• Dr. Mulugeta Mengist

በመስመር የበላይነት ወይስ በሕግ የበላይነት ላይ የተመሰረተ የሕዝብ አስተዳደር?

Updated: Nov 17, 2019ኢህአዴግ ሁለት መስመሮች አሉት። ዴሞክራሲያዊና ልማታዊ መንግስት መስመር አንደኛው ነው። ከዚህ የሚቀድመው ሁለተኛው ደግሞ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው። በቅርብ ቀን በምሰማቸውና በማነባቸው ነገሮች ላይ፤ አንድን ሃሳብ ለመቃወም ወይም ለመደገፍ የሚቀርበው የተለመደው አመክንዮ የሚከተለውን መዋቅር ይከተላል፥

 1. መስመራችን ልማታዊና አብዮታዊ ዴሞክራሲ ነው፤

 2. ይህ የቀረበው ሃሳብ (ከፊል ፕራይቬታይዜሽን) ከመስመራችን ጋር አይጣጣምም/ይጣጣማል፤

 3. ስለዚህ ይህን ሃሳብ እቃወማለሁ/እደግፋለሁ።

የዚህ አመክንዮ ችግሮች

 1. ልማታዊና አብዮታዊ ዴሞክራሲ ማለት ምን እንደሆነ ግልጽ አይደለም። ይህ ሃሳብ ራስ፥ አንገት፥ ጫንቃ፥ ደረት፥ ሆድ፥ እጅ፥ እግር የሌለው ወይም የማይታወቅ ሃሳብ ነው።

 2. የቀረበው ሃሳብ እንዴት ከልማታዊና አብዮታዊ ዴሞክራሲ ጋር እንደማይጣጣም ግልጽ አይደለም። በተለይ ደግሞ ይህ ተቃሙሞ የቀረበበት ሃሳብ ከዚህ በፊት በቋሚነት በተለያዩ መስኮች እየተተገበር ከመሆኑ አንፃር።

 3. በመሆኑም ሙግቱ ይጣጣማል ወይስ አይጣጣምም በሚለው ላይ ያቀነቅናል። ሁሉም እንደመሰለው ልማታዊና አብዮታዊ ዴሞክራሲን እየተረጎመ ይሟገታል። ባጭሩ ጉንጭ አልፋ ሙግት።

በሕዝብ አስተዳደር ላይ የሚቀርቡ ሙግቶችን በሁለት መክፈል ይቻላል። አንደኛው ቅርጽ ተኮር የሚባለው ነው። ብዙ መረጃ መሰብሰብ አይጠይቅም። ለክትትልና ቁጥጥር የተመቸ ነው። ትልቁ ስራ የሚሰራዉ የመገምገሚያ ቅርጹን በመቅረጽ ላይ ነው። የሕግ ሙግቶች ቅርጽ ተኮር ናቸው።

ለምሳሌ ይሄን ሙግት እንመልከት፤ “ይሄ ዉል ሊፈርስ ይገባል። ምክንያቱም ዉሉን ስዋዋል ሙሉ 18 አመት አልሞላኝም። በሕጉ መሰረት ደግሞ ሙሉ 18 ስምንት ያልሞላው ሰው በሕግ ከተፈቀደለት ትንንሽ ዉሎች በስተቀር ሌሎች ዉሎችን ያለሞግዚት ከተዋዋለ ዉሉ ፈራሽ ነው። ይሄ ዉል ደግሞ በሕግ ያልተፈቀደ ነው። ስለዚህ ፍርድ ቤቱ ዉሉን ሊያፈርሰው ይገባል”።

ይሄ ሙግት ቅርጽ ተኮር ነው። የሙግቱ ማጠንጠኛ ሕጉ ነው። ሕጉ ጋር ስለማይጣጣም ዉሉ ይፍረስ የሚል። እንዲህ አይነት ሙግቶች፥ ሕግን ያማከሉ ሙግቶች፥ ጊዜን ወጪን ይቆጥባሉ። እርግጠኝነትን እና ተገማችነትን ያሰፍናሉ። ብዙ ጊዜ እና መረጃ መሰብሰብና መተንተን የሚጠይቀው ሕጉ ሲቀረጽ ነው። ሕጉ ሲቀረጽ የሕጉን ዉጤት የበለጠ ፍትሃዊ የማድረግ እድል አለው። ከዛ በኋላ የሚሰበሰበውና የሚተነተነው መረጃ ውስን ነው።  ሰውየው ሙሉ አስራ አምስት አመት ሆኖታል ወይስ አልሞላዉም? ሙሉ 18 አመት ያልሞላው ሰው ያለሞግዚት እንዲዋዋላቸው ከተፈቀዱ ዉሎች መካከል ይመደባል ወይ ይኽኛው ዉል?

