዎች አላገኘንም፥ ነገር ግን ሳዳም ሁሴንን ያህል ጨቋኝ መሪ በማውረድ የኢራቅን ሕዝብ ነጻ አውጥተናል ማለትም እንዲሁ።

 1. ••

ስለአካባጅነት

አካባጅ መሆን ወይም መባል አለመፈለግ እንደ አዲስ እሴት ብቅ እያለ ነው። አካባጅ መሆኑን እና አለመሆኑን ማንነው የሚወስነው? አድራጊው ወይስ ማህበረሰቡ? ማህበረሰቡ ነው። እናም ማህበረሰቡ ማካበድ ብሎ ሊቆጥረው የሚችለውን ጉዳይ እናስወግዳለን። ማንም ሊያየን በማይችልበት ሁኔታስ? ምንም እንኳን በዚህ ጊዜ ማንም አያየንም በሚል ድርጊቱን ልንፈጽመው ብንችልም፥ ነገር ግን ከቀደመ እምነታችን፥ ድርጊታችን ጋር ላለመጣረስ ሲባል ከድርጊቱ ልንቆጠብ እንችላለን። ስለዚህ የ“ማንነት ግጭት” ጉዳይ ሰዎች ማንም ሊያያቸው በማይችል ሁኔታ እንኳን ድርጊቱን እንዳይፈጽሙ ለማድረግ አስቀድመን በተለያየ መንገድ እንዲቆጠቡ ማድረግ እንቻላለን የሚል ነው። ተገቢውን ነገር ካደረግን፥ የባህሪ ፓሊሲ የግለሰቡ አእምሮ ይሆናል ማለት ነው። ሰዎች ውጫዊ ቅጣትና መገለልን ብቻ ሳይሆን፥ ውስጣዊ የመጣረስ ስሜትንም ይፈራሉ። ለዛም ነው፥ ምርጫው ሚስጥራዊ ቢሆንም አስቀድሞ ለጓደኛው ወይም ለሌላ አካል በቃል ወይም በጽሁፍ እገሌን እመርጣለው ብሎ የገለጸ ሰው፥ የምርጫ ክፍሉ ውስጥ ሲገባ ሌላ ሰው የመምረጥ እድሉ ዝቅተኛ የሚሆነው ።

ማህበራዊ ቅጣት እና መገለል ውጤታማ የሚሆኑት (አንዳንዴም ከመደበኛው ሕግ በላይ) እርስ በእርስ በሚተዋወቁ፥ በሚቀራረቡ፥ መልሰው መላልሰው በተለያየ መስተጋብር በሚገኛኑ ሰዎች መካከል ነው። ስለዚህ ምንም እንኳን አካባጅነት የሚለው የሚወሰነው በማህበረሰቡ ቢሆንም እንዲህ አይነት ኢመደበኛ ድንጋጌዎች ውጤታማ የሚሆኑት የሚከበሩት በእንዲህ አይነት ሁኔታ ነው። ጅብ በማያውቁት ሀገር ሄዶ ቁርበት አንጥፉልኝ ይላል እንዲሉ! በአልፎ ሂያጆች መካከል ግን ይህ ውጤት አይኖረውም። አሁንም ሰውየው በሌላ መልኩ አካባጅነት መጥፎ ነው የሚለውን አቋም እንዲሰማውና እንዲቀበለው ካላደረግን በሰተቀር።

