• Dr. Mulugeta Mengist

መርህ አልባ ጉድኝት በአሜሪካ

Updated: Nov 17, 2019

የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ከአስራ ሰባቱ ቀናት ስብሰባ በኋላ በሰጠዉ መግለጫ፤ የድርጅቱን እና የሀገሪቱን ወቅታዊ ችግሮች አብራርቷል። ከእነዚህ ችግሮች ተብለው ከተለዩት ዉስጥ አንዱ፤ በድርጅቱ ዉስጥ የሚስተዋለው፤ መርህ አልባ ጉድኝት እንደሆነ ተገልጿል። ከመግለጫው በኋላ፤ የተለያዩ ግለሰቦች፤ ይህን አባባል በተረዱበት መንገድ፤ ሲተቹና ሲደግፉ ተስተዉሏል።

መርህ አልባ ጉድኝትን የሚያሳይና በአሜሪካ በአንድ ወቅት ስለተከሰተና ስላለፈ ታሪክ ላጫውታቹ። ታሪኩ የአልኮል መጠጦችን ይመለከታል። በሃያኛው ክፍለዘመን መባቻ ላይ፤ በአሜሪካ ደቡብ የሚገኙ አንዳንድ ግዛቶች፤ የአልኮል መጠጥን ማምረት፥ ማስተላለፍና፥ መሸጥ ከልክለዉ ነበር። ይህን ዘመን፤ የክልከላው ዘመን ይሉታል።

ከክልከላው በፊት፤ እነዚህ ግዛቶች የአልኮል ሽያጭን መቆጣጠር ጀምረዉ ነበር። በተደነገገው የቁጥጥር ስርዓት መሰረት፤ አልኮል የሚሸጡ ድርጅቶች እሁድ አይከፈቱም። በምሽት ከተወሰነ ሰዓት በኋላ አልኮል አይሸጥም። መጠጥ ቤቶች ከትምህርት ቤቶች በተወሰነ ርቀት በላይ መራቅ አለባቸው።  እድሜያቸዉ ላልደረሰ ልጆችና ወጣቶች መጠጥ አይሸጥም። እና የመሳሰሉት።

የቁጥጥር ስርዓቱ በሕግ እንዲዘረጋ ያስገደደበት ምክንያት፤ አልኮል በቤተሰብ ደህንነትና በሃገር ጤና እና ኤኮኖሚ ያለዉ አሉታዊ ተጽዕኖ ከፍተኛ በመሆኑ ነው። ቁጥጥሩ ይህን ተጽዕኖ እንዲቀንስ ያለመ ነበር። ትንሽ ቆይተዉ ግን ሕግ አዉጪዎቹ ከነአንካቴዉ የአልኮል ምርትና ሽያጭን ከለከሉ። ሕጉን ተላልፎ ለተገኘ ደግሞ፤ ጠበቅ ያለ ቅጣት ደነገጉ።

ክልከላው ምን ዉጤት አስገኘ? የታሰበዉን አላማ አሳካ? ሆስፒታል በአልኮል መመረዝ ምክንያት የሚሄዱ ድንገተኛ ታካሚዎች ቁጥር ቀነሰ? በአልኮል ምክንያት የሚደርስ ጉዳትና የሃይል ተግባር ቁጥር ቀነሰ? የአልኮል ጠጪዎች ቁጥር ቀነሰ?

ባጭሩ መልሱ ይህ ነዉ። ክልከላው የታሰበዉን አላማ አላሳካም። እንደዉም ያልታሰቡ ብዙ ጠንቆችን ይዞ መጥቷል። (ነዉ ወይስ አሳክቷል? ያላሳካዉ ያልታሰበለትን አላማ ነው? ጠንቆቹስ ያልታሰቡ ሳይሆኑ የታሰቡ ነበሩ?)

