• Dr. Mulugeta Mengist

በመጀመሪያ መቀየር ያለበት፤ የጦርነትና የመስዋእትነት ትርክት

Updated: Nov 17, 2019

ኢሕአዴግ ወታደራዊውን መንግስት አስወግዶ የፌዴራል ስርአቱን የተከለ ድርጅት ነው። ድርጅቱ ለዚህ የበቃው መቶ ሺዎች የነፃነት ታጋዮች ባደረጉት መራራ ትግልና የህይወት፥ የአካል፥ የእድሜ፥ የተደላደለ ኑሮ መስዋእትነት ነው። እነዚህ ታጋዮች ደመወዝ የሚከፋላቸው ታጋዮች አልነበሩም። ግን ሕይወታቸውን ድረስ መስዋእት ለማድረግ ዝግጁ ነበሩ። በጦርነት ውስጥ መሞት እንዳለ ማወቅና መቀበል አንድ ነገር ነው። ነገር ግን በገዛ ፈቃድ “እኔ ልሙትና እናንተ እለፉ” በማለት ፈንጂ ላይ ተኝቶ መሞትና መቁሰል ግን እንኳን ለማድረግ ለመረዳትም ቀላል አይደለም።

ደመዎዝ የማይከፈለውን ታጋይ እስከዚህ ድረስ መስዋእት ለመክፈል ፈቃደኛ እንዲሆን ማድረግ እንዴት ተቻለ? ወይስ የኢህአዴግ ታጋዮች ትግል ከመግባታቸውም በፊት እንዲህ አይነት ሰዎች ነበሩ? ማለትም ታጋዩን የፈጠረው ድርጅቱ ነው ወይስ ድርጅቱን የፈጠሩት ታጋዮቹ ናቸው? “ድርጅቱን እኔ አልፈጠርኩትም። እኔ የድርጅቴ ነኝ። እኔን የፈጠረኝ ድርጅቴ ነው” ይል ነበር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር።

ሁሉም ታጋይ በረሃ ከመግባቱ በፊትም እንዲህ ቆራጥ የሕዝብ ተቆርቋሪ እና ሕዝባዊ ነበር ማለት ይከብዳል። ምክንያቱም የትግሉን አላማና አደጋ በሚገባ ሳይረዱ የገቡም ነበሩ። የደርግን የከተማ ቀይ ሽብር ሸሽተዉ በርሃ የገቡ ነበሩ። ፍትህን ሸሽተው የሸፈቱ ድርጅቱን ተቀላቅለው ነበር። ጓደኞቻቸው አብዛኛዎቹ በርሃ ሲገቡ፥ የሰው መዘባበቻ እንዳይሆኑ በሚል በርሃ የገቡ ነበሩ። ምናልባትም ወደ ሱዳን ሲሰደዱ መንገድ ጠፍቶባቸው፥ ታመው፥ ወይም ስንቅ ጨርሰው ትግሉን የተቀላቀሉም ይኖራሉ። ነገር ግን ድርጅቱ ሁሉንም ተቀብሎ ሕዝባዊ፥ ደፋር፥ ፅኑ የነፃነት ታጋይ አድርጎ ዳግሞ ወልዷቸዋል። እንዴት አድርጎ? ምን አይነት መሳሪያ ተጠቅሞ?

የተጠቀመው መሳሪያ ውጤታማ ስለመሆኑ ድርጅቱ ደርግን በመጣል ያሳየው ስኬት እና እንደ አሞራው፥ ቀሽ ገብሩ፥ እና ሌሎች ግላዊ ታሪኮች ማሳያዎች ናቸው።  መሳሪያዎቹ ዉጤታማ መሆናቸው ደግሞ ከትግሉ ምህዳር፥ ከአላማው፥ ከጠላት ባህሪ ጋር የተጣጣሙ መሆናቸው ነው። ያለበለዚያ ስኬታማ አይሆኑም ነበር።