ይሄንን ለምሳሌ እንውሰድ? ለምንድን ነው ጉርሻ ወይም ‘ቲፕ’ የምንሰጠው? በአገልግሎቱ ደስተኛ ስንሆን እና ተመሳሳይ አገልግሎት በሌላ ጊዜ ለማግኘት። ማለትም ተመልሰን እንመጣለን ማለት ነው። ለነገሩ ደስተኛ ሳንሆን እንኳን፥ እንደውም ቅሬታችንን ገልጸን እንኳን ጉርሻ ሰጥተን እንሄዳለን። መልካም አገልግሎትን እያበረታታን ነው? ወይስ ጉዳዩ ሌላ ነው? ጉዳዩ ከራስ ጋር መጣረስን በመፍራት ነው። ሌላ ጊዜ መልሰን እንደማንመጣ እያወቅን እንኳን (ለምሳሌ ደግመን በማንመጣበት ከተማ ውስጥ አውቶብስ ተራ ያለ ሻይ ቤት ስንገለገል)፥ ምንም እንኳን በአገልግሎቱ ብንረካም ለምን ብለን ጉርሻ እንሰጣለን? ተመልሰን አንመጣም። ስለዚህ የምናገኘው ጥቅም የለም። ሻይ ቤቱም እኮ አውቶብስ ተራ ሲከፈት፥ አብዛኞቹ ደንበኞች ተመልሰው እንደማይመጡ ስለሚታወቅ ለጥራት ግድ አይኖረውም። የአውቶብስ ተራው ሰራተኛ፥ ሹፌሬ፥ ረዳት፥ ደላላ፥ ኪስ በርባሪ ካልሆነ በስተቀር። እነዚህ ደግሞ የተሻለ አገልግሎት ያገኛሉ። በዛው እንዳይቀሩ በማለት ሳይሆን፥ እነሱ ቢቀሩም ዋናው አልፎ ሂያጆች ናቸው፥ በሌላ ምክንያት፥ ለምሳሌ ለመንገደኞች መረጃ የሚሰጡት እነሱ ስለሆኑ። ድሮ ብዙ መዳረሻዎች ሁለት እና ሶስት ቀን በአውቶብስ በሚወስዱበት ጊዜ ተሳፋሪዎች ባብዛኛው ሹፌሩ መኪናውን ያሳደረበት ሆቴል ያርፋሉ። መኪናው ሌሊት ጉዞውን ስለሚጀምርም እዛው ማረፉ ይሻላል። የተሻለ አገልግሎት ግን ያገኛሉ ማለት አይደለም። ይልቅስ ሹፌሩ በነጻ የተሻለ አገልግሎት ያገኛል። ከመንገደኞች ጥራት ተቀንሶ፥ መንገደኞች ላይ ዋጋ ተጨምሮ ለሹፌሩ ይሰጣል። ከዚህ ሁሉ መንገደኞች ሃምሳ ሃምሳ ሳንቲም አዋጥተው የተሻለ ሆቴል እንዲወስዳቸው ለሹፌሩ ቢከፍሉት ይሻላል። ችግሩ እንዲያም ሆኖ ይህኛው ሆቴል የሚያገኙት አገልግሎት የተሻለ መሆኑን መንገደኞች እንዴት ያውቁታል? ባለሆቴሉም ቢሆን ለምን ለአልፎ ሂያጆች ይጨነቃል? በዚህ ሁኔታ ጉርሻ የምንሰጠው ለተሻለ አገልግሎት ተብሎ ሳይሆን፥ አሰቀድመን በተለያየ መልኩ አቋም ስለያዝን፥ ከራሳችን ጋር ላለመጣረስ ሊሆን ይችላል። አንዳንዴ አስተናጋጆች ቡናችንን እና ምግባችንን ገና አምጥተው ከማሰቀመጣቸው፥ ተመልሰው እንዴት ነው? ወደድከው? ይሉናል። ለመልስህ ተጠንቀቅ! አዎ ካልክ፥ በኋላ ቡናው ውስጥ ጥፍር ብታገኝም፥ ምግቡ ውስጥ የሞተ አይጥ ብታገኝም፥ ጉርሻ ሰጥተህ ልትወጣ ትችላለህ። ካልሰጠህም፥ መልሰህ ለማትመጣበት ቤት፥ አቤቱታህን ለማሰማት ትደክማለህ። አላማህ ማሻሻል አይደለም፥ የቅሬታህ አድራሻ ምግብ ቤቱ አይደለም፥ ራስህ ነው። ጉርሻ ያልሰጠሁት፥ ከራሴ ጋር የተጣረስኩት፥ በዚህ ምክንያት ነው በሚል። ለዛም ይሆናል ቅድም ከራሴ ጋር በተጣረሰ መልኩ፥ ‘ትኬቴን’ ሳስቀይር፥ ወንበሮች ሁሉ ለእኔ እኩል ጥቅም የላቸውም የሚለውን ለማብራራት የሞከርኩት። አስቀድመው ያመሰገኑት ለማማት ይከብዳል እንዲሉ። የ“ማንነት” ጉዳይ ከብዙ ፈርጆች  አንጻር ካየነው የሚያስገርም፥ የሚያስፈራራ፥ የሚጠቅም ነው። በብዙ መልኩ።

 1. ••

መልካም ነገር ምንድን ነው?