ክልከላዉን ተከትሎ፤ የጥቁር ገበያዉ ደራ። አልኮል በሕጋዊ መንገድ በግዛቶቹ ስለማይመረትና ስለማይሸጥ፥ ኮንትራባንዲስቶች ከሌሎቹ የአሜሪካን ግዛት አልኮልን በሕገወጥ መንገድ በማስገባት መቸርቸር ጀመሩ።

ክልከላ እና ታክስ ተመሳሳይ ጸባይ አላቸው። የአልኮል ፍጆታን ለመቀነስ፤ አልኮል ላይ ታክስ መጣል ይቻላል። ታክሱ የአልኮሉን ዋጋ ከፍ ያደርገዋል። እንደ መሰረታዊዉ የገበያ ሕግ ከሆነ ዋጋ ሲጨምር፤ ፍላጎትና ፈላጊ ይቀንሳል። አንዳንዱ አልኮልን ያቆማል። ሌላዉ የሚጠጣዉን መጠን ይቀንሳል። ክልከላውም የታክስ ያህል ነዉ።

ከክልከላው በፊት 10 ብር ይሸጥ የነበረው አልኮል፤ ከክልከላዉ በኋላ በጥቁር ገበያ ላይ ዋጋዉ 20 ብር ቢገባ፤ ክልከላው የ100 ፐርሰንት ታክስ ያህል ነዉ። በእርግጥ 20 ብር ከፍሎ አልኮል ሲገዛ ወይም ሲጠጣ ቢያዝ ቅጣት ሊጣልበት ይችላል። ለምሳሌ የሚጣልበት ቅጣት አስር ብር ነዉ ብንልና፤ ይህ ሰዉ ቢያዝ፤ የአልኮሉ ዋጋ ሰላሳ ብር ይሆናል። ስለዚህ ክልከላዉ የ200 ፐርሰንት ታክስ ያህል ነዉ። ነገር ግን ከተያዘ ነዉ። ሕጉን የጣሰ ሁሉ አይያዝም።

አንድ ሰዉ አልኮል በጥቁር ገበያ ሲገዛ፤ የመያዝ እድሉ 10 ከመቶ ነዉ እንበል። በዚህ ጊዜ፤ ምንም እንኳ ሻጩ የተቀበለዉ ዋጋ 20 ብር ቢሆንም፤ ገዢዉ ግን 21 ብር እንደከፈለ ያህል ነዉ። ዋናዉ ነገር፤ ክልከላ በዉጤቱ የታክስ ያህል መሆኑ ነዉ። የተከለከለዉን ነገር (የአልኮሉን) የገበያ ዋጋ በመጨመር፤ ፍላጎትን እና ፈላጊን ይቀንሳል።

የዋጋ ጭማሪ ፍላጎትን በምን ያህል መጠን ይቀንሳል? ይህ እንደ ተከለከለዉ ጉዳይና እንደ ሸማቹ ባህሪ ነዉ። የሸማቹ ገቢ አልቀነሰም፥ አልጨመረም ብለን እናስብ። እና በምን ያህል መጠን ነዉ የሚቀንሰዉ?

አሁን ባለንበት ዘመን ዜጎችን ከማይገባ ወይም ከጎጂ ነገሮች እንዲርቁ ለማድረግ ታክስን እንደ መሳሪያ መጠቀም የተለመደ ሆኗል። በሲጋራና ጣፋጭ ለስላሳ መጠጦች ላይ የሚጣል ታክስ የዚህ ማሳያ ነዉ። በዚህ ታክስ ምክንያት የሲጋራና የለስላሳ መጠጦች ዋጋ ይጨምራል። ሃሳቡ፤ የአጫሹና የለስላሳ ሸማቹን ቁጥርና ፍላጎት መቀነስ ነዉ። ግን የታሰበዉ ዉጤት ይገኛል?

ብዙ ጊዜ የታሰበዉ ውጤት ሲገኝ አይታይም። ለጥቂት ቀናት ዋጋዉ ያስደነገጣቸው አጫሾች፤ ፍጆታቸዉን ይቀንሳሉ። ወይም ለማቆም ይሞክራሉ። ከጥቂት ቀን በኋላ ግን፤ ከአዲሱ ዋጋ ጋር ይለማመዳሉ። እናም ይቀጥሉበታል። ዋጋው እጅግ ከጨመረ ወደ ጥቁር ገበያ ያመራሉ። የሲጋራ ቀረጥ በሚጣልባቸዉ አገሮች፤ ሲጋራ በጥቁር ገበያ ይሸጣል። ለምሳሌ፤ በእንግሊዝ ሃገር በገበያ ዉስጥ ካሉ አራት ሲጋራዎች ዉስጥ አንዱ በኮንትሮባንድ የሚዘዋወር እንደሆነ ይነገራል።

