• Dr. Mulugeta Mengist

አንዳንድ ጉዳዮች ስለ ብሄራዊ ማንነት እና የሕዝብ አስተዳደር

Updated: Nov 17, 2019


የጽሁፉ ዋና ዋና ነጥቦች

 1. ብሄርን መሰረት ያደረገ የፓለቲካ ፓርቲዎች ሕገመንግስታዊ አይደሉም። ሃይማኖትን መሰረት ያደረገ የፓለቲካ ፓርቲ ሕጋዊ አይደለም። ይሄ የሕግ አቋም ለብሄር ፓርቲዎችም መስራት አለበት።

 2. ብሄርን መሰረት ላደረገ የፓለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት ስር እንዲሰድ ያደረገው ኢሕአዴግ ነው። ዋና ተጠያቂውም ራሱ ነው። የማስተካከያ ምሳሌያዊ እርምጃም መውሰድ ያለበት ኢሕአዴግ ነው።

 3. ደርግን ከጣሉ በኋላ፥ የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ራሳቸውን ወደ ክልላዊ ፓርቲ መቀየር ነበረባቸው።

 4. ብሄርን ማእከል ላደረገ አደረጃጀት መቀጠልና ስር መስደድ የታሪክ አሳሪነት ጽንሰሃሳብ አንደኛው ማብራሪያ ቢሆንም፥ ሌሎች ምክንያቶችም አሉ። ለምሳሌ ለሰው ልጆች እኩልነትና ልዩነት ያለማድረግ ሕግመንግስታዊ መርህ ተቋማዊ ማእቀፍ አለመዘርጋቱና ኢሕአዴግም ብሄርን ተኮር ያደረገ ልዩነትን ችግር እንደሌለበት አስራር መተግበሩ፥ የተሳሳቱ ትርክቶችና፥ አሰራሮች ናቸው

 5. የብሄር ማንነት በሕዝብ አስተዳደር ውስጥ ያለው ወቅታዊ ሚና መፈተሽ አለበት። የብሄር ማንነት የግለሰብ ምርጫ እንጂ በድምጽ ብልጫ የሚወሰን መሆን የለበትም

 6. በክልሎች፥ ቀበሌዎች፥ ወረዳዎች መካከል ያለን አስተዳደራዊ ወሰን ለመወሰን ከማንነት ጥያቄ ጋር ማያያዝ። ለምሳሌ ወልቃይት ትግራይ ክልል ይካለል ወይስ አማራ ክልል፥ ከወልቃይት ነዋሪዎች ማንነት ጋር አይያያዝም። የወልቃይት ነዋሪ እያንዳንዱ የብሄር ማንነቱን የመወሰን ነጻነቱ የራሱ ነው። ይሄ በድምጽ ብልጫም ሆነ በጥናት አይወሰንም። አብዛኛው የወልቃይት ነዋሪ አማራ ነኝ ብሎ ቢወስን፥ የግድ አማራ ክልል መካለል አለበት ማለት አይደለም። እንዲሁም የአብዛኛው የወልቃይት ሕዝብ ትግሬ ነኝ ብሎ ቢወስን፥ የግድ ትግራይ ክልል መካከል አለበት ማለት አይደለም። ይሄ ሁሉ የመጣው የክልልን ባለቤትነት ለአንድ ብሄር የመስጠት፥ ብሄር ተኮር አደረጃጀት፥ እና የመሳሰሉት ናቸው። እንዲሁም የቡድን መብትን ከቦታ ጋር የማያያዝ አስራር ተጠቃሽ ነው። ማንም ኢትዮጲያዊ የብሄር ማንነቱ ምንም ይሁን ምን ሕገመንግስታዊ መብቱ በየትም ክልል ከተከበረለት (ሊከበርለትም ይገባል) ይሄ ጉዳይ ዋጋ አልባ ይሆን ነበር። ነገር ግን በቅርቡ እንኳን ስለ አዲስ አበባና ልዩ ጥቅም የወጣው ረቂቅ ሕግ፥ በአዲስ አበባ ከተማ በኦሮምኛ ለመማር ከልዩ ጥቅም ጋር ማያያዝ የዚህ መገለጫ ነው።

 7. የብሔር ተኮር የፓለቲካ አደረጃጀት፥ አዲስ አበባን፥ ድሬዳዋን፥ እና ሀረር ከተማን የኢህአዲግ አባል ድርጅቶች በኮታ ተከፋፍለው እንዲያስተዳደሩ አድርጓል። ይህ የከተማዋን ነዋሪዎች ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብቶች የሚጥስ ነው።

 8. ባህልን እና ቋንቋን አስመልክቶ ያለን ግንዛቤ በጭቆና እና የነጻነት ትግል ትርክቶች የተበረዘ ስለሆነ በመሰረቱ መሳሪያ እና ማህበራዊ የሆነን ጉዳይ እንደ ተፈጥሯዊና ግብ መውሰዳችን ሌላው ምክንያት ነው።

 9. የፌዴራል መንግስቱ በዚህ ረገድ ሊጫወት የሚገባውን ሚና አልተወጣም። ህወሃት የትግሬ ፓርቲ ሳይሆን የትግራይ ክልል ፓርቲ ነው። በክልሉ ያሉ ነዋሪዎች ትግሬ ሆኑም አልሆኑም ግዴታ አለበት። ከክልሉ ውጪ ላሉ ትግሬዎች ያለበት ሃላፊነት፥ ከክልሉ ውጭ ለሚኖሩ አማራዎች ካለበት ሃላፊነት አይለይም። እንደሁም ከክልሉ ውጭ ከሚኖሩ ትግሬዎች የበለጠ ጌዴታ ያለበት በክልሉ ለሚኖሩ ትግሬ ላልሆኑ ነዋሪዎች ነው። በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል ያሉ ኢትዮጲያኖች በብሄር ማንነታቸው ልዩነት እንዳይደረግባቸው የማረጋገጥ ሃላፊነት የፌዴራል መንግስቱ ሆኖ እያለ፥ በዚህና በተያያዥ ጉዳዮች ምንም አለመስራቱ ሌላው ምክንያት ነው።

 10. ለዚህ ሁሉ ሕገመንግስቱ ምን ያህል ችግሮች አሉበት ለሚለው ጥያቄ፥ ከላይ እንደተገለጸው ዋናው ችግሩ ሕገመንግስቱ ሳይሆን፥ ሕገመንግስቱን የተራድንበትና የተገበርንበት መንገድ ነው። ነገር ግን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የተሰጠው በአንድ አካባቢ ለሚኖሩ ነዋሪዎች ሳይሆን ለብሄርና ብሄረሰቦች መሆኑ፥ እና የክልሎቹ አስያየም፥ የባለቤትነት መንፈስን በሚያንጸባርቅ መልኩ መሆኑ፥ እንደ ችግር ያለባቸው ድንጋጌዎች ሊጠቀስ ቢችልም፥ ዋናው ግን ከሕገመንግስቱ ሳይሆን ከሕገመንግስቱ ውጭ ባሉ ምክንያቶች የሚመጣ ችግር ነው።

 11. ይህ ማለት ግን ብሄርን መሰረት ያደረገ አደረጃጀት ፈጽሞ መፈቀድ የለበትም ማለት አይደለም። እንደውም ቋንቋን፥ ባህልን፥ ታሪክን ለማጥናት፥ ለመጠበቅ፥ለማስተዋወቅ ማህበራት ሊደራጁ ይችላሉ። ነገር ግን ይህን ጉዳይ ፈጽሞ ለግለሰቦች ብቻ ከመተው ይልቅ፥ የፌዴራል መንግስቱ ራሱ በገንዘብና በሌሎች መንገዶች እንዲህ አይነት ማህበራት እንዲደራጁና እንዲንቀሳቀሱ መፍቀድ አለበት።

መግቢያ

የፓለቲካ ፓርቲ፥ የፓለቲካ ስልጣንን ይዞ ሕዝብን ለማስተዳደር አላማን ይዞ፥ በፓለቲካ እንቅስቃሴዎች (ለምሳሌ በምርጫ) የሚካፈል ነው። ሊያስተዳድረው የሚሻው ሕዝብ፤ በሃገር ደረጃ ወይም በክልል ወይም በከተማ ሊሆን ይችላል። በሃገራችን ሃይማኖትን ማዕከል ያደረገ የፓለቲካ ፓርቲ ማቋቋም ክልክል ነው። ይህ የሆነው መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ ስለመሆናቸው በሕገመንግስቱ ላይ በመደንገጉ ነው። ለምን ይህ ድንጋጌ አስፈለገ የሚለውን ማየት ጠቃሚ ነው። መንግስት ሕዝብ አስተዳዳሪ ነው። የሚያስተዳድረው ሕዝብ ደግሞ የተለያየ እምነትና ሃይማኖትን ይከተላል። እንዲሁም እያንዳንዱ ዜጋ የእምነት ነጻነት አለው፥ ሊኖረው ይገባል። መንግስት ስራዉን የሚያከናውነው ከግብር ከፋዩ በሚሰበሰብ ገንዘብ ነው። መንግስት ማንኛውንም አይነት እምነትና ሃይማኖት የመንግስት ስልጣንን በመጠቀም ሊደግፍም ሆነ ሊያደናቅፍ ስለማያስፈልግ፥ መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ መሆን እንዳለባቸው ተደንግጓል። በዚህም የተነሳ ሃይማኖትን ማዕከል ያደረገ የፓለቲካ ፓርቲም ማደራጀት ተከልክሏል።  ይህ እንዲህ ከሆነ ለምንድን ነው ብሄርን መሰረት ያደረገ የፓለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት የማይከለከለው? ይህ ጥያቄ በበቂ ሁኔታ መልስ ያገኘ አይመስለኝም።

