• Dr. Mulugeta Mengist

ስለፍቅር ገንዘብ

Updated: Nov 17, 2019


የአገልጋይን ጌትነት ለማስተካከል ምን ማድረግ አለብን? መመርመር፥ መፈተሽ፥ ማስተካከል፥ መሞከር። የማይጠየቅ ጌታ እንዳልሆነ መቀበል። ለምሳሌ፥ የገንዘብን ከአገልጋይነት ወደ ጌትነት ያለዉን ጉዞ ለማስተካከል እና ቁስአካላዊ ገበያ ያለዉን ክፍተት ለመሙላት፥ እና ሌሎች ችግሮችን ለመፍታት የፍቅር ገንዘብ የሚል በምናዉቀዉ ብር የተለየ የማህበራዊ ግብይት ገንዘብን ስለመፍጠርና ስለመጠቀም ሃሳብ አቀርባለዉ። ይህ አይነት ገንዘብ፥ በአይነቱ ከብር የተለየ ስለሆነ፥ ሊገዛዉ የሚችለዉ ነገር፥ በመጠኑ ብቻ ሳይሆን በአይነቱም ዉስን ነዉ። ለምሳሌ በገንዘብ ብዙ ነገሮችን ምንም እንኩዋን አይነታቸዉ ቢለያይም መግዛት ይቻላል። ዋጋዉ ቢለያይም። ለምሳሌ በእንድ ሺ ብር 50 ኪሎ ጤፍ ወይም አንድ ጫማ መግዛት ይቻላል። ጫማ መግዛት አይችልም የሚባል ከሆነ ምክንያቱ ሊሆን የሚችለዉ ገንዘቡ ብር ስለሆነ ሳይሆን፥ ገንዘቡ በመጠን ዉስን ስለሆነ ነዉ። ነገር ግን አንድ ሺህ የፍቅር ገንዘብ ጫማ አይገዛም ሲባል፥ ምክንያቱ መጠኑ ስላነሰ ሳይሆን የገንዘቡ አይነት ነዉ። የፍቅር ገንዝብ፥ ከምናዉቀዉ አይነት ገንዘብ የሚለየዉ፥ በተለያዩ ነገሮች መካከል ያለዉን አይነታዊ ልዩነት ለመጠበቅ ይሞክራል። ስለዚህ መኪናን፥ የፍቅር ሳንቲም እየተቀበሉ፥ ተሳፋሪዎችን መጫን፥ ብር እየተቀበሉ ከመጫን ይለያል። ድርጊቱ የየቅል ነዉ። በመሆኑም የፍቅር ሳንቲሙ ሊገዛልን የሚችለዉ ዉስን ነገር ነዉ፥ ገንዘቡን የለወጥንበትን አይነት ጉዳዮችን ብቻ። አንድ ኩንታል በቆሎ በመሸጥ የተገኘን ብር፥ ብዙ ነገር ልናደርግበት እንችላለን። በርበሬ፥ ስንዴ፥ ልብስ፥ ትምህርት፥ መዝናኛ፥ እና ሌላም ብዙ ነገር ልንገዛበት እንችላለን። አይ ብሩ የተገኘዉ በቆሎ በመሸጥ ስለሆነ፥ መግዛት የምትችለዉም ነገር በአይነቱ ከበቆሎ ጋር የሚመሳሰል ነገር ብቻ ነዉ ሊባል አይችልም። በዚህም ምክንያት ነው ገንዘብ ከአገልጋይነት ወደ ጌታነት እየተሻገር ያለዉ ብለናል። ይህን ለመቀልበስ ደግሞ የፍቅር ሳንቲም ያግዛል። ወይም ሌላ አይነት ገንዘብ። በዚህ አግባብ መሰረት፥ አንድ መንገደኛ ቤታችን እንዲያርፍ በማደርግ ያገኘነዉን 100 የፍቅር ሳንቲም የፈለግነዉን አይነት ነገር ልንገዛበት አንችልም። የተወሰኑ ነገሮችን ብቻ ነዉ ልናደርግበት የምንችለዉ። ለምሳሌ፥ ከዚህ አዋሳ በግለሰብ መኪና ዘና ብለን ከሹፌሩ ጋር እየተጫወትን ልንጉዋዝበት እንችላለን። 100 የፍቅር ሳንቲም የተቀበለዉ ባለመኪና ደግሞ፥ በሳንቲሙ መቀሌ ሲሄድ ሆቴል ከሚያድር፥ ስፋ ባለ ቤት ዉስጥ የቤት ምግብ እየበላ ከሌሎች ጋር እየተጫወተ ሊያሳልፍ ይችላል።