አንድ ባህሪ፥ ድርጊት መልካም መሆኑ እና አለመሆኑ የሚወሰነው በራሳችን ተሞክሮ ነው ወይስ በተመልካቾች ዳኝነት? ለምሳሌ ምግብ? የበላነው ምግብ መልካም እንደሆነ እንዲሰማን የሚያደርገን ለሰውነታችን ያስገኘው ጥቅም ፥ ለምላሳችን፥ የሰጠን ጣእም ነው? ወይስ ሌሎች ለዚህ ምግብ የሰጡት ቦታ።

ባብዛኛው ወሳኞቹ ሌሎች ናቸው። ማለትም መልካምነት አንጻራዊ ነው። በተለይ ደግሞ አንጻራዊ ባልሆነ መልኩ ራሳችን መገምገም ካልቻልን። ለምሳሌ የምግቡን ጥራት በመቅመስ፥ በማጣጣም፥   ልናየው እንችላለን። ነገር ግን ሙሉ ለሙሉ በዚህ አይታወቅም። በልተነው እንኳን ምግቡ መልካም እንደሆነ ለማወቅ ይከብዳል። ጣእምና እይታም ቢሆንም፥ ይሄ ጣእም ጥሩ ነው ያኛው መጥፎ የምንለው በራሳችን ነው ወይስ አንጻራዊ በሆነ መልኩ ነው? ራሳችንን እንጠይቅ? ይህን ለማምሰልሰል/ለኤህ አምሰልስሎት የሚከተሉትን ጉዳዮች አስብ።

ሃብታም መሆን ትፈልጋለህ እንበል። 100 ሚሊዮን ብር የሚገመት ሃብት ቢኖርህ፥ ራስህን ስኬታማ ብቻ ሳይሆን እድለኛም ብለህ ታስባለህ ማለት ነው እንበል። አሁን አንተ 100 ሚሊዮን ብር አለህ እንበል። የፈለከውን ማድረግ ትችላለህ። ችግሩ ምንም አድርግ ምን ካንተ ውጭ ማንም ሰው አያውቅም እንበል። ማለትም ብር እንዳለህ፥ የፈለግከውን ነገሩ ሁሉ ማድረግ እንደምትችል ማንም አያውቅም እንበል። ስለዚህ እንደማንኛውም ሰው የሕዝብ ትራንስፓርት (አውቶብስ) ተጠቃሚ ነህ። የምትኖረው በከተማው ውስጥ በሃብታቸው ከህብረተሰቡ የመጨረሻው 20 መቶኛ ውስጥ የሚገኙት   ሰዎች የሚኖሩበት አይነት ቤት ተከራይተህ ነው። ሁሉ ነገርህም የሚያሳየው ያንን ነው። ነገር ግን ያማረህ ነገር ካለ የገንዘብ ችግር ሳይኖርብህ፥ ማድረግ ትችላለህ። ነገር ግን ማንም ማወቅ አይችልም እንበል። ይህንን ትፈልገዋለህ? ሃብታም መሆን ከፈለግህ አሁን ራስህን ሃብታም አድርገህ ትቆጥራለህ?

ራስህን እንደ ሃብታም የማትቆጥር ከሆነ፥ የሃብት ትርጉም ሌላ ነው ማለት ነው። ሃብት ሃብት የሚሆነው ሌሎች እንደ ሃብት ሲቆጥሩት ነው። ማለትም ለነገሮች ያለን ዋጋ እና ፍላጎት ከቁጥጥራችን ውጭ ነው ማለት ነው። የዚህ ጉዳይ ጠንቁም ጥቅሙም ዘርፈ ብዙ ነው። በአንድ መልኩ ድህነትን የሚያከፋው፥ ሰዎች በማያቋርጥና በማይደረስ የመልካም ኑሮ መለኪያ/መስፈሪያ በውድድር ያለእረፍት በባተለኔት እንዲኖሩ ማድረጉ ነው። የመረጃ ፍሰት ደግሞ ይህን ጠንቅ ያከፋዋል። በአሁኑ ዘመን በተለይ፥ እንደ ዜጋ መልካምነት ምንድን ነው የሚለውን መፈተሽ የግድ ይላል። ራሳችንን ከአንጻራዊ ግምገማ ነጻ ማውጣት አለብን። ይሄ አባባል ሃይማኖታዊ፥ ‘ቡዲስት’፥ ቢመስልም አንዳንድ ኤኮኖሚስቶች ግን ይደግፉታል። ሃብታም መንግስተሰማያትን ከሚወርስ፥ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ብታልፍ ይቀላታል የሚለው አባባል ምንድን ነው ትርጉሙ? መሰረቱስ?