ሰዎች ለዋጋ ጭማሪ ያላቸው ምላሽ ይለያያል። የሱስነት ባህሪ ያላቸው፥ ወይም ለኑሮ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች፥ ወይም ተተኪ የሌላቸው ምርቶች፤ ዋጋቸዉ ቢጨምርም፤ ፍላጎት ባለበት ሊቀጥል ይችላል። (እንደኛ አገር ከሆነ ደግሞ ዋጋ ሲጨምር ፈላጊዉ ይጨምራል። አንዳንድ ነጋዴዎች እንደሚሉት በትንሽ ዋጋ አገልግሎት ማቅረብ የሚያዋጣቸዉ ቢሆንም ዝቅተኛ ዋጋ ፈላጊ ይሸሽባቸዋል። ዋጋዉ ከፍተኛ ሲሆን ፈላጊ ይመጣል። ለምን? ይህን ለሌላ ጊዜ እናቆየዉ።)

የአልኮል ክልከላዉም ልክ እንደ ሲጋራዉ ታክስ ነዉ። ፍላጎትን እና ፈላጊን አልቀነሰም። እንደዉም ወጣቶች እንደ አድቬንቸር በመቁጠር፥ ወደ ጥቁሩ ገበያ እንዲመጡ ሳያደርግ አይቀርም፤ ከታች እንደጠቀስኩት። ስለዚህ የጥቁር ገበያዉ ደራ።

ሌላ መስረታዊው የምጣኔሃብት ሕግ፤ ዋጋ ሲጨምር፥ የአቅራቢዎች ቁጥር ይጨምራል። ምክንያቱም፤ ንግዱ ስለሚያዋጣ አዳዲስ አቅራቢዎች ገበያዉን ይቀላቀላሉ። እነዚህ አዲስ አቅራቢዎች፤ ሌላ ንግዳቸዉን በመተዉ ወደዚህ ንግድ የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ።

ኮንትራባንዲስቶች፤ ከሌሎች የአሜሪካን ግዛት በርካሽ የገዙትን አልኮል፤ በሕገወጥ መንገድ አልኮል ወደ ተከለከለባቸው የአሜሪካን ግዛቶች በማስገባት ይቸበችቡ ጀመር። ይህ ስራ ሕገወጥ/ወንጀል ነዉ። ከተያዙ ይቀጣሉ። ስለዚህ እንዴት ነዉ ወደዚህ ንግድ የገቡት? ከዚህ በላይ እንደተጠቀሰዉ ወንጀል የሰራ ሁሉ አይያዝም አይቀጣም። የመያዝና የመቀጣት እድል መቼም 100 ከመቶ ሆኖ አያዉቅም። እጅግ ያንሳል። እንዲሁም ይህ ቅጣት ለነሱም ቢሆን የታክስ ያህል ነዉ። ዋጋዉን ነዉ የሚጨምርባቸው።

ለምሳሌ፤ ቅጣቱ 100 ብር ነዉ እንበል። ኮንትራባንዲስቱ አንድ ጠርሙስ ዉስኪ፤ ከሌሎች የአሜሪካን ግዛቶች በ10 ብር ገዛ እንበል። ይህን አልኮል ወደ ደቡባዊ የአሜሪካን ግዛቶች ሲያስገባ፤ የመያዝና የመቀጣት እድሉ 10 ከመቶ ነዉ እንበል። ኮንትሮባንዲስቱ የሚጠብቀዉ ቅጣት 100 ብር ሳይሆን 10 ብር ነዉ። ይህን 10 ብር ዉስኪዉን ከገዛበት ሌላ 10 ብር ጋር ስንደምረው፥ ኮንትራባንዲስቱ አንድ ጠርሙስ ዉስኪ ለማስገባት የሚያወጣዉ ወጪ 20 ብር ይደርሳል።