በፍቅር ሳንቲሙ እና በምናዉቀው ብር መካከል ያለዉ የለዉጥ አግባብ እና መጠን ቁጥጥር የሚደረግበት ይሆናል።

እንደ መነሻነት የተወሰደዉ የአዲስ አበባ ከተማ እና በሌሎች ከተሞች መኪናን በጋር የመጠቀም ባህልን በማስፋፋት፥ የፍቅር አገልግሎቶችን እና ግብይቶችን ማስፋፋት፥ የእየር ንብረት ለዉጥን መዋጋት፥ እርስ በእርስ መተባበር ያስችላል። እንዲሁም ለአየር ንብረት ፕሮጅክቶች የሚዉሉ ሃብትን ማስገኘት። የመንገድ መጨናነቅን፥ ሰልፍም መቀነስ ነዉ። እንዲሁም በገንዝብ እጥረት ምክንያት የሚመጣን መጉላላት መቀነስ ነዉ። ለምሳሌ በተለመደዉ ገንዘብ በሃያ ብር የሚሽጥን አገልግሎት፥ በሶስት የፍቅር ብር ሊቀርብ ይችላል። ይህ ማለት አንድ አይነት አገልግሎት በሁለት አይነት ወጋዎች ሊቀርብ ይችላል። አንደኛዉ ዋጋ የቁስ አካል ወጋ ሲሆን ይህም 20 ብር ነዉ። ይህ ዋጋ ቁስአካላዊ ነዉ። ነገር ግን በፍቅር ከሆነ በሶስት የፍቅር ሳንቲም ሊቀርብ ይችላል። ማለትም ሶስት የፍቅር ሳንቲም ከሃያ ብር ጋር እኩል ይሆናል ማለት ነዉ። በሃብታሞችና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸዉ መካከል ያለዉን ግንኙነት ያጠናክራል። በሌላ መልኩ ደግሞ 60 ብር የሚሽጥ ምግብን በ70 የፍቅር ብር መሽጥና መግዛት ይቻላል። በዚህ ጊዜ የፍቅር ሳንቲም የሚከፍለዉ ሰዉ፥ ተጨማሪዉን 10 ብር ለምግቡ ሳይሆን ለፍቅሩ እንደከፈለዉ ማየት እንችላለን። በቀደመዉ ምሳሌ የ20 ብር መንገድን በሶስት ብር አስከፍሎ የጫነ ስዉ፥ አስራ ሰባት ብር የቀነሰበት ምክንያት የተቀበለዉ ሶስት ብር ካገኘው ፍቅርና እርካታ ስለሚበልጥ ነዉ።

የፍቅር ሳንቲም በትራንስፓርት ዘርፉ እንዴት ይሰራል? መጀመሪያ አንድ የታክሲ ወይም የሌላ አይነት የክፍያ ትራንስፓርት ተጠቃሚን እናስብ። ይህ ሰው ለምሳሌ መቶ ብር ከፍሎ 100 የፍቅር ሳንቲም ገዛ እንበል። የት ገዛዉ የሚለዉን እንተወዉ። ነገር ግን ዋናዉ ቁም ነገር ብርን በፍቅር ሳንቲም መቀየር ጥብቅ ቁጥጥር የሚያስፈልገዉ ግብይነት እንደሆነ ግን ግልጽ ይሁን። የፍቅር ሳንቲም፥ ቁስ አካላዊ ሊሆን (ለምሳሌ በወረቀት ወይም በብር የተስራ) ወይም ላይሆን (ለምሳሌ ልክ እንደ ስልክ ኬሬዲት የማይጨበጥ ሊሆን ይችላል። ዞሮ ዞሮ የፍቅር ሳንቲምን ደህንነት ማረጋገጥ አስፈላጊ ነዉ።

ይህ መቶ የፍቅር ሳንቲም የያዘዉ ግለሰብ ከጦር ሃይሎች ኮተቤ፥ ከዚህ ቀደም አስራ አምስት ብር ከፍሎ በሚኒባስ ታክሲ ይሄድ ነበር። በዚህም፥ በስልፍና በግፊያ እና ጥበቃ ይጉላላ ነበር። አሁን ግን መንገድ ዳር ቆሞ ራይድ መጠየቅ ይችላል። ራይድ ለሰጠዉ ሰዉ 15 የፍቅር ሳንቲም ይከፍላል።