በሌላ መልኩ ደግሞ ዜጎች ያለምንም ቅጣት እና ሽልማት ተፈላጊ የሚባሉ ባህሪዎችን እንዲያሳዩ፥ ከማይፈለጉ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ማድረግ ይቻላል። በተለይ ቁጥጥር ማድረግ በማይቻልበት ሁኔታ፥ ቅጣትም ሆነ ሽልማት ውድ በመሆናቸው መቆጠብ ስላለብን፥ ወይም አንዳንድ ሰዎች ላይ ቅጣትም ሆነ ሽልማት ዋጋቸውን ስለሚያጡ። ከማይፈለጉ ድርጊቶች እንዲቆጠቡ ለማድረግ የሚቻለዉ ግን፥ አንጻራዊ ውድድር ሲኖርና ማን ምን እንዳደረገ በሚታወቅበት ሁኔታ ነዉ። ያለበለዚያ በዚህ መተማመን ውጤቱ የከፋ ነው። የከተማ ኑሮ ግላዊ እየሆነ ነው፥ ማህበራዊ መስተጋብሮች፥ እድሮች፥ የጋራ የመጫወቻ ቦታዎች፥ አብሮ ቡና መጠጣት፥ አብሮ በዓል ማክበር፥ የመሳሰሉት ነገሮች ሲቀንሱ፥ ማህበራዊ እሴቶች የግለሰቦችን ኑሮ ለመግዛት ያላቸው ኃይል ይቀንሳል። በዚህ ሁኔታ አንጻራዊ ግምገማ ያለውን ኃይል ሙሉ ለሙሉ አጥቷል ማለት አይደለም።

 1. ••

ተመልሰን ወደ አካባጅነት

አካባጅነት የማይፈለግ ተደርጎ ይወሰዳል። አንድ ሰው ትንሽ ግላዊ ጥቅሙ፥ መብቱ፥ ሲነካ ዝም ብሎ እንደ ቀላል ነገር አይቶ አለማለፉ፥ እንደ አካባጅነት ይቆጠራል። ሚስቱ በጣሳ የተቀመጠ ውሃ በቸልተኝነት በደፋች ጊዜ የደበደባት ባል፥ “እንዴት ላንድ ጣሳ ውሃ ሚስትህን ትደበድባለህ?” ሲባል፥ “ቅባኑግም ቢሆን ደፍታው ነበር” ብሎ መለሰ  ይባላል። ሰውየውን አካባጅ የሚያደርገው የተጣሰው ጥቅሙ አንሶ እሱ የሰጠው ምላሽ ግን መብዛቱ አይደለም። ለምሳሌ፥ ያለተራህ አልፈህ ሄድህ ታክሲ ውስጥ ገባህ ብሎ ሰውየውን አስወርዶ የደበደበ ሰው መጠሪያው አካባጅ ሳይሆን ወንጀለኛ፥ እብድ ወይም ጅል ነው የሚሆነው። በቀል ከበደሉ ጋር መጣጣም ያለበት ፍትሃዊ ለመሆን ብቻ ሳይሆን ውጤታማም ለመሆን ነው። ይሄ ሌላ ጉዳይ ነው። በዚህ ጽሁፍ ግን አካባጅ የሚያስብለው ተገቢውን ምላሽ እንኳን መስጠትን ነው። ለምሳሌ ተሰልፌ ታክሲ እየጠበኩ ነው። አንድ ሰው መጣና ቀድሞኝ ገባ። በዚህ ጊዜ ተገቢው መልስ፥ ግለሰቡ ይህን ለምንድን እንዳደረገ መጠየቅ፥ ሰልፍ እንዲያከብር መንገር ሊሆን ይችላል። አካባጅ የሚባለው ጥቅሙ ሲነካ፥ ከጉዳቱ ጋር ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ መስጠትንም። ዝም ብሎ የሚያልፍ። አይቶ እንዳላየ የሚሆን ነው። መልስ አለመስጠት ሁልጊዜ ‘ኩል’ አያስብልም። አካባጅ የሚያስብለው፥ ትንንሽ ጉዳዮችን አለማለፍ ነው። ከፍተኛ ጥቃትን ዝም ብሎ ማለፍ ግድ የለሽነት ወይም ፈሪነት ወይም ሰነፍነት ሊባል ይችላል። ለመሆን ጥቃቱ ከባድ፥ ምላሹ ተመጣጣኝ ብሎ የሚወስነዉ ባለቤቱ አይደለም እንዴ? ታዲያ እንዴት ነው ሌላው በአካባጅነት ላይ ዳኝነት የሚሰጠዉ?

