• Dr. Mulugeta Mengist

ኢትዮጲያዊ አሊባባ ያስፈልገናል!

Updated: Nov 17, 2019


መግቢያ

ገበያ ማለት የዜጎች የነጻ ዉድድርና የመስተጋብር ስርአት ነዉ። የገበያ ስርአት፤ ልማትን በፍጥነትና በዘላቂነት ማረጋገጥ ይችላል ይላሉ። ለነገሩ ይህን የሚሉት ኒዮሊብራሎች ብቻ ሳይሆኑ ልማታዊያንም ጭምር ናቸው። ልዩነቱ በመነሻው (በገበያ) ላይ ሳይሆን፥ ዉድድሩና መስተጋብሩ ምን ያህል ነጻ መሆን አለበት በሚለዉና፥ መንግስት ምን አይነት ሚና በምን መልኩ መጫወት አለበት በሚለዉ ነዉ።

ዜጎች በማምረትና በመለዋወጥ የሚያደርጉት የእርስ በርስ ዉድድርና መስተጋብር፥ ሃብትን ለላቀ ዉጤት መጠቀም፤ የእዉቀትና ቴክኖሎጂ እድገት ማረጋገጥ፥ እና የብዙሃኑን የተለያዩ ፍላጎቶችን ማሟላት ይቻላል። ነገር ግን የነጻ ዉድድርና መስተጋብር ስርአት ከተገረጡበት ጋሬጣዎች መካከል አንዱን እንመልከት። ይህም የግብይት ወጪ ነዉ።

የግብይት ወጪ

በዋናነት የገበያ ስርአትን የሚፈታተኑ ማነቆዎች የግብይት ወጪ ይባላሉ፡፡ የግብይት ወጪ ከምርት ወጪ ይለያል፡፡ የምርት ወጪ አንድን ምርት ወይም አገልግሎት ለማምረት የሚወጣ ወጪ ሲሆን የተመረተዉን ምርት ወይም አገልግሎት ለመለወጥ የሚወጣ ወጪ ደግሞ የግብይት ወጪ ይባላል፡፡

ምርቱን ከጉልበተኛ ለመጠበቅ የሚወጣዉ ወጪ ምንም እንኳ ቀጥታ ከግብይት ጋር ባይያያዝም፤ ከምርት ሂደቱ ጋርም ስለማይያያዝ የግብይት ወጪ ልንለዉ እንችላለን፡፡ ይህኛዉ አይነት ወጪ ግብይት ባይኖርም ይኖራል።  ነገር ግን ግብይት እንዲኖር ምርትን ማሳደግ ይጠይቃል። እንዲህ አይነቱ ወጪ ደግሞ ምርትን በመቀነስ ወይም አንድ አይነት ምርቶችን ጭራሽ እንዳይመረቱ በማድረግ ግብይትን ሰለሚቀንስና፥ በአጠቃላይ እድገትን ስለሚጎዳ የግብይት ወጪ ብለን ብንወስደዉ መሰረታዊ ችግር የለዉም፡፡


ራስን እና ምርትን ከጉልበተኛና አታላይ ለመጠበቅ

በአጠቃላይ የግብይት ወጪ እንደሚከተለዉ ክፍለን ማየት እንችላል፡፡ አንደኛዉ የግብይት ወጪ አካልን፤ ሕይወትን፤ ምርትን ከጉልበተኛና ከሌባ ለመጠበቅ ሲባል ለጥንቃቄ፤ ለክትትል፤ ለመከላከልና ለማስመለስ የሚወጣ ወጭ ነዉ፡፡ ይህ ወጭ ከፍተኛ ከሆነ ሰዎች ምንም ጊዜ፤ ጉልበትና ሃብት በሚጠይቅ የኤኮኖሚክ ስራ እንዳይሰማሩ ያደርጋል፡፡

ለምሳሌ የተከሏቸዉ ዛፎች የሚያፈሩትን ፍራፍሬ ከሌባና ጉልበተኛ መጠበቅ ከፍተኛ ወጪ የሚያስወጣ ከሆነ መጀመሪያዉኑ እነዚህ ዛፎች አይተከሉም፡፡ ቢተከሉም እንኳ እነሱን ከጉልበተኛ ለመጠበቅ የወጣዉ ወጭ ምርታማነት በሚጨምሩ ስራዎች መዋል ሲችል፤ በጥበቃ ላይ ይባክናል። እንዲህ አይነት ወጪን ሙሉ ለሙሉ ዜሮ ለማስገባት ጉልበተኛ፥ ሌባና አታላይ ሙሉ ለሙሉ መጥፋት አለባቸዉ ማለት ነዉ፡፡ ይህ ደግሞ የማይቻል ነገር ነዉ፡፡

በመሆኑም መፍትሄ ሊሆን የሚችለዉ መንግስት ዜጎችን ከጉልበተኞችና ከሌቦች በመጠበቅ ግለሰቦች ራሳቸዉን በመጠበቅ እንዳይጠመዱ ማድረግ ነዉ፡፡ መንግስትስ ቢሆን ዜጎችን ለመጠበቅ የሚያወጣዉ ወጭ ግለሰቦች ከሚያወጡት በምን ይለያል–እንደባከነ አይቆጠርም ወይ የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡

በእርግጥ እንደ ብክነት ቢወሰድም እንኳ መንግስት የሚያወጣዉ ወጭ በሁለት ምክኒያት ይቀንሳል፡፡ አንደኛዉ፤ መንግስት ሲኖር በፍርሃትና በፍቃደኝነት፤ በጉልበትና በሌብነት የሚኖረዉ ሰዉ ቁጥር ይቀንሳል። በመሆኑም ወጪዉ ይቀንሳል፡፡ ሁለተኛ፤ መንግስት ስራዉን በተናጠል ሳይሆን በጅምላ ስለሚሰራ ወጪ ይቆጥባል፡፡ ሌላዉ የሚነሳዉ ጥያቄ መንግስት ባለበት አገር ዜጎች ራሳቸዉንና ንብረታቸዉን ለመጠበቅ ሲሉ የሚወስዱት የጥንቃቄ እርምጃ የመንግስትን ድክመት እንዲሁም ብክነትን ያሳያል ወይ የሚል ነዉ፡፡

