• Dr. Mulugeta Mengist

ተፈጽሟል! የዜጋርኒክ ዉጤት

Updated: Nov 17, 2019

1927 በርሊን፡፡ የተማሪዎችና የፕሮፌሰሮች ስብስብ ወደ አንድ ምግብ ቤት ጎራ ይላሉ፡፡ አስተናጋጁ የሁሉንም የእራት ትእዛዝ፤ አንዱን ባንዱ እየደራረበ ይቀበላል፡፡ ምንም አይነት ማስታወሻ ሲጽፍ/ሲይዝ አይታይም፡፡ አያያዙን አይተዉ ጭብጦዉን ቀሙት እንዲሉ፤ ሁሉም ትእዛዛቸዉ እንደሚምታታና እንደሚሳሳት ገምተዋል፡፡ ከአፍታ ቆይታ በኋላ ሁሉም ያዘዙት ያለምንም መምታታትና ስህተት ቀረበላቸዉ፡፡ ተመጋቢዎቹ በአስተናጋጁ አይምሮና የማስታወስ ብቃት ተደመሙ፡፡


እራት ተጠናቆ ምግብ ቤቱን ለቀዉ እንደወጡ ብሉማ ዜጋርኒክ የተባለች ሩሲያዊ የስነ-ልቦና ተማሪ ስካርፏን እንደረሳች ባወቀች ጊዜ ወደ ምግብ ቤቱ ተመለሰች፡፡ ወደ ዉስጥ ስትገባ ቅድም በማስታወስ ችሎታዉ የተደመመችበትን አስተናጋጅ አገኘችዉ፡፡ ስካርፏን ረስታ እንደወጣችና አግኝቶ እንደሆነ ጠየቀችዉ፡፡ አስተናጋጁ ዝም ብሎ አፍጥጦ ያያታል፡፡ ማን እንደሆነች ወይም የት ቦታ ተቀምጣ እንደነበረ አያስታዉስም፡፡


ዜጋርኒክ ተገርማ “እንዴት ልትረሳ ትችላል? በተለይ አንተ፤ በማስታወስ ብቃትህ ያስደነቅከን” አለችዉ፡፡ አስተናጋጁም ተረጋግቶ፤ “የሁሉንም ደንበኛ ትእዛዝ በአይምሮዩ የማቆየዉ ያዘዙትን እስካቀርብና ሂሳብ እስክቀበል ድረስ ብቻ ነዉ” በማለት መለሰላት፡፡


ዜጋርኒክ እና አስተማሪዋ ከርት ሌዊን ይህን እንግዳ ክስተት አጠኑት፡፡ በጥናታቸዉም ሁሉም ሰዉ ቢሆን ከሞላ ጎደል ልክ እንደ አስተናጋጁ ህይወቱን እንደሚመራ ተገነዘቡ፡፡ ሁላችንም ያላለቀ ስራን እንረሳም፡፡ እረፍት አይሰጠንም፡፡ ትኩረት እንደሚፈልግ ህጻን ልጅ ይነዘንዘናል፡፡ በአንጻሩ ስራዉን ከጨረስን በኋላ በአይምሯችን ይዘን ከምንዞረዉ ዝርዝር ዉስጥ እንደመሰስዋለን/እንሰርዘዋለን/እንደልተዋለን፡፡ እንረሳዋለን፤ አናስታዉሰዉም፡፡ ይህ የጥናት ዉጤት የዜጋርኒክ ዉጤት እየተባለ በሳይንቲስቶች ይጠራ ጀመር፡፡


ዜጋርኒክ ከዚህ በተጨማሪ ካልተጀመረ ስራ የተጀመረ ነገር ግን ያላለቀ ስራ የማጠናቀቅ እድሉ ከፍተኛ እንደሆነ በጥናቷ አረጋግጣለች፡፡ አንድ ጊዜ ስራ ከተጀመረ እስኪጠናቀቅ ድረስ አይምሯችን ፋታ ስለማይሰጠን፤ የመቀጠልና የማጠናቀቅ ፍላጎታችን ከፍተኛ ነዉ፡፡ ስራዎችን ለነገ የማሳደር አባዜ የተጠናወተን ሰዎች፤ አንዱ መድሃኒት ስራዉን እንደምንም ብለን መጀመር ነዉ፡፡ ከባድ ስራ ከሆነ፤ ከቀላሉ መጀመር፡፡