ዉስኪዉን በጥቁር ገበያ ከ20 ብር በላይ እስከሸጠው ድረስ ያዋጣል። በዚህ ላይ የመያዝና የመቀጣት እድሉን ለመቀነስ፤ የንግዱን አዋጪነት ለመጨመር የሚወስዳቸው እርምጃዎች ይኖራሉ። ሕግ እንዲያስከብሩ ከተመደቡ ፓሊሶች ጋር ቋሚ የመጠቃቀም ግንኙነት በመመስረት፤ የመያዝ እድሉን ጭራሽኑ ዜሮ ሊያደርገዉ ይችላል። በእርግጥ ለእነሱ የሚከፍለዉ ክፍያ የወጪዉ አካል ተድርጎ ይወሰዳል። ስለዚህ በዉስኪው ወጪና ዋጋ ላይ ይንጸባረቃል። አንድ ዉስኪ ብቻ ከማስገባት፤ እጅግ ብዙ ዉስኪ በማስገባት የድርጊቱን አትራፊነት ሊያሳድገዉ ይችላል። ብዙ ጊዜ ቅጣት የሚወሰነዉ በድርጊቱ መጠን እንጂ በአንድ ጉዞ ባስገባዉ የአልኮል መጠጥ መጠን ስለማይሆን።

ሰዎች ወደፊት ለሚጣል ቅጣት ወይም ለነገ የሚሰጡት ዋጋ ይለያያል። ለዛሬ እጅግ ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጡ፤ ለነገ ቦታ የሌላቸው ወይም ትንሽ ቦታ የሚሰጡ ሰዎች አሉ። እነዚህን ሰዎች አንደ በቅሎና ቸርቻሪ መጠቀም ለኮንትራባንዲስቱ ክፍት የሆነ አማራጭ ነዉ።

በጥቁር ገበያ በብዛት የሚገኙ ምርቶች በዋጋ ከፍተኛ፤ በመጠን/በቮሊዩም ግን ዝቅተኛ የሆኑ ናቸው። ስለዚህ ከፍተኛ የአልኮል መጠን ያላቸው መጠጦች (ለምሳሌ ዉስኪና አረቄ)፤ ዝቅተኛ የአልኮል ይዘት ካላቸው መጠጦች (ለምሳሌ ቢራ እና ለስላሳ ወይኖች) ይልቅ፤ ይመረጣሉ። አንድ በርሜል ቢራ ድንበር ከማሻገር (ግመል ሰርቆ አጎንብሶ!) አንድ ጄሪካን አረቂ ያዋጣል።

ዝቅተኛ የአልኮል ይዘት ያላቸው መጠጦች እየጠፉ፤ በአልኮል ይዘታቸዉ ከፍተኛ እና ቶሎ አስካሪ የሆኑ መጠጦች በዙ። ድሮ ቢራ ብቻ ይጠጡ የነበሩ ሰዎች፤ አሁን አረቂና ውስኪ እንዲጠጡ ተገደዱ (ከዚህ ሁሉ አያቆሙም። አይ መሬት ያለ ሰዉ!)። ይህን ተከትሎ በአልኮል መመረዝ፥ በከፍተኛ ስካርና፥ በተለያዩ ጉዳቶች ሆስፒታል የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ጨመረ። ስለዚህ ክልከላዉ የሆስፒታል ወጪን ሊቀንስ ቀርቶ ጭራሽ ጨመረው።

ከፍተኛ ዋጋ ያላቸውና በጥቁር ገበያ የሚሸጡ ነገሮች ሌላው የሚያመጡት ችግር የጥራት መቀነስ ነዉ። ባዕድ ነገሮችን በመቀላቀል የሚሸጡ መጠጦች ጨመሩ። በአልኮል የሚመረዙት ሰዎች ቁጥር ጨመረ። እኛ አገር እንኳን የሽሮ፥ የቅቤ፥ የበርበሬና፥ የጤፍ ዋጋ ሲጨምር አይደል፤ ሙዝ፥ ቀይ አፈር፥ የጣዉላ ፍርፋሪና፥ የመሳሰሉትን ባዕድ ነገሮች እየቀላቀሉ የሚሸጡ ነጋዴዎች ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩት።

አልኮልን በቤት ማምረት ከፍተኛ ገቢ የሚያስገኝ ስራ ሆነ። እንደ አንዳንድ ሪፓርቶች መሰረት የመታጠቢያ ገንዳቸዉን ሁሉ ወደ አልኮል መጥመቂያ የቀየሩ ብዙ ሰዎች ነበሩ።

ከጠጪዎች መካከል የልጆችና የለጋ ወጣቶች ቁጥር እንደጨመረ ይነገራል። ክልከላዉን መጣስ እንደ አድቬንቸር በመቁጠር። የልጅነትና የወጣትነት ችግር ነዉ። አዳምና ሄዋን ልጅ ወይም ለጋ ወጣት እያሉ ነዉ አይደል በለሱን የበሉት?