መልሱ እንደ ሁኔታዉ ነዉ፡፡ ዉጤታማ መንግስት ቢኖርም እንኳ በመንግስት ከመተማመን ይልቅ የተወሰነ ጥንቃቄ ማድረግ በዜጎች ይጠበቃል፡፡ ዉጤታማ መንግስት ማለት ዜጎች ዜሮ ጥንቃቄ ያደርጋሉ ማለት አይደለም፡፡ የተወሰነ የዜጎች ጥንቃቄ የመንግስትንም ዉጤታማነት ይጨምራል፡፡ ሁለተኛ አንዳንድ ጥንቃቄዎች መንግስት ከሚያደርጋቸዉ ይልቅ ዜጎች ቢያደርጓቸዉ ይሻላል፡፡ መንግስት የንብረት ሕግን በማዉጣትና በማስፈጸም የሚያደርገዉ ስራ በሙሉ እንዲህ አይነት ወጪን የመቀነስ ስራ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

ገዢ ወይም ሻጭ ፍለጋ

ሁለተኛዉ፤ አይነት የግብይት ወጭ ፍላጎትና አቅም ያለዉና ታማኝ የገበያ አጋር ለመፈለግ የሚወጣ የግብይት ወጪ ነዉ፡፡ ለምሳሌ አንድ ዜጋ ትርፍ በቆሎ ካመረተና የሚፈልገዉ በግ ከሆነ፤ የሚፈልገዉን ለማግኘት አቅም ያለዉ አጋር ያስፈልገዋል፡፡ በዚህ ምሳሌ መሰረት በቆሎ አምራቹ የሚፈልገዉ አይነት በግ ያለዉ ዜጋ አቅም አለዉ ልንለዉ እንችላለን፡፡ ነገር ግን ፍላጎት ላይኖረዉ ይችላል፤ ለምሳሌ ይህ ባለበግ በጉን ሊለዉጠዉ ቢፈቅድም እንኳ በልዋጩ ግን በቆሎ ሳይሆን የሚፈልገዉ ጋቢ ሊሆን ይችላል፡፡ ካልሆነ ባለበቆሎዉ፤ ጋቢን በበቆሎ የሚለዉጥ አጋር ማግኘት ይኖርበታል፡፡ ይህን ካገኘና ከለወጠ በኋላ መልሶ ከባለበጉ ጋር ጋቢዉን በበግ ይለዉጠዋል ማለት ነዉ፡፡

ማንኛዉም አይነት የገበያ አጋር ማግኘት በራሱ ወጪ ሆኖ እያለ የሚፈልጉትን ለማግኘት ሁለትና ከዚያ በላይ ልዉዉጥ ማድረግ ደግሞ ተጨማሪ ወጪ ነዉ፡፡ የመጀመሪያዉ ወጪ በመረጃ እጥረት የሚመጣ ነዉ፡፡ ሁለተኛዉ ደግሞ ቀላልና አስተማማኝ የመገበያያ ገንዘብ ካለመኖሩ የሚመጣ ነዉ፡፡ ቀላልና አስተማማኝ የመገበያያ ገንዘብ ቢኖርም እንኳ አስተማማኝ የገበያ አጋር ማግኘት ራሱን የቻለ ወጪ አለዉ፡፡ ብዙ እጅ በእጅ የሚደረጉ ግብይቶች የዚህ አይነት ወጪያቸዉ ዝቅተኛ ነዉ፡፡ ቢሆንም እንኳ የተገበያዬትን ነገር ጥራት እዛዉ ማወቅ ስለሚያስቸግር የዛኛዉ ወገን ታማኝነት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡

ድርድርና መስማማት

ሶስተኛዉ ወጭ ከግብይት አጋር ጋር ለመስማማት የሚወጣ ወጭ ነዉ፡፡ ስምምነት መግባባትን የሃሳብ መገናኘትን ይጠይቃል፡፡ ይህ ዉይይትን፤ ሃሳብ መለዋወጥን እንዲሁም ከተለያዩ ገጽታዎችና ክስተቶች አንጸር በጉዳዮች ላይ መግባባትን ያካትታል፡፡

ስምምነቱም መከታተልና ማስከበር

አራተኛዉ ወጭ ስምምነቱን መከታተል ነዉ፡፡ የቀረበዉ ምርት ወይም አገልግሎት በቀረበዉ ስምምነት መሰረት ስለመሆኑ ምርቱን ወይም አገልግሎቱን መፈተሸ፤ መለካት፤ መቁጠር፤ መመዘን ያስፈልጋል፡፡ በቀላሉ ፍተሻ የማይገኙ ጉድለቶች ሊኖሩ ሰለሚችሉ ወጭዉ በዛዉ ልክ ይጨምራል፡፡