ደርግን በትጥቅ ትግል ለመጣል በተደረገው ትግል፥ ብሄርን ማዕከል ያደረጉ የነጻነት ድርጅቶች ተሳትፈዋል። መደብን መሰረት ያደረጉ ድርጅቶች ቢኖሩም፥ ከአንዱ በስተቀር ይህ ነዉ የሚባል ትግልና ለውጥ ሳያካሂዱና ሳይታገሉ ተበታትነዋል። ብሔርን መሰረት ላደረገ የፓለቲካ አደረጃጀት የሚቀርበው ምክንያት የነበሩ አገዛዞች ጭቆናቸውን ብሔርን መሰረት አድርገው ማካሄዳቸው ነው። ባጭሩ የብሔር ጭቆና መኖር ነው ምክንያቱ። የኢህአዴግ አንዱ አካል የነበረውና በኋላ ስሙን ወደ ብአዴን የቀየረው ድርጅት ትግሉን ያከናወነው እንደ የአማራ ድርጅት አይደለም። መደብን ማዕከል ያደረገና ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል በመጡ ታጋዮች ነው። ከድል በኋላ ራሱን ብአዴን በማለት የአማራ ድርጅትነቱን አውጇል።

“በእርግጥ በታሪክ የብሔር ጭቆና ነበር?” የሚለው ጥያቄ አሁንም የሚያጨቃጭቅ ነው። ኢሕአዴግ መሪ አቋሙ የብሔር ጭቆና ነበር የሚል ሲሆን፥ ሌሎች ድርጅቶች ከዚህ የተለየ ሃሳብ ያቀርባሉ። አሁንም በተለያየ ጊዜና መልኩ ይህ ጉዳይ የሚያጨቃጭቅ መሆኑን ቀጥሏል። በቅርቡ እንኳን የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች መሪዎች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በመካከላቸው ልዩነት እንዳለ ግልጽ ሆኗል። አንዱ ነበር፥ ነገር ግን እንዳይመለስ ሆኖ ከትሟል ይላል። ሌላው ደግሞ አልነበረም፥ የነበረው የመደብ ጭቆና ነው፥ ብሄራዊ ጭቆና የሚለው ትርክት የትግል ታክቲክ ነበር ይላል። ይህን ጥያቄ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍታት አይቻልምም፥ አይገባምም። ይህን ጉዳይ ለታሪክ ባለሙያዎች የማያቋርጥ ሙግት መተው ይገባል። እነሱም ቢሆኑ ባንድ መጽሃፍ፥ ባንድ ጉባኤ፥ ወይም ባንድ ጧት አንድ ዛፍ ስር ተሰብስበው አይፈቱትም። ታሪክ እና የታሪክ ትርክት እየተለወጠ ይሄዳል፥ መሄድም አለበት። ታሪክ መረጃን የሚተነትን፥ የሚያደራጅና፥ የሚተረጉም፥ የሚተርክ ነው። ነገር ግን የታሪክ መረጃዎች ተሟልተው አይገኙም። በተለይ ደግሞ ወደ ኋላ በሄድን ቁጥር የመረጃው ተደራሽነትና ታማኝነት እየቀነስ ይሄዳል። እንዲሁም የታሪክ መረጃዎቹን የጻፉት ሰዎች ገለልተኛ ላይሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ የተሻለ መረጃ እየተገኘ ሲሄድና ቴክኖሎጂ እያደገ ሲሄድ፥ ከዚህ በፊት የተሰነዘሩ የታሪክ መላምቶች እየተለወጡ የመሄድ እድል አላቸው።

ባንድ ነገር ላይ ግን መስማማት እንችላለን። የአሁኗ ሃገራችን በፍጹም የብሄር ጭቆናን የማታስተናግድ መሆን እንዳለባት መስማማት እንችላለን። ይህም በሕገመንግስታችን የፓለቲካ ውሳኔ አግኝቷል። ከመግቢያው ጀምሮ የተለያዩ ባህሎች፥ ቋንቋዎች፥ ሃሳቦች፥ እምነቶች ያለምንም ልዩነት መራመድ የምንገነባው የፓለቲካና የኤኮኖሚ አንድነት መሰረት እንደሆነ ተገልጿል። እንዲሁም በሕገመንግስቱ ውስጥ ይህን የሚያረጋግጡ ድንጋጌዎች እናገኛለን። ለምሳሌ፤ ማንም ሰው በብሔሩ፥ በቋንቋው፥ መሰረት ልዩነት እንደማይደረግበትና ሰዎች ሁሉ እኩል እንደሆነ ተገልጿል።

ሕገመንግስቱ ብሔራዊ ጭቆና ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ ግልጽ ካደረገ ለምንድን ነው አሁንም ብሔርና ብሔረሰብ ባገራችን የፓለቲካ ስርአት ትልቅ ቦታ ያለው ትርክትና የፓለቲካ መደራጃ ማዕከል የሆነው? ይህ የሆነበት ምክንያት ብዙ ነው። ሶስት ዋና ዋና ምክንያቶችን መለየት ይቻላል።

አንደኛው፤ የብሔር ትርክትና የመደራጃ ማእከልነቱ ለረጅም ጊዜ በሃገራችን የተለመደ ነበር። ኢሕአዴግ ራሱ በዚህ ትርክትና ይህን ማእከል ባደረገ አደረጃጀት ነው ለስልጣን የበቃው። የዚህ ትርክት መቀጠልን ሊያብራራልን የሚችለው አንደኛው የታሪክ አሳሪነት ጽንሰሃሳብ ነው። ሁለተኛ፥ ሕገመንግስቱ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የብሔር ብሔረሰብ መብት አድርጎ ማስቀመጡና “ብሔር ብሔረሰብን እና ሕዝብን” የተረጎመበት አግባብ ነው። ሶስተኛ፥ ክልሎችን፥ የፌዴራል መንግስቱን፥ እና የሕገመንግስቱን ባለቤትነት አስመልክቶ ያለው የተሳሳተ ግንዛቤ፥ ትርክት፥ እና አሰራር ነው። አራተኛ፥ በሕገመንግስቱ የተቀመጡ የፓለቲካ ድንጋጌዎችን ተቋማዊ ቅርጽ ለመስጠት አጥጋቢ ስራ አለመሰራቱ ነው። አምስተኛ፥ የፌዴራል መንግስቱ ችላ ያላቸው ሃላፊነቶችና ስልጣኖች።

ስለ ባህልና ቋንቋ አንዳንድ ጠቅላላ ጉዳዮች

ባህልና ቋንቋ የትብብርና ግብይት መሰረቶች ሆነው ያገልግላሉ። ባህልና ቋንቋ የትዉልዶችን ልምድና ታሪክ በመያዝ፥ ልምድን እና ታሪክን ከትውልድ ወደ ትውልድ ለማስተላለፍ ይጠቅማሉ። ባህልና ቋንቋ የአገዛዝ፥ የጭቆና መሰረቶች ይሆናሉ። እንዲሁም ከጭቆናና ጨቋኝ ጋር የሚደረግ የነጻነትና የዴሞክራሲ ትግል ባህልና ቋንቋን ማእከል ያደርጋሉ።

የሰው ልጅ በተፈጥሮው ብቻውን መኖር የማይችል፥ ማህበራዊ ፍጡር ነው። ስለዚህ የባሕል ተገዢነታችን የተፈጥሮ ነው ሊባል ይችላል። በተመሳሳይ መልኩ ቋንቋ እንድንለምድ ሆነን ነው የተፈጠርነው። ቋንቋን ለመልመድ የሚያስፈልጉ አካላዊ ቅርጾችን ይዘናል፥ ድምጽ ማውጣት፥ ማስታወስ፥ ማስላሰል የሚያስችለን አካላዊ ብቃት ይዘን ተፈጥረናል።