ከእነዚህ መሳሪያዎቹ እና የምህዳሩ ባህሪ መካከል የሚቀጥሉት ይገኙበታል

 1. ስልጠና እና ዶክትሪኔሽን፤ ከመሰረታዊ ማንበብና መፃፍ አልፎ የፓለቲካ ንቃተ ህሊናን የሚያሳድጉ ስልጠናዎች በሰፊዉ ይሰጡ ነበር። ለታጋዩ መሰረታዊ እውቀትና ክህሎት ለማስጨበጥ ልብወለዶች ሁሉ ተደርሰው በቡድን ይነበቡ ነበር። ይህን መሰረት አድርገው ይወያዩ ነበር።

 2. አሳታፊ ውሳኔ እና ውይይት፤የድርጅቱ አስራር አሳታፊና ውይይት ላይ የተመሰረተ ነበር። ትልልቅ የመስመር ልዩነቶች ሳይቀር መላው ታግዩን ባሳተፈ ውይይትና ሙግት ይፈቱ ነበር።

 3. ዘፈን እና የስነጥበብና ኪነት ውጤቶች በታጋዩ መካከል የአላማ እርግጠኝነትን ለማስፈን ዉለዋል። የስብከትና ማሳመኛ መሳሪያዎችም ነበሩ።

 4. በአመራሩና በታጋዩ መካከል ያለው ልዩነት የሌለው ኑሮና ግንኙነት ሌላዉ የትግሉ ምህዳር መገለጫ ነበር። በአመራሩና በመደበኛው ታጋይ መካከል የህይወት/የኑሮ ደረጃ ልዩነት አልነበረም ወይም ሰፊ ልዩነት አልነበረም።

 5. የትግል ኑሮ ግልጽነት፤ የትግል ኑሮ ግልጽ ነው። ማን ምን እንደበላ፥ ምን እንደጠጣ፥ ምን ሲስራ እንደዋለና እንዳደረ ይታወቃል። ሌላው ቢቀር በሳሙና ገላህን ስትታጠብ ይታወቃል።

 6. ጦርነቱ እና የበርሃ ኑሮ ችግር የሚፈጥረው የትብብር መንፈስ፥ የጦርነት እንቅስቃሴ የሚፈጥረው የአብሮነትና የትብብር መንፈስ አለ። ጦርነቱ እና በየቀኑ መስዋእት ሆነው የሚያልፉ ጓዶችን ስታይ፥ ስለመኖርህ ሁሉ እድለኝነት ይሰማሃል። በዚህ ሁኔታ ግላዊ ሆኖ መኖር ይከብዳል

 7. ግምገማ፤ ግምገማ የታጋዩና አመራሩ አፈጻጸም የሚመዘንበት ስርአት ነው። ግምገማው የሚያተኩረው በግላዊ ውጤት ሳይሆን በአመለካከት ቁርጠኝነት ነው።

 8. ስለትግሉ ጥርጣሬ የሚፈጥርን ማንኛውም አይነት የተለየ ሃሳብና ቡድን አለመታገስ፤ በእርግጥ ይሄ ጉዳይ ከዚህ በላይ ከተገለጹት ጋር የሚጻረር ነዉ። ነገር ግን በተለይ ደግሞ ትግሉ ወሳኝ ሰአት ባለበት ጊዜ፥ በዉይይት ይፈታል በሚል የሃሳብ ልዩነትን መታገስ የሽንፈት እርሾ ይሆናል። ምንም አይነት ጥርጣሬ መስዋእት የመክፈል ዝግጁነትን ይቀንሳል። ዶግማቲክ፥ ፍጹም እርግጠኝነት ማስፈን አለብህ። ለምሳሌ በትግሉ ጊዜ ቴክኖክራት እና ፕራግማቲክ መሆን ትልቅ ሃጢያት ነዉ።