በጥቁር ገበያ የሚደረግ ማንኛዉም ግብይት፥ የሕግ ጥበቃ አያገኝም። እዳውን አልከፈለም፥ አቀርባለሁ ያለውን አልኮል አላቀረበም፥ ያቀረበው አልኮል ከጥራት በታች ነው፥ እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ጥቅሜ ጎድሎብኛል በማለት ፍርድ ቤት ሙግት ማቅረብ አይቻልም። ስለዚህ በጥቁር ገበያ ዉሎች የሚከበሩት በጉልበት ነዉ። በመሆኑም በእነዚህ አካባቢዎች የጉልበትና የሃይል ተግባራት ቁጥር በመጨመሩ የተነሳ፤ ተጨማሪ የሰላምና ጸጥታ ስጋት ሊሆን ችሏል።

መንግስት የተለያዩ አላማዎችን ለማሳካት የተለያዩ የፓሊሲ መሳሪያዎችን ይጠቀማል። ከእነዚህ ዉስጥ፤ ክልከላ አንዱ ነዉ። ለሰዉ ልጆች የተሰጣቸዉ የመጀመሪያ ሕግ ክልከላ ነዉ። ከዚህ የእዉቀት ዛፍ ፍሬ እንዳትበሉ። የተከለከ ነገር አጓጊ ነዉ። በተለይ ለልጆች እና ለለጋ ወጣቶች። በተለይ ደግሞ፤ ክልከላዉን በሚገባ ክትትልና ቅጣት ማስከበር የማይቻል ከሆነ፥ እና ልክ እንደ ሲጋራና አልኮል ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ ሸማቾች የግብይት ባህሪያቸዉን የማይቀይሩ ከሆነ፥ ክልከላው ዉጤታማ አይሆንም። እንዲሁም ሊከለከል የሚገባዉ ነገር፤ ምንም አይነት ጥቅም የሌለዉና በየትኛዉም ሁኔታ ጎጂ ነዉ ተብሎ ሲታሰብ ብቻ መሆን አለበት። እንዲህ አይነት ጉዳዮች ግን በቁጥር እጅግ ትንሽ ናቸዉ። ብዙ ነገሮች ጎጂ ጎን ቢኖራቸውም፤ ጠቃሚ ጎንም አላቸው። ሲጋራና አልኮል ጠቃሚ ጎን አላቸው እያልኩ አይደለም (በእርግጥ ሲጋራ ማጨስ አገራዊ ጥቅሙ ከጉዳቱ ይበልጣል የሚል ሪፓርት አንድ በሲጋራ አምራቾች የተቀጠረ የምጣኔሃብት ባለሙያ አቅርቧል)። ክልከላ፤ ሌላ አማራጭ ሲጠፋ ብቻ የምንጠቀመዉ መሳሪያ መሆን ይገባዋል።

የአልኮል ክልከላዉ የታሰበውን አላማ እንኳን ሊያሳካ፤ ሌሎች ያልታሰቡ ችግሮችን ይዞ መጥቷል። ይህንን አባባል እንደገና ተመልከቱ። ጥያቄዉ፤ ከላይ የተጠቀሰዉ አላማ እዉነት ሕጉ እንዲያሳካዉ የታሰበ አላማ ነዉ? ያልታሰቡ የተባሉትና ከላይ የተጠቀሱት ችግሮችስ፥ እውነት ያልታሰቡ ናቸው? ችግርነታቸውስ ለማን ነዉ?