ነገር ግን “የኔ” የምለው ቋንቋ እና ባህል ምን ያህል “የኔ” ነው የሚለውን ማየት ይገባል። “የኔ” ሲባል “አብሮኝ የተፈጠረ” ማለት  ከሆነ፥ ምንም አይነት ባህልና ቋንቋ የኔ አይደለም። ነገር ግን በቀን ተቀን የቋንቋ አጠቃቀማችን “የኔ” ማለት አብሮኝ የተፈጠረ ማለት አይደለም። ለምሳሌ ይሄ እርሳስ የኔ ነው ስል፥ አብሮኝ ተፈጥሯል እያልሁ አይደለም። “ማንም ያለእኔ ፈቃድ ሊጠቀምበት አይችልም። እኔ እና እኔ የፈቀድኩለት ብቻ ነው ሊጠቀምበት የሚችለው” ማለቴ ነው። በሁለተኛውም አግባብ ቢሆን፥ ማንኛውንም ቋንቋና ባህል የእኔ ነው ማለት አግባብነት የለውም። ቋንቋና ባህል ትርጉም የሚኖረው በግለሰብ ደረጃ ሳይሆን በማህበረሰብ ደረጃ ነው። በመሆኑም የኔ ሳይሆን የማህበረሰቡ ነው። በሕይወት ያሉና የሌሉ የዚያን ማህበረሰብ አባላት በጋራ ያዳበሩት ባህልና ቋንቋ ነው። በመሆኑም ብሄራዊ ማንነት (ቋንቋና ባህል) የግለሰብ ማንነት አይደለም። የማህበረሰብ ማንነት እንጂ።

ሌላው የባህልና ቋንቋ መገለጫ ተለዋዋጭ መሆኑ ነው። በሰዎች እድገት፥ መስተጋብር፥ እና ማህበረሰባዊ አወቃቀር የተነሳ የባህልና ቋንቋ ይዘት በጊዜና በቦታ እየተቀያየረ ይሄዳል። ቋንቋን ለማሳያ መውሰድ እንችላለን። ብዙ ቋንቋዎች ሶስት አይነት እውነታዎችን በሚገባ ይገልጻሉ። ተጨባጭ እውነታዎች። የሚጨበጡ የሚታዩ የሚዳሰሱ እዉነታዎች። እውነትነታቸው ሊረጋገጥ የሚችሉ እዉነታዎች። ሁለተኛው አይነት እውነት፥ ግላዊና ተጨባጭ ያልሆነ እውነታ ነው። ስሜትና ፍላጎት። ሶስተኛው አይነት እውነት፥ የጋርዮሽ ተጨባጭ ያልሆነ ነው። አንድ ማህበረሰብ እውነት ነው በሚል በስምምነት የተቀበለው። ለምሳሌ ድርጅቶች ሰው ናቸው የሚለው እውነት።

ዘመናዊ የሚባሉ ቋንቋዎች እነዚህን ሶስት እውነታዎች የመግለጽ ብቃት አላቸው። ነገር ግን ሁሉም ቋንቋዎች እንደዛ ናቸው ማለት አይደለም። ለምሳሌ በአማዞን ደን ከሌሎች ማህበረሰቦች ተነጥለው የሚኖሩ ማህበረሰብ ጋር አብሮ በመኖር ቋንቋቸውን ለማጥናት የሞከረ አንድ ተመራማሪ፥ የዚህ ማህበረሰብ ቋንቋ ባብዛኛው በተጨባጭ እውነታ ላይ ብቻ የሚያጠነጥን እንደሆነ በጥናቱ ደርሶበታል። ለምሳሌ እኛ አረንጓዴ የምንለውን ቀለም፥ እነሱ ቅጠልማ ይሉታል። አንድ ቋንቋ ሶስቱን እውነታዎች የመግለጽ የብቃት ደረጃው በማህበረሰቡ የእድገት ደረጃ ይወሰናል ወይም ይገለጻል። የሰው ልጅ የእድገት ደረጃን ከሚወስኑት ነገሮች አንደኛው ለሰፊ ትብብር መሰረቶች የሆኑ ሰውስሪት የጋርዮሽ እውነታዎች ናቸው። የጋርዮሽ እውነታዎች በሰዉ ልጅ መካከል እጅግ ሰፊ ትብብርና ግብይት እንዲኖር ያግዛሉ። ሃሪሪ የሚባል አንድ ፀሃፊ፥ የሰዉ ልጅ ኑሮ የሚሻሻለው በአማካይ የሰዉ ልጅ አይምሯዊ ብቃት ከሌሎች አንሰሳት መብለጡ ሳይሆን ቋንቋን መጠቀሙና ቋንቋው የጋርዮሽ እዉነታን  ለመግለጽ ያለው ብቃት መጠነስፊ ትብብር መፍጠር መቻሉ ነዉ። በመሆኑም የኑሮ ለውጥን ተከትሎ ወይም አስቀድሞ ቋንቋ ለውጥ ያደርጋል። እንዲሁም የቋንቋው ይዘትና ለውጥ ማህበረሰቡ የኖረበት ከባቢ ሁኔታ ይወስነዋል። ባህልም እንዲሁ ነው።

በተጨማሪ፤ የቋንቋና ባህል ይዘት፤ በአንድ ወቅት በአንድ ማህበረሰብ የፓለቲካና ኤኮኖሚ ሃይል የበላይነት ባለው መደብ ወይም ቡድን ጥቅም ይወሰናል። ቋንቋውና ባህሉ የዚህን መደብ ጥቅም የሚያስከብር ይሆናል። የፓለቲካና ኤኮኖሚ ሃይሉ በሁሉም የማህበረሰቡ አባሎች የተሰራጨና የተከፋፈለ ከሆነ፥ ቋንቋውና ባህሉም ሁሉንም የመጠቀም እድሉ ከፍተኛ ነው።


ባህልና ቋንቋ ለምን አስፈለገ?

ቋንቋ ሲጀመር በሰዎች መካከል የልምድና የመረጃ ልዉውጥ እንዲኖር በማድረግ እያንዳንዱ ግለሰብና ትውልድ ኑሮን ሰርክ እንደ አዲስ እንዳይጀምር በማድረግና ኑሮውን በሌሎች ግለሰቦችና ልምዶች የራሱን ልምድ በመደመር እንዲመራ በማገዝ የሰው ልጅን የኑሮ ለውጥ አግዟል። ያግዛል። እንጆሬ ለቅሜ ስመጣ ያደፈጠ ነብር ካየሁ፥ ለሌሎች ሰዎች መረጃውን በማቀበል ህይወታቸውን መታደግ እችላለሁ። እንዲሁም አንድ ፍሬ በልቼ ቀኑን ሙሉ ወደታች ካለኝ፥ ይህን መረጃ ለሌሎች ለመስጠት ቋንቋ ይረዳኛል። እንዲሁም በስዎች መካከል የሚደረጉ ዘርፈብዙ መስተጋብሮችን የማሳለጥ ሚናን ባህል ይጫወታል። የግለሰቦች ውሳኔ፥ ባህሪ ተገማች እንዲሆን በማስቻል፥ መስተጋብሮችን ትብብሮችን ያግዛል። በዚህ ረገድ ባህል የዘመናዊ ሕግ የቀደመ ቅርጽ ነው ሊባል ይችላል። ሕግ ማእከላዊ በሆነ መንገድ የሚደነገግና የሚከበር ቢሆንም፥ ባህል ግን ባልተማከለ መንገድ ከትውልድ ትውልድ እየተለወጠ የሚሄድና ማእከላዊ ባልሆነ መንገድ የሚፈጠርና የሚከበር ስርአት ነው። እንዲሁም በአንድ ማህበረሰብ አባሎች መካከል አንድነትን ለመፍጠር የሚያስችልና አንድነትን የሚገልጽ ነው።

ከዚህ በላይ ያስቀመጥኩት የባህልና ቋንቋ እይታ፥ ፍሬ ተኮር ነው። ለባህልና ቋንቋ ዋጋ የሚሰጠው ጠቃሚ ፍሬ እስካፈሩ ድረስ ነው፥ እይታው። ነገር ግን በታሪክና በዘመኑ ስለባህልና ቋንቋ ያለን እይታ፥ በፍሬ ብቻ የታጠረ አይደለም። ስሜት ይቀላቀልበታል። እንዲህ የሆነበት ምክንያት ባህልና ቋንቋ የጭቆና እና የነጻነት ትግል መሰረት ሆነው በታሪክ ማገልገላቸው ነው።

የፓለቲካ እኩልነት ባልሰፈነበት ማህበረሰብ፤ ቋንቋና ባህል በፓለቲካ ሃይል የበላይነት ያገኘውን የማህበረሰብ መደብ ጥቅም ያራምዳል። ወንዶች የበላይ በሆኑበት ማህበረሰብ፥ ባህልና ቋንቋ የወንዶችን ጥቅም ያራምዳል። ቄሶች የበላይ በሆኑበት ማህበረሰብ፥ ባህልና ቋንቋ የቄሶችን ጥቅም ያራምዳል።