 9. በትንንሽ ቡድኖች፥ ጋንታዎች መደራጀትና፥ ይህም የሚፈጥረው የቤተሰብ ስሜት። ይሄ አደረጃጀት የአሜሪካን ኢሊት ወታደራዊ ሃይሎች አደረጃጀትን ይመስላል። ጋንታን እንደ ቤተሰብ፥ እናት የማየት አዝማሚያ የተለመደ ነበር። ጋንታየ ናፈቀችኝ ብሎ መናገር የሚገርም አልነበረም። ችግርን በጋራ መጋራት አብሮነትን ያዳብራል። መስዋእት ለመክፈል ዝግጁነትን ይጨምራል።

መሳሪያዎቹ ከምህዳሩ፥ አላማውና፥ ተልእኮው ጋር የተጣጣሙ ናቸው። ለምሳሌ ግምገማን እንውሰድ። በትግሉ ጊዜ የሚደረግ ግምገማ ጀግንነት፥ አመለካከት፥ ጽናት ላይ ያተኩራሉ። ዉጤት/ፍሬ ላይ አያተኩሩም። ምን ያህል ጥይት አባከንክ? ምን ያህል ጠላት ገደልክ? አቆሰልክ? በእነዚህ ታጋዩን መገምገም አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም በጦርነት ውጥንቅጥ ውስጥ እንዲህ አይነቱን መረጃ መሰብሰብ አስቸጋሪ ስለሆነ። ስለዚህ ያለው አማራጭ እንዲህ አይነት ግምገማዎች ናቸው። እንዲህ አይነት ግምገማዎች የተሳኩ እንዲሆኑ ደግሞ የሁሉም ታጋይ አኗኗር ግልፅነት አስተዋእፆ አለው። በትግሉ ታሪክ ላይ የተጻፈ መፅሃፍ ላይ አንድ ታጋይ አንፀባረቅሽ ተብላ ተገምግማ እንደነበር ይተርካል። በሳሙና ታጥባ ስለነበር። ማለትም የትኛው ታጋይ በሳሙና እንደታጠበ፥ ከማን ጋር እንደተኛ፥ ምን እንደበላና እንደጠጣ በሚታወቅበት ሁኔታ እንዲህ አይነቱ ግምገማም ዉጤት ሊያፈራ ይችላል። እንዲሁም  ግምገማ ዉጤታማ እንዲሆን የሚያደርገው፥ እከክልኝ ልከክልህ በሚል የሚቃኙ ግንኙነቶች መኖር የለባቸውም። የትግሉ ምህዳር ደግሞ ለእንዲህ አይነት ግንኙነቶች የተመቹ አልነበሩም።

የታጋዩ ኑሮ ግልጽነት፥ የጋንታ አደረጃጀትና ይሄ የፈጠረው የቤተሰብ፥ የወንድማማችነት ስሜት፥ በጦርነት ወቅት በጋራ መስራት ለመኖር አማራጭ የሌለው መሆኑ፥ በየጊዜው እያንዳንዱ ታጋይ ከሞትና ከተሰዋ ጓድ ጋር መፋጠጣቸው፥ እያንዳንዱ ሊከፍለው የሚፈቅደው መስዋእትነት እንዲያድግ ሆኗል።

መስዋእት የችሮታ፥ የበጎ አድራጎት፥ የራስን ጥቅም አሳልፎ የመስጠት ጉዳይ ነው። በእያንዳንዳችን ትንሽም ብትሆን መስዋእት ለመክፈል ዝግጁ ነን። ጓደኞችህ ለተቸገር ሰው ማዋጣቸውን ስታውቅ አንተም ታዋጣለህ። እንደውም እነሱ ካዋጡት አማካይ መዋጮ ያንተም አይርቅም። ነገር ግን ማን ምን እንደቸረ በማይታወቅበት ሁኔታ፥ ያንተ መስዋእት በማይታወቅበት ሁኔታ፥ ያንተም የመስዋእትነት ደረጃ ዝቅ ይላል። ስለዚህ መሳሪያ እና ስነምህዳር የመስዋእት መጠንን ይጨምራል።