ሁለተኛው ሙግት ፍሬ ተኮር ሙግት ነው። አንድን ሃሳብ የምንቃወመዉምና የምንደግፈው በፍሬዉ ነው። ከሌሎች አማራጮች ጋር ተወዳድሮ የላቀና ፍትሃዊ የሕዝብ ጥቅምን የሚያመጣ ከሆነ ሃሳቡ ይደገፋል። ከላይ የተቀመጠውን ሙግት ፍሬ ተኮር ብናደርገው ይህን ይመስላል፤

“ሁለት ሰዎች በነጻነትና በእውቀት የሚዋዋሉት ዉል ሁለቱንም ይጠቅማል። ይህን ዉል የተዋዋለው አንደኛው ሰው ግን በእድሜው ማነስ የተነሳ የተዋዋለውን ዉል የሚያመጣበትን ጥቅምና ሸክም በሚገባ አይረዳም። እንዲህ አይነት ዉሎችን መፍቀድ ማለት፥ ሰዎች በእድሜና አይምሮ ያልበሰሉ ሰዎችን እያሳደዱ መጠቀሚያ ያደርጓቸዋል።”

ይህን በመቃወም የሚቀርበው ሙግት ደግሞ ይህን ሊመስል ይችላል፤

“ያኛው ተዋዋይ ወገን የዚህኛውን የማመዛዝን እና የማወቅ ችሎታ በቀላሉ ማወቅ አይችልም። ይህን ዉል ማፍረስ በንግድ ስርአቱ ላይ ተገማችነት እንዳይኖር በማድረግ ምርትን እና ግብይትን ይጎዳል”።

ሁለቱም ሙግቶች ፍሬ ተኮር ሙግቶች ናቸው። ይህን ሙግት ለመፍታት ከፍተኛ የሆነ መረጃ መሰብሰብና መተንተን ይጠይቃል። እንዲህ አይነት ዉሳኔዎችን የሚወስኑ ሰዎችን ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ነው። ተቆጣጣሪዉ አካል ሌላ መረጃ ስብሰባ እና ትንተና ዉስጥ ያስገባዋል። ጥያቄ የቀረበበት ሙግት ሁለቱንም ወገኖች እንዴት እና በምን ያህል ይጠቅማል?  የተዋዋይ ወገንን የማመዛዘን ብቃት እንዴት ማወቅ ይቻላል? ለዚህ ዉል ጥበቃ መስጠት፥ ሰዎች የማመዛዘን ብቃት የሌላቸውን ሰዎች እንዲያሳድዱ ያበረታታል? ዉሉን ማፍረስ፥ ንግድን እንዴት እና በምን ያህል መጠን ይጎዳል? የማመዛዘን ብቃት የለውም የተባለው ሰው አዉነት የማመዛዘን ብቃት የለውም?

ቅርጽ ተኮር ሙግት ላብዛኛው የሕዝብ አስተዳደር ስራ ተመራጭ ነው። ጥቅሞቹ ከላይ ተቀምጠዋል። ተመራጭነቱ በሚከተሉት ቅድመሁኔታዎች ላይ ይንጠለጠላል፤

 1. የሙግት ማጠንጠኛ የሆነው ቅርጽ፤ የትክክለኛው ምክንያት (የላቀና ፍትሃዊ ሕዝባዊ ጥቅም) ጥላ ሆኖ መቀረጽ አለበት። ይህ ጥላ ግልጽ፥ ሙሉ መሆን አለበት። ትንሽ መረጃን በመሰብሰብና በመገምገም ወደ ትክክለኛው ዉሳኔ የሚያደርሰን አይነት ዉሳኔ መሆን አለበት። ጥላው መጀመሪያውና መጨረሻው በቁመትም በወርድም ግልጽና የሚታወቅ መሆን አለበት። እንዲሁም የጥላው ፊት፥ ወገብ፥ ሆድ፥ እግር፥ እጅ ግልጽ መሆን አለበት። ጥላው ሲቀረጽ በቂ መረጃ ሊሰበሰብና ሊተነተን ይገባል። ይህ መረጃ መሰብሰብና መተንተን ባለሙያዎችን እና ዜጎችን ያሳተፈና ግልጽ ሊሆን ይገባዋል።