 1. ••

አካባጅነት መልካም ነው?

ከዚህ በፊት ባለው ክፍል መልካምነት ባብዛኛው አንጻራዊ ነው ብለናል። ነገር ግን ይህ አንጻራዊ ምልከታ እና ግምገማ አንዳንዴ እንደ ግለሰብ የሚጎዳን፥ አንዳንዴ ደግሞ ጉዳቱ እንደ ማህበረስብ ሊሆን ይችላል። ከዚህ አንጻር አካባጅነት፥ መልካም ነው። እንደ መጥፎ ነገር መቆጠር የለበትም የሚል ሃሳብ ለማቅረብ ነው። ከራሴ ጋር መጣረሴ የፈጠረብኝን የማይመች ስሜት ለመቀነስ የማራምደው ሃሳብ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል።

 1. •••

መጽሐፍ ቅዱስን በሚገባ አላነበብኩም። መተንተንም አልችልም። ነገር ግን የሚደንቁኝ ሁለት አባባሎች አሉ። አንደኛው የመጨረሻውን ቀን፥ ማለትም የኢየሱስ ተመልሶ መምጫ ቀን መቼ እንደሆነ ይጠይቃሉ። እሱም፥ “በውድቅት ሌሊት እንደሚመጣ ሌባ እመለሳለሁ” ይላቸዋል። ሰዎቹ ግን በዚህ መልስ አልረኩም። ጨፍረው ጨፍረው፥ ሰዓቱ ሲደርስ ንሰሃ መግባት ይፈልጋሉ ይመስለኛል። ድሮ ክረምት ላይ ቀኑን ሙሉ ጭቃ ላይ ስንራገጥ እንውል እና፥ የአባታችን መመለሻ ሰዓት ሲደርስ፥ ተጣጥበን መጽሐፋችንን ገልጸን እንጠብቀዋለን። እናም አሁንም መልሰው ጠየቁት። “በቁርጥ ባትነግረንም፥ ምልክቶች ንገረን” አሉት። እሱም ምልክቶች ሰጣቸው። የመንግስታት አንዱ በሌላው ላይ መነሳት ፥ የመሬት መንቀጥቀጥ እና የመሳስሉት።

እናም አሁን የመሬት መንቀጥቀጥ እና ግጭት ስንሰማ ስምንተኛው ሺ እንላለን። በተለይ ክስተቱ ቅርብ ከሆነ፥ ባጭር ጊዜ ዉስጥ ከተደጋገመ ። በተለይ ስእላዊ መገለጫው ዘግናኝ ከሆነ። ጭር ሲል ደግሞ ስምንተኛው ሺ የሚባል ነገር ስለመኖሩም እንረሳዋለን። የገባን አይመስለኝም። መቼ እንደሚመጣ ተነግሮን አልሰማንም። ሳይገባን ቀርቶ ሳይሆን፥ የመምጫውን ጊዜ እና መንገድ አልወደድነውም። እናም ምልክት ስንጠይቅ፥ ማብራሪያ ፈልገን ሳይሆን፥ በሌላ ጊዜ ብትመጣ ይሻላል፥ እየመጣህ አንደሆነ አውቀነው እንድንዘጋጅ ለማለት ነበር። ምክንያቱም 24 ሰዓት ዝግጁ መሆንን አልወደድነውም። 23 ሰአታት ጭቃ ላይ ስንጫወት ውለን በመጨረሻዉ ሰዓት ተጣጥበን፥ መጽሐፋችንን ይዘን መጠበቅ እንፈልጋለን። ስንት ሰዓት ትመጣለህ ስንለው አይታወቅም አለን። ማለትም 24 ሰዓት ተዘጋጁ እያለን ነው። እኛ ግን “እሺ ባይሆን ምልክት ስጠን” ብለን ጠየቅን? የማይታወቅ ከሆነ እንዴት ምልክት እንጠይቃለን። ኢየሱስም በሚገባ የበላን መሰለኝ። “ምልክት ነው የፈለጋችሁት? እንኩ ምልክት” አለን። ምልክቱን፥ የመጀመሪያው መልስ ማብራሪያ ሳይሆን፥ የመጀመሪያውን ውሳኔ አሳምነን ወይም አሳዝነን ያስቀየርን ይመስል፥ ይሄዉ ጭቃ ላይ እንራገጣለን። ሁለተኛው መልስ የተሻሻለ መልስ ሳይሆን፥ የመጀመሪያው መልስ በሚገባን ቋንቋ ተቀይሮ ነው። የሰው ልጅ ከተፈጠረ ወይም ከዝንጀሮ መሰል ፍጡር አፈንግጦ ከወጣ ጀምሮ ግጭት ነበር፥ አደጋዎች ነበሩ። ስለዚህ ሁለተኛው መልስ፥ “መምጫየ አይታወቅም፥ ሁሌ ጥንቁቅ፥ ሁሌ ዝግጁ ሁን” እያለ ነው።

