• Dr. Mulugeta Mengist

ሶሻላይዜሽን፤ አንደኛው የትምህርት ግብ

Updated: Nov 17, 2019

ትምህርት እውቀትን፥ መረጃና፥ ክህሎትን ማስተላለፊያ ስርአት ነው። በደጉ ዘመን። አሁንም፤ አሁንማ እውቀትና መረጃ እድሜያቸው አጥሮ። ድሮ አስራ ሁለት አመታት ወጥረህ ተምረህ እድሜ ልክህን ትጦርበታለህ። አሁን ልጄ፤ የእውቀትና መረጃ አማካይ እድሜ ከሶስት አመት አይበልጥም። ወዲያዉ ያረጃል። ድሮ፥ ፓተንትና ኮፒራይት በሚሰጥህ የ20 እና የ50 አመታት ሞኖፓል፥ ዳጎስ ያለ ገቢ ታገኝበት ነበር። ታዲያ መጣልሃ፥ የመረጃና ኮሚኒኬሽን ዘመን። ወዲያዉ የታየን፥ የፓተንትና የኮፒራይት መብቶች በዚህ ቴኬኖሎጂ መጣሳቸው ነበር። ታዲያ በየቦታው የቅጂና የፈጠራ መብት ይከበር ብለን ጮህን። በቃ ፈጠራና ጥበብ አለቀላት ብለን ሰጋን። እየቆየ ግን አንድ እውነት እየተገለጠልን ነዉ። የ20 አመት ሞኖፓል የግድግዳ ጌጥ ነው። ምክንያቱም በሁለታ ሶስት አመቱ፥ ቴኬኖሎጂዉ አርጅቷል። በጦጣ ሳንቲም እንኳን የሚገዛህ አታገኝም። እንዲያም ሆኖ ፈጠራና ጥበብ እንደ ሰሞኑ ተመችቷቸው አያዉቅም። እያደር አበባ እየመስሉ ነዉ።

ታዲያ እንዴት ነው፥ አስራ ሁለት፥ ሃያ አራት አመት ተምረን እድሜ ልካችንን የምንጦረው? መጦር አይታሰብም። ይልቅስ ምን አዲስ ነገር መጣ እያሉ እያነፈነፉ ከስራ የተረፈች ጌዜያችንን ማሳለፍ ነው። ይሄ ነው እጣ ፈንታችን።

ይሄ ጉዳይ ታዲያ የትምህርት ስርአቱን በተለይ ደግሞ የመጀመሪያዉን ግብ ጥያቄ ዉስጥ የሚከት ነው። እውቀት ከማስተላለፍ ወደ ክህሎች ማዳበር መሻገሩ የግድ ነዉ። ከለውጡ ጋር አብሮ ለመሄድ። ያለዚያ ከበለፀጉ ሀገራት ማእድ ብቻ የምንጠፋው ከሰው ልጅ ዘረመል ነው። የሰው ልጅ መገኛ፥ ከሰው ልጅ ዘረመልማ መጥፋት የለባትም።

እኔ እንኳን በዚህ ማንሳት የፈለኩት ስለሁለተኛው የትምህርት ግብ ነው። ሶሻላይዜሽን የሚሉት። ደንብን/እሴትን/መልካም ባህሪን ማጎልበት። ይህን ግብ ለአንድ ትምህርት ብቻ የመተዉ አዝማሚያ አያለሁ። ለግብረገብ ወይም ስነዜጋ ትምህርት። እንዲሁም ይህ ግብ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ላይ ትኩረት ሲሰጠዉ አላይም።