 2. የጥላ ቀረጻዉና ግምገማው ፍሬ ተኮር ሊሆን ይገባዋል።

 3. ጥላዉን የቀረጸውና፥ ቅርጽ ተኮር ግምገማ በማካሄድ ዉሳኔ የሚሰጠው አካል ሊለያዩ ይገባል።

 4. ምንም ያህል ጥላውን በጥንቃቄ ብንቀርጸውም፥ ባንዳንድ ሁኔታዎች፤ ጥላ ላይ የተመሰረተ አመክንዮ፤ የሚወስደን ከዋናው ምክንያት/አላማ ጋር የማይጣጣም ዉሳኔ ሊሆን ይችላል። ምክንያቱ ቋንቋ፥ የአቀራረጹ ስህተት፥ ወይም ክፍተት የተነሳ ሊሆን ይችላል። በዚህ ጊዜ የመጨረሻውን ዉሳኔ የሚሰጠው አካል፥ ጥላ ተኮር ግምገማን ከፍሬ ተኮር ግምገማ ጋር በማጣመር ዉሳኔ ሊሰጥ ይገባል።

 5. ጥላውን መሰረት አድርገው የሚወሰኑ ውሳኔዎችን እየተከታተሉ፥ ምን ያህል የታሰበላቸውን አላማ እንዳሳኩ መገምገምና፤ ይህንንም ጥላውን በየወቅቱ እያሻሻሉ ለመቅረጽ ማዋል ይገባል።

ልማታዊና አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚባሉ መስመሮች ግልጽ አለመሆናቸው ትልቁ ችግር ነው። የድርጅቱ ሰነዶች ራሳቸው ልማታዊና አብዮታዊ ዲሞክራሲን በጽንሰሃሳብ ደረጃ ይገልፁታል እንጂ በተለያዩ መስኮችና ጉዳዮች ላይ እነዚህ ጽንሰሃሳቦች ያላቸውን አንድምታ አያብራሩም። ልማታዊ መንግስት ምን አይነት የፓሊሲ መሳሪያዎችን ይጠቀማል? ልማታዊ መንግስት የሚያደርገው ሌሎቹ የማያደርጉት ምንድን ነው? አብዮታዊ ዲሞክራሲስ? እነዚህ ግልጽ አይደሉም። በመሆኑም የተለያዩ የድርጅቱ ካድሬዎች በተለያየ መልኩ ሊረዱት ይችላሉ። አንደኛው፤ ይህን የመንግስት ማስታወቂያ በግል የቴሌቪዥን ጣቢያዎች አናስተዋዉቅም፥ ልማታዊ ስለሆንን ይላል። ሌላው፤ ይህን ስራ በግል አማካሪዎች ማሰራት ልማታዊ አይደለም ይላል።

ልማታዊና ዴሞክራሲያዊ መንግስት የሚለው ሃሳብ የእለትተእለት ዉሳኔ መሰረት ሊሆን አይችልም፥ አይገባም። ሃሳቡ፥ በግልጽ ዝርዝር ሙሉ መመሪያዎችና ድንጋጌዎች መተንተን አለባቸው። የዉሳኔ ምክንያት መሆን ያለባቸው እነዚህ ዝርዝር መመሪያዎችና ድንጋጌዎች ናቸው። ያለበለዚያ ወጥ አሰራርን፥ የላቀና ፍትሃዊ ዉጤትን ማፍራት አይቻልም። ውሳኔ ሰጪዎችን መቆጣጠር አስቸጋሪ ያደርገዋል። ልማታዊና አብዮታዊ ዲሞክራሲ በሚሉ መርሆች መሰረት ዉሳኔ እንዲወስኑ ዉክልና የምትሰጣቸው ሰዎችን መቆጣጠር ከባድ ስለሚሆን፥ ስለወኪሎችህ ማንነት አብዝተህ ትጨነካለኽ። የት ዋለ? ከማን ጋር አወራ? እራቱን ምን ከማን በላ ጋር በላ? ከማን ጋር ተኛ እያልህ በጭንቀት መከራህን ትበላለህ። ከዚህ ሁሉ ግን ልማታዊና አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚባሉ ጠቅላላ ጽንሰሃሳቦችን የሚያንጸባርቅ ዝርዝር፥ ግልጽ፥ ሙሉ ጥላዎችን በመቅረጽ፥ ዉሳኔዎች ፈጣን፥ ወጪ ቆጣቢ፥ ፍትሃዊና የላቀ ፍሬ ያላቸው እንዲሆኑ ማድረግ ይቻላል። ዉሳኔ ሰጪዎችንም ለመቆጣጠር ቀላል ነው፤ ጥላውን ተከትሏል ወይስ አልተከተለም?