በአንድ ማህበረሰብ የፓለቲካና የኤኮኖሚ የበላይነት ያገኘው አንድ መደብ፥ የፓለቲካ እና የኤኮኖሚ የበላይነቱን ለማስፋት ሲል በቅርብ የሚገኝን የተለየ ቋንቋና ባህል ያለውን ሌላ ማህበረሰብ መውረር ይፈልጋል።  ለዚህ ደግሞ የገዢ ቡድኑን አባላት ብቻ ሳይሆን የሚፈልገው፥ የተገዢ የማህበረሰቡን አባላትንም ድጋፍ ማግኘት ይኖርበታል። ነገር ግን በአንድ ማህበረሰብ ዉስጥ ያሉ የተገዢውና የገዢው መደብ ጥቅሞች (ተጨባጭ) አንድ ላይሆኑ ይችላሉ። ገዢው መደብ ተገዢውን ለወረራ በጉልበትና በጥቅም ማሰለፍ ቢችልም፥ ይህ ግን ብቻውን በቂ አይደለም። ስለዚህ ቋንቋን እና ባህልን እንደማደራጃ ይጠቀማል። አንድ ባህል፥ ቋንቋ እንዳላቸውና ሌላውን ማህበረሰብ መውረር የጋራ ጥቅም እንደሆነ አድርጎ ይተርከዋል። የእነሱ ባህልና ቋንቋ የበላይ እንደሆነ እና ይህን በተግባር ማረጋገጥ እንዳለባቸው ይሰብካል። በወረራዉ ከተሳካለት፤ የተወረረው ማህበረሰብን ቋንቋና ባህል የማፈን ስራ የመጀመሪያው ያደርገዋል።

ቋንቋቸውን መጠቀም፥ ባህላቸውን ማራመድ ያልቻሉት እነዚህ ሰዎች በዚህ የሚያጡት የኤኮኖሚና የፓለቲካ ጥቅም ይኖራል። በዚህ ሂደት በቋንቋቸውና በባህላቸው የተነሳ ጭቆና እና ወረራ የደረሰባቸው ሰዎች የነጻነት ትግላቸውን በተለያየ መልኩ ያካሂዳሉ። በዚህ የነጻነት ትግል መሰረት የታፈነው ቋንቋና ባህል ነው። የተለያዩ የነጻነት ቡድኖች የተለያየ የቋንቋና ባህል ትርክት ያራምዳሉ። አንዳንዱ ቋንቋቸውና ባህላቸው ከሌላው ጋር እኩል እንደሆነ እና እኩል እውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ ይተርካል። ሌላው፥ ቋንቋቸውና ባህላቸው ከሌሎች እንደሚበልጥ ይተርካል።

ጭቆና፥ የነጻነት ትግል፥ እና የሰው ልጅ ተፈጥሮ ባንድ ላይ ተደምረው፥ ለባህላችን እና ቋንቋችን ፍሬ ተኮር ያልሆነ እና ስሜታዊ ትርክት እንድንሰጥ ያደርገናል። በዚህ ትርክት መሰረት ቋንቋና ባህል ፍሬ ኖራቸው አልኖራቸው በራሳቸው ዋጋ ያላቸው ያስመስላቸዋል። በመሆኑም፥ ጥቂቶችን ብቻ የሚጠቅም ባህል ያለምንም ጥያቄ እንዲቀጥል ይሆናል። እንዲሁም አንድን ባህልና ቋንቋን የምናይበት መነጽር በመውደድና መጥላት እንዲገለጽ ያደርጋል።

በመጽሃፍ ቅዱስ ካለ ታሪክ መረዳት የምንችለው፥ የሰው ልጆች በትብብር ሊሰሩት የሚችሉትን ነገር አስቀድሞ አውቆ ፈጣሪ ቋንቋቸውን እንደለያየው ነው። የቋንቋ መለያየት የመተባበር እድልን እና በመተባበር የሚበዛውን የግለሰቦች አቅም እንደሚገድብ ከዚህ ማየት እንችላለን። ከዚህ በመነሳት ይመስላል፥ የተለያዩ ማህበረሰቦችን በአንድ ማእከላዊ አስተዳደር በማቀፍ አገር ለመገንባት የሞከሩ፥ የቋንቋን ብዝሃነት በአንድ ቋንቋ በሃይል ለመተካት የሞከሩት። አንዳንዶቹ ተሳክቶላቸዋል፥ የቋንቋ አንድነትን በመፍጠር። ነገር ግን ይህ ፕሮጀክት ተገቢ አይደለም። በሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች። አንደኛ ሃይልን መጠቀም ስለሚጠይቅ። ሁለተኛ፥ አንድ ቋንቋና ባህል በጠፋ ቁጥር አብሮ የሚጠፋ የትውልዶች ታሪክና ልምድ ስለሚኖር። ሶስተኛ፤ ቋንቋቸውና ባህላቸው የታፈነባቸው ህዝቦች፥ አዲሱን ቋንቋና ባህል መሰረት በሚደረጉ ማህበራዊ፥ ኤኮኖሚያዊና፥ ፓለቲካዊ እንቅስቃሴዎች እንዲበለጡ ያደርጋል። ፍትሃዊ ያልሆነ ተጠቃሚነት ከትዉልድ ትዉልድ እየባሰ ይሄዳል።

የመተባበር እድልን ለመጨመር የግድ አንድ ቋንቋ በቀላጤ መፍጠር አይገባንም። ዋናው ጉዳይ አንድ ቋንቋ መኖሩ ሳይሆን፥ መግባባቱ ነው። ተርጓሚዎች፥ ደላሎችና፥ ብዙ ቋንቋ ተናጋሪነት የመተባበር እድልን ይፈጥራሉ። እውቀትን እና ልምድን ይጨምራሉ። ነገር ግን ይህም ቢሆን ስለባህልና ቋንቋ ባለን እይታ ይወሰናል። የአንድ ማህበረሰብን ባህል እና ቋንቋ በራሳቸው ዋጋ ያላቸው ተፈጥሯዊ ኹነቶች፥ በመዉደድና መጥላት የምንገልጻቸው አድርጎ መውሰድ፤ ቋንቋና ባህል የትብብር እንቅፋት እንዲሆኑ ያደርጋል።

ሕገመንግስቱ ስለብዝሃነትና አንድነት

የሕገመንግስቱ ባለቤቶች የኢትዮጲያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ናቸው። ሕገመንግስቱን ያጸደቁት የእነርሱ ተወካዮች ናቸው። በመሆኑም ሕገመንግስቱ የኢትዮጲያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ፈቃድና ፍላጎት እንደሆነ መወሰድ ይቻላል። የሕገመንግስቱን መግቢያ ለውይይታችን መግቢያ አድርገን መውሰድ እንችላለን።

እኛ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦች፥ ሕዝቦች፤

በሀገራችን ኢትዮጲያ ዉስጥ ዘላቂ ሰላም፥ ዋስትና ያለው ዴሞክራሲ እንዲሰፍን፥ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገታችን እንዲፋጠን፥ የራሳችንን ዕድል በራሳችን የመወሰን መብታችንን ተጠቅመን፥ በነጻ ፍላጎታችን፥ በሕግ የበላይነት እና በራሳችን ፈቃድ ላይ የተመሰረተ አንድ የፓለቲካ ማኅበረሰብ በጋራ ለመገንባት ቆርጠን በመነሳት፤

ይህን አላማ ከግብ ለማድረስ፥ የግለሰብና የብሔር/ብሔረሰብ መሰረታዊ መብቶች መከበራቸው፥ የፆታ እኩልነት መረጋገጡ፥ ባሕሎችና ሃይማኖቶች ካለአንዳች ልዩነት እንዲራመዱ የማድረጉ አስፈላጊነት ጽኑ እምነታችን በመሆኑ፤

ኢትዮጲያ ሀገራችን የየራሳችን አኩሪ ባሕል ያለን፥ የየራሳችን መልክዓምድራዊ አስፋፈር የነበረንና ያለን፥ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በተለያዩ መስኮችን የግንኙነት ደረጃዎች ተሳስርን የኖርንባትና የምንኖርባት ሀገር በመሆንዋ፥ ያፈራነው የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን ብለን ስለምናምን፤

መጪዉ የጋራ ዕድላችን መመስረት ያለበት የታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል፤

ጥቅማችንን፥ መብታችን እና ነጻነታችንን በጋራና በተደጋጋፊነት ለማሳደግ አንድ የኤኮኖሚ ማኅበረሰብ የመገንባቱን አስፈላጊነት በማመን፤

በትግላችንን እና በከፈልነው መስዋዕትንት የተገኘውን ዴሞክራሲና ሰላም ዘላቂነቱን ለማረጋገጥ፤

ይህ ሕገመንግሥት ከዚህ በላይ ለገላጽናቸው ዓላማዎችና እምነቶች ማሰሪያ እንዲሆነን እንዲወክሉን መርጠን በላክናቸው ተወካዮቻችን አማካይነት ••• አጽድቀነዋል።