ፓሊሲና ሕግ ሕዝባዊ አላማ ሊኖራቸው ይገባል። ይገባል ነዉ። ሁልጊዜ ሕዝባዊ አላማ አላቸው ማለት ግን አይደለም። የፓለቲካ ስርዓቱ ሕዝባዊ ያልሆኑ ዉሳኔዎች እንዲወጡ ምክንያት ይሆናል። ፓሊሲዎቹ፥ ዉሳኔዎቹ፥ ሕጎቹና፥ ፕሮግራሞቹ ሕዝባዊ አላማን እንደ ማስክ/ሽፋን በመጠቀም፥ የጥቂቶችን ጥቅምና ፍላጎት የሚያስከብሩ ይሆናሉ። ስለዚህ እይታችን/ምልከታችን፤ በአደባባይ ከተጠቀሰዉ የመንግስት አላማ በላይ ሊዘልቅ ይገባል።

ማንን ነዉ ሊጠቅም የሚችለዉ፤ ይህ ዉሳኔ? ማንን ነዉ ሊጎዳ የሚችለዉ፤ ይህ ዉሳኔ? ይህን ዉሳኔ ተደራጅተዉ እንዳይወጣ ለማድረግ ወይም ለማስቀየር፤ ተጎጂዎቹ ያላቸዉ እድል ምን ያህል ነዉ? እንዲህ አይነት ሕግ እንዲወጣላቸዉ ለማድረግ፤ ተጠቃሚዎቹ በዉሳኔ ሰጪዎቹ ላይ የተደራጀ ተጽዕኖ ማድረግ ይችላሉ? ዉሳኔ ሰጪዎቹስ ከእነዚህ ተጠቃሚዎች ምን ያገኛሉ? ከተጎጂዎቹስ ምን ያጣሉ? እነዚህን ጥያቄዎች ተገቢዉን ግምገማ በማድረግ ብንመልሳቸው፥ የዉሳኔዉን ማስክ አዉልቀን፤ ትክክለኛውን አላማ እናገኘዋለን። እንዲሁም ችግሮች ያልናቸው ችግርነታቸው ለማን እንደሆነ ስናውቀው፥ ያልታሰቡ ችግሮች ሳይሆኑ የታሰቡ የሕጉ አላማዎች ስለመሆናቸው ልንደርስበት እንችላለን።

ወደ ተነሳንበት ጉዳይ ስንመጣ፤ ከክልከላዉ በፊት የቁጥጥር ስርዓቱ ነበረ። ይህ ቁጥጥር ስርዓት እንዲዘረጋ፤ በዉሳኔ ሰጪዎቹ ላይ ተጽዕኖ ያደረገችዉ ቤተክርስቲያን ናት። ቤተክርስቲያኒቱ (በትክክለኛዉ አባባል የቤተክርስቲያኒቱ መሪዎች) ትልቅ የፓለቲካ ሃይል አላቸው። ስለዚህ ዉሳኔ ሰጪዎቹ ይህን የቤተክርስትያን ድጋፍ ይፈልጉታል። ለመመረጥ። ቤተክርሲያኒቱ ደግሞ ጥቅሞቿን እና ፍላጎቶቿን በዉሳኔዎች እንዲንፀባረቁ ታደርጋለች። ይህን የፓለቲካ ሃይል ያገኘችው በአባሎቿ ነው። የአባሎቿ ቁጥር ሲጨምር፤ የገንዘብ መዋጮ ይጨምራል። እንዲሁም አባሎቿ መራጮች ናቸው። ስለዚህ በትምህርትና ምክር በአባሎቿ የምርጫ ውሳኔ ላይ ተጽዕኖ ማድረግ ትችላለች። የአልኮል መጠጥ ልቅ የሆነ ስርጭት፤ ቤተክርሲያኒቷን አስግቷል። የገንዘብ ገቢዋ ላይ የተጋረጠ ትልቅ አደጋ ነዉ። ቤተክርስቲያን የሚመጡበትን ጊዜ፤ መጠጥ ቤት የሚያሳልፉ ሰዎች ሲበዙ። ይህ ጉዳይ፤ ቤተክርስቲያኒቱ በዉሳኔ ሰጪዎች ላይ ያላትን ተጽዕኖ በረጅም ጊዜ የሚቀንስ ነዉ። ስለዚህ የቁጥጥር ስርዓቱን አስዘረጉ። ለምሳሌ፤ እሁድ መጠጥ ቤቶች አይከፈቱ የሚለዉ ክልከላ የቤተክርቲያኒቱን አላማ ያሳያል።