 1. ••

‘ኮምፕሌክስ’ እና ‘ኮምፕሊኬትድ’

ስርዓቶችን በሁለት መክፈል እንችላለን። አንደኛው ‘ኮምፕሊኬትድ’ የሚባለው ነው። ይህ ስርዓት ምንም እንኳን ውስብስብ ቢሆንም፥ ባህሪውን በሚገባ ማጥናት እና መተንበይ እንችላለን። ምንም እንኳን ውስብስብ ቢሆንም፥ የስርዓቶችን ክፍሎች ለየብቻ በማጥናት፥ እነዚህ ክፍሎች እርስ በርሳቸዉ ያላቸውን ግንኙነት በማጥናት ስለጠቅላላ ስርዓቱ ማወቅ ይቻላል። አካባቢያዊ ለውጦች በስርዓቱ የሚያመጡትን ምላሽ ማወቅ ወይም መተንበይ ይቻላል። እንደ አካባቢያዊ ውጫዊ ግብዓቱ መጠን፥ የሚመጣውን የምላሽ ለውጥ ማወቅ ይቻላል።

በሌላ መልኩ ‘ኮምፕሌክስ’ የሚባለው ስርዓትን ባህሪ እና አሰርራር የስርዓቱን ክፍሎች እና አሰራር ከፋፍሎ በማጣናት የስርዓቱን ጠቅላላ ባህሪ እና አሰራር ማወቅ አይቻልም። ትንሿ አካባቢያዊ ወይም ውጫዊ ለውጥ የምታመጣውን የምላሽ መጠን ማወቅ አይቻልም። አካባቢያዊ ወይም ውጫዊ ለውጡ ምንም እንኳን እየተቀየረ ያለው መደበኛ በሆነ መልኩ ቢሆንም መልሱ ግን ከለውጡ ጋር ተመጣጣኝ አይሆንም። የ‘ኮምፕሌክስ’ ስርዓት ምሳሌ ተፈጥሮ ነው። ለምሳሌ የአየር ንብረት ስርዓቱ። ልቀት በዚህ ያህል ቢጨምር፥ ሙቀት በዚህ ያህል ሊጨምር ይችላል ብሎ በእርግጠኛ መናገር አይቻልም። ታሪካዊ ማስረጃዎችም ቢሆኑ ለግምት የማይመቹ ናቸው። እንዲሁም የስርዓቱ ክፍሎች እና እርስ በርስ ያላቸውን መስተጋብር ሙሉ ለሙሉ ለማወቅ አይቻልም። በመሆኑም አስካሁን የልቀት መጠን በአስር በመቶ ሲጨምር፥ ሙቀት በ1 በመቶ ጨምሮ ነበር በሚል፥ ወደ ፊት ተመሳሳይ የልቀት መጠን ይህን ያህል የሙቀት ጭማሪ ያመጣል ብሎ ለመናገር ያስቸግራል። በተለይ ደግሞ ‘ቲፒንግ ነጥብ’ የሚባለው ቦታ ከደረሰ በኋላ ምላሹ ፍጹም ከፍተኛ፥ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ይችላል። ‘ቲፒንግ ነጥቡ’ ደግሞ ይህ ነው ብሎ ለመናገር ያስቸግራል። ‘ቲፒንግ ነጥብ’ የሚባለዉ አንድ ስርአት ተገማችና ተመጣጣኝ ምላሽ ሲሰጥ ቆይቶ፥ ከቁጥጥርና ግምት በላይ የሆነ ምላሽ መስጠት የሚጀምርበት ነጥ/ጊዜ ነዉ። በዚህ ጊዜ ትንሿ ውጫዊ ምክንያት የምታመጣው የስርዓቱ መዛባት መጠን፥ ከውጫዊ ለውጡ መጠን ጋር ሲነጻጸር በእጅጉ የበዛ ይሆናል።