ሕገመንግሥቱ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረስቦችና፥ ሕዝቦች፤ ፈቃድ፥ ፍላጎት፥ እምነትና፥ አላማ፥ መግለጫ ነው። መግቢያዉ እንደ ጉዞ ወግና ፍኖተ ካርታ ተፅፏል። ትናንትን፥ ዛሬን፥ እና ነገን ይገልፃል። አንድን ወንዝ በጋራ ተሻግረውና ለአፍታ ካረፉ በኋላ፤ ስለቀጣዩ አድራሻና የጉዞዉ ስትራቴጂዎች በመግቢያው ያስቀምጣሉ፤ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና፥ ሕዝቦች።

ወንዙን ሳይሻገሩ በፊት የነበረውን ሁኔታ እንደሚከተለው ገልጸውታል። “የተለያየ አኩሪ ባህል ነበረን፥ የተለያየ መልክዓ ምድራዊ አስፋፈር ነበረን። ነገር ግን ኢትዮጲያ በምትባለው የጋራ ሀገራችን፤ አብረን እንኖር ነበር”።

አብሮ መኖራቸው በምን ይገለጻል? በተለያዩ መስኮችና ደረጃዎች በነበራቸው አስተሳሳሪ ግንኙነቶች ይገለጻል። “በዚህ ግንኝነትም ያፈራነው የጋራ ጥቅምና አመለካከት አለን” ብለው እንደሚያምኑም ይገልጻሉ። ልብ ሊባል የሚገባው፤ በተለያዩ መስኮችና ደረጃዎች የነበራቸው ግንኙነቶች የተወሰነው በሰፈሩበት አካባቢ፤ በተለይም በወሰን አካባቢዎችና በከተሞች ነበር። በእነዚህ አካባቢዎች የነበራቸው ማኅበራዊና ኤኮኖሚያዉ ግንኙነቶች በመጠን ይልቅ ነበር። እንዲሁም በሲራራ ነጋዴዎችና በማዕከላዊ መንግስት አማካይነት ግንኙነታቸው ይገለጻል። በዚህ ውስን ግንኙነትም እንኳን፤ የጋራ ጥቅምና አመለካከት አፍርተዋል። ወንዙ የደርግ አገዛዝ ነው ብለን ብንወስደው፥ ወንዙን ለመሻገር አብረው እንደታገሉና መስዋዕት እንደከፈሉ ገልጸዋል።

ወንዙን ሲሻገሩ ምን አገኙ? ሰላም፥ ዴሞክራሲና፥ ነጻነት። ከዛም አሻግረዉ ተመለከቱ። በዚህ ብቻ መቆም እንደሌለባቸው አመኑ። የተጎናጸፉት ሰላም፥ ዴሞክራሲና፥ ነጻነት ለማሳደግ፥ እነዚህም ዋስትና እና ዘላቂነት እንዲኖራቸዉ፥ የኤኮኖሚና ማኅበራዊ እድገታቸው እንዲፋጠን፥ አሁንም በጋራ መስራት እንዳለባቸው አመኑ። የኤኮኖሚና የፓለቲካ አንድነት ለመገንባት።

የኤኮኖሚና የፓለቲካ አንድነት ቀድሞ አልነበረም ወይ? ነበረ እንጂ። ከላይ እንደተገለጸው፤ በተለያዩ መስኮችና ደረጃዎች ግንኙነቶች ነበራቸው። አብረው ታግለዋል። አብረዉ መስዋዕት ከፍለዋል።  በዚህም የጋራ አመለካከትና ጥቅም አፍርተዋል። አንድነቱ ግን በጣም ዉስን ነበር። በመሆኑም አሁን የገቡት ቃልኪዳን፤ የላቀ አንድነት ለመገንባት ነው። የጋራ አመለካከታቸውን እና ጥቅማቸውን ለማሳደግ። ልብ ሊባል የሚገባው፥ አንድነቱ የተገለጸው በኤኮኖሚና በፓለቲካ ነው። “በባህል፥ ቋንቋ፥ ፆታ አንድ እንሁን” አላሉም። በዚህ ያለው ብዝሃነት፤ ያለምንም ልዩነት ይቀጥላል፥ ይራመዳል።

አላማቸውን ብቻ አይደለም ያስቀመጡት። የአላማቸው (የኤኮኖሚ እና የፓለቲካ አንድነት) መሰረት ላይም ወስነዋል። በዚህ መጽሓፍ ወደ ፊት እንደሚብራራው እነዚህ መሰረቶች ብቻ ሳይሆኑ፤ መሳሪያዎችም ናቸው። አንድነትን የመገንቢያ መሳሪያዎች። የሚገነባው የኤኮኖሚና የፓለቲካ አንድነት የሚመሰረተዉ፤ በሕግ የበላይነት፥ በራሳቸው ፈቃድ፥ በግለሰቦችና በብሔር/ብሔረሰብ መብቶች መከበር፥ በባህሎችና ቋንቋዎች ያለምንም ልዩነት መራመድ፥ በፆታ እኩልነት፥ ከታሪክ ከወረሱትን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማቸዉን በማሳደግ እንደሆነ ይገልጻሉ። ስለዚህ አንድነቱ ከሚገነባባቸው መሰረቶች ወይም መሳሪያዎች አንዱ ብዝሃነትን ያለምንም ልዩነት መጠበቅ ነው።

በሕገመንግስቱ መግቢያ ላይ የተጠቀሰው ብዝሃነት የፆታና የባሕል ቢሆንም፤ መግቢያዉን አልፈን ስንሄድ፤ በሕገመንግስቱ የተደነገጉ ብዝሃነቶች ብዙ እንደሆኑ እንገነዘባለን። ለመጥቀስ ያህል የመንግስት፥ የሃሳብ፥ የሃይማኖት፥ የድርጅት፥ ብዝሃነት ይገኙበታል። እነዚህን የብዝሃነት መገለጫዎች ጠብቀን፥ የኤኮኖሚና የፓለቲካ አንድነት እንገነባለን። ይህን ስናደርግ እስካሁን ካፈራነው የጋራ ጥቅምና አመለካከት፤ በአይነትና በመጠን የበለጠ የጋራ ጥቅምና አመለካከት እናፈራለን። ስለዚህ የሚመሰረተው አንድነት ብዝሃነትን ያጠፋ ሳይሆን፤ ብዝሃነትን የሚቀበልና ጥበቃ የሚያደርግ ነው።

ብሔርን ማእከል ያደረገ የፓለቲካ አደረጃጀት

ብሔርን መሰረት ያደረገ የፓለቲካ አደረጃጀት የደርግ ወታደራዊ መንግስት ከመውደቁ በፊት ጀመሮ በሃገራችን የተለመደ ነበር። የደርግ መንግስት በ1983 ሲወድቅ ብዙ ብሄርን ማእከል አድርገው የተደራጁ የታጠቁና ያልታጠቁ ቡድኖች ነበሩ። ከደርግ ውድቀት በኋላም አዲስ የተመሰረቱ በርካታ የብሄር ድርጅቶች አሉ። በቅርቡ እንኳን የተመሰረተው የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ አንደኛው ነው። ከደርግ ዉድቀት በፊት ለብሄር ድርጅቶች መመስረት እንደምክንያትነት የሚቀርበዉ የነበረዉ ብሄራዊ ጭቆና ነበር። የብሔር ብሔረሰቦች እኩልነት፥ የዜጎች ፍፁም እኩልነትና ልዩነት ያለማድረግ መርህ በሕገመንግስቱ እውቅና ካገኘ በኋላ ለምን እንዲህ አይነት የፓለቲካ ድርጅቶች ሊቀጥሉ ቻሉ።

ብሄርን መሰረት ያደረገ የፓለቲካ ፓርቲ ከሕገመንግስቱ መንፈስና አላማ ጋር በብዙ መልኩ ይጋጫል። እንዴት የሚለውን ከዚህ በኋላ እናየዋለን። በማንኛውም የአስተዳደር እርከን ስር ያሉ ነዋሪዎች የአንድ ብሄር አባላት ብቻ አይደሉም። በሕገመንግስቱ የተረጋገጠው በነጻነት በየትኛውም የሃገሪቱ ክፍል ተዘዋውሮ የመኖርና የመስራት መብት እየተረጋገጠ ሲሄድ ይህ እዉነታ የበለጠ ግልጽ እየሆነ ይሄዳል። ከዚህ አኳያ ብሄርን መሰረት ያደረገ የፓለቲካ ፓርቲ አደረጃጀት አግላይነት ባህሪን ያንጸባርቃል። በሃይማኖት የፓለቲካ ፓርቲ ማደራጀት የማይፈቀድ ከሆነ፥ በብሄርም የፓለቲካ ፓርቲ ማደራጀት ሊፈቀድ አይገባም።