የቁጥጥር ስርዓቱ ራሱ እንደ ከፊል ክልከላ ተደርጎ ይወሰዳል። በእሁድ ቀንና ሌሊት መጠጥ ስለማይገኝ፤ ለዚህ ጊዜ የሚያገለግል ጥቁር ገበያ ተፈጠረ። ይህን ያዩ የጥቁር ገበያ ነጋዴዎች፥ ከነአንካቴዉ ቢከለከል የሚያገኙትን ገቢ አስበዉ፤ ራሳቸዉን አደራጅተዉና ከቤተክርስቲያኒቱ መሪዎች ጋር ተቀናጅተው፤ የቁጥጥር ስርዓቱ በክልከላዉ እንዲተካ አደረጉ። ትናንትህ ዛሬን ያስርብሃል፤ ዛሬ ደግሞ ነገን ለሚለው ማሳያ ይሆናል፤ ይህ ከቁጥጥር ወደ ክልከላ የተደረገዉ ጉዞ።

ከላይ የተጠቀሱት የጥቁር ገበያ ችግሮች፥ ለነጋዴዎቹ ጥቅሞች ናቸው። ያልታሰቡም አይደሉም። በደንብ አስበዉበታል። የሕጉ እዉነተኛ አላማም ይህ ነዉ።

በቤተክርሲያኒቱና በኮንትራባንዲስቶቹ መካከል ያለዉ ግንኙነትን እንመልከተዉ። የመርህ ግንኙነት አይደለም። ሁለቱም የተለያዩ መርሆችን ነዉ የሚያራምዱት። የጥቅም ግንኙነት ነዉ። ማንም የማይጠረጥራቸዉ፤ አንሶላ ተጋፋፊዎች ማለት እነዚህ ናቸው። አብረዉ ይተኛሉ ተብለዉ የማይጠረጠሩ።

የጥቅም ግንኙነት ሁልጊዜ ጎጂ አይደለም። ከዚህ በፊት ስለዚህ ጉዳይ ጽፌያለሁ። የመርህ ግንኙነት ያለበትንም ችግር እንዲሁ ጠቅሻለው። ችግሩን የጥቅም ወይም የመርህ አልባ ግንኙነት ብሎ በደፈናዉ መጥቀስ ግን፤ ግንኙነቶች ሁሉ መርህ ላይ ይመስረቱ የሚል የማይጠቅም መልዕክት አለው።

መጠየቅ ያለብን አንድ ጥያቄ አለ። ችግሩ የመርህ አልባ ግንኙነት ነዉ ወይስ ሌላ ስም ሊሰጠው የሚገባና በስርዓቱ ምክንያት የመጣ ችግር ነዉ? በዚህ ጽሁፍ ባነሳሁት የአልኮል ክልከላ ጉዳይ ችግሩ ማንም የማይጠረጥራቸው (ተቃራኒ የሚመስሉ ሰዎች) አንሶላ መጋፈፍ አይደለም። የፈለጋቸውን ያህል አልሶላ ቢጋፈፉ ዲቃላ ይወልዱ እንደሆነ እንጂ ሕዝባዊ ያልሆነ ሕግ አያወጡም። ችግሩ፤ የፓለቲካ ስርዓቱ፤ ተዋንያን (ዉሳኔ ሰጪዎች) በጥቂት የተደራጁና ፈርጣማ የኤኮኖሚና የፓለቲካ አቅም ባላቸዉ ሰዎች ተጽዕኖ እንዲወድቁ ማድረጉ ነዉ። ችግሩ፤ ዉሳኔ ሰጪዎች ከጥቂት የተደራጁ ሰዎች ጋር ሲሞዳሞዱ የሚጠቀሙ፥ ነገር ግን ሕዝባዊ አቋም ሲያራምዱ የሚጎዱ የሚያደርግ ስርዓት ከሆነ ነዉ። ችግሩ፤ አብዛኛው ሕዝብ ራሱን አደራጅቶ ጥቅሙን ለማስከበር ያለው እድል ዝቅተኛ መሆን ነዉ። ለዚህም የፓለቲካ ስርዓቱ አወቃቀር፥ ሂደትና፥ አሰራር ምክንያት ነው። ይህ እስካለ ድረስ እነዛ አካላት አንሶላ ተጋፈፉ ወይም በዱላ ተናረቱ፥ የፈለጉትን ነገር በሀገራዊ ፓሊሲ ዉስጥ እንዲካተት ከማድረግ የሚያግዳቸው ነገር የለም።