 1. ••

የስርዓቱን መጨረሻ መገመት አይቻልም። የኢየሱስን መምጫ መገመት አይቻልም። ትንሿ ለውጥ እንኳን የስርዓቱን መጨረሻ ልታመጣ ትችላለች። ግጭት እና የመሬት መንቀጥቀጥን በእርግጠኛነት መተንበይ እንደማንችል ሁሉ፥ ግጭትና የመሬት መንቀጥቀጥ የተለመዱ እንደመሆናቸው መጠን፥ ያለተለመደ ምልክት መጠበቅ የለብንም። የተላመድናቸው ጉዳዮች ቢሆኑም በ‘ኮምፕሌክስ ስርዓት’ ውስጥ የሚያመጡት ለውጥ ይህ ነው ብሎ አንደማይገመት ሁሉ፥ የአለም መጨረሻም አይታወቅም የሚል መልእክት ያለው ይመስለኛል።

 1. ••

‘ኮምፕሌክስ ስርዓቶች’ የሚባሉት፥ ማህበራዊ ስርዓቶችም ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ “አይ ትንሽ ነው፥ ተወው፥ እለፈው” ማለት የሚያመጣው ጠንቅ ትንሽ ነው ማለት አይቻልም። በተለይ ደግሞ ጥቅምን እኛን ተክቶ የሚያስከብርልን ሶስተኛ ወገን በማይኖርበት ጊዜ። ጥቅም ሁሉ የሚከበረው በሕግና በቅጣት አይደለም። ኢመደበኛ ስርዓቶች እና እሴቶች ከፍተኛ ሚና ይጫወታሉ። በተለይ ደግሞ ለትንንሽ ጥሰቶች። ነገር ግን ለትንሽ ነገር አታካብድ የሚለው ዘመናዊ እሴት፥ የኢመደበኛ ስርዓቶችን የሚሸረሽር ነው። የእነዚህ መሸርሸር ደግሞ በትንሹ የሚያቆም ወይም በኢመደበኛ ስርዓቶች ብቻ የሚገደብ አይደለም። ሲለመድ፥ ይበዛል። ይህ ጽሑፍ እና ይህን ለመጻፍ ያነሳሳኝ ምክንያት ራሱ “የማንነት ግጭት” ተብሎ ሊወሰድ ይችላል።

 1. ••

መደበኛ ሕግ ግን ማካበድ የለበትም። በተለያዩ የሕግ ስርዓቶች፥ በመጠናቸው እና በውጤታቸው ትንንሽ የሆኑ ጥሰቶችን ሕጉ ራሱ ይቅር ይላቸዋል። በትንንሽ ጥሰቶችን፥ እርምጃዎችን በመውሰድ፥ የከፉ ጥሰቶችን፥ እና ወጪዎችን ማዳን ይቻላል። ማጅራት መቺዎችን እና ነፈሰ ገዳዮችን፥ ከተማን እና የመንግስት ሽንት ቤቶችን በማጽዳት መዋጋት ይቻላል። ከተገቢው ማብሰልሰል በኋላ ግን፥ በተለይ የሕግ ማስከበሪያ ሃብትን ለላቀ ውጤት ለመጠቀም ሲባል፥ ሕጉ ይቅር ባይላቸውም፥ በአፈጻጸም ይቅር ልንላቸው የምንችላቸው ጥሰቶችና ጥፋቶች ይኖራሉ።