ቁምነገሩ ሶሻላይዜሽን የአንድ የትምህርት አይነትና እስከ 12ኛ ክፍል ባለው ደረጃ ብቻ የሚገደብ አይደለም። እንደዉም፥ እዉቀትና ከማስተላለፍ ይልቅ ክፍሎትን ማስተላለፍ የትምህርት ግብ እየዞረ ነው እንዳልኩት ሁሉ፥ ከክህሎት ይልቅ ደግሞ ሶሻላይዜሽን ነዉ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው። እስከዛሬ ወይም እስከቅርብ ጊዜ ድረስ፥ ዜጎች አላስፈላጊ ባህሪ እንዳይኖራቸው፥ ተፈላጊ ባህሪ እንዲያሳዩ ሕግ ትልቅ ሚና ይጫወት ነበር። ማለትም በቅጣትና ሽልማት ዜጎችን ወደ ሚፈለገው እናተጋ ነበር። ሕግ አንዴ ወጥቶ ብዙ ይቆይ ነበር። ድሮ አቤት የሕግ በረከቱ። ወደፊት ግን ይሄ ተረት ተረት ነዉ። መረጃና እውቀት በፍጥነት እየተቀያየረ፥ ሕግ አዊጪዉ አዲሱን ነገር ተረዳሁት ቤሎ ህግ ሲያወጣ ወዲያዉ ተቀይሯል። እንዲሁም ይሄ የእውቀት  እድገት ያመጣው ነገር ቢኖር፥ የግለሰብ ሃይልን/አቅምን ማብዛቱ ነዉ። በሚገርም መጠን። አሁን አንድ ሰው ብቻዉን አለምን ሊያጠፋ ይችላል። አዲሱ እዉቀት ሞትን ድል ይመታል ተብሎ ይጠበቃል ከፈጠነ በሚቀጥሉት ሰላሳ አመታት፥ ከዘገየ በሰባ አመታት  ውስጥ። በእንዲህ አይነት ሁኔታ፥ ግለሰብ እንዴት ሕግን እና ቅጣትን ይፈራል። ሕግ ወይ ወዉጊያህ የታለ እያለ አይንደረደርም?

ለወደፊቱ መፍትሄዉ ሕግና ቅጣት ሳይሆን፥ የግለሰብ ሃላፊነት ነዉ። በወርቃማዉ ሕግ የሚገዛ ዜጋ መፍጠር። ባንተ ላይ የማትፈልገውን በሌላ ላይ አትፈጽም የሚለውን። የቶማስ ፍሪድማን ሃሳብ ነው። እኔ ደግሞ በዚህ መፍትሄ እጠራጠራለሁ። መፍትሄውስ ዜጎችን በፍቅር ማነጽ ነው። ትምህርት ስርአቱ የዚህ ሃላፊነት ጫንቃዉ ላይ ይወድቃል። ባንድ ትምህርት አይነት ብቻ አይደለም። ይልቅስ ትምህርት ቤት ማለት ከጧት እስከ ማታ ተማሪዎች በፍቅር የሚታነጹበት መሆን አለባቸው። እውቀቱና መረጃዉማ ፌሴቡክና ጉግል ምን ሰርተዉ ይኑሩ።

አንተ የደላህ ነህ ትሉኝ ይሆናል። የማወራው የሳይንስ ፊክሽን ስለሚመስል ወይም ስለሆነ። ኳስ በመሬት ካላቹ፥ እሺ ይሁንላቹ። የኢንዱስትሪ ፓርክ እየገነባን ነው። የዉጭ ካፒታል ለመሳብ እየስራን  ነው። ርካሽ ጉልበት አለ በሚል። ጥያቄው ይህ ጉልበት የተማረ ነዉ ወይ? አስፈላጊው እውቀትና ክህሎት አለው ወይ? ይሄ ራሱ ትልቅ ችግር ነዉ።