አምስተኛ፤ አንደኛዉ ወገን ስምምነቱን በፈቃደኝነትና በተስማማዉ መሰረት ባይወጣ ስምምነቱን ለማስፈጸም የሚወጣ ወጭ አለ፡፡ አለመግባባት ቢኖር በጉልበት ለመፍታት ይሞከራል፡፡ ይህ ራሱን የቻለ ወጭ ነዉ፡፡ እንዲሁም የአንደኛዉን ወገን በመፍራት አስቀድሞ የሚደረግ መተማመኛም እንደ ወጭ ይቆጠራል፡፡ የዚህ ወጭ በአንደኛዉና በሌላኛዉ መካከል የጊዜ ልዩነት ከመኖሩ የተነሳ ወይም ጉድለቱን ለማወቅ ጊዜ ከመዉሰዱ የተነሳ የሚወጣ ወጭ ነዉ፡፡ በስምምነቱ ሁለቱም የሚጠቀሙ ቢሆንም እንኳ እና ሁለቱንም የሚበጃቸዉ ቃላቸዉን መጠበቃቸዉ ቢሆንም እንኳ ሁለቱ ወገኖች ስምምነታቸዉን በቀላሉ የሚያስከብሩበት መንገድ እስከሌለ ድረስ ሁለቱም ቃላቸዉን ወደ አለመጠበቅ ሊሄዱ ይችላሉ፡፡


የግብይት ወጪ ምርትና ግብይትን ይቀንሳል

የግብይት ወጪ ምርትን ለመጨመር ሊዉሉ የሚችሉ ሃብቶች ምርትን፥ ህይወትን፥ እና አካላዊ ደህንነትን ከጉልበትና ካታላይ ለመጠበቅ በማዋል የዜጎች ኑሮ በዛዉ ልክ እንዳይሻሻል ያደርጋል፡፡ እንዲሁም ከላይ የተዘረዘሩት የግብይት ወጪዎች የገበያ ስርአት በእጅ ለእጅ ግብይት፤ የጥራት ደረጃቸዉ በግብይት ወቅት ሊገመገሙ በሚችሉ፤ እንዲሁም የክፍያዉ እዉነተኛ ዋጋ በቀላሉ በሚታወቅበት ሁኔታ፤ እንዲሁም ግብይት በተደጋጋሚ በሚገናኙና በሚተዋወቁ ሰዎች መካከል ብቻ እንዲታጠር ያደርጋል፡፡ ይህን በማድረግ እጅግ ብዙ ግብይቶችን ያስቀራል፡፡ በዛዉ ልክ የልማት እድሎችን ያጠባል፡፡ በዚህ ሁኔታ ስለልማትም ማዉራት እጅግ ከባድ ነዉ፡፡


መንግስት የግብይት ወጪን ለመቀነስ ያግዛል

መንግስት የግብይትን ወጪ እንዲቀንስ በማድረግ የገበያ ስርአትን የማገዝ ሚና መጫወት ይችላል፡፡ አስተማማኝ የገንዘብ ስርአት በመዘርጋትና በመጠበቅ የሚኖረዉ ሚና አንደኛዉ የግብይት ወጪን የሚቀንስበት መንገድ ነዉ፡፡

ሁለተኛዉ የግለሰቦችን ሕይወት፤ አካላዊ ደህንነት እና ንብረቶች ከጉልበተኛ እና ካታላይ መጠበቅ ሌላኛዉ መንግስት ይህን ገበያን የማገዝ ሚናዉን የሚወጣበት መንገድ ነዉ፡፡

ሶስተኛ በግለሰቦች ፈቃድ ላይ ለተመሰረተ ዉል ጥበቃ በማድረግ የግብይትን ወጪ ለመቀነስ ይሞክራል፡፡ ይህን ሚናዉን ሲወጣ በዉል ግንኙነት ዉስጥ አንደኛዉ ወገን ሌላኛዉ ወገን በሚሰጠዉ መረጃ ላይ ተመስርቶ ዉል ዉስጥ ቢገባ እና በኋላ የተሰጠዉ መረጃ የዉሸት ከሆነ፤ የዉል ሕግ ለዚህ ተዋዋይ ወገን ጥበቃ ሊያደርግለት ይገባል አግባብነት ባላቸዉ ሁኔታዎች፡፡ ግለሰቦች በሚለዋወጡት መረጃ መተማማን ካልቻሉ፤ የመረጃዎችን ትክክለኛነት አስቀድሞ ለማረጋገጥ የሚያወጡት ወጨ የግብይት ወጪ ተብሎ ይወሰዳል፡፡

አራተኛ በግለሰቦች መካከል አለመግባባት ሲፈጠር፤ አለመግባባታቸዉን በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበት ስርአት በመፍጠር መንገድ የግብይት ወጪን የመቀነስ ሚናዉን ይወጣል፡፡

ሕግ ግብይትን የማበረታት ሚናዉ

የዉል ሕግ ሶስት ዋነኛ ተግባራትን ያከናዉናል፡፡ አንደኛ በሕግ ተፈጻሚ የሚሆኑ ስምምነቶችን ይለያል፡፡ ማለትም ዉሎች ተፈጻሚ ይሆኑ ዘንድ፤ ማሟላት የሚገባቸዉን ቅድመ ሁኔታዎች ይዘረዝራል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊፈርሱ የሚችሉ ዉሎች ምን አይነት እንደሆኑና ዉሎቹን የማፍረሻ ስርአቱንም ይደነግጋል፡፡

ሁለተኛ ቀዳዳ ደፋኝ የሚባሉ ድንጋጌዎችን ያስቀምጣል፡፡ ተዋዋይ ወገኖች ስለግንኙነታቸዉ ለሚነሱ ማንኛቸዉንም ጉዳዮች ላይስማሙ ይችላሉ፡፡ ዉላቸዉ ሙሉ ላይሆን ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ የዉል ሕግ የሚያስቀምጣቸዉ ቀዳዳ ደፋኝ ድንጋጌዎች ግንኙነታቸዉን ይገዛሉ፡፡

ሶስተኛ ዉሎች የሚፈጸሙበትን መንገድ ይደነግጋሉ፡፡ ተዋዋይ ወገኖች በዉል የገቡትን ግዴታ መፈጸም ባይችሉ ለሌላዉ ወገን ሕግ የሚጠዉን መፍትሄዎች ይዘረዝራል፡፡