ነገር ግን ዜጋርኒክ በጥናቷ ዉስጥ ምክንያት ያላገኘችላቸዉ ልዩ ክስተቶችንም ተመልክታለች፡፡ አንዳንድ ሰዎች ምንም ያህል ከደርዘን የሚበልጥ ያላለቁ ስራዎች ቢኖሯቸዉም ሙሉ ለሙሉ ንጹህ/ነጻ አይምሮ እንደሚኖራቸዉ አስተዉላለች፡፡ ይህን ልዩ ክስተት በተመለከተ በቅርብ ጊዜ ሮይ ቦቢስተርና የምርምር ጓዶቹ ብርሀን ፈንጥቀዉበታል፡፡ ተመራማሪዉ ለፈተና አንድ ወር የቀራቸዉን ተማሪዎችን በመምረጥ በሶስት ቡድን ከፈላቸዉ፡፡ በመጀመሪያዉ ቡድን ያሉትን በቀራቸዉ አንድ ወር ዉስጥ ስለ ፓርቲ ብቻ እንዲያስቡና እንዲያተኩሩ አዘዛቸዉ፡፡ በሁለተኛዉ ቡድን ያሉትን ደግሞ በፈተናቸዉ  ላይ እንዲያተኩሩ አዘዘ፡፡ በሶስተኛዉ ቡድን ያሉ ተማሪዎችን በፈተናዉ ላይ እንዲያተኩሩና ዝርዝር የጥናት እቅድ እንዲያወጡ አዘዛቸዉ፡፡


በመቀጠልም ተመራማሪዉ ተማሪዎችን በተወሰነ ጊዜ ዉስጥ የሚጠናቀቅ ፈተና አቀረበላቸዉ፡፡ ፈተናዉ የጎደሉ ፊደሎችን በመሙላት ቃላትን እንዲፈጥሩ የሚያዝ ነዉ፡፡ አንዳንድ ተማሪዎች “Pa….” የሚለዉን “Panic” በሚል ሲሞሉ ሌሎቹ “Party” ወይም “Paris” በሚል ሞሉ፡፡ በተማሪዎች አይምሮ ምን እየተመላለሰ እንደሆነ ለማወቅ የሚረዳ ፈተና ነበር፡፡


እንደተጠበቀዉ በመጀመሪያዉ ቡድን ያሉ ተማሪዎች አይምሯቸዉን ፈታ/ዘና አድርገዋል፤ ስለፈተናዉ ብዙም አልተጨነቁም፡፡ በሁለተኛዉ ቡድን ያሉት ደግሞ ከፈተና ዉጭ ምንም ማሰብ አልቻሉም፡፡ በጣም የሚገርመዉ ዉጤት በሶስተኛዉ ቡድን ያሉ ተማሪዎች ጉዳይ ነዉ፡፡ ምንም አንኳ ስለፈተናቸዉ እንዲያስቡ ትእዛዝ ቢሰጣቸዉም አይምሮአቸዉ ከፍርሃትና ከጭንቀት ነጻ ነበር፡፡ ተጨማሪ ጥናቶችም ይህን አረጋግጠዋል፡፡


ያላለቁ ስራዎች አይምሮአችንን የሚቆጣጠሩትና የሚረብሹን ምን ማድረግ እንዳለብን/በምን መልኩ ልናጠናቅቃቸዉ እንደምንችል ግልጽ የሆነ እቅድ/ሃሳብ እስኪኖረን ድረስ ነዉ፡፡ ዜጋርኒክ ለአይምሮ እረፍት ያላለቁ ስራዎችን ማጠናቀቅ አስፈላጊ እንደሆነ ስትናገር አዲሱ የጥናት ዉጤት ግን የግድ ስራዎቹ መጠናቀቅ የለባቸዉም፡፡ ዝርዝር የስራ እቅድ ከተቻለ በጽሁፍ ከተዘጋጀ የስራዉ መጠናቀቅ የሚሰጠዉን አይነት የአይምሮ እረፍት ማግኘት ይቻላል፡፡ ይህ የስራ እቅድ ዝርዝርና ጉዳዮን ለማጠናቀቅ የሚያስፈልጉ እያንዳንዱ ዝርዝሮችን ደረጃ በደረጃ ማስቀመጥ አለበት፡፡

I was reading, on a plane, The Art of Thinking Clearly, an interesting book that summarizes the extensive scientific literature on cognitive/behavioral sciences. I am amazed by the focus of some who can work on a project while flying with little interruption. I, on the other hand, mix sleeping, watching movies, listening to music and walking while on air. But yesterday I decided to translate a chapter from the book that I was reading. Here it comes:

11 views

Recent Posts

See All

የሽግግር መንግስት ህገመንግስታዊ ነው?

የዶር መሃሪ ታደለን ፅሁፍ አነበብሁት። https://meharitaddele.info/2020/05/the-limits-of-legal-solutions/ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው ለመንግስት ተጨማሪ ስልጣን በመስጠትና መብቶችን በመገደብ በሽታውን ለመዋጋትና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ ከሆኑ ብቻ ነው። መንግስ

አንዳንድ ጉዳዮች ስለ ህገመንግስት እና ፍርድ (ትርጉም)

መንደርደሪያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ዘመን ከማለቁ በፊት ምርጫን ማከናወን እንደማይችል፤ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ካሳወቀ ጊዜ ጀምሮ፤ የጉዳዩ ህገመንግስታዊ ገፅታዎች በተለያዩ መድረኮች ውይይት እየተደረገባቸው ነው። አራት አማራጭ መፍትሄዎች የቀረቡለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ በጉዳዩ ላይ የህገመንግስት

  • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.