ይህ እንዴት ሊቀጥል ቻለ? የታሪክ አሳሪነት

ከዚህ በላይ እንደተገለጸው ብሄራዊ ማንነት የፓለቲካ መደራጃ ማእከል ሆኖ እንዲቀጥል ካደረጉት ነገሮች አንዱ፥ የብሔር ትርክትና የመደራጃ ማእከልነቱ ለረጅም ጊዜ በሃገራችን የተለመደ መሆኑ ነው። ኢሕአዴግ ራሱ በዚህ ትርክትና ይህን ማእከል ባደረገ አደረጃጀት ነው ለስልጣን የበቃው። የዚህ ትርክት መቀጠልን ሊያብራራልን የሚችለው የታሪክ አሳሪነት ጽንሰሃሳብ ነው። ይህን ሃሳብ መሰረታዊ ምንነት በሌላ ጽሁፍ አብራራለሁ።

ይህ እንዴት ሊቀጥል ቻለ? ራስን በራስ የማስተዳደር መብት

በሁለተኛ ደረጃ ሊጠቀስ የሚችለው፥ ሕገመንግስቱ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የብሔር ብሔረሰብ መብት አድርጎ ማስቀመጡና “ብሔር ብሔረሰብን እና ሕዝብን” የተረጎመበት አግባብ ነው። በሕገመንግስቱ የተቀመጡ መብቶችን በሁለት መክፈል እንችላለን። የግለሰቦችና የቡድኖች። የቡድን መብት ባለቤቶች ተብለው የተጠቀሱት ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና፥ ሕዝቦች ናቸው። የቡድን መብቶች ተብለው ከተጠቀሱት ዉስጥ፥ ባህልን ማራመድና ማበልጸግ፥ ቋንቋን የመጠቀም፥ ታሪክን የመጠበቅና፥ ራስን በራስ የማስተዳድር ናቸው። ከእነዚህ ዉስጥ ራስን በራስ የማስተዳደርን መውሰድ እንችላለን። ራስን በራስ ማስተዳደር በከባቢያዊ፥ ክልላዊና ብሄራዊ መንግስታት የመወከል መብትን ይጨምራል። የዚህ መብቶ ባለቤቶች ብሔር፥ ብሔረሰቦችና፥ ሕዝቦች ናቸው።

ሕገመንግስቱን ስንጽፈ ከፈጸምናቸውን ግድፈቶች አንደኛው ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ለብሄር፥ ብሄረሰቦችና፥ ህዝቦች መስጠታችን ነው። በዚህ የተነሳ፥ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ለማግኘት መጀመሪያ ብሄራዊ የማንነት ጥያቄን ማንሳት ተገቢ እንዲሆን ሆኗል። ለምሳሌ በሰሜን ጎንደር ያለውን የቅማንት ጥያቄን መወሰድ እንችላለን። የቅማንት ሕዝብ ያቀረበው ጥያቄ፥ የራሳችን ባህል፥ ታሪክና፥ ቋንቋ፥ እና መልካምድራዊ አሰፋፈር ስላለን፥ እንደ አንድ ራሱን እንደቻለ ብሄረሰብ እንቆጠር፥ ራሳችንን በራስ እናስተዳድር የሚል ነው። ጉዳዩን የተመለከተው የክልሉ ምክር ቤት፥ የተወሰኑ ቀበሌዎችን ለይቶ የቅማንት ቀበሌዎች መሆናቸውን እና ራሳቸውን በራስ ማስተዳደር እንደሚችሉ ወሰነ። እነዚህን አካቢዎች በምን መመዘኛ እንደለየ በሙሉ ግልጽ ባይሆንም፥ በእነዚህ ቀበሌዎች የቅማንት ተወላጆች በብዛት መገኘታቸው ነው።

ሕገመንግስቱ ብሄር፥ ብሄረሰብና ህዝብን ሲተረጉም፥ ቋንቋን፥ ባህልን፥ ታሪክን የሚጋሩ ነዋሪዎች ያሉትና በአንድ የተለየ አካካቢ የሚኖር ማህበረሰብ በሚል ነው። ስለዚህ በእነዚህ ቀበሌዎች ተመሳሳይ ባህልና ታሪክ ላይ ለተመሰረተው የቅማንት ማህበረሰብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብቶ ሰጥቶታል። ራስን በራስ ማስተዳደር በመንግስት ተቋማትና የማቋቋምና የመወከል መብት ይሰጣል። ማለትም የቅማንት ማህበረሰብ በእነዚህ ቀበሌዎች ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት የመንግስት ተቋማትን የማቋቋምና የመወከል መብት አለው።

ይሄ የሕገመንግስቱ ድንጋጌ ብዙ ጥያቄዎች ያስነሳል፤ በእነዚህ ቀበሌዎች ከቅማንት ማህበረሰብ ውጭ የሆኑ ነዋሪዎች የሉም ወይ? አሉ። ታዲያ እነዚህ ነዋሪዎች በሚቋቋሙ መንግስታዊ ተቋማት እንዴት ይወከላሉ? እንዴት አገልግሎት ያገኛሉ? በእነዚህ ቀበሌዎች የሚኖሩ ሁሉም ነዋሪዎች፥ የቅማንት ብሄረሰብ አባላት የሆኑትም ያልሆኑትም፥ ለምን ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት አይሰጣቸውም? ለምን የቅማንት ብሄረሰብ አባላት ብቻ?

ዋናው ችግሩ ግን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፥ ከዜጎች የመዘዋወር ነጻነት ጋር የሚጋጭ መሆኑ ነዉ። ከላይ በተጠቀሰው ምሳሌ በተለዩት ቀበሌዎች የቅማንት ህዝብ ራሱን በራሱ የማስተዳደር መብት ያገኘው በቁጥር በመብለጡ ነዉ። በመሆኑም ይህን ብልጫዉን አስጠብቆ መቆየቱ፥ የራስ በራስ የማስተዳደር መብቱን እንዳያጣ ያደርገዋል። ይሄ ደግሞ የዜጎችን የመዘዋወር ነጻነት በተለያየ መልኩ ለመገደብ ጥረት እንዲያደርጉ ያደርጋል።  የዜጎች ፍልሰት መገለጫችን እንዲሆን ያደርጋል።

ብሄርን ያማከለ ፓለቲካና የሕዝብ አስተዳደር እና ፍሬዎቹ

ግጭትና ማህበራሰባዊ ለውጥን ማደናቀፍ

የዚህ የሕገመንግስት ድንጋጌው ውጤት እንመልከት። ይሄ ድንጋጌ የፈጠረው ልዩ ዞን፥ ልዩ ወረዳ የሚባሉ ትርክቶችን ነው። አንደ ክልል በዞን፥ ወረዳ፥ ቀበሌዎች ይደራጃል። ባብዛኛው ዞን የቅንጅት መዋቅር እንጂ፥ አስተዳደራዊ አይደለም። ታዲያ እንዱ ዞን ከሌላው ዞን እንዴት ልዩ ይሆናል? አንዱ ወረዳ፥ ሌላው ልዩ ወረዳ ይሆናል። ለምሳሌ የአማራ ክልልን ስንወስድ፥ ልዩ የኦሮሞ ዞን እና ልዩ የአገው ዞንን እናገኛለን። በእነዚህ ዞኖች አብዛኛው ነዋሪዎች አማራ ስላልሆኑ። ስለዚህ እነዚህ አማራ ያልሆኑ ማህበረሰቦች ራሳቸውን በራሳቸው ማስተዳደር ስላለባቸው ይሄ ልዩ የሚባል አደረጃጀት ተፈጥሯል። ስለዚህ የዞን ምክር ቤት አለ። የራሱ አስፈጻሚ አለው። የራሱ የፍርድ ቤት አደረጃጀት አለው። ዞኑ የተለየ የስራ ቋንቋ ይኖረዋል። በምክር ቤቱ የሚወከለው ብሄረሰቡ ነው። በተግባር በእነዚህ ልዩ ዞኖችና ወረዳዎች በአመራርና የመንግስት ሰራተኝነት የሚቀጠሩትም የብሄረሰቡ አባላት ናቸው። ልብ ሊባል የሚገባው ልዩ ወረዳ ወይም ልዩ ዞን የሚለው አባባል የመጣው በክልል ያሉ ዞኖች የአማራ ሲሆኑ ይህኛው ግን የሌላ ነው ከሚል ነው።

ሕገመንግስቱ ማንኛውም ኢትዮጲያ በሃገሪቱ ተዘዋውሮ የመኖርና የመስራት መብት አለው። በሌላ መልኩ ደግሞ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የተሰጠው፥ ለብሄር፥ ብሄረሰብና ሕዝብ ነው። ከላይ እንደተጠቀሰው፥ የተወሰኑ ቀበሌዎች ውስጥ የቅማንት ብሄረሰብ ራሱን በራስ ማስተዳደር ይችላል የሚለው ዉሳኔ፥ በእነዚህ ቀበሌዎች ካሉ ነዋሪዎች የቅማንት ብሄረሰብ አባላት መብዛታቸው ነው። በመሆኑም ራስን የማስተዳደር መብታቸውን ላለማጣት በእነዚህ ቀበሌዎች የቅማንት ብሄረሰብ አባላት አብዛኛነታቸውን መጠበቅ አለባቸው። ይሄ ሁለት ጫናን ይፈጥራል። አንደኛ የሌላ ብሄረሰብ አባላት በቀበሌዎቹ ለስራ ወይም ለኑሮ መምጣታቸውን፥ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት አደጋ ሆነው እንዲታዩ ያደርጋል። ሁለተኛ፥ በቀበሌዎቹ ያሉ የሌላ ብሄረሰብ አባላት ደህንነት እንዳይሰማቸው ያደርጋል። ሶስተኛ፥ ከእነዚህ ቀበሌዎች ውጭ የሚኖሩ የቅማንት ብሄረሰብ አባላት ደህንነት እንዳይሰማቸው ያደርጋል።