የዉል ሕግ እነዚህ ተግባራትን በማከናዉን የግብይት ወጪን ለመቀነስ ይሞክራል፡፡ ይህን በማድረግም ግብይትን ያበረታታል፡፡ የግብይት ወጪ ተብሎ ከዚህ በፊት ከተጠቀሱት ወጪዎች መካከል አንደኛዉ የፍለጋ ወጪ ነዉ፡፡ የፍለጋ ወጪ ታማኝ አስተማማኝና ብቃት ያለዉ ተዋዋይ ወገንን ለማግኘት የሚወጣ ወጪ ነዉ፡፡ ተዋዋይ ወገኑ ግዴታዉን በገባዉ ዉል መሰረት ባይፈጽም የሚፈጠርን ኪሳራ ለመቀነስ ሲባል ከመጀመሪያዉ ከታማኝ አስተማማኝና ብቃት ካለዉ ሰዉ ጋር መዋዋልን ይጠይቃል፡፡ ስለተዋዋይ ወገኑ መረጃ መሰብሰብን ይጠይቃል፡፡ ይህ በራሱ ለብዙ ወጪ ይዳርጋል፡፡ የዉል ሕግ ለዉሎች ጥበቃ በማድረግ ተዋዋኝ ወገኖች የተወሰነ ፍተሻ አድርገዉ ዉል እንዲዋዋሉ ያበረታታል፡፡ መሰረታዊ መረጃዎች ከሰበሰብን በቂ ነዉ፤ በኋላ ግለሰቡ ግዴታዉን መፈጸም ቢያቅተዉ የሕግን ሃይል መጠቀም ይቻላል የሚል መልእክት የዉል ሕግ ያስተላልፋል፡፡

ለምሳሌ ካንድ ሰዉ ጋር ዉል ለመፈጸምና ላለመፈጸም በሚደረግ ዉሳኔ ላይ ተዋዋይ ወገኑ ያቀረበዉ መረጃ ወሳኝ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ይህ መረጃ በምን ይታመናል? ዉሸት ቢሆንስ? ዉሸት ነዉ ወይስ እዉነት በሚል ተጨማሪ ምርመራ ማድረግ የግብይት ወጪን ይጨምራል፡፡ ነገር ግን ዉሸት ለመሆኑ የሚያሳይ መረጃ ከሌለና ይህኛዉ ተዋዋይ ወገን በቅን ልቦና በተሰጠዉ መረጃ ተመስርቶ ዉል ቢዋዋልና በመጨረሻ ዉሸት ሆኖ ቢገኝ የዉል ሕግ በቅን ልቦና የተነገረዉን አምኖ ዉል ለተዋዋለዉ ወገን ጥበቃ ያደርጋል፡፡ ይህ የዉል ሕግ እንዴት የፍለጋን ወጪ እንደሚቀንስ ማሳያ ነዉ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የዉል ሕግ የስምምነትንና የድርድርን ወጪ ይቀንሳል፡፡ በድርድር ወቅት ተዋዋይ ወገኖች የሚያደርጉት የዉል ግንኙነታቸዉን አስመልክቶ ለሚነሱ ጥያቄዎች መልስ መስጠት ነዉ፡፡ ለዚህ ደግሞ ድርድር ይደረጋል፡፡ ይህ ራሱን የቻለ ወጪ አለዉ፡፡ ይህን ወጪ ለመቀነስ የዉል ሕግ ቀዳዳ ደፋኝ ድንጋጌዎችን ያስቀምጣል፡፡ መልእክቱም–ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ስምምነት እስከተደረሰ ድርስ ምንም ችግር የለዉ፡፡ ቀዳዶቹ በዉል ሕግ ድንጋጌዎች ይሞላሉ የሚል ነዉ፡፡

በሶስተኛ ደረጃ የዉል ሕግ የስምምነት ማስፈጸሚያ ወጪን ይቀንሳል፡፡ ይህ የግብይት ዋነኛ ወጪዉ ነዉ፡፡ ተዋዋይ ወገኖች በሚያደርጉት ስምምነት መሰረት ግዴታቸዉን እንደሚፈጽሙ እንዴት እርግጠኛ መሆን ይቻላል፡፡ ወይም በስምምነታቸዉ መሰረት ግዴታቸዉን እንዲፈጽሙ እንዴታ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡ ይህ ተዋዋይ ወገኖችን ለብዙ ወጪ ይዳርጋል፡፡ ለምሳሌ ዋስትና የሚሆን ነገርን መያዝ ይጠይቃል፡፡ ወይም የሃይል ተግባርን ዉልን ለማስፈጸም ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የዉል ሕግ ለዉል እዉቅና በመስጠትና በሕጉ መሰረት ለተቋቋመ ዉል ጥበቃ በመስጠት ግለሰቦች ከሃይልና ብዙ ወጪ ካለዉ የማስፈጸሚያ መንገድ ያላቅቃል፡፡

ከላይ እንደተጠቀሰዉ የዉል ሕግ የግብይት ወጪዎችን ለመቀነስ ሶስት አበይት ተግባራትን ያከናዉናል፡፡ ነገር ግን ምን ያህል ወጪን ይቀንሳል የሚለዉ በዉል ሕግ ይዘት ይወሰናል፡፡ ከዚህ በታች ደግሞ የዉል ሕግ የግብይት ወጪን በሚገባ ይቀንስ ዘንድ ሊኖረዉ ስለሚገባ ባህሪዎች ወይም የጥራት መለኪያዎች ያብራራል፡፡