 1. ••

ባጭሩ “አታካብድ” የከፋ የመብት ጥሰቶችን፥ እና ዝምታን የሚያበረታታ ዘመናዊ ማህበራዊ እሴት ስለሆነ/ስለሚሆን ልንሞግተው ይገባል። ድሮ ድሮ በፍትህ ከሄደች በቅሎየ፥ ያለፍትህ የሄደች ዶሮየ ይባላል። በግል የደረሰብንን የመብት ጥሰት ትንሽ ነው በሚል እንድንተወው የምንበረታታ ከሆነ፥   ግላዊ ጉዳቱ ከዛም ያነሰ፥ ነገር ግን አገራዊ ጉዳቱ ከፍተኛ የሆነን ጥሰት እንዴት ነው የምንከላከለው? የመንግስት አገልግሎት ለማግኘት ስንሄድ፥ ጉቦ ክፈል ተባልክ እንበል። 30 ብር ጉቦ መክፈል ወይስ ሁለት ሳምንት ሙሉ መመላለስ? ወጪና ጥቅሙን ስናሰላ፥ ማህበራዊ ወጪዎችና ጥቅሞች ግምት ውስጥ የማይገቡ ከሆነ ምርጫው ግልጽ ነው። 30 ብር ጉቦ መክፈል። “አታካብድ” በነገሰበት አለም ታዲያ እንዴት ነው፥ ሁለት ሳምንት መመላለስ የምትመርጠው? የድርጊቶችን ወጪ/ኪሳራ አድራጊው ሙሉ ለሙሉ የማይሸከመው ሲሆን፥ ማለትም አንዳንዱ ወጪ ማህበራዊ ሲሆን፥ አድራጊው ሙሉ ወጪውን እንዲሸከም ማድረግ የመንግስት ሃላፊነት ተደርጎ ይወሰዳል። ታዲያ እንዴት ነው፥ መንግስት የሙስና ማስረጃ ከዜጎች የሚጠብቀው፤ በተለይ አታካብድ እየነገሰ?

 1. ••

ሌላኛው መልእክት፥ የ“ማንነት ግጭት” ጉዳይን ልብ በል። ልትጠቀምበት ትችላለህ፤ ወይም ሊጠቀሙብህ ይችላሉ። ቃልህ ያስርሃል። አንዳንዴ በውል ሕግ። ዋናው ማሰሪያህ ግን ራስህ ነህ። ስለዚህ ስለቃልህ ተጠንቀቅ። የውል ሕግ ከመፈረምህ በፊት አንብብ፥ ተረዳ፥ እና ወስን ይልሃል። የውል ህግ ባይኖርም ግን ይህን አድርግ። ሳታምንበት ምንም ነገር አታድርግ። ድርጊቱ ትንሽ ቢሆንም ያልነበረህን እምነት ሊያሰጨብጥህ ይችላል። “በፈጣሪ መኖርና አለመኖር አላምንም” ስትል፥ “ግዴየለም እሱ በራሱ ጊዜ ይመጣል፥ ለተወሰነ ጊዜ የእኛ የእምነት ቦታ ተከታተል” ትባላለህ። በእርግጥ ተሳትፎአዊ ጥናትን ሳይንሳዊ ማድረግ ይቻላል፥ ይሄ ለሌላ ጊዜ ይቆየን።

ስለ “ማንነት” ግጭት ያወጋሁት ወዳጄ፥ “የኢህአዴግ ደጋፊ የሆንከው ታዲያ፥ ያኔ የመጀመሪያ አመት ተማሪ እያለን፥ ስለጎጃም መሬት ክፍፍል የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች ተቃውሞ ሲያደርጉ አብረህ ታፍሰህ ሽጎሌ ቆይተህ፥ ለመለቀቅ ብልህ በፈረምካት ወረቀት ምክንያት ነዋ!” እያለ ያፌዝብኛል። ያኔ ‘ድንገት’ አቀላቅለው አፍሰውኝ ነው እንጂ ተቃውሞው ስለምን እንደሆነም ሳላውቅ ነው በቦታው የተገኘሁት። በኋላ “ይቅርታ ጠይቁና” ትፈታላቹ አሉን። እኔም በፊርማየ ጠይቄ ተፈታሁ። የፈረምነው አንድ አይነት ፎርም ነው። ቃል በቃል ባይሆንም እንዲህ ይላል። ‘እኔ ስሜ የተጠቀሰው በዚህ ቀን ሰአትና ቦታ የአዲስ አበባን ህዝብ ሰላም ለማደፍረስ አቅጄ ተንቀሳቅሼ አልተሳካልኝም፥ በዚህም ተጸጽቼአለሁ፥ በይቅርታ እንድፈታ በፊርማየ እጠይቃለሁ።’

 • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.