ባጭሩ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ለብሄር፥ ብሄርሰቦች መብት አድርጎ መወሰድና ብሄር ብሄረሰብን ስንተረጎም በአንድ የተለየ አካባቢ የሚኖሩ በሚል መሆኑ፥ የግጭት ምንጭ ይሆናል። እንደ ሰው ተወልዶ ያደገበት አካባቢ ሲለቅ ብሄራዊ ማንነቱን ግን አይቀይርም። ነገር ግን የብሄር ብሄርሰብ ትርጉም አባላቱ አካባቢውን ሲለቁ፥ ከማህበረሰቡ ተነጥለው ሲኖሩ፥ ብሄራዊ ማንነታቸውን የለቀቁ ያስመስላቸዋል።  መልካምድራዊ አስፋፈር ቋሚ እንዲሆን ግፊት ይፈጥራል። በሕገመንግስቱ የተረጋገጡ መብቶችን አደጋ ውስጥ ይከታል። ሕገመንግስቱ መሬት የጋራ ሃብት ነው እያለ፥ ነገር ግን ክልሉ፥ ወረዳው፥ ቀበሌዉ፥ ዞኑ እከሌ የሚባለው ብሄረሰብ ነው የሚል እምነት ስር እንዲሰድ ሆኗል። በአንድ አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ምንም እንኳን የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪዎችና የተለያየ ባህል አራማጆች ቢሆኑም ሁሉም በጋራ ለምን ራሳቸውን በራሳቸው አያስተዳድሩም?

ራስን በራስ ማስተዳደር ማለት አካባቢያዊ መንግስት ተቋማትን የማደራጀት ማለት ነው። በእነዚህ ተቋማት ደግሞ ተወካይን የመላክ፥ የመወከል መብት ነው። የመንግስት ተቋማት ሚና ግለስቦችን መጠበቅ፥ ሰላምና ደህንነትን ማስከበር፥ የተለያዩ ማህበራዊ አገልግሎቶችን ማቅረብ ከሆነ፥ በእነዚህ ተቋማት ላይ፥ ሁሉም የአካባቢዉ ነዋሪዎች የመወከል መብት የላቸውም ወይ። ለምን የእከሌ ወረዳ፥ ዞን ነው ማለት አስፈለገ? ለምን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለአካባቢያዊ ማህበረሰብ መስጠት አልተመረጠም? ለምን ራስን በራስ የማስተዳደር መብት ለብሄረሰብ መስጠት አስፈለገ? ብሄራዊ ማንነትስ ከሕዝብ አስተዳደር ጋር ምን አገናኘው?

ማንም ሰው በብሔር ማንነቱ የተነሳ ልዩነት ሊደረግበት አይገባም። ሁሉም ባህሎችና ቋንቋዎች ያለምንም ልዩነት ሊራመዱ ይገባል። ሁሉም ብሄረሰቦች፥ ታሪካቸውን መጠበቅ ይችላሉ። እነዚህ ለማድረግ ግን፥ ብሄራዊ ማንነትን የሕዝብ አስተዳደር መሰረት ማድረግ አይገባም። እንዲህ ማድረግ የግጭት ምክንያት እና የማህበረሰባዊ ለውጥ መሰናክል ይሆናል። መንግስታዊ ተቋማት ማህበራዊ አገልግሎትን ያቀርባሉ። የሚቀርቡት ማህበራዊ አገልግሎቶች ነዋሪው የሚፈልገው መሆኑን እና ባለስልጣናት እና ተቀጣሪ ባለሙያዎች ነዋሪውን ማገልገላቸውን ለማረጋገጥ፥ የነዋሪዉ ራስን በራስ የማስተዳደር መብት፥ ማለትም የመወከል መብት ወሳኝ ነው። ይሄ ግን ከብሄርን ማንነት ጋር የሚያገኛቸው ጉዳይ የለም። ራስን በራስ የማስተዳደር መብት የዴሞክራሲያዉ የመንግስት መዋቅር የመዘርጋት መብት ነው። ለዚህ ደግሞ የብሄራዊ ማንነት አያስፈልግም። ከመንግስት የምንፈልገው ማህበራዊ አገልግሎት እይነት፥ መጠን፥ እና ጥራት በኑሯችን ደረጃ፥ በአካባቢው ሁኔታ ይወሰናል። በብሄር ማንነታችን አይወሰንም።

የወሰን አለመግባባት

በክልሎችና ክልሎች መካከል፥ በቀበሌና ቀበሌ መካከል፥ በወረዳና ወረዳ መካከል ያሉ የወስን ግጭቶች እንዲበዛ ያደርጋል። እነዚህ ወሰኖች የብሄረሰብ ወሰኖች ተደርገው እንዲወሰዱ ያደርጋል። ባህል፥ ቋንቋ፥ እና ታሪክ የወሰኖች መሰረት እንዲሆን ያደርጋል። ይሄ ደግሞ ስምምነትን አይፈጥርም። ምክንያቱም በወሰን አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦች በረጅም ጊዜ አስተሳሳሪ ግንኙነቶች የተነሳ የሚወራረስ ባህልና ቋንቋ አላቸውና። በእርግጥ ሕገመንግስቱም ወሰንን በተመለከተ፥ ብሄራዊ ምንነትን እንደመሰረት አይወስድም።

ሕገመንግስቱ ሁለት አይነት የመንግስት መዋቅርን አቋቁሟል። የፌዴራል መንግስቱን እና ክልሎችን። ዘጠኝ ክልሎች ተጠቅሰዋል። ይህ በመሆኑም በሀገራችን ቢያንስ አስር መንግስታት እንዲኖሩ ሆኗል። ቢያንስ የተባለበት ምክንያት፥ የከተሞችን እና የወረዳና፥ የቀበሌ መስተዳድሮችን ግምት ውስጥ ካስገባን፤ ቁጥሩ እጅግ ስለሚልቅ ነው።

የፌዴራል መንግስቱና ክልሎች፤ በተሰጣቸው የስልጣን ክልል ውስጥ እስከሆኑ ድረስ፥ አንዱ ለሌላው ታዛዥ አይደለም። ክልሎች የፌዴራሉን ስልጣን እንዲያከብሩ፥ የፌዴራሉ መንግስት ደግሞ የክልሎችን ስልጣን እንዲያከብር ሕገመንግስቱ ደንግጓል።

ሕገመንግስታችን የሕዝብ ማስተዳደር ሃላፊነትን እና ስልጣንን፤ በፌዴራል መንግስቱና በክልሎች መካከል ያከፋፍላል። በአንቀፅ 51 ላይ የፌዴራል መንግስቱ ስልጣኖች ተብለው የተዘረዘሩ 21 ጉዳዮች አሉ። እንዲሁም የጋራ ስልጣኖች ተብለው የተገለፁም አሉ። በአንቀፅ 52 ደግሞ የክልል ተብለው የተለዩ ጉዳዮች ለምሳሌነት ተጠቅሰዋል። እነዚህ የተጠቀሱት፤ ለምሳሌነት ብቻ ነው። በጠቅላላው ለፌዴራል መንግስቱ ለብቻው፥ ወይም ለፌዴራል እና ለክልሎች በጋራ፥ ከተሰጡት ስልጣኖች ውጭ ያሉት በሙሉ ለክልሎች የተተዉ ናቸው። ይህ አባባል፤ የፌዴራል መንግስቱን የፈጥሩት እነዚህ ዘጠኝ ክልሎች እንደሆኑ ያስመስላል። እዉነታው ግን ከዚህ የራቀ ነው። የፌዴራል መንግስቱን እና ክልሎችን የፈጠረው፤ የኢትዮጲያ ብሔሮች፥ ብሔረሰቦችና፥ ሕዝቦች በተወካዮቻቸው በኩል ያጸደቁት ሕገመንግስት ነው። በእርግጥ ሕገመንግስቱ ከመጽደቁ በፊት ክልሎች ነበሩ። ነገር ግን እነዚያ ክልሎች፥ ሕገመንግስቱ ሲጸድቅ እንደፈረሱ ይቆጠራል። እንዲሁም ከሽግግር ወቅቱ በፊት የነበሩት ክፍለሃገሮች በመጀመሪያ በሽግግሩ መንግስት ቻርተር፥ በመቀጠልም በሕገመንግስቱ ፈርሰዋል። በመሆኑም ከሕገመንግስቱ በፊት የነበሩ ክልሎችን እና ክፍለሃገሮችን መስረት አድርጎ፥ የሚነሱ ሙግቶች ተቀባይነታቸው ዝቅተኛ ነው።