አንደኛ የዉል ሕግ ድንጋጌዎች ግልጽነት ሊኖራቸዉ ይገባል፡፡ ግልጽነታቸዉ ለተገማችነት አስፈላጊ ነዉ፡፡ ይዘቱ ምንም ይሁን ምንም (በተለይ የቀዳዳ ደፋኝ ድንጋጌዎች) ግልጽ እስከሆኑ ድረስ በድንጋጌዎቹ የማይስማሙ ተዋዋይ ወገኖች ግልጽ የሆነ ተቃራኒ ስምምነት በመስማማት ይህን የሕጉን ድንጋጌዎች በእነርሱ የዉል ግንኙነት ተፈጻሚ እንዳይሆኑ ማድረግ ይችላሉ፡፡ እንዲሁም ፍርድ ቤቶች የዉል ሕግን ድንጋጌዎች ተገማች በሆነ መልኩ ሊተረጉሟቸዉና ስራ ላይ ሊያዉሏቸዉ ይገባል፡፡

ሁለተኛ የቀዳዳ ደፋኝ ድንጋጌዎች ይዘትም ምን ያህል ሕጉ የግብይት ወጪን እንደሚቀንስ ይወስነዋል፡፡ ምንም እንኳ የእነዚህ ድንጋጌዎች አላማ የዉል ክፍተትን መሸፈን ቢሆንም የድንጋጌዎቹ ይዘት ብዙ ተዋዋይ ወገኖች የሚመርጧቸዉ አይነት መሆን አለበት፡፡ በተዋዋይ ወገኖች የተለመዱ መሆን አለባቸዉ፡፡ ያለበለዚያ ተዋዋይ ወገኖች የማይፈልጓቸዉ ይሆንና ሌላ አይነት መፍትሄ በድርድርና በስምምነት በግልፅ ዉላቸዉ ላይ እንዲያካትቱ በማድረግ ለተጨማሪ የግብይት ወጪ ይዳርጋቸዋል፡፡

ሶስተኛ አስገዳጅም ሆኑ ቀዳዳ ደፋኝ የሕጉ ድንጋጌዎች ምን ያህል የግብይት ወጪን ይቀንሳሉ የሚለዉ ምን ያህል እቅድን ይደግፋሉ በሚለዉ ይወሰናል፡፡ እቅድ ደግሞ ግምትን መሰረት ያደርጋል፡፡ በመሆኑም ሕጉ የሚጠቀመዉ መለኪያ ተመሳሳይ መረጃ ያለዉ አንድ ሰዉ ሊገምተዉ የሚችለዉ መሆን አለበት፡፡

አራተኛ የዉል ሕግ ብልጣ ብልጥነትን ምን ያህል ይቆጣጠራል የሚለዉ ጉዳይም እንዲሁ ሕጉ ሊቀነስ የሚችለዉን የግብይት ወጪ መጠንን ይወስናል፡፡

አምስተኛ ምንም እንኳ ከዚህ በላይ ያሉትን ነጥቦች ግምት ዉስጥ አስገብቶ የዉል ሕግ ቢቀረጽም የሕግ ስርአቱ በተግባር ለዉል የሚሰጠዉ ጥበቃ የዉል ሕግን ዉጤታማነት ይወስነዋል፡፡ በመሆኑም ዉሎች በፍጥነትና በትንሽ ወጪ በፍርድ ቤት ተፈጸሚነታቸዉ መረጋገጥ መቻል አለበት፡፡ ያለበለዚያ የዉል ሕግን ተማምነዉ ዉልን ማቋቋም ስለማይችሉ ለተለያዩ ወጪዎች ወይም ሕገወጥ ተግባራት ራሳቸዉን ሊያጋልጡ ይችላል፡፡

ትንንሽ ያለመያዣ የሚሰጡ የብድር ዉሎች በማይተዋወቁ ሰዎች መካከል

ከላይ ያስቀመጥኩት የዉል ሕግ ሚና ምን ያህል ትንንሽ ዉሎችን እንደሚመለከት እንይ። በመጀመሪያ ደረጃ የዉል ሕግ ዋናው ሚና በማይተዋወቁ ሰዎች መካከል ምን ያህል የብድር ዉሎች ያለመያዣ እንዲደረጉ ያበረታታል የሚለዉ ጉዳይ እንደሆነ ግልጽ መሆን አለበት። በሚተዋወቁ ሰዎች መካከል የዉል ሕግ ባይኖርም ዉል ይኖራል። እንዲሁም በመያዣ የሚደረግ ዉል ቁጥር ማደግ የዉል ሕግ ስኬት መለኪያ መሆን አይችልም።

የብድር ዉሎች ስል የገንዘብ ብድርን ብቻ አይደለም። እጅ በእጅ ያልተደረጉ ግብይቶች በሙሉ የብድር ዉሎች ሊባሉ ይችላል። ከዚህ አንጻር ምን ያህል እንዲህ አይነት ዉል አስፈላጊ እንደሆነ ግልጽ ነዉ።

ለምሳሌ፥ ጎረቤት ሱቅ ሄደህ የአስር ብር ሳሙና በዱቤ ትወስዳለህ። ባለሱቁ ሳሙናዉን በዱቤ የሰጠህ፥ የዉል ሕግን እና ፍርድ ቤቶችን ተማምኖ አይደለም። ይልቅስ ስለሚያዉቅህ እና ባትከፍል ‘እንዳትሸጥ እንዳትለወጥ’ አድርጎ ስምህን ስለሚያጠፋው ነዉ፥ ወይም ድጋሚ ዱቤ ስለማታገኝ ነዉ። እንዲሁም ምግብ ቤት አስቀድመዉ ሂሳብ የማይቀበሉት፥ አልከፍልም ገንዘብ የለኝም ብትል፥ አንድ ጆንያ ሽንኩርት ስለሚያስከትፉህ ነዉ። በእርግጥ ፓሊስ ጣቢያ ሊወስዱህ ይችላሉ። በወንጀል ሕጋችን ውስልትና ጥፋት ነዉ። ነገር ግን ለአርባ ብር ሽሮ ፓሊስ ጣቢያ ድረስ መድከም አይፈልጉም።