ራይዱን የሰጠዉ ሰዉ አሁን ብቻዉን ከመጉዋዝ ተርፎዋል። በዚህ አጋጣሚ አንድ ሰዉ ተዋዉቆዋል። መረጃና እዉቀትም ሊያገኝ ይችላል። እንዲሁም እግረኛም በመርዳት የሚያገኘዉን ጥሩ ስሜት ይሰማዋል። ከዚህ በተጨማሪ ግን 15 የፍቅር ሳንቲም ያገኛል። በዚህ ምን ይገዛበታል? ጫማ? ምሳ? ነዳጅ? ብር ቢሆን ኖሮ የፈለገዉን ሊገዛበት ይችል ነበር። አሁን ግን የፍቅር ሳንቲም የሚገዛዉ ዉስን ነገሮችን ነዉ። ገንዘቡ የተገኘበትን ድርጊት በአይነት የሚመስሉ ዉስን ነገሮች። ለምሳሌ፥ ገንዘቡን ለእናት ወግ ማህበር በእርዳታ መስጠት። ድሮም ቢሆን አስራ አምስት ብር ለእናት ወግ ሊሰጥ ይችል ነበር። ይህን ሲያደርግ ከኪሱ አስራ አምስት በር በማዉጣት ነዉ። ምናልባት ይህን ብር ለማግኘት 30 ደቂቃ የትርፍ ስራ ሰርቶ ሊሆን ይችላል። አሁን ግን 15 ብር እርዳታ ለመስጠት ትርፍ ስራ መስራት አይጠበቅበትም። ለምሳሌ ለአንድ ሰዉ ራይድ በመስጠት፥ አንድ እግረኛ በፍጥነት እና በምቾት የስራዉ ቦታ እንዲደርስ ከማደረጉ ተጨማሪ፥ አንድ ህጻን ተማሪን ምሳዉን መመገብ ችሎዋል፥ እንዲሁም ማህበራዊ የትዉዉቅ ሰንሰለቱን፥ እና እዉቀቱን አብዝቶዋል፥ ድብርትን ቀንሶዋል፥ አገሪቱን ከተጨማሪ የነዳጅ ወጪ ታድጎዋታል፥ አየር ንብረትን እየተዋጋ ነዉ፥ የመንገድ መጨናነቅን በመቀነስ ብዙ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞችን አስገኝቶዋል። ድሮም ቢሆን እኮ ራይድ መስጠት ይችል ነበር። ልዩነቱ አንድ ትንሽ በጎ ስራ በጣም እጅግ ብዙ በጎ ስራዎችን እንዲያስከትል በማድረግ፥ ለተግባሩ ተነሳሽነትን ያሳድጋል። በዚህ አስራር ድሮ ራይድ ከሚያገኙት ሰዎች በላይ፥ እጅግ ብዙ ሰዎች እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል። እናት ወግም ቢሆን ድሮ ያገኘዉ ከሚችለዉ በላይ እርዳት ድሃ ሕጻናትን በትምህርት ቤት ለመመገብ የሚያስችለዉ በላይ ገንዘብ እንዲያገኝ ያስችለዋል። ራይድ በመስጠት የተንሳ የሚመጡ እዉቀትን፥ ትውዉቅን እና የመሳሰሉት ጥቅሞችን በማብዛት ማህበራዊ መሰረቶች እንዲጠናከሩ ያደርጋል።

ከዚህ በላይ የተጠቀስኩትን አማራጭ የግብይት ገንዘብ እንዴት እንደሚሰራ ለማሳየት የአዲስ አበባን የትራንስፓርት ምሳሌ ተጠቅሜያለዉ። በእርግጥ ይህን ሃሳብ በተግባር ለመለወጥ የሚያስፈልጉ ብዙ ዝርዝር ጥናቶች፥ መረጃዎች፥ ድርጅታዊ ዝግጅት እና መንግስታዊ ዉሳኔዎች ያስፈልጋሉ። እንዲሁም ተመሳሳይ ሃሳብ በሌሎች መስኮች ሊዉሉ ይችላሉ።

የጽሁፌ ዋናዉ መልእክት ግን፥ አገልጋይ በቀላሉ ወደ ጌትነት ሊያድግ ይችላል። ይህ መሆን የለበትም። ለዚህ ማሳያነት ገንዘብን እንደምሳሌ ተጠቅሜያለዉ።

2 views
  • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.