ሕገመንግስቱ ዘጠኙን ክልሎች በስም ሲዘረዝር፥ አዲስ የተቋቋሙ ሳይሆን፥ ቀድሞም የሚታወቁ አድርጎ ስለመሆኑ ከሚያሳየው ውስጥ አንደኛው፥ ክልሎቹን በስም ከመዘርዘር ውጭ የክልሎቹን ወሰን አለመለየቱ ነው። ለነገሩ የሃገሪቱን ወስንንም በተመለከተ፤ በአለም አቀፍ ሕግ ከሚታወቀዉ ከማለት ውጭ ምንም አላለም። አለም አቀፍ ሕግ ደግሞ የክልሎችን ወሰን ለመወሰን አይጠቅምም። ነገር ግን በክልሎች መካከል የወሰን አለመግባባት ሲፈጠር አለመግባባቱ እንዴት እንደሚፈታ ይደነገግጋል። የወሰን አለመግባባት በመጀመሪያ በስምምነት ይወሰናል። ነገር ግን ክልሎቹ በስምምነት መወሰን ካልቻሉ፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሚወስን ሕገመንግስቱ ይደነግጋል። የክልሎቹ አወሳሰን የተመሰርተበትን እና መሰረት ማድረግ ያለበትን መመዘኛዎችንም ሕገመንግስቱ ያስቀምጣል። የሕዝብ አስፋፈር፥ ቋንቋ፥ ማንነትና፥ ፈቃድ ናቸው። ሕገመንግስቱ ሲጸድቅ፥ በመግቢያዉ ላይ የኢትዮጵያ ብሔር፥ ብሔረሰቦችና፥ ሕዝቦች የየራሳቸው አኩሪ ባህልና አስፋፈር እንደነበራቸው ግልፀዋል። እንዲያም ሆኖ በተለያዩ መስኮች በተለያዩ ደረጃዎች በግንኙነቶች እንደተሳሰሩና በዚህም የጋራ ጥቅምና አመለካከት እንዳፈሩም ገልፀዋል። በመግቢያዉ እንደተገለገጸው ግንኝነቶቹ በደረጃና በአይነትም በወሰኖችና ከተሞች ላይ የጎላ እንደነበረ ተገልጿል። በመሆኑም እነዚህን ቦታዎች አስመልክቶ አስፋፈር፥ ቋንቋና፥ ማንነት አለመግባባትን ለመፍታት ያላቸው ጥቅም ብዙም አይደለም። ወሰኖች አካባቢ ያሉ ሕዝቦች፥ ከዚህ በላይ በተጠቀሰው ታሪካዊና ልዩ ግንኙነቶች የተነሳ፤ የብዙ ቋንቋ ተናጋሪዎች ናቸው። ባህሎቻቸውም እርስ በርስ የሚወራርረሱ ናቸው። ማንነት ደግሞ የሚወሰንበት ሕጋዊ ስርዐኣት የለም። ማንነት የግለሰቡ እምነትና ምርጫ ነው። በመሆኑም ዞሮ ዞሮ አለመግባባቶች በስምምነት መፍታት ካልተቻለ፥ የሚፈታው የሕዝቦችን ፈቃድ መሰረት በማደርግ በፌዴራሽን ምክር ቤት ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት ደግሞ ይህን ለመፍታት የሚችለው ጥናትን፥ ታሪክን፥ እና የሚመለከታቸውን ክልሎች ሙግት በመስማት ሳይሆን፥ ጭቅጭቅ በተነሳባቸው አካባቢዎች ሕዝባዊ ምርጫ በማድረግ ነው። ይህ የሚሆነው ግን፥ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክልሎች ባልተስማሙበት ሁኔታ ነው። ለነገሩ ሲስማሙስ፤ “የስምምነታቸው ይዘትና ቅርጽ፥ እንዲሁም ዉጤት ምንድን ነዉ?” የሚለውን የሚገዛ የሕግ ማዕቀፍ የለም። የፌዴራሽን ምክር ቤት በዚህ ጉዳይ ላይ የሕግ ማዕቀፍ እንዲዘጋጅ ማድረግ አለበት። ወሰንን ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ጉድዮችን አስመልክቶ፤ ክልሎች እርስ በርስ የሚያደርጓቸውን ስምምነቶች የሚገዛ ሕግ መኖር አለበት። ከዚህ በተጨማሪ፤ በክልሎች መካከል ያለ የወሰን ጉዳይ፤ ለዘላለም የቆመ ሳይሆን፤ በየጊዜዉ ሊለዋወጥ የሚችል መሆኑን መገንዘብ ይገባል። “ከሃያ አምስት አመታት በኋዓላ እየተነሱ ያሉ የወሰን ሙግቶች አሁል ለምን ገነው ወጡ?” የሚለውን ጉዳይ መመርመርም ያስፈልጋል።

መደምደሚያ

ስለዚህ ፓለቲካን እና ብሄራዊ ምንነትን መለየት ያስፈልጋል። ልክ ሃይማኖትን እና መንግስትን እንደለየነው። ብሄራዊ ማንነት የቋንቋ፥ የታሪክ፥ የባህል ጉዳይ ነው። እነዚህ መብቶች ለመተግበር ሲባል ብሄርን ያማከለ የፓለቲካ ፓርቲ ማደራጀት አያሰፈልግም። የሚያስፈልገው ሌላ አይነት አደረጃጀት ነው። ያም፥ የቋንቋ፥ ታሪክ፥ እና ባህል ድርጅቶችን ማቋቋም ነው። ስለዚህ የፌዴራል መንግስቱ ለእነዚህ መብቶች መረጋገጥ በሕግ የቋንቋና ባህል ማህበራት ማደራጅት ይገባዋል ወይም ለተደራጁ ማህበራት የገንዘብና ሌላ ድጋፍ መስጠት ይገባዋል። እነዚህ ማህበራት በመንግስት በሕግ ቢደራጁም፥ የሚያስተዳድራቸውን ግን አባላቶቹ ናቸው። መንግስት የበጀት ድጋፍ ያደርጋል። እነዚህ ማህበራት ተልእኳችው ሕዝብ ማስተዳደር ሳይሆን፥ አንድን ቋንቋ/ባህል/ታሪክ ማራመድ፥ መጠበቅ፥ ማስተዋወቅ ነው። የተልእኳቸው አድማስ መላ ኢትዮጲያ ነው። ለምሳሌ የአማራ ብሄረሰብ ማህበር ቢቋቋም፥ ተልእኮው የአማርኛን ቋንቋ ጥናት ማራመድ፥ መጠበቅና ማስተዋወቅ ይሆናል። ለዚህም ለምሳሌ በአማርኛ የሚታተሙ መጽሃፍትን ይደግፋል። በአማርኛ የሚሰሩ የጥበብ ስራዎችን ይደግፋል። አማርኛ ቋንቋ ትምህርት መማር ለሚፈልጉ፥ የቋንቋ ትምህርት ቤቶችን ያስፋፋል። ይህን የሚያደርገው በመላው ሃገር እንጂ በአንድ ክልል ተወስኖ አይሆንም። በተመሳሳይ መልኩ ሌሎች የብሄረሰብ ማህበራት። እነዚህ ማህበራት በአባላቱ ይመራሉ።

ብሄራዊ ማንነትን እና መንግስትን መነጠል ያስፈልጋል። ለዚህ ደግሞ ብሄራዊ ማንነትን ከፓለቲካ እና የሕዝብ አስተዳደር መነጠል፥ ራስን በራስ የማስተዳደር መብትን ከብሄራዊ ማንነት መነጠል፥ እና በሕግ የብሄረሰብ ማህበራትን ማደራጀት ያስፈልጋል። ይሄ ብቻ ግን አይበቃም። የፌዴራል መንግስቱ በሕገመንግስቱ ለተቀመጠው የእኩልነት መብት የሕግ ማእቀፍ መዘርጋትና መተግበር ይገባዋል። እንዲሁም የወረዳና የቀበሌ አስተዳደሮች የራስን በራስ የማስተዳደር መብት መገለጫዎች ስለሆኑ፥ የፌዴራል የሕግ ማእቀፍ ያስፈልጋቸዋል።

ለዚህ የመጀመሪያዉን እርምጃ መውሰድ ያለበት ኢህአዴግ ነው። የኢህአዴግ አባላት ራሳቸውን ወደ ክልላዊ ፓርቲነት መቀየር አለባቸው። ለምሳሌ ብአዴን የአማራ ፓርቲ ሳይሆን፥ የአማራ ክልል ፓርቲ ነው። በመሆኑም ብአዴን ድሬዳዋን እና አዲስአበባን በማስተዳደር ረገድ ሚና ሊኖረው አይገባም። አዲስ አበባ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው ማስተዳደር ያለባቸው።

 • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.