በነገራችን ላይ ሕግ ባጠቃላይ እና የውል ሕግ በተለይ የሚያገለግሉት ለትልልቅ ጥፋቶችና ግብይቶች ብቻ፥ እንዲሁም ኢመደበኛ ስርአቶች ደግሞ ለትንንሽ ግብይቶች ብቻ ነዉ እያልኩኝ አይደለም። የአለም የአልማዝ ገበያን ለምን የአክራሪ አይሁድ እምነት ተከታዮች ብቻ ተቆጣጠሩት የሚለዉን ሲያብራራ አንድ የጥናት ጽሁፍ፥ ምክንያቱን ከግብይት ወጪ ጋር ያይዘዋል። የዚህ እምነት ተከታዮች እርስ በርስ ያላቸዉ ግንኙነቶች አጅግ የጠነከሩ ናቸው። የእምነት ቦታዎቻቸው ባሉበት አካባቢ በአንድ ቦታ ተሰብስበዉ ይኖራሉ። ስለዚህ በተለያዩ ማህበራዊ መስተጋብሮች ይገናኛሉ። እንዲሁም የሃይማኖት አባቶችን በመካከላቸዉ የሚከሰቱ አለመግባባቶችን ለመፍታት ይጠቀማሉ። በዚሁም ዉጤታማ ናቸው። በዚህ ሁኔታ እርስ በርስ የሚያደርጉትን ማንኛዉንም መስተጋብርና የግብይት ወጪዉን፥ መደበኛ ስርአትን በመጠቀም ሊቀንሱ ከሚችሉት በላቀ ሁኔታ፥ የእምነት ስርአታቸዉን በመጠቀም ይቀንሱታል። እርስ በርስ በሚያደርጉት የአልማዝ ግብይት፥ የሻጩና የገዢው ቃል ማሰሪያ ነዉ። ስለዚህ አልማዙ የተባለዉ አይነት ጥራትና መጠን ነዉ ወይ ያለዉ የሚል ተደጋጋሚ ፍተሻ በባለሙያና መሳሪያ ማከናወን የለባቸዉም። እንዲሁም ግብይቶች እጅ በጅ መሆን የለባቸዉም። እጅግ ትልልቅ መጠን ያላቸዉ የብድር ዉሎች ያለመያዣ ይከናወናሉ።

ስለዚህ አጅግ በተለያየ መልኩ በተቆራኙና መልሰዉ መላልሰዉ በሚገናኙ ሰዎች መካከል፥ ሕጉን ተማምነዉ ሳይሆን፥ ግንኙነታቸዉን እና ኢመደበኛ ስርአቶችን ተማምነዉ፥ ትልልቅ ዋጋ ያላቸዉን የብድር ዉሎች ያከናዉናሉ።

ይህ አይሁዶችን ጠቅሟቸው ይሆናል። ነገር ግን እንደ አገር ስናየዉ፥ መያዣ የሌላቸዉ የብድር ዉሎች በእጅጉ በተቆራኙና ደግመው ደጋግመዉ በሚገናኙ ሰዎች መካከል ብቻ የሚደረግ ከሆነ፥ በዛዉ ልክ የታፈኑ የምርትና የልማት አቅሞችና እድሎች አሉ ማለት ነዉ።

ስለዚህ ምን ማድረግ ይገባል? በተለይ ደግሞ ትንንሽ የብድር ዉሎች በማይተዋወቁ ሰዎች መካከል እንዲከናወኑ ለማደረግ ከዉል ሕግ በተጨማሪ ምን አይነት ስርአትን መፍጠር ይቻላል።

አሊባባ

ጃክ ማ ቻይናዊ ቢሊየነር ነዉ። ከእንግሊዘኛ አስተማሪነት ተነስቶ አሁን ስሙ በአለም ደረጃ የሚታወቅ ቱጃር ሆኗል። የሃብት ምንጩ ምንድን ነዉ? የጃክ ማ የሃብት ምንጭ በዋናነት አሊባባ የሚባለዉ ዲጂታል የግብይት ስርአት ነዉ። አሊባባ ሻጭ፥ ገዢ፥ አከፋፋይ፥ አጓዥ፥ አበዳሪ፥ አይደለም። አሊባባ ዲጂታል መንግስት ነዉ ማለት ይችላል። አሊባባ የግብይት ወጪን የሚቀንስ ስርአት ነዉ።

አሊባባ እያሰብከዉ ያልከዉ የግብይት አጋር ምን ያህል ታማኝ እንደሆነ በሰከንዶች ዉስጥ ገምግሞ ይነግርሃል። እንዲሁም የትኛዉ አቅራቢና አጓዥ የበለጠ ልምድና አቅም አንዳለዉ እንዲሁም ያሳውቅሃል። በዚህ የግብይት ስርአት ያሉ ተዋናዮች ያላቸው ስምና ዝና በሚያደርጓት እያንዳንዷ ግብይት ይወሰናል።

ባጭሩ በሚኖርበትና በሚሰሩበት ስፍራ ባይገናኙም፥ እንኳ በዲጂታል ገበያዉ ግን እንዲያ እንዲሆኑ ያደርጋል። በእርግጥ ድጋሚ የማይገናኙ ተዋንያን ቢሆኑም፥ የዛዉ ያህል እንደሆኑ እንዲሰማቸው ያደርጋል።