እንዲሁም ፍጹም ዶግማቲክ አሰራር ለዚህ ስኬታማነት አስፈላጊ ነው። ስለትግሉ፥ ስትራቴጂውና፥ አመራሩ ምንም አይነት ጥርጣሬ የሚያሳድር ነገር፥ የታጋዩን የትግል ስሜትና የመስዋእትነት ደረጃ ይቀንሳል። በመሆኑም የተለየ ሃሳብ የሚያራምድ ቡድንም ሆነ ግለሰብ ቦታ የለውም። እንደውም “እከሌ ፕራግማቲክ ወይም ቴክኖክራት ነው” ማለት ትልቅ የሚባል ክስ ነው። ሌላው ቢቀር “የቻይና ሶሻሊዝም ዶግማቲክ ነው” ብሎ ማመን ለትልቅ ሂስ የሚያጋልጥ ጉዳይ ነው።

በትግልና መስዋእትነት ወታደራዊ መንግስትን አስወግዶ ኢህአዴግ የመንግስት ስልጣንን ከያዘ ብዙ አመታት ሆኑት። አሁን የሕዝብ አስተዳዳሪ ነው። ነገር ግን በትግሉ ጊዜ የሚጠቀምባቸውን መሳሪያዎች አሁንም ይጠቀማል።

 1. በፕሮፕጋንዳና ስልጠና ማንንም ማብቃት ይቻላል ብሎ ያምናል

 2. አባላቶቹን እና አመራሩን አሁንም በውስን የግምገማ ነጥቦች ይገመግማል። ፍሬ ትኮር ግምገማ ሳይሆን፥ ቅርፅ ተኮር

 3. የአባላቱን መስዋእትነት ይጠብቃል። ድሃ ሆነን ብዙዎችን ባለጸጋ አድርገናል ሲሉ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ተናግረዋል። ችግሮችን ሲተነትን፥ የአባላትና የአመራሮች መስዋእት የመክፈል ዉስንነት በሚል ነዉ።

 4. የጋንታ አደረጃጀት በመንግስት አደረጃጀት ይንፀባረቃል። እያንዳንዱ የመንግስት ድርጅትና ሃላፊ ያለው ፈቃደስልጣን የጎሪላ ትግል ስልትን ይመስላል።

 5. ስለ አላማው፥ ተልእኮውና፥ ፓሊሲዉና ስትራቴጂው ፍጹም እርግጠኛ ነው። የፓሊሲ ችግር የለብንም ብሎ ይጀምራል። ችግር ካለም ከአፈጻጸም እንጂ ከፓሊሲዉ አይደለም።