የሕዝብ ጥቅምን መሰረት አድርጎ ውሳኔ እንዲሰጥ አንድን አካል መወከልም እንዲሁ ነው። ለምሳሌ በይቅርታ የሚፈቱ ሰዎች የሚያቀርቡትን ማመልከቻ እያየ ዉሳኔ እና የዉሳኔ ሃሳብ የሚስጠዉ ቦርድ፥ የቀረበለትን የይቅርታ ጥያቄ ሳይቀበለው ሲቀር የሚሰጠው ዉሳኔ እንዲህ የሚል ነው፤”ያቀረብከውን ማመልከቻ መርምረን አንተን በይቅርታ መልቀቅ ለሕዝብ የማይጠቅም በመሆኑ አይተቀበልነውም”። ይህን መሰል የዉሳኔ መሰረቶች የሕዝብ አስተዳደር ስራዎች እንደ ወሳኙ የጫማ ቁጥር እንዲለያዩ ያደርጋል።

ቅርጽ ተኮር ሙግትን መጠቀም ያለበት ማን ነው? ከላይ እንደተገለጸው ቅርጽ ተኮር ሙግት ጥቅሞች ቢኖሩትም ተመራጭ ከሆነባቸው ቅድመሁኔታዎች አንዱ፥ ቅርፁን ለመቅረፅ ፍሬ ተኮር ግምገማ መጠቀም አለብን። በኢህአዴግ ደረጃ አብዛኛው ካድሬ በቅርጽ ተኮር ግምገማ እንዲመራ ማድረግ ተገቢ ነው። ነገር ግን ይህን ቅርጽ የሚቀርጹት አካላት፤ ማእከላዊና ስራአስፈጻሚ ኮሚቴዎች፤ የሚሰጡት ዉሳኔ እና የሚያቀርቡት ሙግት በአብዛኛው ፍሬ ተኮር መሆን አለበት። ፍሬ ተኮር ሙግት ለማካሄድ የሚያስችላቸውን የሙያ እና የመረጃ አቅርቦት፥ በሙያና መረጃ ከተደራጀ የግንባሩ ጽህፈት ቤት ማግኘት ይኖርባቸዋል። በተመሳሳይ መልኩ ፓሊሲን፥ አዋጅን፥ መመሪያን የሚቀርጹ የመንግስት አካላት። እነዚህ አካላት የዉሳኔያቸው መሰረት መሆን ያለበት፥ ይህን ሃሳብ ብንቀበለውና ብንተገብረው ሕዝብን በምን ያህል መጠን እና ፍትሃዊነት እንጠቅማለን የሚለው ነው። ቅርጹን የሚቀርጸው አካል ራሱ ቅርጽተኮር ግምገማ የሚያካሂድ ከሆነ፥ የራሱን ቅርጽ እያመለከ ነው ማለት ነው። በዚህ ደግሞ ተራማጅነት የለም። በዚህ የሚኖረው መበስበስ ነው።

ሌላው ከባዱ ጠንቅ፥ በአንዳንድ ሁኔታዎች ቅርጽ ተኮር ግምገማ፥ በተለይ ደግሞ ቅርጹ ራስ፥ ሆድ፥ እግር፥ጠርዝ የሌለው ከሆነ፥ በጣም በተለይ ደግሞ ይህን ግምገማ የሚያካሂደው ከታች እስከ ላይ ያለው የድርጅቱ መዋቅር ከሆነ፥ አስመሳይነት ገዢው የድርጅቱ መገለጫ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው። አስመሳይነት በዱር ያሉ እንሰሳት ሁሉ የሚጠቀሙበት የመኖር ስትራቴጂ ነው። ስለዚህ መናደፍ የማይችለው እባብ ልክ እንደ ተናዳፊው እባብ አይነት ቅርጽ፥ ቀለም፥ ድምጽ ያዳብራል። በዚህም ይኖራል፥ ሳይናደፍ። ስለዚህ በእነዚህ አይነት ሁኔታዎች መልክን ያማከለ ግምገማ/ውሳኔ ለአስመሳዮች በር የሚከፍት ነው።

Recent Posts

See All

የሽግግር መንግስት ህገመንግስታዊ ነው?

የዶር መሃሪ ታደለን ፅሁፍ አነበብሁት። https://meharitaddele.info/2020/05/the-limits-of-legal-solutions/ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው ለመንግስት ተጨማሪ ስልጣን በመስጠትና መብቶችን በመገደብ በሽታውን ለመዋጋትና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ ከሆኑ ብቻ ነው። መንግስ

 • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.