ስለዚህ ጥያቄዉ፤ ዋናውን መሰረታዊ ችግር ያመጣዉ ምንድን ነዉ? ችግሩ ሀገራዊ ከሆነ፥ የፓለቲካ ስርዓቱ ጥቂቶች ተጎዳኝተዉ ፍላጎቶቻቸውን ለማሳካት የሚችሉበት ነዉ? ችግሩ የአንድ ድርጅት ከሆነ፤ የድርጅቱ አሰራር፥ አወቃቀር፥ ሂደት ጥቂቶች ተጎዳኝተው ፍላጎቶቻቸውን ለማሳካት የሚችሉበት ነው? ስርዓቱ ለጥቂት ሃብታሞች ወይም ልዩ የፓለቲካ ሃይል ላላቸው ሰዎች የተጋለጠና ተጠቂ ነዉ?

ምሁሩ እንዳለዉ፤ የጧት ዳቧችንን የምናገኘዉ በዳቦ ጋጋሪዉ ሕዝባዊነት ሳይሆን፤ በዳቦ ጋጋሪዉ ግለኝነት ነዉ። ሰዎች በተፈጥሯቸው ግላዊ ናቸው። በእያንዳንዳችን ዉስጥ ትንሽም ቢሆን ሕዝባዊነት አለ። ይህ ሕዝባዊነት መገለጥና አለመገለጡ፥ ማበብና መክሰሙ፤ የሚወሰነው በምህዳሩ ጸባይ፥ በግንኙነታችን መጠን፥ በአላማው ግልጽነትና በተፈላጊዉ የድርጊት ባህሪ ነው። አንዳንድ ጊዜ እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች በላቀደረጃ በማሟላት፥ ራሳቸውን ረስተው፥ ግላዊ ስሜቶችና ፍላጎቶችን ደምስሰው፥ ሕይወታቸውን ሁሉ ለሕዝብ የኖሩና የተሰው ሰዎችን ‘መፍጠር’ ይቻላል። ባብዛኛው ግን ሕዝባዊ ዉሳኔዎች የሚመነጩት በተዋንያኑ ሕዝባዊነት ብቻ በመተማመን ሳይሆን በስርዓቱ ነዉ። የስርዓቱ አወቃቀር፥ ሂደትና፥ አሰራር ሁልጊዜ ባይሆንም እንኳን ባብዛኛው ሕዝባዊ ዉጤት እንዲኖረዉ ማድረግ ይገባል። ስለዚህ አስር ሲጎዳኙና እንሶላ ሲጋፈፉ ቢውሉ፥ ሃገራዊ ፓሊሲዎችን ለግል ጥቅማቸው ለማዋል የማያስችላቸው ስርዓት ሊገነባ፥ ሊጠናከር ይገባል። ሕዝባዊነት በላቀ ደረጃ የሚረጋገጠው በግለሰቦች ሕዝባዊነት ሳይሆን፤ ሕዝባዊ በሆነ አሰራር፥ ሂደት፥ አደረጃጀትና፥ ደንቦች ነው።

1 view

Recent Posts

See All

የሽግግር መንግስት ህገመንግስታዊ ነው?

የዶር መሃሪ ታደለን ፅሁፍ አነበብሁት። https://meharitaddele.info/2020/05/the-limits-of-legal-solutions/ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀው ለመንግስት ተጨማሪ ስልጣን በመስጠትና መብቶችን በመገደብ በሽታውን ለመዋጋትና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊ ከሆኑ ብቻ ነው። መንግስ

አንዳንድ ጉዳዮች ስለ ህገመንግስት እና ፍርድ (ትርጉም)

መንደርደሪያ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስራ ዘመን ከማለቁ በፊት ምርጫን ማከናወን እንደማይችል፤ ብሄራዊ የምርጫ ቦርድ ካሳወቀ ጊዜ ጀምሮ፤ የጉዳዩ ህገመንግስታዊ ገፅታዎች በተለያዩ መድረኮች ውይይት እየተደረገባቸው ነው። አራት አማራጭ መፍትሄዎች የቀረቡለት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፤ በጉዳዩ ላይ የህገመንግስት

  • @insights.of.jaaj

©2019 by fujaaj. All rights reserved.