ዋናው ነገር ግን ይህ ጉልበት፤ አስፈላጊውን እሴት የታጠቀ ነው ወይ? ይሄ የበለጠ የሚያሳስብ ነው። እንዳልኩት እሴትን የምናስታጥቀው በስነዜጋ ትምህርት ብቻ አይደለም። ሁሉም ትምህርት ይህን ማስታጠቅ አለበት። ሶሻላይዜሽን፥ በልምምድ፥ በምህዳር፥ በግንኙነትና፥ በተዋንያኑ የሚወሰን ነገር ነው። ሶሻላይዜሽን ባታስብበትም እንኳ መከናወኑ አይቀርም። ጥያቄው ዉጤቱ የምትፈልገው ላይሆን ይችላል። ስለዚህ ምን አይነት እሴቶችን ነው የምንፈልገው? እነዚህን ለማረጋገጥ የምዘና ስርአቱ ምን ያህል ሚናውን ይጫወታል? የትምህርት ቤት ኑሮና አስተዳደር ከምንፈልገው እሴት ጋር ይጣጣማል ወይ? የተማሪና አስተማሪ፥ የተማሪዎች የእርስ በርስ፥ የአስተማሪና የአስተዳደሩ፥ የአስተማሪና የድጋፍ ሰጪዉ ግንኙነት እና ይህ ግንኝነት በሚመራበት መደበኛና ኢመደብኛ ደንቦች ምን ያህል ከምንፈልገው እሴቶች ጋር ይጣጣማሉ።

አንድ ዲግሪ ለማግኘት አራት አመት ይወስዳል እንበል። በየሴሚስትሩ የተወሰኑ ትምህርቶች እየወሰዱና እየተፈተኑ። እንበልና፥ አንደ ሰው ትምህርቱንም ይቅርብኝ፥ከፈለጋቹ የአራቱን አመት ትምህርቶች ፈትኑኝና ሁሉንም ከደፈንኩ ዲግሪዉን ስጡኝ ቢልስ? ዲግሪ የሚስጠው ፈተና ላለፈ ብቻ ነው ወይስ አራት አመት መጠበቅ አለበት? የምን መንቀልቀል ነው? እንደኔ ይህን የማንፈቅደው፥ በሁለተኛው የትምህርት ግብ ምክንያት ነዉ። ሶሻላይዜሽን። ሶሻላይዝድ ያልሆነን ሰው ዲግሪ መስጠት አይገባም። ሶሻላይዜሽን ደግሞ ጊዜ ይወስዳል። ሶሻላይዝ ለማድረግ የምንሞክረው እሴት ምንድን ነዉ? ትግስትን። አቋራጭ አለመፈለግን። መድከምን። በቡድን መስርታን። ጓደኝነትን።

ጥያቄየ ታዲያ፥ የትምህርት ስርአታችን ምን ያህል ይሄን ሃላፊነት እየተወጣ ነው? ምን አይነት ስልቶችን ይጠቀማል?

የኢንዱስትሪው ኤኮኖሚ ከግብርናው ኤኮኖሚ በተለየ የሚፈልገው ምን አይነት እሴቶችን ነው? እነዚህን እሴቶች ይገነባል፥ የትምህርት ስርአታችን?

የትምህርት ስርአታችን፥ ጥላቻን ይንዳል? የትምህርት ስርአታችን መደጋገፍን ያበረታታል? የትምህርት ስርአታችን ትንንሽ አጥሮችን ያበረታታል ወይስ አጥር ዘለል ግንኙነትን፥ መደራደርን፥ መወዳጀትን ያበረታታል?

የትምህርት ስርአታችን ተማሪዎች ራሳቸውን በራሳቸው (በጥቅል ብቻ ሳይሆን በግለሰብም) እንዲያስተዳደሩ፥ሃላፊነትን ያለማምዳል ወይስ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የወላጆችን የሞግዚትነት ሚና ተክተዉ የሚጫወቱበት ቦታ ነው?

ለነገሩስ እውቀቱንስ ቢሆን የምናሳያቸው የዘመኑ እውቀት የደረሰበት ጥግ ድረስ ነው?

የትምህርት ስርአቱ በይዘቱ ምን ያህል ብዝሃነትን (yehasab) ያስተናግዳል? እና የመሳሰሉት።

20 views
  • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.