ባለሱቁ ዱቤ የሚሰጠዉ በሚያወቀውና በሚያምነዉ ሰዉ ነዉ። ዱቤ ጠያቂዉ በእርግጥ ጎረቤት ከሆነ፥ ከዚህ በፊት የወሰዳቸዉን ዱቤዎች ከከፈለ፥ የጠየቀዉን ዱቤ የማግኘት እድሉ ከፍተኛ ነዉ። ስለዚህ ባለሱቁ ቢያንስ ዱቤ ጠያቂው የሚኖርበትን የሚያዉቅና ስለሰዉየው ማህበራዊ ግንኙነቶች የሚያውቅ መሆን አለበት። ባለሱቁ እንዲህ አይነት መረጃዎችን አስመልክቶ ሊያውቀው የሚችለዉ ሰዎች ቁጥር ውስን ነዉ። በሱቁ ዙሪያ ባለዉ ዉስን አካባቢ ብቻ። ከዛ ወሰን ዉጭ ያሉ ሰዎች ቢመጡ ዱቤ የማግኘት እድላቸው ዝቅተኛ ነዉ። እሱ እንቢ ቢላቸውም እንኳን በቅርባቸዉ ሌላ ሱቅ ይኖራል፥ የሚያውቃቸዉ። ነገር ግን ይህም ቢሆን ችግር ነዉ። ምክንያቱም በባለሱቆች መካከል የዱቤ አቅርቦትን አስመልክቶ ዉስን ዉድድር እንዲኖር ያደርጋል። በዚህም የዱቤ መጠን ይቀንሳል፥ የዱቤ ዋጋ ይጨምራል። ይህ የሚጨነግፉ ግብይቶች የጨነገፉ የልማት እድሎችና ያሳያል።

አሊባባ ያደረገዉ ይህን ነዉ። የዱቤ መጠን እንዲጨምር፥ ዋጋዉ እንዲቀንስ አድርጓል። ይህን ያደረገዉ ደግሞ፥ ከምድራዊ መንደር የሰፋ አገራዊ (እንደዉም አለም አቀፋዊ) የዲጂታል መንደር እንዲፈጠርና በዚህ መንደር ዉስጥ ያሉ ተዋንያንን አስመልክቶ የዱቤ ዉሳኔ የሚያግዙ ዉሳኔዎች በግል ትውውቅና በሚኖሩበት ስፍራ ሳይወሰን የሚፈልገዉ ሁሉ እንዲያገኘዉ በማደረግ ነዉ።

ያንተ መኖሪያ ቤትና ሱቁ ያላቹ ርቀት አንድ ሺ ኪሎሜትር ቢሆንም፥ ከዚህ በፊት በአካልም ሆነ በምስል ተያይታቹ ባታዉቁም፥ በዲጂታል ገበያዉ ስትገናኙ ግን ልክ ጎረቤት የሆናቹ ያህል ነዉ። መላልሳቹ የምትገናኙ ሰዎች ናቹ። መላልሰዉ በሚገናኙ ሰዎች፥ ሕግ ባይኖርም፥ የብድር ዉል ይዋዋላሉ። ልብ በሉ ባለሱቁ የሚያበድርህ ባትከፍል ሌላ ጊዜ አላበድርህም በሚል ብቻ ሳይሆን፥ እኔ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም እንዳያበድሩህ፥ እንዳያምኑህ ስምህን አጠፋዋለዉ በሚል ነዉ። ስለዚህ በዲጂታል ገበያዉ፥ ከአንድ ተዋናይ ጋር መልሰህ የመገናኘት እድል ባይኖርህም፥ ከሌሎቹ ተዋንያን ጋር የመገናኘት እድል አለህ። ካንዱ ጋር ባለህ ግንኙነት የተነሳ ታማኝነትህ ሲቀንስ፥ ከሱ ጋር መልሳቹ ባትገናኙም ከሌሎቹ ጋር የመገናኘት እድልህም ይቀንሳል። ስለዚህ፥ የተዋዋልከዉን ዉል ታከብራለህ።

የብድር ዉል ግንኙነቶች በሚተዋወቁና መልሰው መላልሰዉ በሚገናኙ ሰዎች ብቻ እንዳይታጠር በማድረግ፥ አሊባባ የብዙዎችን የምርት አቅምን ነጻ አውጥቷል አሳድጓል። በዚህ የሚጠቀሙት በተለይ ደግሞ ትናንሽ አምራቾችና ትንንሽ ግብይቶች ናቸው። የትናንሽ አምራቾችና ትንንሽ ግብይቶች ገበያ ወሰን አገራዊ ሆኗል። ስለዚህ ዉድድሩም አገራዊ ነዉ።

ኢትዮጲያዊ አሊባባ

በተለያየ አጋጣሚ ከሰዎች ጋር ከተወያየንባቸዉ ነገሮች ዉስጥ አንዱ በገበያ ስርአት ዉስጥ የብሄር ማንነት ቦታ ነዉ። አንዳንድ ድርጅቶች የብሄር ማንነት እንዳላቸዉ ተደርጎ ይወሰዳል። ሰራተኞቻቸው ባብዛኛዉ የአንድ ብሄር ማንነት ያላቸው ናቸው ተብሎ ይወሰዳል። ደንበኞቻቸውም እንዲሁ። በእርግጥ እንደኛ ባለ የኤኮኖሚ አይነትና ደረጃ ይህ የማይገርም ነዉ። እንደዉም እነዚህ የንግድ ድርጅቶችና ነጋዴዎች፥ ብሄርተኝነትን በግልጽ የሚያራምዱ ናቸዉ። የማርኬቲንግ ስትራቴጂ ነዉ። ዉድድርን የመግቻ መንገድ ነዉ። ነገር ግን ይህ ስትራቴጂ ቀጣይነት አይኖረዉም። በዝግታም ቢሆን እድገታቸዉ የሆነ ደረጃ ሲደርስ፥ ይህን ስትራቴጂ ጥለዉ አገራዊ ስትራቴጂ መከተላቸዉ አይቀርም። ከዛም አልፈዉ አህጉራዊና አለማዊ መሆናቸዉ አይቀርም።