 6. አባላቱን እንደ ሰራዊት/ታጋይ ይቆጥራል። ስለዚህ የአባላት መብዛት የአቅም መብዛት ነው ብሎ ያምናል።

በእርግጥ በትግሉ ጊዜ እነዚህ መሳሪያዎች ዉጤታማ ነበሩ። ዉጤታማ የነበሩት ግን ከአላማው፥ ከተልእኮውና ከምህዳሩ ጋር ስለተጣጣሙ ነው። ከድል በኋላ አላማውና ተልእኮው ከነጻነት ታጋይነት ወደ ሕዝብ አስተዳዳሪነት ተቀይሯል። የትግሉ ሜዳ የእያንዳንዱ ታጋይ የአኗኗር ግልጽነት ከድል በኋላ ጠፍቷል (ምናልባት በካምፕ ከሚኖሩት የሰራዊነት አባላት ውጭ)። ማን ሽሮውን በልቶ ወለል ላይ እንደተኛ፥ ማን ጮማ እየቆረጠ ውስኪ እየተራጭ እንዳደረ ማወቅ አስቸጋሪ ነው። ማን በቅንነትና ታማኝነት እያገለገለ እንደሆነ፥ ማን እየሞሰሰ እንደሆነ አይታወቅም። በእንዲህ አይነት ሁኔታ የትግሉ ግምገማ እንደቀድሞው ውጤት አይኖረውም። ይልቅስ እየተደራጁ ለመራኮት እድል ይሰጣል። እንዲሁም እያንዳንዱ ካድሬ ሊከፍለው የሚፈቅደው የመስዋእትነት ደረጃ ውስን ነው። ይህም ሆኖ ግን አሁንም እነዚህን መሳሪያዎችና ልምምዶችን የሙጥኝ እንዳለ ነው። እንደውም መሳሪያዎቹን ሳይቀይር ድርጅቱ፥ የሕዝብ አስተዳደር ተልእኮውን በነጻአውጪነት ትርክት ቀይሮታል። አሁንም ጦርነት ላይ ነው። የድሮው ጦርነት ደርግን ለመጣል ነው። የአሁኑ ጦርነት ከደርግ የባሰውን ዋና ጠላት ለማሸነፍ ነው። ድህነትን። ይህኛው ጠላት ይከፋል። ደርግ የድህንነት ዘበኛ ነበር። አሁንም ድርጅቱ ነጻአውጪ ነው። አሁንም ጦርነት ላይ ነው። በመሆኑም ከካድሬዎቹ ከፍተኛ መስዋእት ይጠብቃል። እንደውም ካድሬዎቹን የልማት ሰራዊት አርጎ ይወስዳቸዋል። በመሆኑም ሰራዊቱ ሲበዛ፥ ድል የቀረበች ይመስለዋል። ምህዳርን በትርክት ለመቀየር መሞከር። አጎቱ/አያቱ አሳ ከመውደዳቸው የተነሳ፤ አሳ ሲጠፋም እንኳ ጠቦታቸውን ጣና ሃይቅ ወርውረው “አሳ ነህ ብያለው አሳ” እያሉ ጠቦታቸውን እንደ አሳ አጥምደው እንደሚበሉት በእውቀቱ ስዩም ተርኮልናል።

ከዚህ በፊት አንድን ሰው ጠቅሼ እንዳልኩት፤ “በአንድ ወቅት የጠቀሙንን ልምምዶች የሙጥኝ ማለት፥ ወንዙን ከተሻገሩ በኋላ ጀልባውን ተሸክሞ የየብሱን ጉዞ መቀጠል ነው”። የተሸከምነው ስለሚጠቅመን ሳይሆን ድሮ ጠቅሞን ስለነበረ ነው። በዛ ላይ የየብሱን ጉዞ፥ በትርክት የባህር ጉዞ ለማድረግ እንሞክራለን።

የማይጠቅም ሸክም ማውረድና፤ በሚጠቅም ሸክም መተካት አስፈላጊ ነው። ከሚጠቅሙ ሸክሞች መካከል ፍሬን ማእከል ያደረገ ግምገማና ተቋማትና የሕግ የበላይነት፥ የሃሳብ ብዝሃነት ናቸው፤ ጥቂቱን ለመጥቀስ።

ከሁሉ የሚቀድመው ግን እነዚህን መሳሪያዎች የሙጥኝ ብለን እንድንቀጥል የሚያደርገንን ትርክት መቀየር ተገቢ ነው። የጦርነትና የመስዋእትነት ትርክት። አዲሱ ተልእኮ፥ ሕዝብ የማስተዳደር ነው እንጂ የነጻአዉጪነት፥ የትግልና የመስዋእትነት አይደለም። ለአላማው፥ ከተልእኮው፥ ከምህዳሩ ጋር የሚጣጣሙ ተቋማትና መሳሪያዎች መጠቀም ያስፈልጋል።

የትግሉ መሳሪያዎች ከተማ ዉስጥ እንደማይሰሩ የመጀመሪያው ማሳያ ታምራት ላይኔ እንደነበረ ድርጅቱ ራሱ ያምናል። በእሳት ያልተፈተነው በስኳር ተበላሸ የተባለለት። እሳትን የሚቋቋሙ መሳሪያዎች ስኳርን አይቋቋሙም።

 • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.