የዚህ ለዉጥ ማሳያ የሚሆኑ ድርጅቶች በሃገራችንም እየታዩ ነዉ። ሌላዉን አጨቃጫቂ ነገር ትተን፥ የኢትዮጲያ አየር መንገድን መዉሰድ እንችላለን። የኢትዮጲያ አየር መንገድ የትርፉ ምንጭ የሆኑ የሌሎች ሃገሮችን ዜጎች ረስቶ ሙሉ ለሙሉ ኢትዮጲያዊነትን እየዘመረ መቀጠል አይችልም። ስለዚህ የሌሎች አገር ዜጎችን መቅጠር ጀምሯል። የኤዡያ አገራትን ዜጎች ጨምሮ።

አሁን አለምአቅፍ ገጽታ ያላቸዉ የአሜሪካና የአዉሮፓ አገራት ኩባንያዎች ባንድ ወቅት የአለምአቀፍ ውድድርና ንግድ ተቃዋሚዎች ነበሩ። ብሄራዊነትን የሚያቀነቅኑ ነበር። ነገር ግን ሲያድጉ፥ ከሃገራቸዉ ዉጭ ገበያ ፈለጉ። ከዛም አለምአቀፋዊነትን ማራመድና መግለጥ ጀመሩ።

ስለዚህ አሁን የአንድ ብሄርተኝነትን በተለያየ መልኩ የሚያንጸባርቁ ድርጅቶች እያደጉ ሲሄዱ ህብረብሄርተኝነትን መግለጣቸዉ አይቀርም። ነገር ግን ጊዜን ይወስዳል። በዚህ ሁኔታ ለማደግ ጊዜ ይወስዳል። በዚህ ሁኔታ አገርም ለማደግ ጊዜ ይወስድባታል።

ይህን ጊዜ ማሳጠር ይቻላል። በአካባቢ የታጠረዉን ዉድድርና መስተጋብር፥ በዲጂታል ቴክኖሎጂ አማካይነት አገራዊ በማድረግ፥ እድገትን ማፋጠን ይቻላል። በአካባቢና በጅ በጅ ግብይት የታፈኑ ግብይቶችን እና ዉድድሮችን አገራዊ ማድረግ ይቻላል። አገራዊ የዲጂታል ገበያ መፍጠር ይቻላል።

ይህ አይነት የዲጂታል ገበያ የዉጭ ንግዳችንንም ዘመናዊ በማድረግ፥ በማሳደግ፥ የዉጭ ምንዛሬ ገበያችንን ያሳድጋል። አሁን ባለዉ ሁኔታ ምርቶችን ወደ ዉጭ መላክ የሚቻለዉ በገፍ እና በሌተር ኦፍ ክሬዲት አማካይነት ነዉ። ለምሳሌ አንድ ጆንያ የአክስቴን ሽሮ መላክ ብፈልግ አሁን ያለዉ የግብይት ስርአት ትልቅ ወጪ ያስወጣኛል። ስለዚህ ዉጭ የሚሄድ ሰዉ እየፈለኩ በትንንሹ ለመላክ እገደዳለዉ። በዚህም ምክንያት በመደበኛ ስርአቱ ሊገባ የሚችለዉ የዉጭ ምንዛሬ በኢመደበኛ መንገድ ይስተናገዳል። የዚህ መፍትሄዉ ተጓዦች ወደ ዉጭ ይዘዉት የሚሄዱትን የሽሮና በርበሬ መጠን መገደብ አይደለም። የግብይት ስርአታችን ለትንንሽ ግብይቶች የተመቸ መሆን አለበት።

ዘግይተን መምጣታችን በተወሰነ መልኩ እድለኞች ነን። ምክንያቱም የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀምና ዲጂታል ገበያ በመዘርጋት ይህን ማድረግ እንችላለን። በዚህም ልማታችንን ማፋጠን ብቻ ሳይሆን፥ መስተጋብራችንን ማላቅ እንችላለን።

ሕገመንግስታችን በመግቢያ እንዲህ ይላል፤ “እኛ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች ኢትዮጶያ በምትባለዉ የጋራ አገራችን አብረን ስንኖር በተለያዩ መስኮችና ደረጃዎች ስንገናኝ ነበር••• በዚህም የጋራ ጥቅምና አመለካከት አፍርተናል”።

ይህን ያፈራነዉን የጋራ ጥቅምና አመለካከት ለማሳደግ የግንኙነታችን ደረጃዎችና አይነቶች ማደግ አለባቸዉ። በፍጥነት። ግንኙነቶቻችን በሚተዋወቁ ሰዎች መካከል ወይም በእጅ በጅ ግብይቶች ብቻ መወሰን የለባቸዉም። በዚህ መልኩ እድገታችን ይወሰናል። ምክንያቱም የታፈኑ የምርት አቅሞችና ግንኙነቶች ስለሚኖሩ።

የእድገታችን ምንጩ ነጻ የወጡና እየሰፉ የሚሄዱ የልማት አቅሞችና ግንኙነቶች ሲሆኑ፤ የልማት ድሎቻችንም የታሪክ ቅርስ ከመሆን ያልፋሉ። አልፎ አልፎ ብቅ ብለው ቅርስ ትተዉ ከሚያልፉ አቅሞች መዝለል እንችላለን።

ስለዚህ ኢትዮጲያዊ አሊባባ ያስፈልገናል። እንዴት ይዘርጋ? ማን ይዘርጋዉ? ምን አይነቶ ችግሮች ናቸዉ ያሉት? የሚለዉን በቀጣይ ክፍል።

6 views
  • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.